Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉበአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል...

በአገራዊ ውይይት ውስጥ የውጭ ኃይሎች የተሳትፎ ሚናና የሌሎች አገሮች ተሞክሮ (ክፍል ሁለት)

ቀን:

በመኮንን ዛጋ

የውጭ ኃይሎች መሠረታዊ ሚና

በቀጣይ የጽሑፌ ክፍል የውጭ ተዋናዮች በብሔራዊ የውይይት ሒደቶች ውስጥ የሚጫወቷቸውን በርከት ያሉ ሚናዎች ለመዘርዘር እሞክራለሁ። በእርግጥ የውጭ ኃይሎች በሚጫወቷቸው ጉልህ ሚናዎች መካከል የጎራ መደበላለቅና የድርጊት ውጤት መደራረቦች እንዳሉ ግልጽ ሲሆን፣ ከታች የተቀመጠው ምደባ የውጭ ተዋናዮች ጣልቃ ገብነታቸውን በሚገባ እንደሚያስተባብሩ ለምክክር ኮሚሽኑ ተገቢውን መንገድ ለመጠቆም ነው፡፡

ብዙውን ጊዜ እነዚህ ተዋንያን በጊዜያዊ ሁኔታና ባልታቀደ መልኩ የሚሳተፉ ሲሆን በአብዛኛው በራሳቸው የፍላጎት-ጥቅም ሰንሰለት ማዕቀፍ ውስጥ የሚሽከረከሩ ናቸው። ከዚህም በላይ ለውጭ ተዋንያን ተሳትፎ ‘አንድ መጠን ለሁሉም’ ‘One Size-Fit-To-All’ የሚባል አካሄድ የለም። ስለሆነም በተሳትፏቸው ውጤታማ ለመሆን በሚያደርጉት እያንዳንዱ ጣልቃ ገብነት ውስጥ የአንድን አገር ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ዓውድ ግምት ውስጥ ማስገባት አለባቸው።

እንዲሁም ይህ የጽሑፍ ክፍል በፖለቲካዊና በልማት ተዋናዮች ሚና ላይ አጠር ያለ ማብራሪያ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ በእርግጥ ሁለቱም አካላት አገራዊ ውይይቶችን በአንድም በሌላ በኩል የመደገፋቸው ድርጊት ዘልማዳዊ የሚና ክፍፍሎሽ ብዥታ መከሰቱን የሚያመለክት ነው፡፡ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ልማታዊ ተዋናዮች ወደ ድጋፍ ተግባር የሚገቡት የፖለቲካ ውይይት፣ ምክክር፣ ድርድርና መግባባት ሒደቱ ከተጠናቀቀና የስምምነት ማዕቀፍ ከተፈረመ በኋላ በትግበራው ምዕራፍ ሒደት ውስጥ ያለውን ክንውን ለመፈጸምና ስምምነት የተደረሰበትን የመልሶ ግንባታና የልማት ሥራዎችን ለመደገፍ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ የልማት ተዋናዮች በርካታ ሚናዎችን በአንድ ላይ አሰባጥረው በመያዝ ብሔራዊ ውይይቶችን በመደገፍ ረገድ፣ በፖለቲካ ሒደቶች ውስጥም ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛሉ።

እነዚህ ሚናዎችም በዋናነት በተወያይ ኃይላት መካከል የእርስ በርስ መተማመንን የማጎልበት ዕርምጃዎችን ማመቻቸት፣ ተአቅቦ የመረጡ አገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት በውይይት ሒደቶች ውስጥ እንዲሳተፉ ማኅበረ ፖለቲካዊ ማበረታቻዎችን በመስጠት፣ የልማት ጉዳዮች በአገራዊ ውይይቶች ውስጥ መካተታቸውን ማረጋገጥ፣ የሎጂስቲክስ፣ የፋይናንስ ድጋፍ መስጠትና ቴክኒካዊ/ሙያዊ ዕውቀትን ማቅረብ፣ የውይይት መሠረተ ልማቶችን መደገፍ፣ ማጎልበት፣ እንዲሁም ከብሔራዊ ውይይት የተገኙ ውጤቶችን ተግባራዊነት ማሳለጥን ያጠቃልላል። ስለሆነም ውጫዊ ኃይሎች በዋናነት ስድስት ሚናዎችን የሚጫወቱ ሲሆን፣ ከአገር አብነታዊ ተሞክሮ ጋር እንደሚከተለው በዝርዝር ቀርበዋል፡፡

