Sunday, March 3, 2024

የመንግሥት ጡረታ ፈንድ መንግሥታዊ ተቋማት ገቢ ያላደረጉት 2.2 ቢሊዮን ብር ማግኘቱን አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የመንግሥት ሠራተኞች ማኅበራዊ ዋስትና ፈንድ አስተዳደር በ3,106 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ባደረገው ምርመራ፣ በ2013 ዓ.ም. ገቢ መደረግ ሲኖርበት ወደ ፈንዱ ያልገባ 2.27 ቢሊዮን ብር የጡረታ መዋጮ ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡

ፈንዱ ከሰባት ሺሕ በላይ ከሚሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ገቢ ያደረጉትን የጡረታ ገንዘብ መጠን ኦዲት የሚያደርግ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ያገኘው 2.27 ቢሊዮን ብር በ3,106 መሥሪያ ቤቶች ላይ ካደረገው ምርመራ ያገኘው መሆኑን ገልጿል፡፡ ገቢ ያልተደረገ ገንዘብ ከተገኘባቸው መሥሪያ ቤቶች ጋር በተደረገ ንግግር፣ ገንዘቡን ገቢ ያደረጉ እንዳሉ ሁሉ አስተዳደሩ ክስ የመሠረተባቸው መሥሪያ ቤቶች ስለመኖራቸው የአስተዳደሩ ዕቅድ፣ ጥናትና ሪፎርም ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ማናዬ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ፈንዱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ውስጥ 28.3 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ 26.4 ቢሊዮን ብር በመሰብሰብ የዕቅዱን 93 በመቶ አሳክቷል፡፡ አቶ አሰፋ እንደሚያስረዱት ከዕቅዱ ውስጥ 1.8 ቢሊዮን ብር ያልተገኘው ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ ከትግራይ፣ አማራ፣ አፋርና ኦሮሚያ ክልሎች መዋጮ ባለመሰብሰቡ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በተያዘው ዓመት የተመሠረተው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት መዋቅር በሚፈለገው ደረጃ ባለመዘርጋቱ መዋጮ ማሰባሰብ ላይ እክል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

ፈንዱ በጊዜው ገቢ ከሚደረግለት የጡረታ መዋጮ ባሻገር ገቢ የተደረገው መዋጮ መጠን ትክክለኛነት ለማረጋገጥ በመሥሪያ ቤቶቹ ላይ የምርመራ ሥራ እንደሚያከናውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዓመት በተደረገው ምርመራ በ2013 ዓ.ም. ወደ ጡረታ ፈንዱ መግባት እያለበት ያልገባ 2.27 ቢሊዮን ብር ተገኝቶ 995 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡ ይኼ ገንዘብ መመለስ የቻለው ከመሥሪያ ቤቶቹ አመራሮች ጋር በተደረገ ንግግርና ከሒሳብ አካውንታቸው ተቆርጦ ወደ ጡረታ ፈንዱ ገቢ እንዲሆን በማድረግ መሆኑን አቶ አሰፋ ገልጸዋል፡፡ አሁንም ክስ የመሠረተባቸውና ጉዳያቸው በሒደት ላይ ያለ መሥሪያ ቤቶችም እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ሠራተኞች ገንዘብ ለሌላ አገልግሎት መዋልና በሌላ አካውንት መቀመጥም የለበትም፤ ግን አንዳንድ ኃላፊዎች ክትትላቸው ደከም ባለበት ሁኔታ እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ይፈጠራል፤›› ሲሉ ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

በዚህም የዘንድሮን ጨምሮ በ2013 ዓ.ም. እና ከዚያ ቀደም በነበሩ ዓመታት በወቅቱ ያልገባ 2.2 ቢሊዮን ብር ገቢ ማስደረግ ቢቻልም፣ አሁንም በወቅቱ ወደ ጡረታ ፈንዱ ያልገባ 1.5 ቢሊዮን ብር ውዝፍ ገንዘብ መኖሩ ተገልጿል፡፡

ፈንዱ ከመሥሪያ ቤቶች ከሚሰበስበው መዋጮ ባሻገር፣ በፈንዱ ውስጥ የሚገኘውን ገንዘብ ኢንቨስት በማድረግ ገቢውን ያሳድጋል፡፡ አስተዳደሩ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከኢንቨስትመንት 7.22 ቢሊዮን ብር ገቢ ያገኘ ሲሆን ይህም የዕቅዱ 130 በመቶና ባለፈው ዓመት ከኢንቨስትመንት ካገኘው ገቢ በ3.2 ቢሊዮን ብር የሚልቅ ነው፡፡ ዳይሬክተሩ እንደሚያስረዱት ይኼ ገቢ የጨመረው ፈንዱ ኢንቨስት የሚደርግባቸው አማራጮች በመስፋታቸው ነው፡፡

የመንግሥት ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ አዋጅ መጋቢት ወር 2014 ዓ.ም. ተሻሽሎ የጸደቀ ሲሆን፣ በዚህ አዋጅ ላይ ትልቁ ለውጥ ከዚህ ቀደም ፈንዱ ከግምጃ ቤት ሰነድ ውጪ ኢንቨስት እንዳያደርግ የነበረበት ክልከላ መነሳቱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የነበረው አዋጅ ቦርዱ ሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ፈሰስ ማድረግ የሚችለው የገንዘብ ሚኒስቴር ሲፈቅድለት ብቻ ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ ግን የፈንድ አስተዳደሩ ሥራ አመራር ቦርድ አትራፊና አስተማማኝ ኢንቨስትመንቶች ላይ ፈሰስ ለማድረግ ውሳኔ የማሳለፍ ሥልጣን አለው፡፡

ይሁንና አሁን 7.22 ቢሊዮን ብር ያስገኙት የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ፈሰስ የተደረገው ከአዋጁ መጽደቅ በፊት ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በነበረው ሕግ በገንዘብ ሚኒስቴር ፈቃድ ከግምጃ ቤት ሰነድ ውጪ ኢንቨስት ማድረግ የሚቻል የነበረ ቢሆንም እስከ ባለፈው ዓመት ድረስ ሚኒስቴሩ ፈቃድ እንደማይሰጥ አስታውሰዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ በ2013 ዓ.ም. መጨረሻ በፈንዱ ቦርድ ጣልቃ ገብነት ገንዘብ ሚኒስቴር በሰጠው ፈቃድ፣ ከግምጃ ቤት ሰነድ ውጪ ፈንዱ እንደ ቡናና ብርሃን ባሉ አምስት ባንኮች አክስዮን ላይ ኢንቨስት አድርጓል፡፡ የባንኮቹ አክስዮን ከ20 በመቶ በላይ የሆነ ትርፍ በየዓመቱ እንደሚያስገኙ አስረድተዋል፡፡

የግምጃ ቤት ቦንድና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ቦንድ ሌሎቹ የኢንቨስትመንት ዓይነቶች ናቸው፡፡

ፈንዱ ከኢንቨስትመንቶቹ ያገኘው ገቢ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ገቢዎች አንጻር ከፍተኛ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ካለው የዋጋ ግሽት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ መሆኑን አቶ አሰፋ አስረድተዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የዋጋ ግሽበቱ ከ30 በመቶ በላይ ሆኖ ሳለ በተለይ ከቦንዶች የሚገኘው ገቢ ከዘጠኝ በመቶ የማይበልጥ መሆኑን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -