Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ግራ ግብት ሲለንስ!

ሰላም! ሰላም! ክረምቱና ቅዝቃዜው እንዴት ይዟችኋል? የዘንድሮ ክረምት ጫን ያለ ነው የሚል ትንበያ የሰማ አንዱ የእኔ ቢጤ ደላላ፣ ‹‹ከረምናታ… ከረምናታ…›› እያለ ፈርቶ ሊያስፈራራን ሲሞክር፣ ‹‹ሰውዬ ይኼ ያንተ ነጠላ ዜማ በፉከራ ወይስ በሽለላ ዘርፍ እንመድበው?›› ብሎ አንዱ አስታገሰልን፡፡ አንዳንዴ እኮ ተናጋሪ ያስፈልገናል፡፡ ያኔ በአብዮቱ ዘመን፣ ‹‹ሞት ተረማመደ… ሞት ተረማመደ…›› እያለች ጓዳ ጎድጓዳውን ትንጎራደድ የነበረችው ሴት አርጅታ ዛሬም አለች አሉ። ለነገሩ ‹ሰው የሚሞተው ሞትን የፈራ ቀን› ነው ይባላል። አንዳንዶች በተለይ የአንዳንዱን ዕድለ ቢስ ትውልድ አጥንት ርብራብ በማድረግ ተረማምደው ሥልጣን ማማ ላይ መውጣት ሲያምራቸው የሚሰብኳት የተነቃባት አቀናቀን ናት አሉ። ግን ሳይፈራ ያልሞተ ማን አለ? ‹እነሆ በመጀመርያ ፍርኃት ነበር፣ ፍርኃትም ከሞት በፊት ነበር…›› ሲል ያላነበበ ይመስክር እስኪ። እውነቴን ነው አይደል? ‹ያንተ ቤት ሲንኳኳ ይሰማል እኔ ቤት› ዘፈን ብቻ ሆኖ በቀረባት አገሬ ለፋይዳ ቢስ ሴራ ካልሆነ ለበጎ ምግባር ተባብረን አንሞትም። ‹‹ለምን?›› ብላቸው አዛውንቱ ባሻዬ ተቆጡ። ‹‹ምነው በሐምሌ ሞት ሞት ትላለህሳ? ዘመን የማይለውጥ ስንት ሰው እያለ?›› እያሉ ከዚያ የዚያችን ጎረቤቶቿን ተራ በተራ ቀብራ አርባቸውን ሳታወጣ፣ ‹ሞት ተረማመደ… ሞት ተረማመደ…› እያለች በፍርኃትና በሥጋት ተሸብባ ያሸበበችንን ሴት ዝክረ ነገር ሳመጣባቸው፣ ከዘራቸውን አንስተው ሁለት ጊዜ ሳቱኝ። ባሻዬን እንደ አባት ስለማያቸው አላኮረፍኩም። ግን ያለ ወትሯቸው እንዲህ ሲቃጡብኝ ጠየቅኩ። ለምን ማለት መልካም!

የባሻዬ ከዘራ በንዴት አግድም የሚወነጨፈው በሁለት ምክንያቶች ብቻ እንደሆነ አስተዋልኩ። አንድ ሞትን ስለመፍራት ‹ፎቢያ› ዝቅ አድርጎ የሚያወራባቸው ሲያገኝ፣ ሁለት ዕድሜ ጠገብ ነው ተብሎ ለሞተ ሰው አላለቅስም የሚል ሰው ሲያጋጥማቸው ነው። እንግዲህ ይኼን ሒሳብ ለማጠቃለልና ለመዝጋት ለዕረፍት የሚበተን ፓርላማ መሰብሰብ አይጠበቅብንም መቼም። እናም እላችኋላሁ ይኼው እያደር ባሻዬ ላይ እንደ አዲስ የማስተውለው ነገር ገጥሞኛል። አደራ ለማንም ትንፍሽ እንዳትሉ፡፡ ባሻዬ ሲበዛ ሞት ይፈራሉ። ግን እኔን የገረመኝ ባሻዬን የሚያህሉ ክፉና ደጉን በቅጡ ያወቁ ሰው ከሞት ይልቅ አሟሟት ሊያስፈራቸው ይገባ ነበር ብዬ እንደ እናንተ በሹክሹክታ ያወራሁት ምሁሩ ወዳጄ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፣ ‹‹ዘንድሮ ደግሞ አኗኗሩን እንጂ አሟሟቱን ማን ይፈራል…›› ብሎ ዓይኔን ገለጠው። በሉ ኑሮን ፍሩማ!

ኑሮን የመሰለ ተኝተን ተነስተን የምንሠራው ሥራ እያለ ዕረፍት የሚሏት ስላቅ ታስገርመኛለች። ይኼን ስለው ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ተገርመህ ታልቃለህ…›› አለኝ። ባትሪ ድንጋይ አደረገኝ እንዴ እያልኩ በልቤ (ባትሪ እንኳ ቻርጀር አለው) ስጦዝ ሌላ ጡዘት ሰማሁ፡፡ ያው እንደምታውቁት ትንሽ ትልቁ ፖለቲከኛ ሆኗል። ‹‹ፖለቲካ… ድንቄም ፖለቲከኛ እቴ?›› ትላለች የማይገጥም ነገር ሲገጥማት የምወዳት ማንጠግቦሽ፡፡ እውነቷን እኮ ነው፡፡ በወሬና በፖለቲካ መሀል መስመሩ ስለጠፋ ነገር ተምታቶብን የለ? መንገዱስ ላይ ግዴለም ዜብራው ቢደበዝዝ ነው፡፡ ግን ምን አለበት በወሬና በፖለቲካ መሀል ያለውን ዜብራ ደመቅ አድርጎ የሚያሰምርልን ሰው ቢሰጠን? ‹ሰውማ መቼ ጠፋ ሞልቶ በአገር ምድሩ፣ መስመር ነው የጠፋው በግና ፍየሉ› ሲባል ትዝ ይለኛል። ምን ትዝ የማይል አለ ዘንድሮ!

ትዝ የሚለኝ ብዙ ነበር። ግን እኔም በትዝታዬና በነገዬ መሀል ዛሬን ማስመር አቅቶኝ ተወዛግቤያለሁ፡፡ እናም ተወዛግቤ ሰው አወዛግባለሁ፡፡ አወዘጋገቤ ያልተመቸው ሌላ አወዛጋቢ መቀየር ይችላል ብዬ ማስታወቂያ ስለጥፍ ጥላችሁኝ ብትሄዱ አይዟችሁ አልቀየምም፡፡ መቀየምን የመሻር የልቤ ችሎታ በጨለምተኛነት ለመደብዘዝ ገና ይቀረዋል፡፡ እዚህ ምን እያልን ደረስን? አዎ፣ እረፍት የሚሏት ስላቅ ታስገርመኛለች ብዬ ነበር የጀመርኩት። ኧረ ለመሆኑ ማረፊያ ስላጣን፣ መሸሻ ስለቸገረ አይደለም እንዴ የመጣ የሄደውን፣ የሰይጣን ንፋስ ያሾረውን አቧራ ሁሉ አብዮት ነው እያልን ፖለቲከኛ ነን የምንል? አንዳንዴ ኗሪ ከመሆን ጉጉት ነገር ጠንሳሽ የመሆን ስሜታዊነታችን ብዙ ስለሚያሳስበኝ እኮ ነው እዚህ እዚያም የምረግጥባችሁ። ወጥ ረገጠ አሉት እንጀራ ሲፈልግ ያለው ማን ነበር? እንጃ!

እንግዲህ ፓርላማው ወደ እረፍቱ እየሄደም አይደል? እዚህ ላይ መቼም ውስጥ አዋቂ አስፈላጊ አይመስለኝም። ውስጥ አዋቂ ነኝ ባዩስ የውስጡንማ እንዴት ገልጦ ይነግረናል? እኔ ራሴ በወሬና በፖለቲካ መሀል መስመር ጠፍቶብኛል አይደል? ምን ላድርግ የሕዝብ ልጅ ነኛ። ሰው እኮ ውሎውንና ኑሮውን ነው የሚመስለው። በተወዛገቡት መሀል እየኖርኩ ማረፊያ መተንፈሻ ገለል ያለ ሥፍራ ተነፍጎ፣ ነገር ሁሉ ለአሉሽ አሉሽ በተመቻቹለት ኅብረተሰብ መሀል እየኖርኩ መስመር ካሰመርኩ እንዴት ብዬ ተመሳሳይ ማሊያ ለብሰናል ማለት እችላለሁ? ግን አንዳንዶች እንደዚያ የሚሉ አሉ የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ‹‹ምንድነው እንዲህ ጭፍንፍን ድፍንፍን ያለ  ነገርየምታወራው? ምሁር አይደለህ እንዴ አንተ? ማለት የፈለግከውን ለምን ፊት ለፊት አትለውም?›› ስለው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፣ ‹‹እኔም እንዳንተ ስለሆንኩ ነዋ፡፡ ማለት የፈለግኩትን ማለት ከቻልኩ፣ ንቃቴ ከንቃትህ ከበለጠ፣ አንደበቴ ከአንደበትህ ከጣፈጠ፣ የምሰጠው መግለጫ አብረን ነዋሪነታችንን እንዴት ይገልጻል?›› እያለ ግራ አጋባኝ፡፡ ብዙ ቅኔ ከዘረፈብኝ በኋላ ሲገባኝ እያወራ የነበረው ስለተወካዮቻችን ነው። እረፍት ስለሚወጡት!

በዚህ ጉዳይ ብዙ ሲለኝ ቆይቶ፣ ‹‹ፓርላማው ከእረፍቱ ለአስቸኳይ ልዩ ስብሰባ ተጠራ ቢባል አይገርምም? ድሮስ ከእረፍት ውጪ ምን ሥራ አለው?›› ሲለኝ ተቀባዠረብኝ። አቤት መንግሥት እንዲህ የሚተቹትን ለሚያጋልጥ በዶላር ወሮታውን እከፍላለሁ ቢል የምንከዳዳው መዓት ነበርን። ደግነቱ ከአፍ ለቀም እያደረጉ ለጥብስ የሚያደርሱ በዝተው አይደል እንዴ ከመንገድ ለቀም የሚደረጉት አድራሻቸው ጠፍቶ እናትና አባት የሚያነቡት። እኔን ግን በጣም የሚያሳዝነኝ ልክ የባሻዬ ልጅ እንዳለው መንግሥት በነፃነት ተናገሩ፣ ጻፉ፣ ተቹ ብሎ ሲያበቃ ሰምቶ እንዳልሰማ አውቆ እንዳላወቀ የማለፍ መብት እንዳለው አለማሳወቁ ብቻ ነው። እንዲያ ባይሆን ኖሮ ታዲያ ይኼ ሁሉ ጩኸትና ምሬት አገር ማደንቆር ነበረበት? እንዲያው ነገሩን ማለቴ እንጂ አሁንም  ደላላነቴን አለቀቅኩ፡፡ ግና ለአንድ ወገኔ መብት እቆማለሁ!

ታዲያላችሁ እንደተለመደው ሽቀላዬን ላጧጡፍ እሯሯጣለሁ፡፡ አንድ ደላላ ወዳጄ ባለሦስት መኝታ ኮንዶሚኒየም ቤት እንዳሻሽጥ አሳልፎ ሰጠኝ፡፡ አሳልፎ ከሚሸጥ ወዳጅ ይሰውራችሁ፣ እንደኔ አሳልፎ እንጀራውን ከሚጥል ወዳጅ ያጋጥማችሁ ብያለሁ። እናም ይኼን ኮንዶሚኒየም ቤት ለማየት ሄድኩና ምን እንደሆንኩ አላውቅም አቅጣጫው ጠፋብኝ፡፡ ለነገሩ ከአቅጣጫ ጠቋሚም አቅጣጫ ይጠፋል፡፡ ግን መነጫነጭ ሲያዋጣ አላየሁም፡፡ አቅጣጫ አሳቱን እያሉ አቅጣጫ የመሳት የቁልቁለት ግርግር ብዙ ሊያስተምረን ይገባል ጎበዝ፡፡ ወዲያው ነቃ ብዬ ወደ አንድ መንገደኛ ተጠጋሁ፡፡ ቀለዋጭ ስልኩ ላይ አፍጦ (ለስማርት ፎን ያወጣሁት ስም ነው) ጀማሪ አናጢ እንደ ቦረቦረው ሰው ሠራሽ ዋሻ አፉን አሞጥሙጦ ከፍቶ ዩቲዩብ ላይ ተቸክሏል፡፡ አንዳንዱ ደግሞ የዋለ ያደረ የጠነዛ ወሬ ድንገት ሲሰማ ልቡ ይሰወራል፡፡ ከጫት ምርቃና ላይ የሚነሱ ሰዎች ናቸው አሉ እንዲህ የሚሆኑት፡፡ ለነገሩ ኑሮም ከምርቃና ብሷል!

‹‹ወንድም…›› አልኩት፣ አይመልስም። ‹‹ኧረ አንዴ አናግረኝ?›› አልኩ ደግሜ። አይሰማኝም። ሁኔታችንን ያስተዋለ አንድ አልፎ ሂያጅ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹አይሰማህም ክራሽ ላይ ነው…›› ብሎኝ አለፈ። ‹‹ምንድነው ደግሞ ክራሽ?›› አዲስ ፖለቲካ ፓርቲ መጣ ደግሞ? እላለሁ እኔ ሞኙ። ኋላ ነው የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹የፍቅር ጅንጀና እየተለማመደ›› መሆኑን የነገረኝ። ምን ዓይነት ትውልድ ላይ እንደ ደረስን አላውቅም ብሎ ይኼ ‹ክራሽ› የተባለ ነገር በመላው ዓለም ሰውን በየመንገዱ እየገተረ እንዳስቀረው አጫወተኝ፡፡ መቼም ሰው ሲበላሽ ሁሉም አይደለምና አቅጣጫ የሚጠቁመኝ አንድ ሰው አግኝቼ ቤቱንም አይቼ ውሎ አድሮ ጆሮውን አልኩት። አልፎ አልፎ ታዲያ ምን አሰብኩ በደላላ ተፈላልጎ የሚሸጥ፣ የሚከራይ፣ የሚገዛ ዲጂታል ነገር ልፈልስፍ እንዴ? ስል ዋልኩ። ኋላ ደግሞ መሠረተ ልማት ተገንብቶ ባላለቀበት አገር ሰውን ሁሉ በየመንገዱ ገትሬው ከማን ጋ አወራለሁ? ከማን ጋር እበላለሁ እጠጣለሁ? ብዬ ተውኩት፡፡ ዓይኔ እያየ በሰው ‹‹ክራሽ›› ተለውጬ ላረጅ ይሆን ግን? አዛውንቱ ባሻዬ እንዴት ታድለዋል እናንተ!

በሉ እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር የሰሞኑን ዓበይት ዓበይት ወሬዎች ስንጫወት ቆይተን በወሬ ተሟሟቅና ወደ ግሮሰሪያችን አመራን፡፡ ስንገባ የመሰንበቻው ጥልቅ ሐዘንና ዋይታ ተረስቶ ዘፈኑ፣ ዳንኪራው፣ ጭለጣው ደርቷል፡፡ ማን ነበር፣ ‹‹የሞተ ተጎዳ እንጂ እኛ ምን እንሆናለን ቀናችን እስኪደርስ…›› ያለው? የቀደሙን ላይ ለመድረስ ተፍ ተፉን ተያያዝነው። ሞቅታው እየጨመረ ሲሄድ ነው፣ ‹‹ወይ ፈረንጅ እነሱም እንደ እኛ የሚሰማቸው ሲያጡ ነው ራቁታቸውን ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ የጀመሩት…›› አለ አንዱ ከወደ ጥግ፡፡ ‹‹ምን ሰማህ ደግሞ?›› ሲለው ካጠገቡ፣ ‹‹የዩክሬን ኮሜዲያን ፕሬዚዳንት ደጋፊዎች ናቸዋ…›› ብሎ ሙልጭልጭ ስልኩን አቀበለው፡፡ ያኛው አተኩሮ ለሦስት ደቂቃ አይቶ ሲያበቃ፣ ‹‹እንግሊዝኛ ነው እንዴ?›› ብሎ መለሰው። ‹‹ካላነበብከው ይኼን ያህል ስታጠና የነበረው ምንድነው?›› ሲለው ጥግ የያዘው ተናዶ፣ ‹‹አማርኛ መስሎኝ ነዋ?›› ብሎ አስቀየሰው። ‹‹በቀኝ አሳይቶ በግራ መታጠፍ ይሉሃል ይኼ ነው…›› ሲል የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሁሉም ሰው ቢነቃ እኮ ጭቅጭቁም፣ ትንቅንቁም፣ ውጣ ውረዱም፣ መጎሻሸሙም ሆነ ሌላው እንዲህ እጥፍ እየተባለ ያልፍ ነበር…›› ሲል ሌላው፣ የባሻዬ ልጅ አጀንዳ ለማስቀየስ አዲስ ሐሳብ ይዞ ብቅ አለ። ተነቃቅተናል!

‹‹የችግራችንን መሠረት ለመረዳት ካስፈለገ አንድም ያለ ዕድገታችንና ያለ ኩራታችን በተራቆተ ገላና ልቅ ወሲብ ቀረፃ ዓይናችን መሟሟቱ፣ አንድም ከሁሉ የባሰውን የተራቆተ አዕምሮ ተይዞ ሠልፍ፣ ተቃውሞና አፍራሽ ድርጊት መብዛቱ ነው። የተሻለ ሐሳብ፣ የተሻለ ዕቅድ፣ የተሻለ አመራር እንደ አማራጭ ማቅረብ የተሳነው አዕምሮ እንዲያው ሲሉ ሰምቶ የሸመደደውን የነፃነትና የዴሞክራሲ መነባነብ እያንበለበለ ሲኩራራ ሳይ በአየቅጣጫው ለእርቃን መስገዳችን ያናድደኛል…›› ብሎ ዞር ዞር እያለ እንደ መንጎራደድ ሲያደርገው ብዙዎች ግራ ተጋብተው እያዩት ነበር። እንግዲህ እኔስ ለምን ይቅርብኝ ብዬ ሌላ ግራ አጋቢ ዲስኩር እንደ አቅሚቲ ጀመርኩ፡፡ ‹‹ያው እንደምታውቁት ስልካችን ሲከፈት ነውራችን ሙሉ፣ አፋችን ሲከፈት ጭንቅላታችን ባዶ። ለምን? በደርግ ጊዜ ነው አሉ፡፡ ሱፍና ከረባት የኢምፔሪያሊስቶች ነው ተብሎ ሁሉም ካኪ እንዲለብስ ተወሰነ፡፡ ይኼኔ አንዱ ነገረኛ፣ ‹ምነው አምና በሞትክ እንዲያ እንዳማረብህ፣ በሱፍህ ላይ ካኪ ሳይደረብብህ…› ብሎ ተሳለቀ አሉ፡፡ አሁንም እኛም ራሳችንን ‹ምነው አምና በሞትኩ እንዲያ እንዳማረብኝ… ብንለው መልካም አይደለም ወይ…›› ብዬ ቀና ስል ብዙዎቹ ያስቀዱት መለኪያ ላይ አፍጥጠው ነበር፡፡ አንዱ ከወዲያ ጥግ በኩል፣ ‹‹ዛሬ ግራ አጋቢው አጀንዳ ላይቭ የሚለቀቀው ከዚህ ግሮሰሪ ነው ወይ?›› ሲል ግራ የተጋቡት ጠጪዎች አንገታቸውን በመስማማት እየነቀነቁ ነበር፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት