Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጫት የወጪ ምርት ምዝገባ ላልተወሰነ ጊዜ ተቋረጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፣ ‹‹አገሪቱ ከጫት ምርት ንግድ የሚገባትን ጥቅም እንዳታገኝ አንቅፋት የሆኑ አሠራሮች ተበራክተዋል፤›› በሚል ከግንቦት 22 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በአስገዳጅነት ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየውን የጫት የወጪ ምርት የውል ምዝገባ ሥርዓት ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን አስታወቀ፡፡

በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወ/ሮ ቁምነገር እሸቱ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ የውል ምርት ምዝገባ ሥርዓቱ ለአሠራር አመቺ ሆኖ ባለመገኘቱ፣ መመርያ እየተጣሱ የሚሠሩ ሥራዎች አሁንም ከመበራከታቸው ጋር ተያይዞ፣ የምዝገባና ቁጥጥር ሥርዓቱን ቋሚ ቅርፅ ለማስያዝ ሲባል ለጊዜው አገልግሎቱ መቋረጡን ተናግረዋል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከአገር ውስጥ የሚወጡ ማናቸውንም የጫት ምርቶች በየጊዜው በመመዝገብ የመላኪያ ፈቃድ ለመስጠት በማሰብ፣ የአንድ መስኮት አገልግሎቱን ከግንቦት 2014 ዓ.ም. አንስቶ ተግባራዊ ማድረግ ጀምሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ሆኖም ተግባራዊ ከተደረገው አሠራር ጋር ተያይዞ ችግሮች በመባባሳቸው፣ ቅሬታዎች በመጨመራቸው፣ እንዲሁም ለአሠራር ዓመቺ ባለመሆኑ ምክንያት፣ የተወሰኑ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቶች ተደርገው ዳግም የቁጥጥር ሥርዓቱ መጀመሩ እስኪገለጽ፣ የጫት ፍቃድ አሰጣጥም ሆነ የቁጥጥር ሥራን ማቋረጥ የተሻለ አማራጭ ሆኖ መገኘቱን የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ ገልጸዋል፡፡

በግንቦት ወር ተግባራዊ ተደርጎ የነበረውን አሠራር ተከትሎ የተወሰኑ ለውጦች  ይኖራሉ የሚል ዕምነት እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ነገር ግን ችግሮቹ አልተቀረፉም፡፡ በመሆኑም ፍትኃዊና እኩል ተጠቃሚነት ባለው መንገድ ከዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማሳደግ በቀጣይ የጫት ምዝገባና አፈጻጸም ሥርዓት የሚዘጋጅ ይሆናል ተብሏል፡፡

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጫት የወጭ ምርት ሽያጭ ውል አፈጻጸም ላልተወሰነ ጊዜ መቋረጡን አስመልክቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ጉምሩክ ኮሚሽን በላከው ደብዳቤ ላይ እንዳስታወቀው፣ በጫት ምርት የላኪነት የንግድ ሥራ ፍቃድ አተገባበር፣ በጫት ምርት ውል አግባብና አፈጻጸም፣ በመላኪያ ፍቃድ አሰጣጥና በጫት ምርት የውጭ ምንዛሪ ክፍያ አፈጻጸም ችግሮች የሚታዩበት በመሆኑ ከዘርፉ መገኘት የሚገባው ገቢ እየታጣ ይገኛል፡፡

ኢትዮጵያ ለውጭ ገበያ ከምታቀርባቸው ዋና ዋና የግብርና ምርቶች አንዱ የጫት ምርት ሲሆን፣ ከዘርፉ የሚገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም፣ በጫት ምርት የላኪነት የንግድ ሥራ ፍቃድ አተገባበር፣ በጫት ምርት ውል አገባብና አፈጻጸም፣ በመላኪያ ፍቃድ አሰጣጥና በጫት ምርት የውጭ ምንዛሪ ክፍያ አፈጻጸም ችግሮች ይገኛሉ ሲል የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

በተያያዘም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር  በግንቦት ወር ፈቃዳቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው የሰጡ ናቸው ያላቸውን 40 የጫት ላኪዎችን ጨምሮ የላኪነት የንግድ ሥራ ፍቃድ አላሳደሱም ያላቸውን 830 የጫት ላኪ ድርጅቶች የንግድ ፈቃዳቸውን በጊዜያዊነት ከማገድ አንስቶ የመሰረዝ ዕርምጃ መውሰዱ ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሯ፣ ከዚህ ቀደም በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከታገዱ እንዲሁም ፍቃዳቸው ተሰርዞ ከነበረው ከ870 በላይ የጫት ላኪ ድርጅቶች ውስጥ አስፈላጊውን ሒደት አስተካክለው የተመለሱ ድርጅቶች እንዳሉ ገልጸው፣ በዚያው ልክ ወደ ዘርፉ ሳይመለሱ የቀሩ የጫት ላኪ ድርጅቶች ይገኛሉ ብሏል፡፡

በተያዘው ዓመት 11 ወራት የኢትዮጵያ የወጭ ንግድ አፈጻጸም ውስጥ ከቡና፣ ወርቅ እንዲሁም አበባ በመቀጠል ጫት ከፍተኛ የወጪ ንግድ ድርሻ ያስመዘገበ ምርት ሲሆን፣ በተጠቀሱት ወራት አገሪቱ ከጫት ብቻ 372.28 ሚሊዮን ዶላር ገቢ እንዳገኘች ይታወሳል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች