ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ፣ ኢትዮጵያን የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች በይነ መንግሥታት ኮሚቴ አባል እንድትሆን መርጧታል፡፡ የማይዳሰሱ ቅርሶች ጥበቃ ኮንቬንሽን አባል አገሮች 9ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ከሰኔ 28 ቀን 2014 ጀምሮ ለሦስት ቀናት ጉባዔውን ባካሄደበት ወቅት በበይነ መንግሥታት ኮሚቴው አፍሪካን ከሚወክሉት መካከል ኢትዮጵያን መምረጧን በዩኔስኮ ድረ ገጽ ተመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ በአባልነት ዘመኗም በዩኔስኮ የሚመዘገቡ የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ሚዛናዊና የዓለምን ውበትና ብዝኃነት የሚያንፀባርቁ እንዲሆኑ ትሠራለች ተብሎ ይጠበቃል።
ዩኔስኮ በጠቅላላ ጉባዔው እ.ኤ.አ. በ2003 ያፀደቀው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ስምምነትን ኢትዮጵያ በ1998 ዓ.ም. በፓርላማዋ ማፅደቋ ይታወሳል፡፡ በፈረመችው ስምምነት መሠረት በኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ማለትም ብሔረሰቦች ባህላቸው አድርገው የተቀበሏቸውን ድርጊቶች፣ ዕውቀቶች፣ ሥነ ጥበባት፣ ሕግጋት፣ እምነቶች፣ ማኅበራዊ ክዋኔዎችና ሥነ ሥርዓቶች እንዲሁም ክብረ በዓላት ላይ ስትሠራ መቆየቷ ይታወሳል፡፡