Wednesday, September 27, 2023

‹‹ፓርላማው ራሱ ወሳኝ ራሱ ፈራጅ ሆኖ የጎንዮሽ የቁጥጥር ሥራ እንዳያበላሽ እፈራለሁ›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አንቀጽ ጠቅሶ፣ ራሱ ወሳኝ፣ ራሱ ፈራጅ ሆኖ የጎንዮሽ የቁጥጥር ሥራ እንዳያበላሽ እፈራለሁ ሲሉ ለፓርላማው ተናገሩ፡፡

  ለ2015 ዓ.ም. በቀረበው ረቂቅ በጀት ላይና በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከምክር ቤት አባላት ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት፣ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በፓርላማው የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) የፓርላማ አባላቱን ዳኞች አይደላችሁም፣ አንድ ጉዳይ በዚህ አንቀጽ መጠቀስ አለበት ካላችሁ፣ ነገር ታዛባላችሁ ሥራችሁ እሱ አይደለም፣ ሥራችሁ ሕግ ማውጣት ነው ሲሉ አሳስበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የተናገሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የምክር ቤት ተወካይ የሆኑት አቶ ሙሉቀን አሰፋ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ላይ የተጠቀሱትን የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሠልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብትን በመጥቀስ፣ መንግሥት እነዚህን መብቶች እየከለከለ መሆኑን አስመልክቶ ማብራሪያ ከጠየቁ በኋላ ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ የሚተረጉም ሙያተኛ በወጣው ሕግ አግባብ መሠረት አንድ ወንጀል በየትኛው አንቀጽ እንደሚከሰስ፣ በየትኛው አንቀጽ እንደሚጠየቅ ይጠይቃል እንጂ፣ እናንተ እዚህ ተቀምጣችሁ በዚህ አንቀጽ ወንጀል ነው ካላችሁ የቁጥጥር ሥራው (Check and Balance) ይበላሻል ሲሉ ለአባላቱ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ይህ ደግሞ እናንተ የምትፈልጉት ሥርዓት እንዳይኖር የሚያደርግ በመሆኑ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ሥልጠናም የሚያስፈልግ ይመስለኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡››

‹‹ከልቤ ነው የምናገረው ሕግ አውጪዎች ትልቅ ኃላፊነት አለባችሁ፣ የ100 ሚሊዮን ሕዝብ ችግር ተሸክማችኋል፣ እዚህ መጥታችሁ ስትናገሩ ዳኛ ሆናችሁ ሚኒስቴር ሆናችሁ›› አይሆንም፣ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እናንተ የምክር ቤት አባል ናችሁ፣ ትልቅ ሥራ አለባችሁ፣ መሥራት ያለባችሁ እሱን ነው፣ ሌላውም ሰው እንደዚሁ በማለት አስረድተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በቅርቡ በፓርላማው ቀርበው ለአብን ተወካይ አቶ ክርስቲያን ታደለ መልስ በሰጡበት ወቅት ‹‹ክቡር አቶ ክርስቲያን ወደ ተመረጡበት ሄደው ሕዝቡን ቢያወያዩ መልካም ነው፡፡ ጠፍተዋል የሚል ሐሜት ሰምቻለሁ፤›› በማለት መልስ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡

በተመሳሳይ ኦነግ ሸኔን ለማውገዝ ይቸገራሉ በሚል ይታማሉ ተብለው ከአባላቱ ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹መጀመርያ የተከበረው ምክር ቤት በጣም ትልቅ ወንበር ነው የያዛችሁት፣ ሐሜት እዚህ አታምጡ፣ ይህ እኮ ትልቅ ቤት ነው፡፡ እንዴት ይታማሉ ብላችሁ ሐሜት እዚህ ታመጣላችሁ፣ እንደዚህ አየሁ እንደዚህ ሰማሁ ሄጄ አረጋግጬ ጠይቄ ነው የሚባለው፣ እኛም የምክር ቤት አባል ነበርን፤›› ብለዋል፡፡

አክለውም እዚህ ምክር ቤት እንደዚህ አይጠየቅም፣ ሐሜት እዚያ ቡናና ጫት ላይ፣ እዚህ ሲሆን ደግሞ ቁምነገር አጣርታችሁ ጠይቃችሁ መምጣት አለባችሁ እንጂ እንደዚህ ዓይነት ሐሜት ሰምቻለሁ ሐሜቱን እንዴት ታዩታላችሁ አይባልም በማለት ለአባላቱ ተናግረዋል፡፡

ስለዚህ ሐሜትን አስታኮ መልሶ መስጠት እንደሚያስቸግር፣ ነገር ግን የተባለው ዕሳቤው ስለመኖሩ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መጀመሪያም ይህ ምክር ቤት አልነበረም ሸኔን አሸባሪ ያለው፡፡ ‹‹እናንተ አልነበራችሁም›› ሸኔን እናንተ አሸባሪ እንዳላችሁ አታስመስሉ፣ የቀደመው ምክር ቤት ነው ሸኔን አሸባሪ ያለው እናንተ አይደላችሁም ብለዋለዋቸል፡፡

Ethiopian-Parliament-Dr-Abiy-Ahmed-Photo-By-Ethiopian-Reporter-1

‹‹ልክ እናንተ አሸባሪ ብላችሁ፣ እኛ ቸል እንዳልነው ለማስመሰል ከሞከራችሁ ስህተት ነው›› በመሆኑም እናንተ ሳትመረጡና ሳትገቡ ነው ሸኔን አሸባሪ ያልነው፡፡ ነገር ግን አሸባሪነት መባሉ ሳይሆን እኛ በየቀኑ እየተዋጋነው ነው፣ ነገር ግን መባሉ ብቻ ምን ያደርጋል ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዘር ጋር የምትታገሉ ሰዎችና ሸኔ የኦሮሞ ተወካይ ነው ብላችሁ አሳንሳችሁ የምታዩ፣ ሸኔ የአሮሞም ቀንደኛ ጠላት ነው ሲሉ መልስ ሰጥተዋል፡፡

በተመሳሳይ በአሸባሪነት ከተሰየመው ሕወሓት ጋር ድርድር እንዴት ይካሄዳል ተብለው ከአባላቱ ለተጠየቁት ጥያቄ፣ መልስ ሲሰጡ ‹‹ሕወሓት አሸባሪ ሲባል እናንተ አልነበራችሁም›› ነገር ግን አሸባሪ ጋር ድርድር አይካሄድም የሚለው አባባል በደንብ ቢታይ ጥሩ ሰለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ስለድርድር ሲነሳ ደርግ ሁልጊዜም ከሻቢያና ሕወሓት ጋር ይደራደር እንደነበር፣ የየመን ሃወቲዎች ሮኬት እየተኮሱ ይደራደሩ እንደነበር በመግለጽ ውጊያ ውስጥ ይነገርም አይነገርም፣ ሁልጊዜም ድርድር እንደሚካሄድና ድርድር የሚካሄደውም ከድርድር ውስጥ ትርፍ ካለ ለማግኘት ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ መንግሥትን መጠየቅ ያለበት አገራዊ ጥቅምን አደጋ ውስጥ ከተህ የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፈህ ሰጥተሃል ከሆነ እሱ አዳጋች እንደሆነ ዓቢይ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም በንግግር የሚፈታ ነገር ካለ ግን አለፍ ብሎ ማየት ጉዳት የለውም፡፡

በአንድ በኩል ተፈናቀልን ችግር አለ፣ ሰው ሞተ እያልን በሌላ በኩል ደግሞ በሰላምና በድርድር አንዳንዱን እንቀንስ ስንል ‹‹ካልፈቀዳችሁ እንዴት እንፈታዋለን ታዲያ›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከሁሉም ጋር ተዋግተን አንችለውም፣ ‹‹የሚዋጋን ኃይል፣ ኃይል ብቻ አይደለም ታውቃላችሁ፣ ብዙ ኃይሎች በገንዘብ ከእኛ የሚሻሉ አብረው እየተዋጉን ነው›› ከሁሉም ጋር ውጊያ ጥፋት ስለሆነ በሰላም መለስ የሚል ኃይል ካለ ዕድል መስጠት መጥፎ አይደለም በማለት ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -