Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየብልፅግና መንግሥት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በጥልቀት ሲፈተሽ

የብልፅግና መንግሥት የፖለቲካል ኢኮኖሚ ፖሊሲ በጥልቀት ሲፈተሽ

ቀን:

በኢዮብ አሠለፈች ባልቻ

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥት የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ክፍት ለማድረግ (ሊበራላይዜሽን)፣ የሕዝብና የአገር ሀብትና ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ (ፕራይቬታይዜሽን) እያደረገ ያለውን ከፍተኛ ጥረት በጥልቅ መፈተሽና መንቀስ ነው። እንደ መግቢያ እንዲሆን ይህን የብልፅግና መንግሥት ዋና የፖሊሲ አቅጣጫ የርዕዮተ ዓለማዊ፣ የገንዘብና የሰው ኃይል ድጋፍ ከሚሰጡት ከዓለም ባንክና ከዓለም የገንዘብ ድርጅት አንፃር፣ ከኢሕአዴግ መንግሥት በ1980ዎቹ መጨረሻና በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ የነበራቸውን ግንኙነት አሳያለሁ። በመቀጠል የብልፅግና መንግሥት የሊበራላይዜሽንና የፕራይቬታይዜሽን ፖሊሲዎች በዕውቀት፣ በጥናትና በመረጃ የተደገፉ አለመሆናቸውን፣ ይልቁንም ውስን ዕይታ ባለው ዋልታ ረገጥ ርዕዮተ ዓለማዊ ታማኝነት የሚመሩ መሆኑን በማሳያ ለማስረዳት እሞክራለሁ። ይህንን አጭር ምልከታ እንደ መግቢያ በመጠቀም በቀጣይ ጽሑፎች ደግሞ አጠቃላይ የሸቀጣ ሸቀጥ ንግዱን ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የመክፈት አዝማሚያን፣ የባንክና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውንና በቴሌኮም ዘርፍ ላይ እየተደረጉ ያሉ ከፍተኛ መዘዝ የሚያስከትሉ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለዓለም አቀፍ ገበያ የመክፈትና (ሊበራላይዜሽን) የሕዝብና የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ የማዛወር (ፕራይቬታይዜሽን) ፖሊሲ አቅጣጫዎችን በጥልቀት በማየት፣ ሊነሱ የሚገቡ ጥያቄዎችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ኢትዮያና ዓለም የገንዘብ ድርጅት

የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ ሥልጣን ሲመጣ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅትና በዓለም ባንክ ከፍተኛ ተቀባይነትን ወዲያው እንዳገኘ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩና የብልፅግና ፓርቲ ሰዎች አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ የሚሉት፣ ነገር ግን ምዕራባውያን መንግሥታትና የዓለም ባንክን የመሰሉ ድርጅቶች እስከ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ብድርና የገንዘብ ድጋፍ ያደረጉበት አገራዊ የልማት ዕይታን ከልማታዊ መንግሥት አካሄድ ወደ ገበያ ተኮር አመለካከት የተቀየረበት ሒደት አንዱና ዋና ማስረጃ ነው። የመልካም ወዳጅነቱ ዋና ማጠንጠኛ የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት አራምዳለሁ ብሎ ቃል የገባው የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለዓለም የገበያ ሥርዓት ክፍት የማድረግ ወይም የሊበራላይዜሽን ፖሊሲ ነው። በልማታዊ መንግሥት ዕይታ ሲመራ የቆየውን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ ሲተቹና በፍጥነት ወደ ገበያ መር ኢኮኖሚ መገባት አለበት እያሉ ሲወትውቱ ለከረሙት፣ ለእነዚህ የዓለም የከበርቴው መደብ ዋና አጋፋሪዎች የዓብይ (ዶ/ር) መንግሥት አቋም ጮቤ የሚያስረግጥ ነበር።

የዓለም የገንዘብ ድርጅትና የዓለም ባንክ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠርና የገበያን የበላይነት የሚያስረግጥ ሥርዓት በኢትዮጵያ ለማስፈን ያላቸው ቁርጠኝነት ተቀይሮ አያውቅም። የሚቀያየረው በአገራችን የበላይነትን የሚይዘው ዋናው የፖለቲካ ኃይል አመለካከትና አሠላለፍ ነው። ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት በኋላ ዋናውን ሥልጣን የተቆጣጠሩት ግለሰቦችና (አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ዶ/ር ዓብይ አህመድ) ዋና ዋና አማካሪዎቻቸው ኢትዮጵያን በይበልጥ በዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ከበርቴዎች ቁጥጥር ሥር እንድትሆን ጉልህ ሚና ተጫውተዋል፣ እየተጫወቱም ነው።

ለዚህ አንድ ማስረጃ የሚሆነን ተጨባጭ ታሪካዊ ሒደት ሮበርት ዋድ (Robert Wade) በሚባል የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ምሁር የተጻፈ፣ “Capital and Revenge: the IMF and Ethiopia” የሚል እ.ኤ.አ. በ2001 ዓ.ም. የተጻፈ ምጥን ጽሑፍ ነው። የጽሑፉን ዋና ሐሳብ ከዚህ በታች አሳጥሬ አቀርባለሁ። በ1980ዎቹ መጨረሻ እንዲህ ሆነ። ኢትዮጵያ የተራዘመ የመዋቅር ማሻሻያዎችን በመተግበር የዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋም ያስቀመጣቸውን ቅድመ ሁኔታዎች በማሟላት፣ ብድር እንደሚሰጣት የተደረገ ድርድር ነበር። የድርድሩ ዋነኛ መለኪያዎች የመንግሥት የበጀት ጉድለትን መቀነስ፣ የመንግሥት ግምጃ ቤት ሰነዶች ገበያ ማቋቋም፣ የባንኮች የወለድ ምጣኔ በገበያ እንዲወሰን ማድረግና ወደ አገር ውስጥ የሚገባና የሚወጣ ገንዘብ ላይ የሚኖርን ቁጥጥር ማስወገድን ያካትታል። የእነዚህ ፖሊሲዎች ጥቅል ዓላማ ከኒዮሊበራል ርዕዮተ ዓለም መርሆዎች የሚቀዳ ሲሆን፣ መንግሥት የዜጎቹን ሁለንተናዊ ፍላጎቶችና የልማት ተጠቃሚነት ለሟሟላት የሚያደርጋቸውን የትኛውንም ዓይነት የፖሊሲና የሕግ ማዕቀፎችን በማስወገድ ገበያው አስፈላጊ የሆነውን የሀብት ክፍፍል እንዲያደርግ ማመቻቸት ነው። በጊዜው በጦርነት፣ በዓለም አቀፍ የኃይል ሚዛን መለወጥና በውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ ኢኮኖሚያቸው ችግር ውስጥ የገቡ አብዛኛው የአፍሪካ አገሮች ከችግሮቻቸው ለማገገም ሲሉ በቅድመ ሁኔታዎች የታጠረ የገንዘብ ድጋፍ ያገኙበት የነበረ ጊዜ ነው።

