ወደ ሥራ ለመሄድ ከባለቤቷ ማልዳ ነበር የተነሳችው፡፡ እየተዘገጃጀች እያለ ከእንቅልፉ ያልተነሳው ባለቤቷ በተለየ ድምፅ ሁለት ጊዜ ማንኮራፋቱን ታስታውሳለች፡፡ ምን ሆነ ብላ ተጠግታ ስትጠይቀው ግን መልስ አልነበረም፡፡ ተደናግጣ ስትጮህ ከደረሱላት ጎረቤቶቿ ጋር በመሆን ባለቤቷን ወደ ግል ሆስፒታል ይዘው ይሄዳሉ፡፡ ሆስፒታል ሲደርሱ ግን ከባለሙያዎች የተነገራቸው ሕይወቱ አልፎ ሆስፒታል እንደደረሱ ነው፡፡
‹‹ከዚህ ቀደም አመመኝ ብሎ አያውቅም፣ ደህና ሆኖም ሥራውን ይሠራ ነበር፤›› የምትለው ባለቤቱ፣ በፖሊስ አማካይነት መጀመርያ ከተወሰደበት የግል ሆስፒታል ወደ አቤት ሆስፒታል መወሰዱንና በኋላም ከፖሊስ ባገኙት መረጃ መሠረት ለባለቤቷ ድንገተኛ ሞት ምክንያት የነበረው የልብ የደም ቧንቧ መጥበብ መሆኑን መረዳታቸውን ነግራናለች፡፡
ይህን እንደ አንድ ገጠመኝ አነሳነው እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በድንገት ሕይወታቸውን ያጣሉ፡፡ በመኪና አደጋ፣ ውኃ ውስጥ ገብቶ በመስመጥ፣ በመውደቅ፣ በሰው በመመታት፣ በትንታና በተለያዩ ምክንያቶች ሰዎች በድንገት የሚሞቱበት አጋጣሚ አለ፡፡
የሚታይ ክስተትን ተከትሎ ከሚሞቱት ውጭ ደግሞ በርካቶች ማታ ታይተው ጠዋት ሞታቸው የሚሰማበት፣ በተቀመጡበት ሸርተት ብለው የሚቀሩበት፣ ከሰዎች አብረው እየተወያዩ አሊያም እየተዝናኑ ድንገት ሕይወታቸው የሚያልፍበት ሁኔታ መኖሩን መታዘብ ይቻላል፡፡
በቅዱስ ጴጥሮስ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የድንገተኛና ጽኑ ሕሙማን ክፍል ዳይሬክተርና ስፔሻሊስት ሙሉነህ ሰለሞን (ዶ/ር) እንደነገሩን፣ ለድንገተኛና ሞት የመጀመርያ ምክንያቱ ከልብ ሕመም ጋር የተያያዙ ችግሮች ናቸው፡፡ የልብ ምት ሲዛባ ድንገት ፀጥ ሊያደርግም ይችላል፡፡
ከዚህ በመቀጠል ስትሮክ/ምት ለድንገተኛ ሞት ምክንያት ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ማታ በሰላም ተኝተው ጠዋት መነሳት ሳይችሉ ኮማ ውስጥ ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ስትሮኩ በጣም የከፋ ደረጃ ከደረሰ ደግሞ ሰው በተኛበት ሞቶ ሊገኝ ይችላል፡፡
ሳይታወቅና ሳይታከም ሥር የሰደደ ካንሰር፣ በተለይ የጭንቅላት ካንሰር የሚያስከትለው ደም መፍሰስ ድንገተኛ ሞትን ሊያስከትል ይችላል፡፡ ክትትልና ቁጥጥር ያልተደረገበት ከፍተኛ የደም ግፊትም እንዲሁ፡፡
እንደ ሙሉነህ (ዶ/ር)፣ ማስቀረት የማይቻሉ ድንገተኛ የሞት ምክንያቶች ቢኖሩም ብዙዎቹን መቆጣጠር ይቻላል፡፡ የመጀመርያው በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ መፍጠር ነው፡፡
በኅብረተሰቡ በኩል አንድ ሰው አመመኝ ሲል ባህላዊ መንገዶችን መሞከር፣ ቆይቶ ይሻለዋል በማለት ወደ ሕክምና አለመውሰድ በኋላ ችግሩን መቆጣጠር ከማይቻልበት ደረጃ ሲደርስ ሆስፒታል የማምጣት ልማድ አለ፡፡ ይህ ሰዎች ችግራቸውን ቀድመው ሳያውቁ ለሞት እንዲዳረጉ የሚያደርግ አጋጣሚ ነው፡፡