አስቻይ የውጭ ተዋናዮች ከአስቻይነት ሚናቸው አንፃር ሲታዩ

እነዚህ ኃይሎች በመሠረታዊነት ሊያከናውኑት ከሚገባው ተግባር ዋነኛው፣ በሁሉም የአገራዊ ውይይቱ ተሳታፊ አካላት መካከል ለውይይትና ተግባቦት ምቹ አስቻይ ከባቢን መፍጠር ነው፡፡ እነዚህ አካላት በአንድ አገር ለሚከናወን አገራዊ ውይይት ድጋፍ ለመፍጠር ሲሰባሰቡ፣ አዎንታዊና አሉታዊ ተፅዕኖአቸውን (የካሮትና የአርጩሜ መርሆዎችን) በሁሉም ያልተግባቡ አካላት ላይ ሲጠቀሙ፣ እንዲሁም ውስጣዊ የፖለቲካ ኃይሎቹ ከሌላኛው የሐሳብ ተቃራኒ ወገናቸው ጋር ወደ ውይይት እንዲያመሩ ለማድረግ ተገቢ ጫና ሲፈጥሩ እንደ ‘አስቻይ ኃይል’ ተደርገው ይወሰዳሉ።

የውጭ ተዋናዮች የምንላቸው ፖለቲካዊና ልማታዊ ኃይሎች የተለያዩ የፖለቲካና ማኅበረሰባዊ ወገኖች በአገራዊ ውይይት እንዲሳተፉ ለማደፋፈር፣ እንደ አግባብነታቸው በተመረጠ ሥልት ልዩ ልዩ ጫናዎችና ማበረታቻዎችን አደባልቀው ሊጠቀሙ ይችላሉ፡፡ ይኸውም በመደበኛ የአደባባይ የውግዘት ወይም ድጋፍ መግለጫዎች፣ ለስለስ ያሉ ማዕቀቦችን በመጣል፣ የኢኮኖሚ ጭቆናዎችና ዕገዳዎችን በመፍጠር (የጉዞ ዕገዳዎችን ጨምሮ)፣ የነፃ እንቅስቃሴ ክልከላዎች በማድረግ ወይም ደግሞ በተቃራኒው አዎንታዊ ማበረታቻዎችን ለመንግሥታት እንደ የዕዳ ዕፎይታ ዕርምጃዎች፣ ልዩ ልዩ የድጋፍና የዕርዳታ ማዕቀፎች (ፓኬጆች)፣ እንዲሁም ግንኙነቶችን ውጥረት አልባ ወይም መደበኛ በማድረግ፣ በተገባው ቃል መሠረት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍና ከለላ በመስጠትና በሌሎችም ማትጊያው ሊመጣ ይችላል። ሆኖም ውጫዊ ኃይሎች እነዚህን ስስና የተጠኑ የማዕቀብ ፖሊሲዎች ሲተገብሩ በጥንቃቄ ጥቅም ላይ ማዋል አለባቸው፡፡ ምክንያቱም እንደ ከፍተኛና ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ስለሚቆጠሩ የተወያይ ኃይሎችን የአቅም ሚዛን ሊያዛቡ ይችላሉ፡፡ በአንፃሩ ደግሞ እነዚህ ፖሊሲዎች በጥንቃቄ በተጠና መንገድ ጥቅም ላይ ከዋሉ፣ ለነባራዊ ሁኔታው በሚገባው ልክ ምቹ መደላድል በመፍጠር ተዋናይ ወገኖች ሙሉ ፈቃደኛና ለውይይት የበለጠ ምቹ እንዲሆኑ ይረዳሉ፡፡

ፖላንድ ለዚህ ዓይነቱ የአስቻይነት ውጫዊ ጫናና ድጋፍ ሁነኛ ማሳያ ናት። በ1989 በአገሪቱ የተካሄደውን የፖለቲካ ሽግግር ሒደት ላይ ለመደራደር በተቋቋመው አገራዊ የውይይት መድረክ ውስጥ አስቻይ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ የውጭ ኃይሎች ሚናና ውጫዊው ሁኔታ ትልቅ ድርሻ የተጫወቱባት ነበረች፡፡

በእርግጥ አስቀድሞ በ1980ዎቹ መጀመርያ አካባቢ በሶቭየት ኅብረት ኮሙዩኒስት ፓርቲ ውስጥ በሚገኙ የለውጥ ኃይሎች እንቅስቃሴና በመሪው ሚኻኤል ጎርባቾቭ በተነደፈው በፔሬስትሮይካ (መልሶ-ማበጀት) እና ግልጽነት (ግላስኖስት) የለውጥ ፖሊሲ ተነሳሽነት መሠረት ብሔራዊ ውይይት ለሚፈልጉ የለውጥ አራማጆች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ሆኖም የምዕራቡ ዓለም መሪዎች በአገሪቱ እውነተኛና ሥር ነቀል ለውጥ ካልመጣና የሥርዓት ማሻሻያዎች በምሉዕ ካልተተገበሩ የቀጥታ ገንዘብ ድጎማና የዓይነት ድጋፍ ጭራሽ እንደሚከለክሉ ማስፈራራታቸው በፖላንድ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል። ይህ ተከታታይና መጠነ ሰፊ ጫና መፈጠር የፖላንድ መንግሥት ከየካቲት እስከ ሚያዝያ 1989 በሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች መካከል የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት ሒደት ለማካሄድ ከተስማማባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነበር።

ለውጭ ኃይሎች የአስቻይነት ሚና ማሳያ ሌላው ዓይነተኛ ተምሳሌት ደግሞ የደቡብ አፍሪካው ድርድር ሒደት ነው፡፡ በአገሪቱ ላይ የተጣለው ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በኤፍ. ደብሊው. ደ ክለርክ ፕሬዚዳንትነት የሚመራው የአፓርታይድ አገዛዝ፣ በኔልሰን ማንዴላ ከሚመራው ከአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ ፓርቲ ጋር ወደ ውይይት እንዲገባ አሉታዊ ማበረታቻ ወይም አስቻይ አቅም ሆኖ አገልግሏል። በፕሬዚዳንቱ መኖሪያ መንደር በተደረገው በውይይቱ ጅማሮም ሁለቱም ወገኖች የተስማሙበት የግሩተ ሹር ስምምነት ቃለ ጉባዔ (Groote Schuur Minute) ለሕዝብ በይፋ እንዲገለጽ ተደርጓል፡፡ በእርግጥ በዚህ ቅድመ-ድርድር ውይይት መጀመርያ ላይ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ፣ የፓን አፍሪካኒስት ኮንግረስ፣ የደቡብ አፍሪካ ኮሙዩኒስት ፓርቲና የተባበሩት ዴሞክራሲያዊ ግንባር አካላት ተሳታፊ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ውይይቱ እጅግ ሰላማዊ የፖለቲካዊ ሽግግርን አስከትሏል።

ከዚህም በላይ የሶሪያ አገራዊ ውይይት መድረክ ጉዳይ የሚያሳየው ሌላው ነጥብ ደግሞ የውጭ ተዋናዮች የብሔራዊ ውይይቶችን ሐሳብ አጠንክረው በማንሳትና በሰላማዊ ድርድሮች ላይ በማዕከላዊ አጀንዳነት እንዲቀነቀን በማድረግ፣ ሁሉም ኃይሎች በአገራዊ ውይይት ላይ ቁርጠኝነት እንዲኖራቸው ለማረጋገጥ አስችሏቸዋል።

በአንዳንድ የአገራዊ ውይይቶች ምዕራፎች፣ ወቅቶች፣ አጀንዳዎችና ሁኔታዎች ውስጥ ደግሞ የውጭ ተዋናዮች ከአስቻይነት ይልቅ “አሰናካይ” ሆነው ሊገኙ ይችላሉ፡፡ ይኸውም የግጭቱ ተዋንያንና የፖለቲካ ተፎካካሪ አካላት በብሔራዊ ውይይት ውስጥ በንቃት እንዳይሳተፉ የሚያበረታቱ ከሆነ፣ ወይም የተለያዩ ስንኩል ምክንያቶች በመፍጠርና የራስን ፖለቲካዊ መሻት በሚያስጠብቅ መልኩ ቡድኖችን በማደራጀት በተሳትፎው ላይ ሳንካ የሚፈጥሩ ሲሆን ነው፡፡ በዚህም የተለያዩ ሰበቦችና መሰናክሎችን በመፍጠር በተጋላጭ አካላት መካከል የሚፈጠር ማንኛውንም ስምምነት በማንኳሰስና የሚደረስበትን ውጤት አናሳ የሚያደርግ መጠነ ሰፊ ዕርምጃ እየወሰዱ፣ ውይይቱን በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ተመቶ ሽባ እንዲሆን በማድረግ እንደ ‘አሰናካይ’ ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ።

ለዚህም ዓይነተኛ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የቀደመ የዩክሬን ጉዳይ ነው፡፡ በየካቲት 2014 ዓ.ም. ከፈነዳው ከማይዳን አብዮት (Maydan Revolution) በኋላ በምሥራቅ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱ፣ እንዲሁም በምሥራቅና በምዕራቡ ክንፍ መካከል እየጨመረ የመጣው የጂኦ-ፖለቲካዊ ቅርምት ውድድር በተለያዩ የዩክሬን ማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ከመነጋገር ይልቅ ሥር የሰደደ የግጭት አመክንዮ እንዲኖር አድርጓል። በዚህም በርካታ የዩክሬን ግዛቶች ራሳቸውን እንደ ሉዓላዊ አገር እንዲቆጥሩ አድርጓቸዋል፡፡ የቅርብ ጊዜው የሩሲያና የዩክሬን ጦርነትና የተለያዩ ግዛቶች የራስ ገዝነት ጥያቄ የእዚሁ መሰናክል አንድ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህም የውጭ ኃይሎች በማኅበረሰቡ መካከል ለውይይት አስቻይ ምኅዳር ከመፍጠር ይልቅ፣ ከፋፋይ ሐሳቦችን በማንሳትና የጎራ ሽሚያ በመፍጠር ዩክሬን በሁለት ባላ የተወጠረች አገር እንድትሆን አድርገዋል፡፡

በአገራዊ ውይይት ሒደት ምዕራፎች ውስጥ የውጭ ተዋናዮች የአስቻይነት ተግባር ወሳኝ የሚሆነው የቱ ጋር ነው ስንል? ብንጠይቅ መልሱ ገና ከጅምሩ ምናልባትም በቅድመ ዝግጅት ወቅት ነው፡፡ ይህ ሚና ተዋናይ ወገኖች በውይይት ለመሳተፍ ያላቸው ፍላጎት ገና እየተፈጠረ ባለበት የመግደርደር ጊዜ በመሆኑ በጣም አስፈላጊ ነው። ሌላው የውጭ ኃይሎች የአስቻይነት ተሳትፎ አስፈላጊነት በክንውን ሒደት ላይ እያለ ድርድሩ ሲታገድ (ወይም ቅርቃር ውስጥ ሲገባ) ወይም በተደራዳሪ ወገኖች ግትርነት ወደ መቋረጥ አፋፍ ላይ ሲደርስ ሲሆን፣ እንዲሁም በአፈጻጸም ወቅት ያለውን የትግበራ መነሳሳት ለማስቀጠል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ፈንድ አቅራቢ (ገንዘብ ሰጪ)

በዚህ ሚና የሚካተተው የፋይናንስና ሎጂስቲክስ ድጋፍ ሲሆን፣ ይህም የውጭ ተዋናዮች ለብሔራዊ የውይይት ሒደት የተሻለ አፈጻጸም የሚረዱ አማራጭ የገንዘብ ምንጮችን፣ የፋይናንስና ሎጂስቲክስ ድጋፎችን ሲያቀርቡ እንደ ደጓሚ (ፈንድ አቅራቢ) ሆነው ሊሠሩ ይችላሉ።

በአብዛኞቹ ሁኔታዎች የምክክር ኮሚሽኖች ጽሕፈት ቤቶች (ሴክሬታሪያት) መደበኛ የቢሮ ሥራዎችን ለማስኬድ፣ የውይይት ማድረጊያ ቦታዎችን ኪራይ ክፍያ ለመፈጸም፣ ተሳታፊዎችን ለማስተናገድ፣ የጥናትና ምርምር ባለሙያዎችን ለመጋበዝ፣ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለማሰናዳትና ሌሎች ተያያዥ ሥራዎችን ለመሥራት ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል። ለምሳሌ ያህል የየመን ብሔራዊ የውይይት ጉባዔን ለማዘጋጀት የተበጀተው በጀት 37 ሚሊዮን ዶላር ነበር። ይህን ገንዘብ ለአገራዊ ውይይት መበጀት እንደ የመን ላለ የደቀቀ ኢኮኖሚ አገር ፍፁም የማይቻልና የማይታሰብ ነበር፡፡ ሆኖም የውጭ ኃይሎች የየመን ሰላማዊ ፖለቲካዊ ሽግግርና ግጭት መቆም ለአካባቢው የሚኖረውን ጂኦፖለቲካዊ ፋይዳ በመገንዘብ ድጋፉን በቀጥታ ለማድረግ አንዳችም ማቅማማት አላደረጉም፡፡ እነዚህ የውጭ አካላት የፋይናንስና ሎጂስቲክስ ድጋፉን እንደ የመን በቀጥታ ወይም እንደ ኔፓል ደግሞ በተዘዋዋሪ ሁኔታ የፖለቲካ ሽግግር ሒደቱን በሚደግፍ አካባቢያዊ ዘዴ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡

ለምሳሌ የመን ውስጥ በተካሄደው አገራዊ ውይይት የክንውን ሒደቱ ወጪ የሚሸፍነው ከተለያዩ ቋቶች የሚመጡ ድጋፎችን በአንድ እንዲያሰባስብ በተቋቋመው ትረስት ፈንድ አማካይነት ነበር። ይህም ለጋሾች ድጋፋቸውን ፈሰስ የሚያደርጉበትና እንደ ድርሻቸው የሚጠበቅባቸውን አስተዋጽኦ የሚከፍሉበት የገንዘብ ቋት (ፋሲሊቲ) ሲሆን፣ በዚህ ሁኔታ የተሰበሰበው ሀብት በድንገተኛ ወይም አጣዳፊ ፍላጎቶች ላይ በመመሥረት በተለዋዋጭ መንገድ ጥቅም ላይ ሲውል ነበር።

የገንዘብ ድጋፍ ተለዋዋጭነት (እንደ ተጨባጭ ሁኔታው መሆን) ጠቀሜታ የብሔራዊ ውይይቶች በየምዕራፎቻቸው የቆይታ ጊዜና ግለትን (ፍጥነትን) ጠብቆ መቆየት ረገድ በእጅጉ ሊለያዩ ስለሚችሉ ብቻ ሳይሆን፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ወደ ሌላ ቦታ፣ ሁኔታና ጉዳይ ሊቀየር በሚችልበት ጊዜ በለጋሾች ዘንድ የረጅም ጊዜ ቁርጠኝነትን ለማረጋገጥ እጅጉን አስፈላጊ በመሆኑ ነው።

አብዛኛውን ጊዜ በትረስት ፈንዶች አማካይነት የሚሰጥ የድጋፍ ዘዴ ዘለቄታዊነትና ወጥነት፣ እንዲሁም ለውስጣዊ አካላት የመወሰን ነፃነት ስለሚኖረው ለብሔራዊ ውይይቱ ውጤቶች ትግበራም ሆነ ከፖለቲካ ሽግግር ሒደቶች ጋር ተያያዥ የሆኑ ሌሎች ተግባራትን ለመደገፍም ጥቅም ላይ ይውላል። ለምሳሌ በኬንያ በተደረገው አገራዊ ውይይት የገንዘብ ድጋፎች በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የገንዘብ ልገሳ በተቋቋመ ትረስት ፈንድ አማካይነት መውጣታቸው፣ ውይይቱና ድርድሩ ያለ ምንም ሳንካ በፍጥነት እንዲጀመር ከማስቻሉም በላይ ውይይቱን የመሩት የአፍሪካ ታዋቂ ሰብዕና ያላቸው ግለሰቦች ስብስብ (Panel of Eminent African Personalities) ከፋይናንስና ሎጂስቲክስ ችግሮች ነፃ በሆነ መንገድ ሥራቸውን ማከናወን እንዲችሉ አድርጓቸዋል፡፡

ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአገራዊ ውይይት ሒደትን በተቀመጠለት ግብና የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማስቀጠልና የውጤቶቹን አፈጻጸም ለመደገፍ በቂ የገንዘብ ድጋፍ አስፈላጊ ነው፡፡ የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ሁኔታ እንደሚያሳየው ከሆነ ደግሞ በብሔራዊ ውይይት ላይ ብቻ ማተኮር ሳይሆን፣ በተመሳሳይ ጊዜ በሒደቱ ውስጥ በተጓዳኝነት መሠረታዊ የመንግሥት ተግባራት እንዲቀጥሉ ማድረግም አስፈላጊ ነው፡፡ በእርግጥም ውጤታማ የሕዝብ አገልግሎቶች አቅርቦት ለውይይት ሒደት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልና ነው።

የገንዘብ ድጋፍ ፈርጅ የውጭ አካላት ተሳትፎ በየትኞቹ የሒደቱ ምዕራፎች ያስፈልጋሉ የሚለውን ብንመለከት በእያንዳንዱ የዝግጅት፣ የክንውን ሒደትና የትግበራ ደረጃዎች ላይ የገንዘብ ድጋፍ የሚያስፈልግ ቢሆንም በክንውን ሒደቱ ደረጃ ከፍተኛ ፍላጎቶች ይከሰታሉ።

ታዛቢና ዋስትና ሰጪ

ይህ ተግባር የውጭ ተዋናዮች በውይይት ሒደቱ ውስጥ ምንም ዓይነት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሳያደርጉና የነቃ ሚና ሳይጫወቱ ወይም ግልጽ ድርሻ ሳይወስዱ ሲገኙ ነው፡፡ እነዚህ አካላት በውይይቱ ሒደት እንደ ገለልተኛ ምስክር ሆነው ወይም ስለሒደቱ ክንውን ትክክለኛነት ዓለም አቀፋዊ ድጋፍ ሲያረጋግጡ ወይም ግድፈቱን ነቅሰው ሲተቹ ‘ታዛቢዎች’ ተብለው ይጠራሉ። ስለሆነም ገለልተኛ ታዛቢዎች የውይይቱ ተሳታፊ አካላትን የበለጠ ለማቀራረብና በተወያይ ወገኖች መካከል የጎንዮሽ ስምምነት በመፍጠር ረገድ በመተማመን ላይ የተመሠረተ ድርድር ለማድረግ ምቹ ሁኔታን መፍጠር ይችላሉ። ከዚህ ጋር አብሮ ተያይዞ የሚነሳው ሌላው የውጭ ኃይሎች ተሳትፎ ደግሞ የ‘ዋስትና ሰጭነት’ ሚና ነው። የውጭ ተዋናዮች ይህን ሚና የሚጫወቱት ለውይይቱ እንደ በላይ ጠባቂ (ሞግዚት) ሆነው ነው፡፡ በዚህም በከፍተኛ ደረጃ ቁርጠኝነታቸውን ሲያሳዩና እንደየተወከሉበት አገርና ማኅበረ ፖለቲካዊ መሠረት ፖለቲካዊ ድጋፋቸውን ለብሔራዊ ውይይት ሒደቱና ለውጤቶች አፈጻጸም ሲሰጡ ነው።

ከዚህ አንፃር የአገር የፖለቲካ ተዋናይ ወገኖች በውይይቱ ላይ ትንሽም እንኳ፣ ወይም ጭራሽ እምነት በሌላቸው ሁኔታዎች ውስጥ የውጭ ተዋናዮች እንደ ገለልተኛ ታዛቢነት ወይም ዋስትና ሰጪነት (የበላይ ጠባቂዎች ሆነው) ተሳትፈው መገኘት ጠንካራ የመተማመን መንፈስ ለመፍጠር ከማገዙም በላይ፣ በተቃራኒ ወገኖች ዘንድ በሒደቱ ውስጥ የመሳተፍን ሥጋት ለመቀነስ ይረዳል። ሆኖም እነዚህ ሚናዎች ጠንካራ የኋላ አቋምንና አቅምን የሚጠይቁ በመሆናቸው፣ ብዙውን ጊዜ ተፅዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ኃያላን መንግሥታት ወይም ጠንካራ ዓለም አቀፋዊና ክልላዊ ድርጅቶች እንዲሟሉ ሊደረግ ይገባል።

ለምሳሌ በጓቲማላ በተደረገው አገራዊ ውይይት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደ ታዛቢነት መሳተፉ በሒደቱ የመጀመርያ ደረጃ ላይ በተወያይ ኃይሎች መካከል የነበረውን አለመግባባት በመቅረፍ መተማመንን ለመፍጠር እጅግ አስፈላጊ የነበረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የታዛቢነት ተሳትፎ በራሱ ሁሉም የውይይት ሒደቱ ደረጃዎች ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናና ሕጋዊ ቅቡልነት እንዲኖራቸው አበረታቷል።

በብሔራዊ የውይይት ሒደቶች ውስጥ የታዛቢነትና የዋስትና ሰጪነት ተግባር ወይም ሚና በየትኛው የሒደቱ ደረጃዎች አስፈላጊ ይሆናል የሚለውን ብንመለከት፣ ከምዕራፍ ወደ ምዕራፍ ሊለያይ ይችላል። ሆኖም ለአብነት ያህል በዝግጅትና በክንውን ሒደት ደረጃዎች ውስጥ ታዛቢዎች በውይይቱ ተዋናዮችና በሒደቱ መካከል መተማመንን ይፈጥራሉ፣ እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ ድጋፍን መኖርን ያረጋግጣሉ፡፡ በአተገባበር ደረጃ ደግሞ የውጤቶቹን አፈጻጸም በትክክለኛ መስመር ላይ መሆኑን ለመጠበቅ የዋስትና ሰጭነት ተግባር በእጅጉ ያስፈልጋል።

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል mekonnenza@gmail.com አድራሻቸው ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...