ከ17 ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት በቅጡ ያላገገመው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበረው የኢሕአዴግ መንግሥት በወሰዳቸው ብዙም መረን የለቀቁ ዕርምጃዎች ከሶሻሊስት የኢኮኖሚ እየወጣ ነበር። የመጀመሪያው የመዋቅር ማሻሻያ ስምምነት ከተደረሰና የታሰቡት ፖሊሲዎች በሚደረጉበት ጊዜ ውስጥ ግን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የዓለም አቀፍ ከበርቴዎቹን ያላስደሰተ ዕርምጃ ወሰደ። እሱም የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሜሪካ ከሚገኝ ባንክ ተበድሮ የገዛቸው አራት አውሮፕላኖችን በተመለከተ የወሰደው ዕርምጃ ነው። ለአየር መንገዱ ብዙም ምቹ ያልሆነውን የብድር ስምምነት ሰበብ አድርጎ አውሮፕላኖቹን ለመውረስ ያሰፈሰፈው የአሜሪካ ባንክ፣ በብድር አከፋፈሉ ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ለመደራደር ፈቃደኛ አልነበረም። የባንኩ አካሄድ ያላማረው የኢትዮጵያ መንግሥት ለአየር መንገዱ ሙሉ ለሙሉ ብድሩን የሚከፍልበት ገንዘብ በማበደር ነገሩ እንዲቋጭ ያደርጋል። ያበደሩትን ገንዘብ ከማስመለስ በላይ ዓላማ የነበራቸው የአሜሪካው ባንክ ኃላፊዎች በነገሩ ባለመደሰታቸው ለአሜሪካ ግምጃ ቤት አቤቱታ ያቀርባሉ። የአሜሪካ ግምጃ ቤት ደግሞ ወደ ገንዘብ ድርጅቱ ስሞታውን ያሰማል። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ኃላፊዎችም የኢትዮጵያን የመዋቅር ማሻሻያ ተግባራት በመገምገም ሒደትና በሚፈቀደው ብድር ላይ ያላቸውን የወሳኝነት ሚና ተጠቅመው፣ የአሜሪካኖቹን በኢትዮጵያ መንግሥት የመከፋት ስሜት ማንፀባረቅ ጀመሩ። ለቀጣይ ብድር ከነበሩት ቅድመ ሁኔታዎች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ክምችትን ማሳደግ ነበረ። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ለአየር መንገዱ ገንዘብ ስላበደረ በጊዜው የነበረው የውጭ ምንዛሪ ክምችት ከታቀደው በታች ነበረ። ብድሩ ተመላሽ በሚሆንበት ጊዜ የሚፈለገውን መጠን ማሟላት ቢችልም፣ የገንዘብ ደርጅቱ ዓላማ ሌላ ስለነበረ ይህን ከግምት ውስጥ መክተት አልፈለገም።

የገንዘብ ድርጅቱ ምላሽ ሁለት ዋና ነገሮች ላይ ያተኮረ ነበር። አንደኛው ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ምንዛሪውን ለምን ጉዳይ እንደሚጠቀምበት ከገንዘብ ድርጅቱ ፈቃድ ማግኘት አለበት›› የሚል የአገርን ሉዓላዊነት የሚፃረር ምላሽ ነው። ሁለተኛው ተያያዥ ምላሽ ደግሞ ቀጣይ የገንዘብ ድጋፍ ለመቀበል ተጨማሪ መደረግ ያለባቸው የፖሊሲ ለውጦችን ማስቀመጥ ነው። እነዚህም መንግሥት አገራዊ የሀብት መዝገቡን (Capital Account) ክፍት እንዲያደርግና የወለድ መጠንም ሆነ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ ዋጋ እንዲወሰኑ በቶሎ የማድረግ ዕርምጃ ዋነኞቹ ናቸው። በተጨማሪም የአገሪቱን የባንክና የፋይናንስ ሥርዓቱን ለገበያ ክፍት እንዲያደርግና የግምጃ ቤት ሰነድ ገበያ እንዲቋቋም የሚሉ ናቸው። በኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ያልተደሰቱት የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ተደራራቢ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ፣ የኢትዮጵያን ፖለቲካል ኢኮኖሚ በቶሎ የሚቆጣጠሩበትን መላ እያበጁ ነበር።

ይህን ለመሰለ የፖሊሲ ጫና ዝግጁ ያልነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ነገሮች ከልክ ማለፋቸውን በመረዳት የገንዘብ ድርጅቱን ኃላፊዎች ‹‹በቃ›› በማለት የውይይት ሒደቱን አቆመ (በጊዜው በስብሰባው ተሳታፊ ከነበሩ ሰዎች የሚነገረው እንዲያውም የገንዘብ ድርጅቱ ተሳታፊዎች ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በወጣ ቀጭን ትዕዛዝ በቀጥታ ወደ አየር ማረፊያ ተወስደው ከአገር እንዲወጡ መኪና በፍጥነት እንዲዘጋጅላቸው የሚል ነበር)። በጊዜው በገንዘብ ድርጅቱ ውስጥ የነበረውን አክራሪ ገበያ አምላኪነት ይገዳደሩ የነበሩ ሰዎች፣ በተለይ በዓለም ባንክ ውስጥ መኖራቸው ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል ፈጥሯል። በኢትዮጵያ በነበረው የዓለም ባንክ ቢሮ ውስጥ ይሠራ የነበረ ባለሙያ የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ያደረጉትን አላስፈላጊ ጫና በመረዳት፣ በጊዜው የዓለም ባንክ ዋና ኢኮኖሚስት የነበረው ጆሴፍ ስቲግሊዝን (Joseph Stiglitz) ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ጉዳዩን ከሥሩ እንዲመለከትና አስፈላጊውን ዕገዛ እንዲያደርግ ይጋብዘዋል። ጆሴፍ ስቲግሊዝ በጊዜው የነበረውን መረን የለቀቀ የኒዮሊበራል ርዕዮተ ዓለም ይገዳደር የነበረ ጎምቱ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ሲሆን፣ የነበረበትን ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ከልክ ያለፈ ገበያ አምላኪነትን ለመግራት ይጠቀምበት ነበር።

ጆሴፍ ስቲግሊዝም በ1990 ዓ.ም. አጋማሽ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረውን የመንግሥት የልማት ዕቅድና አጠቃላይ አቅጣጫ በመገምገምና የሚችለውን ሙያዊ ዕገዛ በማድረግ ጭምር፣ ከገንዘብ ድርጅቱ ጋር በበለጠ አቅም ለመደራደር የሚያስፈልገውን ሰነድና ሥልት ከኢትዮጵያ መንግሥት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ጋር ሆኖ ያዘጋጃል። በቀጣይም በጊዜው የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ለነበረው ጀምስ ዎልፈንሰን ኢትዮጵያን የሚመለከት ሪፖርት በማዘጋጀት፣ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ ሁኔታዎችን ያመቻቻል። በጥር 1990 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ የመጣው የዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት ከመንግሥት ጋር የነበረው ውይይት ላይ የተራዘመ የመዋቅር ማሻሻያ መርሐ ግብርና ቃል የተገባው ርካሽ ብድር ዋነኛ አጀንዳ እንዲሆን ጆሴፍ ስቲግሊዝ ከፍተኛውን ሚና ተጫውቷል። ፕሬዚዳንቱ ወደ ዋሽንግተን ከተመለሰ በኋላ ከገንዘብ ድርጅቱ መሪዎች ጋር ጉዳዩን በተደጋጋሚ በማንሳት የተቋረጠው ብድር ለኢትዮጵያ እንዲለቀቅ በሚያዝያ 1990 ዓ.ም. አዲስ መርሐ ግብር እንዲጀመር ምክንያት ሆኗል። ጆሴፍ ስቲግሊዝ በወቅቱ ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ጋር የነበረውን ውይይት ሲያስታውስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ለ17 ዓመታት ያህል በበረሃ የተዋጋሁት የዓለም አቀፍ ቢሮክራቶች ለአገሬ ሕዝብ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ፈቃድ ለመለመን አይደለም፤›› ብለው መልሰውልኛል በማለት ‹‹Globalisation and its Discontents›› በሚለው መጽሐፉ ላይ ጠቅሶታል።

አዲሱ ድርድር በሚደረግበት ወቅት የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሀብት መዝገብ ክፍት እንዲሆንና በዓለም ገበያ ሒደት እንዲወሰን አስቀምጦት የነበረውን አቋም እንዲቀይር የሚያስገደድ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። እ.ኤ.አ. በ1997 በምሥራቅ እስያ አገሮች ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ አንደኛው ገፊ ምክንያት፣ የገንዘብ ድርጅቱ የአገሪቱ ብሔራዊ የሀብት መዝገብ ለገበያ ክፍት እንዲሆን ያደረገው ጫና መሆኑ በማስረጃ የቀረቡ ጥናቶች ነበሩ። በመሆኑም በኢትዮጵያ መንግሥት የቀረበውን በጥንቃቄ የተሞላ አካሄድ ለመቀበል ተገዶ ነበር። በመጀመሪያ ዙር የተቀመጡ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ግቦችን በሚገባ ያሳካው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በቀጣዩ ዓመት ለሌላ ድርድር ዋሽንግተን ሲደርስ ግን የገጠመው ምላሽ ያልተጠበቀ ነበር። እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጡ መለኪያዎች ቢሳኩም፣ የኢትዮ-ኤርትራን ጦርነት ምክንያት አድርገው ኢትዮጵያ ልታገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እንዲቋረጥ አደረጉ።

 ለብድሩ መከልከል ዋነኛ ምክንያት የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ከገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ለመጣው ጫና ያሳየው ዕንቢተኝነት ነበር። ለዚህ ማስረጃ የሚሆነው መንግሥት ተስማምቶበት የነበራቸውን የመዋቀር ማሻሻያ ጉዳዮች በተገቢው መንገድ አሳክቶ የነበረ ቢሆንም፣ የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ኢትዮጵያን በተመለከተ ይሰጡት የነበረው የተዛባ መረጃ ነበር። የበቀል ስሜት በሚመስል ከፍተኛ የዕዳ ጫና የነበረባቸው አገሮች የሚያገኙትን ዕድል ኢትዮጵያ እንዳትጠቀም እስከ መከልከል ድረስ የሄደ ተግባር የዓለም የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ፈጽመዋል። በተቃራኒው ያለ ምንም ማንገራገር የገንዘብ ድርጅቱን የፖሊሲ ትዕዛዝ የተቀበሉ አገሮች ግን አፈጻጸማቸውና የልማት ዝግጁነታቸው ምንም ውኃ ባያነሳ እንኳ ድጋፍ ይደረግላቸው ነበር። የገንዘብ ድርጅቱ ኃላፊዎች ሌላው ትልቁ ግባቸው ደግሞ፣ በተለይ ሌሎቹ የአፍሪካ አገሮች የኢትዮጵያን ፈለግ ተከትለው የፖሊሲ ጫናዎችን አንቀበልም እንዳይሉና ይህ ዓይነት አለመታዘዝ የሚያመጣውን መዘዝ እንዲያስቡበት ነው።

የብልፅግና መንግት ፖሊሲዎች ምን ያህል የታሰበባቸው ናቸው?

ይህ ሁለት አሠርት ዓመታት ያለፈው ታሪክ በአሁኑ ጊዜ በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ የፖሊሲ ውሳኔዎችን በጥልቅ ለመፈተሽ ያግዛል። የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ዋነኛ ርዕዮተ ዓለማዊ ግባቸው የዓለም ከበርቴዎች የሚቆጣጠሯቸው ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች፣ ድርጅቶቹን ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የሚደግፏቸውን የምዕራባውያን አገሮችን የፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ዕውን ማድረግና በበለጠ የበላይነት እንዲዘልቅ ማድረግ ነው። ለዚህ የሚጠቀሙት ደግሞ የገበያ ሥርዓትና የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ዋነኛ የፖለቲካ ኢኮኖሚ መሪዎች እንዲሆኑ በማድረግ፣ በዚህ ሒደት ውስጥ ደግሞ ያላቸውን ከፍተኛ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ የበላይነት ተጠቅመው ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ትርፍ ማካበትን ነው። ለዚህም እንዲረዳ በተለይ የአፍሪካ መንግሥታት የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ዕመርታና ዕድገትን የመወጠን፣ የመምራትና የመቆጣጠር አቅም እንዳይኖራቸው ከፍተኛ ጫና ያደርጋሉ። ለዚህም እንዲረዳ አስተሳሰባቸውን ለማስረፅ የፕሮፓጋንዳ፣ የትምህርት፣ የመገናኛ ብዙኃንን፣ የመንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን አስፈላጊ ሲሆን ደግሞ ወታደራዊ ኃይልን ይጠቀማሉ። የእነሱን የሊበራላይዜሽን አጀንዳ ሳያቅማማ ተቀብሎ ለመተግበር ዝግጁ ለሆነ መንግሥት ደግሞ ከልክ ያለፈ እንክብካቤ፣ ዕውቅናና መወደስ ይሰጣሉ።

ታሪካዊ መረጃዎች የሚያሳዩት ሀቅ ግን መንግሥታዊ አመራርና የማስፈጸም አቅም ከፍተኛ ወሳኝ የልማት ኃይል እንደሆነ ነው። በየትኛውም የዓለማችን ክፍል በመንግሥት የደረጀ አቅም ሳይደገፍ ያደገ የግል ክፍለ ኢኮኖሚ የለም። ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ የሚቻለው በገበያ አመክንዮ ብቻ ሳይሆን፣ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ማነቆዎችን በመንግሥታዊ አሠራር በመጣስ ጭምር ነው። የመንግሥትን ሀብት የመቆጣጠርና የማከፋፍል ሚና በአግባቡ ሳይጠቀም ኢኮኖሚውን ያበለፀገ አንድም አገር በዓለማችን የለም። ከምዕራብ አውሮፓውያን የኢንዱስትሪ አብዮት ጀምሮ የአሜሪካ የኢኮኖሚ ብልፅግና፣ የሰሜን አውሮፓ አገሮች ዕድገት፣ የሩቅ ምሥራቅና የደቡብ ምሥራቅ እስያ አገሮች የፖለቲካል ኢኮኖሚ ታሪክ የሚያሳየው ይኼንን ሀቅ ነው። ደቡብ ኮሪያዊው የኢኮኖሚ ሊቅ ሃጁን ቻንግ እንደሚለው፣ ምዕራባውያኑ ታሳቢ የተደረገው የኢኮኖሚ ዕምርታ ላይ ከወጡ በኋላ ሌሎች አገሮች ወደ ዕምርታው እንዳይደርሱ መወጣጫውን የመገፍተር (Kicking Away the Ladder) መንገድ ነው እየተከተሉ ያሉት። ይህንን ደግሞ ዕውን የሚያደርጉት በዓለም ባንክ፣ በዓለም የገንዘብ ድርጅትና በዓለም የንግድ ድርጅት በመሳሰሉ የምዕራባውያን ጥቅም አስከባሪ ድርጅቶችና ይህን ርዕዮተ ዓለም በሚቀበሉ የአፍሪካ መንግሥታት አማካይነት ነው።

የብልፅግና መንግት ገበያ አምላኪነት

ዓብይ (ዶ/ር) ሥልጣን ላይ በወጡ በዘጠነኛ ወራቸው (ጥር 2011 ዓ.ም.) የዓለም ከበርቴዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው የሚሰበሰቡበት በዴቮስ ስዊዘርላንድ የዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ ሄደው፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ መቆጣጠሪያ የከፍታ ሥፍራ የሆኑትን ድርጅቶች ለዓለም ገበያ ለሽያጭ እናቀርባቸዋልን ሲሉ ያደረጉት ንግግር፣ በግለሰብም ሆነ በመንግሥት ደረጃ ያላቸውን የኒዮሊበራል አቋም ያሳያል። ከ17 ዓመታት ጦርነት በቅጡ ያላገገመ ኢኮኖሚን ለመቀራመት አስበው ያልተሳካላቸው የዓለም ከበርቴዎችና ደጋፊ መንግሥቶቻቸው፣ አሁን በብዙ እጥፍ አድጎና በልፅጎ ያለውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር ሰፊ ዕርምጃ ጀምረዋል። ይህን ለማድረግ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወትላቸው ደግሞ  ዓብይ (ዶ/ር) የሚመሩት መንግሥትና የከበርቴዎችን ዕይታና ፍላጎት የሚያራምዱት የፖሊሲ አማካሪዎቻቸውና ባለሙያዎቻቸው ናቸው።

የብልፅግና መንግሥት የኒዮሊበራል ፖሊሲን ሳያቅማማ እንደተጋተው ማሳያ የሚሆኑ ብዙ ማስረጃዎች አሉ። አንደኛው ማስረጃ ያለ ምንም ጥናትና ግምገማ (ቢያንስ ለሕዝብ ግልጽ የተደረገ ጥናት የለም) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዴቮስ ስዊዘርላንድ ያደረጉት ንግግርና ከዚያ በኋላ ለጊዜውም ቢሆን ትተነዋል የተባሉት ዋና ዋና የአገር ሀብት የሆኑ ተቋማትን የመሸጥ ጉዳይ ነው። ሌላው ማስረጃ ደግሞ በአዲሱ ፓርላማ የተሾሙ ሚኒስትሮችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ ነው። በትምህርት ሚኒስትርነት የተሾሙትን ብርሃኑ ነጋን (ፕሮፌሰር) ለዘርፉ ካላቸው ዝግጁነትና ዕውቀት ከኢኮኖሚ ባለሙያነት አንፃር ከኢኮኖሚው ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ቦታ ላይ ለምን አልተሾሙም ለሚለው ጥያቄ፣ ዓብይ (ዶ/ር) የሰጡት ምላሽ ብዙ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአደጉት አገሮች የትምህርት ሚኒስቴር የላቸውም የግሉ ዘርፍ ነው የሚወጣው። በአደጉት አገሮች የጤና ሚኒስቴር የሚባል የላቸውም የግሉ ዘርፍ ነው የሚመራው፤›› የሚል ነበር።

ይህ ምላሽ ቢያንስ ሁለት ነገሮችን ያሳያል። አንደኛ ዓብይ (ዶ/ር) ‹‹ያደጉት አገሮች›› የሚሏቸውን አገሮች መንግሥታት እንዴት እንደተዋቀሩ፣ ምን ምን ዓይነት የሥራ ክፍፍል በአስፈጻሚው አካል ደረጃ እንዳለ ያላቸው ዕውቀት በጣም በከፍተኛ ደረጃ ውስን እንደሆነ ያሳያል። ያው መቼም የአደጉት አገሮች ሲባል ብዙ ሰው የሚጠራው አሜሪካ ወይ የአውሮፓ መንግሥታትን ስለሆነ፣ በእነዚህ አገሮች ያሉትን የትምህርትና ጤና ዘርፍ የሚከታተሉትን የመንግሥት ተቋማትና ሚኒስቴሮች ማንሳት ይቻላል። ሁለተኛ ምናልባትም በጣም ትልቁ አሳሳቢ ጉዳይ ግን ያለው በዓብይ (ዶ/ር) ንግግር ውስጥ ያለው መንግሥት በዜጎች ሁለንተናዊ ሕይወት ውስጥ የሚኖረውን ሚና የማሳነስና አስፈላጊነቱን የማጣጣል፣ በተቃራኒው ደግሞ ለትርፍ የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶችን ሚና ከልክ በላይ የሚያጎላው አስተሳሰብ ነው። የኒዮሊበራል አስተሳሰብ የበላይነትን ለማግኘት ከሚጠቀምባቸው መንገዶች መካከል መንግሥትን ማንቋሸሽ፣ አስፈላጊነቱን ማጣጣል፣ ችግር ፈጣሪና የተግዳሮት ምንጭ ብቻ አድርጎ መበየንና መሰል ትርክቶችን ማጉላት ዋነኛው ነው። በተቃራኒው ደግሞ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ የሚባለውን የከበርቴዎቹን ሚና አግዝፎ መሣል፣ የገበያ ውድድር ለሁሉም ዜጎች የተሻለ ሁለንተናዊ አዎንታዊ ለውጥ እንደሚያመጣ መስበክ፣ የኅብረተሰብ የጋራ እሴቶች ሳይሆን የግለሰቦች የአሸናፊነት፣ የብልፅናና የተወዳዳሪነት ሚና ይበልጥ ሊዳብር እንደሚገባ መወትወት ደግሞ ሌላው ተረክ ነው። የእነዚህ አስተሳሰቦች ድምር ውጤት የመንግሥታትን አወቃቀር፣ የሀብት ክፍፍል ቀመርን፣ የፖሊሲዎችን መርሆዎችና ዓላማዎች፣ ከዚያም አለፍ ብሎ የሰዎችን ባህሪ፣ ተግባራትና በኅብረተሰብ ውስጥ ያለውን ገዥ ሐሳብ ለዓለም አቀፍ ከበርቴዎችና ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶቻቸው ምቹ እንዲሆን ማድረግ ነው።

ማጠቃለያ

ለማጠቃለል እንዲረዳ ሁለት ነጥቦችን ላንሳ። አንደኛ ዓለም አቀፉ የከበርቴዎች መደብ (ድንበር ተሻጋሪ ድርጅቶች፣ በተለይ ምዕራባውያን አገሮች፣ የመገናኛ ብዙኃኖቻቸው፣ የአማካሪነትና የወትዋችነት ሚና የሚጫወቱት መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶቻቸው፣ ወዘተ) ሁሉም ማለት ይቻላል ኢትዮጵያን የሚያዩት እንደ አንድ ከፍተኛ የገበያ ዕድል የሚያገኙባትና ጂኦፖለቲካል ጥቅም ያላት አገር አድርገው ነው። ለዚህ ምኞታቸው ማሳኪያ የሚጠቀሙት ዋነኛው መንገድ የኢትዮጵያ መንግሥት የእነሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ የፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ሥርዓት እንዲተገብር በማገዝ፣ በማሳመንና በማስገደድ ነው። ይኼ አካሄድ ድሮም የነበረ ነው፣ አሁንም ይቀጥላል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ካሉብን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶች በተጨማሪ፣ ይህንን የአገርን ሉዓላዊነት የሚያሳጣ በተለይ ደግሞ ለባሰ ኢኮኖሚያዊ ድህነትና ለከፍተኛ አገራዊ ብዝበዛ የሚያጋልጥ አካሄድን አውቀን ልንገዳደረው ይገባል።

በሁለተኛ ደረጃ የብልፅግና መንግሥት ከምርጫው በፊትም ሆነ በኋላ እየሄደባቸው ያላቸውን አካሄዶች በጥልቀት ሊፈትሽ ይገባል። የመንግሥትን ሀብት የማመንጨት፣ የማከፋፈልና የመቆጣጠር አቅም አብዛኛውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጥተኛ ተጠቃሚ ሊያደርግ በሚያስችል አኳኋን መምራት ሲገባ፣ ውስን የሆኑ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ከበርቴዎችን የበላይ ተቆጣጣሪና ዋነኛ ተጠቃሚ የሚያደርግ አካሄድ መከተል ከፍተኛ ስህተት ነው። የአገራችን ዋነኛ የፖለቲካል ኢኮኖሚ ማነቆ ያለው የምርታማነት አቅማችንን የሚያሳድጉ ልማታዊ ሥርዓታት አለመኖር፣ ያሉት ሥርዓታት ውስንነትና በቂ ካፒታል አለመኖሩ ነው። ይህንን መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ችግር በፕራይቬታይዜሽንና በሊበራላይዜሽን ለመፍታት መሞከር የችግሩን ጥልቀትና ውስብስነት ካለመረዳት የሚመነጭ ነው። መንግሥታዊ የማስፈጸም አቅም ሊጎለብትና ለሕዝቡ የሚገባውን የልማት ትሩፋት ማስገኘት ሲገባው ለነጋዴዎች አመቻች ሆኖ መገኘት የለበትም። ስለዚህም መንግሥት ፖሊሲዎቹን በደንብ ደጋግሞ ሊፈትሻቸው ይገባል።

በቀጣይ ጽሑፌ አጠቃላይ የሸቀጣ ሸቀጥ ንግዱን ለዓለም አቀፍ ኩባንያዎች የመክፈት አዝማሚያን፣ የባንክና ኢንሹራንስ ኢንዱስትሪውንና በቴሌኮም ዘርፍ ላይ እየተወሰዱ ያሉ ቁጥጥርን የማላላት (ዲሬጉሌሽን)፣ ለዓለም የገበያ ሥርዓት የመክፈት (ሊበራላይዜሽን) እና ወደ ግል ይዞታ የማዛወር (ፕራይቬታይዜሽን) ሒደቶችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው ebalcha@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...