በቅዳሜው የሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ ለተሰንበት ግደይ ለአሸናፊነት ተገምታለች
በአሜሪካ ኦሪገን የሚከናወነው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሊጀምር የሦስት ቀናት ዕድሜ ይቀሩታል፡፡ ባለፉት ወራት የተለያዩ የማጣሪያ ውድድሮችን አሰናድተው፣ ዝግጅት ሲያደርጉ የከረሙት ተካፋይ አገሮች ጉዟቸውን ጀምረዋል፡፡ ከሳምንት በፊት የመጨረሻዎቹን አትሌቶችን ስም ዝርዝር ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድኑን የመጀመርያ ልዑካን ወደ ሥፍራው ልኳል፡፡
ዓርብ ሐምሌ 8 ቀን 2014 ዓ.ም. በሚጀምረው 18ኛው አትሌቲክስ ሻምፒዮና በመጀመርያው ዙር ላይ የሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ሰኞ ሐምሌ 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው አቅንተዋል፡፡
የመጀመርያዎቹ ልዑካን ቡድን ውስጥ በመካከለኛውና በረዥም ርቀት የሚሳተፉ አትሌቶች ተካተዋል፡፡ በዚህም መሠረት ዓርብ በወንዶች 3,000 ሜትር ማጣሪያና ሴቶች 1,500 ሜትር ማጣሪያ ያደርጋሉ፡፡ በሁለተኛው ቀን የሴቶች 3,000 ሜትር ማጣሪያና የሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ እንዲሁም ወንዶች 1,500 ሜትር ማጣሪያና ሴቶች 1,500 ሜትር ግማሽ ፍፃሜ ይጠበቃል፡፡
በእነዚህ ርቀቶች ላይ የሚሳተፉ አትሌቶች ቀድመው ወደ ሥፍራው አቅንተዋል፡፡ ከመካከለኛ ርቀት ባሻገር በሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ ላይ የሚካፈሉ አትሌቶች ወደ ሥፍራው አቅንተዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሴቶች 10,000 ሜትር ፍፃሜ ለተሰንበት ግደይ፣ እጅጋየሁ ታዬና ቦሰና ሙላት ተወክላለች፡፡
ኢትዮጵያ ወርቅ ታገኝባቸዋለች ተብለው ከሚጠበቁ ርቀቶች መካከል የሴቶች 10,000 ሜትር ይጠበቃል፡፡ የርቀቱ ክብረ ወሰን ባለቤቷ ለተሰንበት ግደይ በአንደኛነት እንደምታጠናቅቅ በዓለም አትሌቲክስ ተገምቷል፡፡ ሆኖም በቶኪዮ ኦሊምፒክ በተቀናቃኟ ሲፋን ሐሰን ‹‹ፈተና ይገጥማት ይሆን?›› የሚለውም የብዙኃን ጥያቄ ነው፡፡ ሲፋን በዓለም ሻምፒዮናውም 1,500 ሜትር፣ 5,000 ሜትርና 10,000 ሜትር እንደምትካፈል የተጠቀሰ ሲሆን፣ በኦሊምፒኩ ተመሳሳይ ርቀቶች ላይ መካፈሏን ተከትሎ ጉዳት ስለገጠማት ከርቀቶቹ በአንዱ እንደማትካፈል እየተጠቀሰ ይገኛል፡፡ በዚህም የማትካፈልበትን ርቀት ከወዲሁ እንደምታሳውቅ አሠልጣኟ አስታውቋል፡፡
ለተሰንበት ያለችበት ወቅታዊ አቋም ከፍተኛ ግምት እንዲሰጣት ያስቻለ ሲሆን፣ በዚህም ምክንያት በ5,000 ሜትር እንደምትሳተፍ ተገልጿል፡፡ በመጀመርያ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዝርዝር ውስጥ ተካታ የነበረችው የሪዮ ኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ አልማዝ አያና በቡድን ውስጥ አልተካተተችም፡፡
በወንዶች 10,000 ሜትር በሰለሞን ባረጋ፣ በወንዶች 3,000 ሜትር በለሜቻ ግርማና በሴቶች 1,500 ሜትር፣ 800 ሜትርና 1,500 ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ልታሳካ የምትችልባቸው ርቀቶች እንደሆኑ ተገምቷል፡፡
በዘንድሮ ዓለም ሻምፒዮና ላይ አራት አትሌቶች ሁለት ርቀቶች ላይ ይሳተፋሉ፡፡ በወንዶች ሰለሞን ባረጋ 10,000 እና 5,000 ሜትር፣ በሴቶች ለተሰንበት ግደይና እጅጋየሁ ታዬ በሁለቱም ርቀቶች እንደሚካፈሉ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ሒሩት መሸሻ በ800 እና 1,500 ሜትር ኢትዮጵያን ወክላ እንደምትሳተፍ ተጠቅሷል፡፡
በምርጫው ሒደት የተለያዩ ቅሬታዎች ሲነሱ የከረሙ ሲሆን፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫውን በማሳወቅ የመጨረሻዎቹን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል፡፡ በዚህም ምርጫው ‹‹ሒሳባዊ ሥሌት ያልተደረገበትና ቀድመው ተመርጠው ልምምድ ሲያደርጉ የነበሩትን አትሌቶች በመተው በልምምድ ላይ ያልነበሩ አትሌቶችን መርጠዋል›› የሚል ክስ እየቀረበበት ይገኛል፡፡
በአንፃሩ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ሁለት ርቀቶችን መካፈል የሚችሉ አትሌቶችን ዕድል ባለመስጠቱ ማሳካት የሚቻለውን ሜዳሊያ በማጣቱ፣ በዓለም ሻምፒዮናውም ስህተቱ እንዳይደገም ዕርምት ማድረጉ በበጎ ጎኑ ተነስቷል፡፡
ከሐምሌ 8 እስከ 17 ድረስ የሚዘልቀው ሻምፒዮናው 1,900 በላይ አትሌቶችና 192 አገሮች ኦሪጎን እንደሚከትሙ የዓለም አትሌቲክስ አስታውቋል፡፡
እ.ኤ.አ. 2019 በዶሃ ኳታር ዓለም ሻምፒዮና ላይ ሻምፒዮን መሆን ከቻሉ 43 አትሌቶች መካከል 37ቱ በአሜሪካ ይከትማሉ፡፡ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ወርቅ ያመጡ 42 አትሌቶችም በኦሪጎን ሻምፒዮና ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