የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የትግራይ ክልልን እያስተዳደረው ያለው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ክልሉን እያስተዳደረበት ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚደረግ የሥራ ግንኙነት ወንጀል እንደሆነ የሚደነግግ ሕግ መሆኑን አስታወቀ፡፡
ኮሚሽኑ፣ የፌዴራል መንግሥት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ከትግራይ ክልል ከወጣ በኋላ ያለውን ሁኔታ ለመጀመርያ ጊዜ ባወጣበት በዚህ ሪፖርት፣ ሕወሓት ያወጣቸው ሕጎች ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የወንጀል ሕግ ጋር የሚጣረሱ መሆናቸውን አስታውቋል፡፡
ኢሰመኮ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ያስታወቀው ዓርብ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ይፋ ባደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ዓመታዊ ሪፖርት ላይ ነው፡፡ በዓመቱ ውስጥ የነበረውን አጠቃላይ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታን በዝርዝር የሸፈነው የኮሚሽኑ ዓመታዊ ሪፖርት ከሰብዓዊ መብቶች ጋር በተያያዙ አሥር አንኳር ጉዳዮችን ዳስሷል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው የሲቪልና ፖለቲካ መብቶች የሚለው ሲሆን፣ በዚህ ሥር ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች ተብለው ከተጠቀሱት ውስጥ በዘፈቀደ እስር፣ ጠለፋና አስገድዶ መሰወር የመጠበቅ መብቶች የሚል ይገኝበታል፡፡ በዚህ ንዑስ ርዕስ ሥር ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ ሲገልጽ፣ የትግራይ ኃይሎች ትግራይን ከተቆጣጠሩ በኋላ የክልሉ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማሻሻያ ቁ. 359/2014 እና የአዋጁ ማስፈጸሚያ ደንብ ቁ. 117/2014 በማውጣት ክልሉን በአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ እያስተዳደሩ መሆኑን አሥፍሯል፡፡
እንደ ኮሚሽኑ ገለጻ ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሰዎችን መብቶች በከፍተኛ ሁኔታ የገደበ ሲሆን፣ የተወሰኑት የአዋጁ አንቀጾች የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትና የአገሪቱን የወንጀል ሕግ ጋር የሚጣረሱ ናቸው። ‹‹ለምሳሌ የፌዴራል መንግሥቱ ‘ጠላት’ ተብሎ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር የሚደረግ ማንኛውም ግንኙነት (የሥራ ሊሆን ይችላል) በወንጀል የሚያስጠይቅ መሆኑንና ከአዋጁ ጋር ተያይዞ የሚታሰሩ ግለሰቦች ቁጥር እየጨመረ [መጥቷል]›› በማለት የኮሚሽኑ ሪፖርት ያስረዳል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በትግራይ ክልል ወላጆች በግዳጅ ልጆቻቸው የሕወሓትን ሠራዊት እንዲቀላቀሉ ማድረግ እንዳለባቸው ትዕዛዝ እንደሚሰጣቸውና ይህንን ትዕዛዝ በማይፈጽሙት ላይ ከፍተኛ የሆነ እንግልትና እስር የሚደርስ መሆኑን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡
‹‹በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአጠቃላይ በትግራይ ክልል በተፈጠረው ችግር ምክንያት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ለመፈናቀልና ለስደት ተዳርገዋል፤›› ሲልም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት የደረሰውን ችግር አስረድቷል፡፡
በትግራይ ክልል በሕወሓት የወጣውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ለማስፈጸም ከተቋቋሙት ልዩ የወንጀል ችሎቶች (Special Benches) ውጭ መደበኛ ፍርድ ቤቶች እስካሁን ሥራ እንዳልጀመሩ የጠቀሰው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣ የግል ተበዳዮች መብታቸውን የሚያስከብሩበት ገለልተኛ ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት፣ ለተለያየ እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጿል፡፡ በትግራይ ክልል ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም. ጀምሮ የወንጀል ተጠርጣሪዎች የሚያዙት መደበኛ ባልሆኑ ፖሊሶች በመሆኑና ታስረው የሚቆዩባቸው ቦታዎች መደበኛ ባልሆኑ ቦታዎች በመሆኑ፣ ለተለያዩ የመብት ጥሰቶች ተጋላጭነት መጨመሩም በሪፖርቱ ላይ ተካቷል፡፡
የአመለካከትና ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብቶች በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር ኮሚሽኑ እንደገለጸው፣ በክልሉ ‹‹15 የሚዲያ ሠራተኞች በትግራይ ባለሥልጣናት የታሰሩ ሲሆን፣ ይህ ሪፖርት ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በእስር ላይ ናቸው፤›› ብሏል፡፡ ምስግና ስዩም፣ ተሾመ ጠማለው፣ ኃይለ ሚካኤል ገሰሰና ሃበን ሐለፎም በትግራይ ክልል ታስረዋል ከተባሉት ጋዜጠኞች መካከል ናቸው፡፡
ይሁንና ኮሚሽኑ በክልሉ ያሉ ዜጎች ሐሳብን በነፃ የመያዝና የመግለጽ እንዲሁም መረጃ የማግኘት መብቶች የተጣሱት፣ ጦርነቱን ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት በክልሉ መደበኛ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎት በማቋረጡም ጭምር መሆኑንም ገልጿል፡፡ እነዚህ አገልግሎቶች በመቋረጣቸው ምክንያት ሰዎች መረጃ መፈለግ፣ መቀበልና ማስተላለፍ አለመቻላቸውን የገለጸው ኢሰመኮ ወደ ትግራይ ክልል የሚደረጉ የየብስና የመንገድ ትራንስፖርት በመቋረጣቸው የሰዎችን የመዘዋወር ነፃነት መገደቡንም አክሏል፡፡ ኮሚሽኑ ምክረ ሐሳቦችን ባስቀመጠበት የሪፖርቱ ክፍል ‹‹የፌዴራል መንግሥት በትግራይ ክልል የተቋረጠውን የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎት እንዲያስጀምር›› በማለት ጠይቋል፡፡
ሪፖርቱ ይፋ በሆነበት መግለጫ ላይ ኮሚሽኑ በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ በምን ዓይነት መንገድ መረጃ እንደሚሰበስብ ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኮሚሽኑ የመቀሌ ቅርንጫፍ ከወራት በፊት መዘጋቱን ተናግረዋል፡፡
ኢሰመኮ በሪፖርቱ ላይ ‹‹የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በመቀሌ የኮሚሽኑ ሠራተኞች ላይ ጫና በማሳደርና የኮሚሽኑ መቀሌ ጽሕፈት ቤት እንዲዘጋ ማድረጋቸው፣ ለኮሚሽኑ ሥራ እንቅፋት ሆኗል፤›› ሲል ይህንን ጉዳይ በመግለጫው ላይም ጠቅሶታል፡፡ ሪፖርቱ እንደሚያስረደው የመቀሌው ጽሕፈት ቤት የተዘጋው በትግራይ ክልል የደረሰውንና እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለመመርመር እየሠራ መሆኑ ተከትሎ ነው፡፡
የኢሰመኮ ሪፖርት በትግራይ ክልል ውስጥ ስላለው ሁኔታ ካስቀመጠው ገለጻ ባሻገር በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የትግራይ ተወላጅ በሆኑ ነዋሪዎች ላይ የደረሱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችንም አካቷል፡፡
የአፋር ክልል ፀጥታ ኃይሎች ከኪልበቲ ረሱ ዞንና አካባቢ ከመኖሪያ አካባቢያቸው ‹‹ደኅንነታቸውን ለማስጠበቅ›› በሚል የሰበሰቡዋቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የትግራይ ተወላጆች ሰመራ ከተማ በሚገኙ ሰመራና አጋቲና ካምፖች ስለመገኘታቸው ያስታወሰው ኮሚሽኑ ነዋሪዎቹ ሪፖርቱ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ ከፈቃዳቸው ውጭ እንደተያዙ እንዳሉ አስረድቷል፡፡
ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል (ዶ/ር) ነዋሪዎቹ በሁለቱ ካምፖች ውስጥ ያሉት ‹‹በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ›› ቢሆንም፣ ቦታው ‹‹የእስር ቦታ›› እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተጨማሪም በአማራ ክልል ሐይቅ ከተማ ውስጥ በተመሳሳይ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ተወላጆች መኖራቸውን አስታውቋል፡፡ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መለሰ ጉዳዩ ምርመራ እየተደረገበት በመሆኑ ሪፖርቱ ውስጥ እንዳልተካተተ ገልጸው በቀጣይ ይፋ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