- እንዴት መንግሥት የዜጎችን ደኅንነት ማስጠበቅ አልቻለም ይባላል? መንግሥት ስንት ነገር እያደረገ እንዴት ይወቀሳል?
- እንዴት ክቡር ሚኒስትር?
- አንተም ጥያቄ አለህ?
- ለመወያየት እንጂ እንዳሰቡት አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
- እንዴት እንዲህ አልክ?
- ለማለት የፈለግኩት ምን መስልዎት ክቡር ሚኒስትር …
- ተወው … መንግሥት አማፂውን ቡድን ለመደምሰስ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ ላይ መሆኑ እየታወቀ መወቀሱ ገርሞኝ ነው ጥያቄውን ያነሳሁት።
- ቢሆንም ክቡር ሚኒስትር አንድ አካባቢ ላይ በተደጋጋሚ ዜጎች ሲገደሉ ጥያቄ መፈጠሩ አይቀርም።
- እሱን ችግር ለመቅረፍ አይደለም እንዴ ዘመቻ የተጀመረው?
- እሱ ትክክል ነው ነገር ግን አማፂው ቡድን በተለመዱት አካባቢዎች ነዋሪዎች ላይ የአጠፋ ጥቃት እንደሚሰነዝር ታስቦ ጥበቃ መደረግ ነበረበት የሚል ወቀሳ ነው ማኅበረሰቡ የሚያነሳው።
- እየታገልነው ያለው ታጣቂ ርህራሄ ያልፈጠረበት መሆኑን አትዘንጋ እንጂ። አልሰማህም እንዴ መንግሥት የገለጸውን?
- ምን?
- ይህ ቡድን ሰሞኑን በአንድ አዛውንት ላይ ስለፈጸመው ጭካኔ?
- ምን አደረገ?
- ልጃቸው የዚህ ቡድን አባል መሆኑን ያወቁ አንድ አባት ነገሩን ለመንግሥት በማሳወቅ በግቢያቸው የተቀበረ የጦር መሣሪያም እንዲወጣ ያስደርጋሉ።
- አዎ። ስለዚህ ጉዳይ ሲገለጽ ሰምቻለሁ።
- ሰምተሃል አይደል? አባት መጠቆማቸውን የሰማው ልጃቸው አባቱን ከነቤታቸው ነው ያቃጠለው።
- ክቡር ሚኒስትር መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት እያስጠበቀ አይደለም ተብሎ የሚወቀሰው ለዚህ ነው።
- እንዴት?
- እኚህ አባት ኃላፊነታቸውን ሲወጡ መንግሥት ግን ኃላፊነቱን አልተወጣም።
- መንግሥት ምን ማድረግ ነበረበት?
- አባት ልጃቸው ማመጹን በማሳወቅ የቀበረውን የጦር መሣሪያ ለመንግሥት እንደጠቆሙ፣ አማፂው ቡድን ሲሰማ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ከባህሪው አንፃር መገመት ቀላል ነው።
- እና?
- ስለዚህ መንግሥት ኃላፊነታቸውን ለተወጡት አባት ጥበቃ በማቆም ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባ ነበር።
- መንግሥት ይህ እንደሚከሰት አላወቀማ?
- ማወቅ ነበረበታ ክቡር ሚኒስትር። መንግሥት አይደል እንዴ?
- እሱስ ልክ ነው።
- እሱ ብቻ አይደለም ክቡር ሚኒስትር?
- ሌላ ምን አለ?
- እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ በፍፁም ለሕዝብ መገለጽ አልነበረበትም።
- ለምን?
- ይህንን ክስተት እንዲሰማ የተደረገ ማኅበረሰብ ፍርሃት ውስጥ ነዋ የሚወድቀው። ይህ ብቻ አይደለም…
- እ…
- ነግ በእኔ ብሎ ማኅበረሰቡ እንዲሰጋና መንግሥትን እንዳይተባበር የሚያሰንፍ መረጃ ነው።
- እህ…
- እንዲህ ዓይነት መረጃ በፍፁም መለቀቅ አልነበረበትም።
- መንግሥት ነገሩን በዚህ መንገድ የተረዳው አልመሰለኝም።
- ግን መረዳት ነበር።
- ኦ….ኦ እንደዚያ አልተረዳነውም በቃ! ደግሞ ተጠንቀቅ?
- ምን አጠፋሁ ክቡር ሚኒስትር?
- እንዲህ ያለ ነገር ሌላ ቦታ እንዳታወራ!
[ክቡር ሚኒስትሩ የእረፍት ቀናቸውን ከመኖሪያ ቤታቸው ሳይወጡ ማሳለፋቸው ግራ ያጋባቸው ባለቤታቸው መጠየቅ ጀመረዋል]
- ዛሬ ከቤትም አልወጣህ በሰላም ነው?
- ሰላም ነው ትንሽ ዕረፍት ማድረግ አስፈልጎኝ ነው።
- ግን ዕረፍት እያደረክ አይመስልም?
- እንዴት?
- ለረዥም ሰዓት ፀጥ ብለሃል … ያሳሰበህ ነገር አለ እንዴ?
- እረ በጭራሽ። የለም!
- ለነገሩ መጠየቅ አልነበረብኝም።
- ለምን?
- በርካታ ችግርና ቀውስ ያለበት አገር አመራር ሆኖ አለመጨነቅና አለማሰብ አይቻልም ብዬ ነው።
- እረ በጭራሽ። ዕረፍት ማድረግ አሰኝቶኝ ነው እያልኩሽ?
- እንዲያውም ዛሬ ልጠይቅ እስኪ?
- ምን? ጠይቂኝ።
- አሁን ካለንበት ሁኔታ እንቅልፍ የሚነሳህ የሚያሳስብህ ነገር ምንድን ነው?
- ጭራሽ እንቅልፍ የሚነሳ ነገር? እውነት እልሻለሁ ምንም የሚያሳስበኝ ነገር የለም።
- በአገሪቱ ብዙ ችግር እያለ እንዴት የሚያሳስብህ ነገር አይኖርም? ቢያንስ እያሻቀበ ያለው የኑሮ ውድነትና የሕዝቡ ችግር አያሳስብህም?
- የኑሮ ውድነት በኢትዮጵያ ብቻ የተከሰተ ችግር እኮ አይደለም?
- እንዴት?
- ተመልከች አሜሪካን። ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ገጥሟቸዋል። አውሮፓውያኑም ቢሆኑ በነዳጅ አቅርቦት ችግርና በዋጋ ግሽበት እየተሰቃዩ ነው።
- የእኛ አገር ግን የተለየ ነው።
- ግሽበት ግሽበት ነው፣ በምን ይለያል?
- እኛን ግሽበት ብቻ አይደለም እየፈተነን ያለው። በየአካባቢው ሰላምና መረጋጋት የለም፣ ዜጎች ያለምክንያት ይገደለሉ … ብዙ መከራ አለ?
- ልክ ነው ግን ሌሎች አገሮችም በተመሳሳይ እየተሰቃዩ ነው። ለምሳሌ ሰሞኑን በጃፓን የተከሰተውን ተመልከች።
- ጃፓን ምን ተከሰተ?
- የቀድሞ የአገሪቱ መሪ በአደባባይ ንግግር እያደረጉ ነው በጥይት የተገደሉት። በአውሮፓም ተመሳሳይ ችግር ነው ያለው።
- እሱ ድንገተኛ ክስተት ነው። በዚያ ላይ እነሱ የተረጋጋ ፖለቲካ ውስጥ ነው ያሉት።
- አይምሰልሽ። የተረጋጋ ፖለቲካ ቢኖር የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ለምን ከሥልጣን ይወርዳሉ? ሩቅ ሳትሄጂ በሱዳን ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት አታስተውይም?
- በል ተወው!
- ለምን? ምነው?
- የእኔ ጥያቄ ስለኢትዮጵያ ነበራ?
- እና?
- አንተ ግን እየመለስክልኝ ያለኸው ስለሌላ አገር ነው።
- እያነፃፀርኩልሽ እኮ ነው?
- አይ ይቅርብኝ። ባትመልስልኝም ይገባኛል።
- ምኑ ነው የሚገባሽ?
- አትናገረውም እንጂ የአገራችን ሁኔታ በጣም እንደሚያሳስብህ ይገባኛል።
- እንዴት?
- እንደሚያሳስብህ ብቻ ሳይሆን፣ ከሚያስጨንቅህ ሐሳብ ምን እረፍት እንደሚሰጥህ አውቃለሁ።
- ምንድን ነው?
- ችግኝ መትከል።