Wednesday, September 27, 2023

የብሔራዊ የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ተላከ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የከተማና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ብሔራዊ የከተማ ልማት ፖሊሲን ጨምሮ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ ረቂቅ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን አስታወቀ፡፡

የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ደኤታ ወንድሙ ሴታ (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የብሔራዊ የከተማ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ይህ ረቂቅ ፖሊሲ የቤት ልማት፣ የመሬት አቅርቦት፣ የከተማ አገልግሎቶችንና የከተማ መሠረት ልማት አቅርቦትን የሚመለከት ነው ብለዋል፡፡

ከተሞች ለአገር ዕድገት ያላቸውን ግዙፍ ሚና ለማሳደግ በዘርፉ የሚገኙ ፖሊሲዎችን፣ ስትራቴጂዎችንና መመርያዎችን ከወቅቱ ጋር ለማጣጣም እየተሠራ መሆኑን፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችና ኃላፊዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ሲያነሱት የቆየ ጉዳይ እንደሆነ፣ በተለይም በዘርፉ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ግልጽ በሆነ መረጃ ላይ እንዲመሠረቱና ከተሞች በኢኮኖሚው ውስጥ ያላቸው ድርሻ እንዲመዘን ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎችም እየተከናወኑ እንደሚገኙ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

ብሔራዊ የከተማ ልማት ፖሊሲው የሚመራበት ረቂቅ ተፈላጊውን የዝግጅት ሒደቶች አልፎና ተጠናቆ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እንደተመራ የተናገሩት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ከዚህ በተጨማሪም በ2006 ዓ.ም. ተዘጋጅቶ የነበረው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፖሊሲ በዚህ ወቅት ያለውን ነባራዊ ሁኔታና የማልማት ፍላጎት ሊደግፍ የሚችል ነው ወይ? የሚለው ታይቶ ፖሊሲውን የመከለስ ሥራ ሲከናወን መቆየቱን አስረድተዋል፡፡

የፖሊሲ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ከተጠናቀቁ በኋላ ያንን ፖሊሲ ለማስፈጸም የሚያስችል ምቹ የሕግ ማዕቀፎች ዝግጅት የሚቀጥል ይሆናል ተብሏል፡፡ ከላይ የተጠቀሱት አዋጆች ረቂቃቸው ተዘጋጅቶና ተጠናቆ ውሳኔ ለሚሰጠው አካል መላካቸውን ያስረዱት ሚኒስቴር ደኤታው፣ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ረቂቆቹ ይፀድቃሉ የሚል እምነት እንዳለቸው ጠቁመዋል፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ሥራዎች ባሻገር በሚኒስቴሩ በኩል የ30 ዓመታት የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱን ያስታወሱት ወንድሙ (ኢንጂነር)፣ ፍኖተ ካርታው ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት ሦስት አሠርት ዓመታት በዘርፉ ለመድረስ የወጠነቻቸውን ግቦች ያሠፈረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በዚህ ወቅት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በውጭ አገሮች ተቋራጮች ላይ ጥገኛ መሆኑን ያነሱት ሚኒስቴር ደኤታው ከዚህ ጥገኝነት የሚወጣው በመመኘት ብቻ አለመሆኑን ገልጸው፣ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ የኮንስትራክሽን ተቋራጮችና አማካሪዎች እንዲፈጠሩ ከተፈለገ አቅማቸው መገንባት እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡

በተያያዘም በከተማና በመሠረተ ልማት ሚኒስቴር ይሁንታ የተሰጠው በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ ያሉ አማራጮችን እንደሚያሳይ የታመነበት ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ንግድ ትርዒት፣ በመጪው ዓመት ግንቦት ወር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡

‹‹ዲኤምጂ ኢቨንትስ›› በሚባል መቀመጫውን ዱባይ ባደረገና በኢትዮጵያ አጋሩ በሆነው ኢትኤል ኢቨንትስና ኮሙዩኒኬሽን በሚዘጋጀው ዓለም አቀፍ የንግድ ትርዒት፣ ዘርፉ የደረሰበትን የኮንስትራክሽንና የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ በአገር ውስጥ የሚታዩ ማነቆዎችን ለመፍታት አጋዥ መሆኑን የከተማና የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ወ/ሮ ጫልቱ ሳኒ፣ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም በሐያት ሬጀንሲ ሆቴል በተዘጋጀ የጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡

በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚሰናዳ በተገለጸው የንግድ ትርዒት ከ100 በላይ ዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ምርቶች፣ አገልግሎት ሰጪና የቴክኖሎጂ ድርጅቶች፣ እንዲሁም አገር በቀል የኮንስራክሽን ዘርፉ የሚመለከታቸው ተቋማት ይገኛሉ ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -