Sunday, September 24, 2023

አብን በአማራ ተወላጆች ላይ “ግድያ እንዲፈጸም አነሳስተዋል” ያላቸውን የኦነግና የኦፌኮ አመራሮችን ወቀሰ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኦነግና ኦፌኮ ወቀሳውን አንቀበልም ብለዋል

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ “የዘር ጭፍጨፋ” እንዲፈጸም የሚያነሳሳ “የሐሰት መረጃ” አሠራጭተዋል ያላቸውን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) እና የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራሮችን ወቀሰ፡፡ የአገሪቱን ከፍተኛ የሥልጣን እርከን የያዙ ባለሥልጣናት “ወደ ዘር ማጥፋት ሊሄድ የሚችል” ንግግሮችን እያደረጉ መሆኑን ጠቅሶ ከዚህ ድርጊት እንዲታቀቡም ጠይቋል፡፡

በሁለት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ በወለጋ ዞኖች የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎችን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው አብን፣ ባለፉት አራት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ “የተቀናጀ፣ ተከታታይና ሥልታዊ የዘር ማጥፋት” ወንጀል እየተፈጸመ መሆኑን ገልጿል፡፡ ፓርቲው ወንጀል እየተፈጸመ ያለው “ኦነግ ሸኔ በይፋዊና በህቡዕ ከሚንቀሳቀሱ ጋር በመተባበር” በሚያደርገው እንቅስቃሴ እንደሆነ አስታውቆ፣ ለዚህም የመንግሥትን ሀብትና መዋቅር እየተጠቀመ ነው የሚል ክስ አቅርቧል፡፡

የፓርቲውን መግለጫ በጽሑፍ ያነበቡት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጣሂር መሐመድ፣ “የተቀናጀ ተከታታይና ሥልታዊ” ነው ያሉት “የዘር ማጥፋት ወንጀል” እየተፈጸመ ያለው፣ በብዙ ምዕራፍ ተከፋፍሎ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም የፌዴራልና የክልል መንግሥታት በተለያዩ መንገዶች “የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ ሆነዋል” በማለት አብን እንደሚያምን አስታውቀዋል፡፡

አብን በመግለጫው እንደገለጸው እነዚህ የመንግሥት አካላት፣ ‹‹በአማራ ተወላጆች ላይ ሲፈጸም የቆየውንና እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በመካድ፣ በመሸፋፈን፣ በማቃለልና ወንጀሉን በስሙ ባለመጥራት›› መተባበራቸውን አስረድቷል፡፡ ከዚህም ባሻገር እነዚህ አካላት የወንጀሉን ቀጣይነት ለመግታት የሚያስችል ስምምነትና ተግባራዊ ዕርምጃዎችን ለመውሰድ “ፈቃደኛ እንዳልሆኑ” ገልጿል፡፡

ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ክልልን የጠቀሰው ፓርቲው፣ ‹‹በክልሉ ሰላምና ፀጥታ ለማስፈን ያለበትን ትንሹን መንግሥታዊ ግዴታ ባለመወጣቱና የዜጎችን በሕይወት የመኖር ተፈጥሯዊ መብት ማክበር ያልቻለ›› ሲል የክልሉን መንግሥት ወቅሷል፡፡ አክሎም፣ ‹‹በመዋቅር ደረጃም ለዘር ጨፍጫፊ ቡድን ያለሰለሰ የመረጃ ግብዓትና የመዋቅር ድጋፍ በማድረጉ ተጠያቂ እንደሆነ እናምናለን፤›› ብሎ አቋሙን ገልጿል፡፡

 ‹‹የፌዴራል መንግሥትም መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያስከብር የተጣለበት ግዴታ ባለመወጣቱና በአማራው ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጥፋት ዓለም አቀፍ ወንጀል መከላከል ባለመቻሉ ተጠያቂ ነው፤›› በማለት አብን ወቅሷል፡፡

ፓርቲው ይህ ዓይነቱ “የዘር ጭፍጨፋ” ወንጀል እንዲፈጸም ቅስቀሳ አድርገዋል ያላቸው የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች፣ ግለሰቦችና መገናኛ ብዙኃን በወንጀል ተጠያቂ እንዲሆኑ ጠይቋል፡፡ ፓርቲው ይህንን ሲያብራራ፣ የኦነግና የኦፌኮ አመራሮች የሐሰት መረጃ በማሠራጨት ወንጀሉ እንዲፈጸም ሲያነሳሱ ነበር ብሏል፡፡

አብን አክሎም፣ ‹‹የኦሮሞ ልሂቃን ነን የሚሉ ግለሰቦች የአማራ ክልል ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ገብተዋል የሚል ሐሰተኛ መረጃ ሲያሠራጩ እንደነበር ለመጠቆም እንወዳለን፤›› ብሏል፡፡ አቶ ጣሂር የፓርቲውን መግለጫ ሲያነቡ፣ ‹‹በዩጎዝላቪያ ሰርቦች በኮሶቮ ጦርነት እንደከፈቱት፣ አላማው በኦሮሞ ላይ ጦርነት አውጇል የሚል ሐሰተኛና እጅግ አደገኛ ቅስቀሳ ማድረጋቸውን በሚዲያ ተከታትለናል፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡

አቶ ጣሂር ከጋዜጠኞች በተነሱ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡም፣ ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮችን ጉዳይ በድጋሚ አውስተዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥትም ከተቃዋሚም የአገሪቱን ከፍተኛ የሥልጣን እርከን የያዙ ሰዎችን በግልጽ ወደ ዘር ማጥፋት ሊሄድ የሚችሉ ቅስቀሳዎችና ኃላፊነት የጎደላቸው ንግግሮች እዚህ አገር እየተመለከትን ነው፤›› በማለት፣ ፓርቲያቸው ይህ ሁኔታ ንፁኃን እንዲገደሉ ምክንያት ይሆናል የሚል እምነት እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኦፌኮና የኦነግ አመራሮች በአብን የተሰነዘረባቸውን ወቀሳ ተቃውመዋል፡፡ የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ‹‹የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ኃይሎች ወደ ኦሮሚያ ክልል ሊገቡ ነው›› የሚለው ሐሳብ ባለፈው ሳምንት የሁለቱ ክልል መንግሥታት ርዕሰ መስተዳድሮች ባካሄዱት መግለጫ ላይ የተጠቀሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጃዋር መሐመድ ስለዚህ ጉዳይ የተናገሩት “ይህ አካሄድ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ማነሳሳት ነው” በሚል እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ አክለውም፣ የአንድ ክልል ኃይል ወደ ሌላ ክልል ይገባል ስለመባሉ የተነሳውን ሐሳብ፣ “አብን ራሱ ይህንን ሐሳብ ሊቃወመው ይገባ ነበር” ሲሉ ወቀሳ በአብን ላይ  ሰንዝረዋል፡፡ 

የኦነግ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ በቴ ኡርጌሳም በተመሳሳይ የአብንን ወቀሳ ተችተው፣ “እኛ [የአማራ ክልል መንግሥት ኃይሎች] እየገቡ ነው አላልንም፣ የሚገቡ ከሆነ ግጭት ያባብሳል ነው ያልነው፤” ብለዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድም ሕገ መንግሥቱንና የፌዴራል ሥርዓቱን የሚጥስ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከሰሞኑ በወለጋ ዞኖች የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች በገለልተኛ አካላት መጣራት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው አስታውቀዋል፡፡

አብን ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ ላይ የውጭ ገለልተኛ አካላት ጭፍጨፋዎቹን ያጣሩ የሚለው ሐሳብ ላይ ስላለው አቋም ጥያቄ ቀርቦለት ነበር፡፡ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ጣሂር ፓርቲያቸው ሕጋዊ መስመሩን ተከትሎ የሚመጣ ገለልተኛ አካል ካለ ሐሳቡን እንደሚቀበለው ገልጸው፣ ብዙዎቹ የውጭ አካላት ግን ገለልተኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል፡፡ ለዚህም ማሳያነት የውጭ ተቋማት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ይዘውታል ያሉትን አቋም ጠቅሰዋል፡፡

ፓርቲው እየተፈጸመ ነው ያለውን “የዘር ማጥፋት” ወንጀል አስመልክቶ የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ሲጠቁም፣ ‹‹ላለፉት ዓመታት የተፈጸመውና እየተፈጸመ ያለው የዘር ማጥፋት ወንጀል በስሙ እንዲጠራ›› የሚል አቋሙን አስታውቋል፡፡ በዚህ ዓይነቱ ወንጀል ላይ ተጠያቂነት ለማጣራት ሲባልም ልዩ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ እንዲቋቋምና የወንጀል ፈጻሚዎች በግልጽ ችሎት እንዲዳኙ ጠይቋል፡፡

ከዚህም ባሻር ፓርቲው ይፋዊ ውይይት በማድረግ የዜጎችን ሞት የማስቀረት ጥረት ላይ ማገዝ እንደሚፈልግ አስታውቆ፣ ‹‹ከዚህ ወንጀል ነፃ ከሆኑና ይህ ችግር እንዲቆም ከሚፈልጉ የመንግሥት አመራሮች›› ጋር ውይይት ለማድረግ ጥሪ ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -