Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አኃዱ ባንክ ለተዘነጉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ብድር ማቅረብ የቅድሚያ ትኩረቱ እንደሚሆን አስታወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪን ለመቀላቀል የተሰናዳው አኃዱ ባንክ አ.ማ. በዘርፉ ያለውን የአገልግሎት ጉድለት ለይቶ የበኩሉን ሚና ለመጫወት ታሳቢ ያደረጉ አዳዲስ የባንክ አገልግሎቶችን ይዞ ሥራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

እንዲህ ያለውን ችግር ለመቅረፍና ለኢንዱስትሪው አዲስ የሚባል አሠራሮችን ይዤ ቀርቤያለሁ ያለው አኃዱ ባንክ አ.ማ.፣ እስካሁን ባልተለመደ ሁኔታ አዳዲስ የብድር አቅርቦቶችን ይዞ ገበያውን የሚቀላቀል መሆኑን ገልጿል፡፡ 

በተለይ ባንኩ በየዓመቱ ከሚሰጠው ብድር ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነውን ለአነስተኛና ለመካከለኛ ማክሮ ቢዝነሶች ለማበደር የባንኩ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉ ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ 

ባንኩ ሐምሌ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. በይፋ ሥራ የሚጀምር መሆኑን ለማስታወቅ በሰጠው ጋዝጣዊ መግለጫ በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ሽፋን ያላገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አዲስ አሠራሮችንና አገልግሎቶችን ይዞ ገበያውን እንደሚቀላቀል አስታውቋል።

በተለይ ባንኩ በየዓመቱ ከሚሰጠው ብድር ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነውን ለአነስተኛና ለመካከለኛ ቢዝነሶች (የንግድ ሥራ ዘርፎች) ለማበደር የባንኩ ቦርድ ውሳኔ ማሳለፉን የባንኩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ለአብነት ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ አብዛኛው የገጠሩ ክፍል ሥራ ፈጣሪዎች፣ አነስተኛ ኢንተርፓራይዞች፣ እንዲሁም አንዳንድ የማኅበረሰቡ ክፍሎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ለባንክ አገልግሎቶች በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ባለመሆናቸው ባንካቸው ይህንን ክፍተት ለመሙላት የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት መወሰኑን የአኃዱ ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አንተነህ ሰብስቤ ገልጸዋል።

በመሆኑም ባንኩ በየዓመቱ ከሚያቀርበው ብድር እስከ 15 በመቶ ያህሉን ለሥራ ፈጣሪዎችና ለአነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ለማበደር መወሰኑን ገልጸዋል። በተጨማሪም በተለያዩ የባንኩ ቅርንጫፎች ለተመረጡ ሥራ ፈጣሪዎች የምርት ማሳያ ቦታ ለማጋራት መዘጋጀቱን የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ባንኮች ለተበዳሪዎች ካሠራጩት የብድር ክምችት ውስጥ ሦስት አራተኛው በአዲስ አበባና በአካባቢው ለሚገኙ ተበዳሪዎች የቀረበ መሆኑን የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ የብድር ሥርጭቱ መዛባት የሚታይበት በመሆኑ አኃዱ ባንክ ይህንን ክፍተት በማየት የብድር አቅርቦቱ ለገጠሩ አካባቢ ጭምር እንዲደርስ የሚሠራ ይሆናል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ መበደር ከሚችሉት ዜጎች የብድር ተጠቃሚ የሆኑት ከአንድ በመቶ በታች መሆናቸውን፣ በአገልግሎት ተደራሽነት በኩል ደግሞ ከአጠቃላይ የባንክ አገልግሎት ተደራሽ የሆነው ሕዝብ ቁጥር ከ40 በመቶ በታች መሆኑን የገለጹት አቶ አንተነህ፣ ይህንን ክፍተት በማየት ተደራሽነቱን ለማስፋት ብዛት ያላቸው የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ወኪሎችንም ይዞ ወደ ገበያ እንደሚገባ ገልጸዋል። ተደራሽነቱን ለማስፋትም ከተለመደው በሠራተኛ ከታገዘ የቅርንጫፍ አገልግሎት በተጓዳኝ ደንበኞች በራሳቸው የዲጂታል አገልግሎት የሚያገኙበትን የቅርንጫፍ ውስጥ አገልግሎት አደረጃጀት እንደሚያመቻች፣ እንዲሁም የገጠር የባንክ አገልግሎትን ለአርሶ አደሮችና የገበሬ ማኅበራት፣ እንዲሁም በግብርና እሴት ሰንሰለት ለሚሳተፉ ተዋናዮች በስፋት ለማዳረስ የሚያስችለውንም ዝግጅት ማድረጉን ዘርዝረዋል፡፡ የመጀመርያው የአኃዱ ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን የተሰየሙት የቀድሞ የቡና ባንክ ፐሬዚዳትን አቶ እሸቱ ፋንታዬ በበኩላቸው፣ ባንኩ ከብድር አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በኢንዱስትሪው አዲስና የመጀመርያ የሚባሉ አገልግሎቶችን የሚተገብር መሆኑን አስታውቀው፣ ይህንንም ለመተግበር የሚያስችሉ በቂ ዝግጅቶች መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፡፡   