የሕክምና አገልግሎትን ጤና ተቋም ከመሄድ በፊት ማወቅ ድንገተኛ ሞን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ የመጀመርያ ዕርዳታ መስጠትን ማወቅና መልመድም ይገባል፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው በነስር ብቻ ድንገት ሊሞት ይችላል፡፡ ነስርን በተመለከተ ኅብረተሰቡ የሚያውቀው እየነሰረው ያለውን ሰው ቀና ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ትክክለኛው መፍትሔ አይደለም፡፡ የነሰረው ሰው ዝቅ እንዲል በማድረግና አፍንጫውን ለ10 ደቂቃ እና 15 ደቂቃ በመያዝ ነስሩ እንዲቆም ማድረግ ነው፡፡ ይህ ሁለት ጊዜ ተሞክሮ ካልተሳካ ወደ ሆስፒታል መውሰድ ያስፈልጋል፡፡
አንድ ሰው በእሳት ቢቃጠል፣ ቢወድቅ፣ ትን ቢለውና ቢዝለፈለፍ፣ አየር ቢያጥረው ሊሰጡ የሚገባቸው የመጀመርያ ዕርዳታዎችን በተመለከተ ጤና ሚኒስቴር መመርያ አውጥቷል፡፡ ይህንን ሁሉም ኅብረተሰብ እንዲያውቀው የሚፈለግ ቢሆንም ገና አልተነካም ማለት እንደሚቻል፣ በመሆኑም የመጀመርያ ዕርዳታ አሰጣጥ ግንዛቤና ተግባር ላይ በስፋት መሥራት እንደሚጠበቅ ሙሉነህ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የመጀመርያ ዕርዳታ ሕክምና ላይ በስፋት በሚመለከተው አካል ሁሉ መሥራት አለበት የሚሉት ሙሉነህ (ዶ/ር)፣ በአንዳንድ የግንባታ ቦታዎች የመጀመርያ ዕርዳታ ግንዛቤ በጥቂቱ ቢሰጥም ይህ ተጠናክሮ በሁሉም ዘርፍና አካባቢ መቀጠል እንዳለበት ይጠቁማሉ፡፡
ለእያንዳንዱ ድንገተኛ ሕመም የራሱ ድንገተኛ የሕክምና ምላሽ ስላለው ይህንን ለኅብረተሰቡ ማስረፅ ቢያስፈልግም፣ ይህንን በተመለከተ በአማርኛ የተዘጋጀ ሰነድ (ዶክመንት) ቢኖርም ይህንንም ያህል ወደ ታች ወርዶ በስፋት እየተተገበረ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
ትንፋሽ በአርቴፊሻል መንገድ በመስጠት፣ በአስቸኳይ አምቡላንስ በመጥራት ድንገት ሕመም የገጠማቸውን ሰዎች መርዳት የሚቻል ቢሆንም፣ ሰዎች የጤና እክል ውስጥ ከመግባታቸው በፊት የጤና ክትትል እንዲያደርጉ ይመከራል፡፡
ከዘመናዊ አኗኗርና ከአመጋገብ ጋር ተያይዞ በልብ ላይ ከሚከሰት ችግር በተጨማሪ አልኮል መጠጣትም ለድንገተኛ ሞት መንስዔ ነው፡፡
አንድ ሰው ማታ አልኮል ጠጥቶ ጠዋት ሞቶ ሊገኝ እንደሚችል፣ ለዚህም ምክንያቱ አልኮልን በሰውነት ውስጥ ያለው ጉሉኮስ የሚቀንስና የጉሉኮስ መቀነስ ሞትን ሊያስከትል ስለሚችል መሆኑንም ሙሉነህ (ዶ/ር) ነግረውናል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ሞትን ለመቀነስ ጤናማ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል፣ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በቤተሰብ ታሪክ ድንገተኛ ሞት ካለ ቅድመ ሕክምና መከታተል ያስፈልጋል፡፡