Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊዓለም አቀፍና ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ከአገሪቱ ሕግ ውጪ እየሠሩ ነው ተባለ

ዓለም አቀፍና ማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ከአገሪቱ ሕግ ውጪ እየሠሩ ነው ተባለ

ቀን:

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ዓለም አቀፍና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች አሠራር፣ ከተማሪ ወላጆችና ከአገሪቱ ሕግ ጋር አለመግባባት ፈጥሯል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙና በውጭ አገሮች ኤምባሲዎችና ግለሰቦች የተከፈቱ 27 ትምህርት ቤቶች ያሉ ሲሆን፣ አብዛኞቹ የክፍያ ሥርዓታቸውና የትምህርት ቤቶቹ ቁመና አለመግባባት ትምህርት ሚኒስቴር ደርሷል፡፡

ከ27ቱ ትምህርት ቤቶች መካከል የተወሰኑት ከአገሪቱ ሕግ ውጪ በውጭ ምንዛሪ ክፍያን የሚቀበሉ ሲሆን፣ ሌሎች ደግሞ ከተቋቋሙለት ዓላማ ውጪ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ለአብነትም በማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ከተመሠረቱ በኋላ፣ ወደ ትምህርት ኢንቨስትመንት ተቀይረው የሚያስከፍሉት ክፍያ ከፍተኛ መሆኑን ሪፖርተር ከተማሪ ወላጆችና ከትምህርት ሚኒስቴር ለመረዳት ችሏል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉና በጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት ልጃቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች ለሪፖርተር እንደተናሩት፣ ትምህርት ቤቱ የልጆቻቸውን የትምህርት ክፍያ በውጭ ምንዛሪ፣ በውጭ አገር በሚገኝ ባንክ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

የወላጆቹን ቅሬታ ተቀብሎ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት የሚመለከታቸውን የኤምባሲው የባህልና ኢኮኖሚ ክፍል ኃላፊ ካለ ሆልስፈዝ (ዶ/ር)፣ ትምህርት ቤቱ እ.ኤ.አ በ2004 የጀርመን ኤምባሲ ከኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ባደረገው ስምምነት መሠረት፣ በራሱ አሠራር የሚተዳደርና ክፍያውን የመወሰን ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በዚሁ ትምህርት ቤት ከሚማሩ 327 ተማሪዎች መካከል 96 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ብር እንዲከፍሉ የሚደረግ መሆኑንና ቀሪዎቹ የውጭ አገር ፓስፖርት የያዙ ተማሪዎች በዩሮ እንዲከፍሉ እንደሚያደርጉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ለሪፖርተር ቅሬታ ያቀረቡት ወላጆች እንደተናሩት፣ ልጆቻቸው ትውልደ ኢትዮጵያዊ ሆነው የውጭ ፓሰፖርት የያዙ በመሆኑ ብቻ ለመጪው እ.ኤ.አ 2022/2023 የትምርት ዘመን ክፍያ በውጭ አገር በሚገኝ ባንክ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

እ.ኤ.አ በ2004 ዓ.ም. የተደረገው ስምምነት እንደሚያመለክተው፣ የጀርመን ኤምባሲ ትምህርት ቤት የክፍያ ሁኔታ በብር ወይም በውጭ ምንዛሪ ይክፈል የሚለውን በግልጽ ባያስቀምጥም፣ የትምህርት ቤቱ ቦርድ ስለከፍያ እንዲወስን ልዩ ሥልጣን ይሰጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ሪፖርተር ያገኘውና በትምህርት ሚኒስትር አጠቃላይ የትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ አስፋው መኮንን፣ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. ለ27 ዓለም አቀፍና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች የጻፉት ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የትምህርት ክፍያ ተደጋጋሚ የሆነ የቅሬታ ምንጭ እየሆነ ስለመምጣቱ ያመላክታል፡፡

በመሆኑም የማንኛውም ትምህርት ቤት ክፍያ በብር ብቻ መደረግ እንዳለበትና የዶላር የክፍያ ሥርዓትን /dollarization/ የማይፈቀድ መሆኑንና የመመዝገቢያ ክፍያ ከ25 በመቶ በላይ መብለጥ እንደሌለበት በደብዳቤው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

ይሁን እንጂ የኤምባሲው የባህልና ኢኮኖሚ ክፍል ኃላፊ ካለ (ዶ/ር) ይህ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው የገለጹ ሲሆን፣ ያም ሆኖ ግን ትምህርት ቤቱ የዓለም አቀፍ ፓሰፖርት የያዙ ተማሪዎችን በዩሮ የማስከፈል ሥልጣን እንዳለው አክለው ገልጸዋል፡፡

ለትምህርት ቤቶቹ የማሳሰቢያ ደብዳቤ የጻፉትን አቶ አስፋውን ስለጉዳዩ ማብራሪያ ለመጠየቅ ሪፖርተር በተደጋጋሚ ስልክ ቢደወልላቸው ለማናገር ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ፕሮግራሞችና ጥራት ማሻሻል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ወጋሶ እንደሚሉት፣ እነዚህ ዓለም አቀፍና የማኅበረሰብ ትምህርት ቤቶች ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ ችግሮች እንዳሉባቸው ከወላጆች እየተነሳባቸው ስለመሆኑ አብራርተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ የወላጆችን ቅሬታና አቤቱታ ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት የባለሙያ ቡድን በመላክ እየተነሱ ያሉትን ችግሮች ተለይተው አሠራር ለሚያስፈልጋቸው አሠራር እንዲዘረጋ፣ በአደረጃጀት መመለስ ያለበትን በአደረጃጀት እንዲሁም በመመርያ መመለስ ያለበትን ደግሞ በመመርያ ለመመለስ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የጀርመን ትምህርት ቤት ወላጆች በውጭ ምንዛሪ እንዲከፍሉ ስለመጠየቃቸው ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው አቶ ዮሐንስ፣ ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር በመሆኗ በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ ማናቸውም ዓይነት ግብይት በአገሪቱ ገንዘብ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ የጀርመን ኤምባሲ፣ የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትና ሌሎችም ስማቸውን ያልጠቀሷቸው ትምህርት ቤቶች አመሠራረታቸው በማኅበረሰብ (Community School) ቢሆንም፣ አሁን ላይ ወደ ትምህርት ኢንቨስትመንት እንደገቡና ከፍተኛ የሆነ ገንዘብ እንደሚያስከፍሉ ገልጸዋል፡፡

የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት አጀማመሩ ለግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ለመስጠት በሚል የተቋቋመ ቢሆንም፣ በጊዜ ሒደት አሁን ወደ ኢንቨስትመንት መቀየሩንና በተለይም ከ90 በመቶ በላይ የሚሆነው ተማሪ የሌላ አገር ዜግነት ያላቸው እንደሆኑ መረጋገጡን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤትን ጨምሮ በርካታ ትምህርት ቤቶች ድሮ ከተነሱበት ዓላማ ውጪ በዓለም አቀፍ ትምህርት ቤት ስም ወደ ኢንቨስትመንት በመግባታቸውና ይህንንም ሕጉ ስለማይፈቅድ ለትርፍ ያልተቋቋመ ትምህርት ቤት ሆነው እንዲመዘገቡ የሚረዳ መመርያ እየተዘጋጀ መሆኑን አክለው ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም የግሪክ ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት እስከ መጪው መስከረም በሲቪል ማኅበራት ባለሥልጣን እንዲመዘገቡ ማስጠንቀቂያ መሰጠቱን አቶ ዮሐንስ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...