ለቀጣይ ዓመት 786 ቢሊዮን ብር በጀት ፀድቋል
ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በፀደቀው 786 ቢሊየን ብር ውስጥ ለወልቃይት አካባቢ አለመመደቡ ከፓርላማ አባላቱ ጥያቄ አስነሳ፡፡
የአማራ ክልል ‹‹የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ፣ ትግራይ ክልል ደግሞ ‹‹ምዕራብ ትግራይ›› በሚል የሚጠሩትና የይገባኛል ጥያቄ እየተነሳበት ላለው የወልቃይት አካባቢ፣ በጀት ለምን እንዳልተመደበለት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካይ ደሳለኝ ጫኜ (ዶ/ር) በፓርላማው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የወልቃይት አካባቢ በኢሕአዴግ አገዛዝ ሥርዓት ወቅት በትግራይ ክልል ውስጥ የነበረ ሲሆን፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ ‹‹ቦታው ይገባኛል›› የሚለው የአማራ ክልል መቆጣጠሩ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ የአገሪቱን የበጀት ቀመር የሚያወጣው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የበጀት ቀመሩን እሳካሁን ሲሠራበት በነበረውና ወልቃይት በትግራይ ክልል ውስጥ እንዳለች ተደርጎ በጀቱ የሚመደብ በመሆኑ የአካባቢው አዋዛጋቢነት በክልሎቹና በፌዴሬሽን ምክር ቤት እስካልተፈታ ድረስ ቦታው በአማራ ክልል ውስጥ ቢሆንም የበጀት ድልድሉ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚያልፍ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በነበረው የፓርላማው የመጀመርያ ዓመት የመጨረሻ ስብሰባ ደሳለኝ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ ‹‹ይህ በጭፍጨፋ ያለፈ ሕዝብ፣ መንግሥት እንዴት በጀት ሳይመድብለት ይቀራል›› ሲሉ ጥቄያቸውን አቅርበዋል፡፡ አክለውም የፋይናንስ ሚኒስትሩ ሕገ መንግሥታዊነትን መሠረት አድርገን ነው የምንመልሰው ማለታቸውን አቅርበዋል፡
የክልሎች ድንበር የተቀየሰው ሕገ መንግሥቱ ከመውጣቱ በፊት ስለመሆኑና ሕገ መንግሥቱ ከፀደቀም በኋላ ብዙነ ቦታዎች ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል እንደተካለሉ በማስተወስ፣ ይህ ሕዝብ ከፌዴሬሽኑ የልማት ተጠቃሚነትን በተመለከተ የሚያነሳው ጥያቄ ባይታለፍ ጥሩ መሆኑን በጥቄያቸው አንስተዋል፡፡
በተመሳሳይ ሌላኛው የምክር ቤት አባል፣ በአንድ አገር ውስጥ መንግሥት የሚያስተዳድረውን የወልቃይት አካባቢ በጀት አለመመደቡ፣ ታሳቢ አለመደረጉና ግምት ውስጥ አለመግባቱ ለምንድነው ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
የምክር ቤት አባላቱን ጥያቄ ተከትሎ መልስ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ (ዶ/ር)፣ ከዚህ ቀደም ወልቃይትን በሚመለከት ከምክር ቤት አባላቱ ጋር በዝግ ውይይት እንደተደገረበት፣ ጥያቄው የቆየ በመሆኑና የፍትሕ ጥያቄ ያለበት በመሆኑ፣ ሕግን በተከተለ መንገድ መፈታት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም ሁሉም ሰው በአንድ ድምፅ ካልተማመነ፣ መወሰን ቀላል ቢሆንም ነገር ግን በውሳኔው ‹‹ልጆቻችን እየተባሉ እንዲኖሩና ሁለጊዜ መበላላት እንዲኖር መፍቀድ የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
የወልቃይት ሕዝብ የተጎዳና የተሰደደ ሕዝብ በመሆኑ ሌላ ጦርነት የሚያመጣበት ውሳኔ ከሚወሰን በብስለት የተሞላና ሕግን የተከተለ ውሳኔ ለመወሰን እንደሚያስፈልግ ለፓላርማ አባላቱ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ያም ሆኖ ግን ይህ የእናንተ ሥራ አይደለም፡፡ ፌደሬሽን ምክር ቤት ከክልል ጋር ተነጋግሮ ሲወሰን እናስፈጽማለን፤›› ብለዋል፡፡
ወልቃይት እስካሁን በትግራይ ክልል የነበረ በመሆኑ፣ ለትግራይ ክልል የሚመደብ በጀት አሁንም ይመደባል፡፡ ነገር ግን ከተመደበ በኋላ እንዴት ይተዳደር የሚለውን ጉዳይ በመንግሥት የበጀት አስተዳድር በኩል ይታያል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የገንዘብ ሚንስቴር የወልቃይትን በጀት በተመለከተ ባለፈው ዓመትም አይቶታል፡፡ ዘንድሮም ያየዋል፡፡ ነገር ግን አሁን ቦታው ባለበት የይገባኛል ጥያቄ ምክንያት ለማን ተብሎ ይመደባል ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ የተሰደደው ሕዝብ መመለስ እንዳለበትና በልማት የተጎዳው መልሶ እንዲቋቋም መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
ለ2015 ዓ.ም. የቀረበው 786 ቢሊየን ብር በጀት በአራት ድምፀ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጥ ፀድቋል፡፡ ከአጠቃላይ በጀቱ ለትግራይ ክልል 12 ቢሊዮን ብር ተመድቧል፡፡
የበጀቱ ዋና ትኩረት ከዚህ በፊት በተለይ በጦርነት የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመገንባትና ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲሁም የዕዳ ክፍያ ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ተጠቁሟል፡፡