‹‹በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጥናት መሠረት ተቀማጭ ገንዘብ እየተሰባሰበ ያለው ከብዙዎች ነው፡፡ ነገር ግን ብድሩ እየተሰጠ ያለው ለጥቂቶች ነው፤›› ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ አቶ አንተነህ፣ ይህን አሠራር የሚለውጥና ከብዙዎች የተሰበሰበውን ሀብት ለብዙዎች የሚያደርስ የአገልግሎት አሰጣጥ ባንካቸው እንደሚከተል አስረድተዋል፡፡ ይህንን መርህ በመከተልም፣ ከገጠሩ የተሰበሰበውን ለገጠሩ ለማዋል ጭምር መታቀዱን ገልጸዋል። በአነስተኛ ደረጃ ያሉ ተበዳሪዎች ከ100 እስከ 1,000 ብር መበደር የሚችሉበትን ዕድል ባንኩ የሚያመቻችላቸው እንደሆነም የባንኩ ኃላፊዎች አብራርተዋል፡፡  ብድር ለወራት ብቻ ሳይሆን ጠዋት ተበድሮ የገዛውን ዕቃ ሸጦ ማታ የሚከፍልበት አዲስ አሠራርን ባንኩ እንደሚዘረጋ አስታውቀዋል፡፡  

በርካታ አዳዲስ አገልግሎቶችን ይዞ እንደሚመጣ የገለጹት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ እሸቱ በበኩላቸው፣ ‹‹በኢትዮጵያ የመጀመርያው ባንክ ሊያደርጉን የሚችሉ አዳዲስ አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ በድፍረት የምንገባባቸው ሥራዎች ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡ በባንኩ ራዕይ ላይ ጎልቶ የተቀመጠው መርህ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ፋይናንስ ዘርፍ መሪ ሆኖ ለወገንና ለአገር አለኝታነቱን ማረጋገጥ›› የሚል እንደሆነ ጠቅሰው፣ ‹‹የምንሰጠው አገልግሎት ለአገር ትርጉም አለው ወይ፣ ኢትዮጵያን ያራምዳል ወይ? ብለን የምንተገብረው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ዕድሜ 104 ዓመት እንደሞላው ያስታወሱት አቶ እሸቱ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውጪ ያሉት ሌሎች የግል ባንኮች በቆዩባቸው ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ በሚሆነው ጊዜ ውስጥ ለግብርና የሰጡት ብድር ከአንድ በመቶ ወይም 0.65 በመቶ እንደሆነ አስረድተዋል። የኢትዮጵያ የንግድ ባንክ ተጨምሮ የአገሪቱ ባንኮች በጠቅላላ ለግብርናው ዘርፍ ያቀረቡት ብድር ከአጠቃላይ የብድር መጠናቸው 3.65 በመቶ አካባቢ ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም ይህንን መለወጥ የሚቻል መሆኑን በማመን፣ ‹‹የግብርና ብድር አክሳሪ ነው›› የሚለውን አስተሳሰብ ‹‹የግብርና ብድር ያዋጣል›› ወደሚል ሽግግር ለመምጣት በድፍረት የሚገቡበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ 

Ahadu-Bank-Photo-By-Ethiopian-Reporter--Ethiopian-News-1

አቶ እሸቱ ባንካቸው የሚከተለውን የብድር አሰጣጥ መርህም የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ‹‹የብድር አገልግሎትን በምናከናውንበት ጊዜ ራሳችንን የምንመዝነው ምን ያህል ብድር ሰጥተናል ሳይሆን፣ የሰጠነው ብድር ምን ያህል ሠራተኞችን ለመቀየር አስችሏል በሚል ነው ራሳችንን የምናየው፤›› ብለዋል፡፡ 

ባንኩ ይዤዋለሁ ያለው ሌላው የብድር አገልግሎት ከአነስተኛ መጠን ካለው ገንዘብ ጀምሮ የሚሰጥ ሲሆን፣ ከ100 ብር ጀምሮ ብድር የሚመቻች ይሆናል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጠውም በስልክ ሲሆን፣ ሌላው ቀርቶ አንድ ሰው መደብር ውስጥ ገብቶ አንድ ዕቃ ለመግዛት ብር ቢጎድለው በዚያ ቅስፈት አካውንት ከፍቶ ቀሪውን ገንዘብ ወዲያው ተበድሮ ዕቃውን ገዝቶ መሄድ እንዲችል የሚያስችል አሠራር የሚፈጥር አገልግሎት ጭምር ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡  

ባንኩ 15 በመቶ የሚሆነውን ብድር ለአነስተኛና መካከለኛ ተበዳሪዎች ለመስጠት ውሳኔ ላይ መድረሱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክን ሕግ ሊፃረር ይችል እንደሆነ ተብለው ተጠይቀው በሰጡት ማብራሪያም፣ ብሔራዊ ባንክ ራሱ አኃዱ ባንክ ወደተከተለው መርህ እየመጣ መሆኑን የሚያሳይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ እሸቱ እንደሚሉት ባንኮች የሚሰጡትን ብድር ምን ያህሉ ለየትኛው የኢኮኖሚ ዘርፍ መሄድ አለበት የሚል ተመን ወይሞ ምደባ እስከዛሬ በብሔራዊ ባንክ ባይወሰንም፣ ለመጀመርያ ጊዜ በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከወራት በፊት ባለፈው ውሳኔ የአገሪቱ ባንኮች ከአጠቃላይ ብድራቸው ውስጥ 15 በመቶ የሚሆነውን ለግብርና ዘርፍ እንዲያቀርቡ ማዘዙን ገልጸዋል። ስለዚህ ይህ ውሳኔያቸው ከብሔራዊ ባንክ አሠራር ጋር የማይጋጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ውሳኔ በስተቀር በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠ ሌላ ገደብ ባለመኖሩ፣ በዚሁ መሠረት ዕቅዳቸውን ዳር እንደሚያደርሱ ተናግረዋል፡፡ በኢትዮጵያ ብድር የሚያገኙ በቀጥታ ከምርት ጋር የተያያዙ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ሰዎች እምብዛም መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ እሸቱ፣ ብድር የሚያገኙት በአብዛኛው የንግድ ዝውውር ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች በመሆናቸው ምክንያት በአገር ደረጃ የሚፈጠሩ የምርት አቅርቦት እጥረቶች ምንጫቸው ይኼው የብድር አሰጣጥ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ሌሎች ባንኮችም በተመሳሳይ ከሚሰጡት ብድር አምስትና 15 በመቶውን ለአነስተኛና ለመካከለኛ ቢዝነሶች ቢሰጡ ‹‹በኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬ ከዕቃ አቅርቦት ጋር የሚፈጠሩ እንከኖች ሊሰበሩ የሚችሉና ከዋጋ ግሽበት አዙሪት ውስጥ ልንወጣ እንችላለን፤›› ብለዋል፡፡ 

ባንኩ ወደ አገልግሎት የሚገባው 556 ሚሊዮን ብር የከፈለና 702 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ በመሆኑ፣ ይህ የካፒታል መጠን ከሌሎች ባንኮች አንፃር ሲታይ አነስተኛ መሆኑ ተፅዕኖ አይኖረውም ወይ ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ጠንካራ የባንክ ካፒታል መያዝ አስፈላጊ ቢሆንም፣ ውጤታማ አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ሲመዘን ግን ትርጉም እንደማይኖረው ገልጸዋል።

በአንዳንድ አገሮች ውስጥ አንድ ባንክ መያዝ ያለበት የካፒታል መጠን ከአጠቃላይ ሀብቱ ስምንት በመቶ እንደሆነ፣ በኢትዮጵያ የባንክ ሕግ ላይም የተቀመጠው ድንጋጌ በተመሳሳይ ስምንት በመቶ ካፒታል እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ መሆኑን ጠቅሰዋል። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በምሳሌነት የጠቀሱት አቶ እሸቱ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል መጠን 51 ቢሊዮን ብር መሆኑን፣ ነገር ግን የሚንቀሳቅሰው ገንዘብ ወደ 1.2 ትሪሊዮን ብር እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካፒታል ከሚያስተዳድረው አጠቃላይ ሀብት አንፃር ያለው ሬሾ ከስምንት በመቶ በታች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ በሌሎች ባንኮችም ሲታይ ካፒታላቸው ከሚያስተዳድሩት ሀብትና ዕዳቸው (ሊያብሊቲ) ጋር ሲመዘን የሚያንቀሳቅሱበት ሀብት ከካፒታሉ ከ14 እስከ 18 ጊዜ እጥፍ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም ለውጤታማ የባንክ አግልግሎት ካፒታል መሠረታዊ ነገር ተደርጎ መውሰድ እንደሌለበት ገልጸዋል።

የውጭ ባንኮች ቢመጡ ግን ተወዳዳሪነትን ለመጨመር ካፒታል ወሳኝ መሆኑን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ለዚህ ደግሞ ባንካቸው ቢበዛ በአራት ዓመት ብሔራዊ ባንክ ያስቀመጠውን የአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ለማሟላት ዕቅድ በመያዙ ሥጋቱን መቀነስ እንደሚችል አመልክተዋል፡፡ 

በዚሁ ጥያቄ ዙሪያ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ አንተነህ በበኩላቸው፣ አኃዱ ባንክ አሁን ላይ ከ702 ሚሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታል ያለውና የተከፈለ ካፒታሉ ደግሞ ወደ 565 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ አሁን ካለው አንፃር ይህ የካፒታል መጠን ምን ያህል ያስኬደዋል የሚለው የምንጠቀምበት የንግድ ንድፈ ሐሳብ ወስነዋል ብለዋል፡፡

ባንኩ በሚደራጅበት ወቅት አሁን ያለውን ካፒታል ማሰባሰብ የቻለው በስድስት ወራት ውስጥ ነውና አዲስና ተወዳዳሪ የሆነ ጽንሰ ሐሳብ ይዞ በመጣ የባንክ አገልግሎት ደግሞ አምስት ቢሊዮን ብር አይደለም ከዚያ በላይ ለማድረስ እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡ የውጭ ባንኮች ከመጡም ለዚያ በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው ያሉት አቶ አንተነህ፣ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በቂ ዝግጅት ከወዲሁ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በ17 አደረጃጀት ኮሚቴ አባላት ታኅሳስ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. የተጠነሰሰውንና 10 ሺሕ የሚደርሱ ባለአክሲዮኖችን ያሰባሰበው አኃዱ ባንክ በዋናው መሥሪያ ቤት ባደራጀው ዘመናዊ ቅርንጫፍ ሥራውን በይፋ የሚጀምር ይሆናል፡፡ ከምርቃቱ ዕለት አንስቶ በተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች ዝግጁ የሚያደርጋቸውን አቅርንጫፎች በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፍ ብዛቱን እስከ መስከረም 30 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 50 ለተከታታይ ቀናት የሚያስኬድ መሆኑን ያስታወቀው አኃዱ ባንክ፣ በአደረጃጀቱ ተሠርቶ የነበረውንና ሲገለገልበት የነበረውን መለያ ዓርማውን በአዲስ በመተካት ባለፈው ሐሙስ ሰኔ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች