Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
እኔ የምለዉአገርን ከጥፋት ለመታደግና ሰላሟን ለማስቀጠል የሚተገበር የግዴታ ውትድርና አስፈላጊነት

አገርን ከጥፋት ለመታደግና ሰላሟን ለማስቀጠል የሚተገበር የግዴታ ውትድርና አስፈላጊነት

ቀን:

በአብረሃም ይሄይስ

ብሔራዊ ውትድርና በአንድ አገር የሚገኙ ወንድና ሴት ዜጎች (ዕድሜያቸውና አቅማቸው ታይቶ)  በጦር ሠራዊት ውስጥ የሚያገለግሉበት የውዴታ ግዴታ ሒደት ነው፡፡ ይህ ተግባር የሚከወነው በሰላም ጊዜ ሲሆን፣ በዚህ የውዴታ ግዴታ ሒደት አገሮች ለተሳታፊ ዜጎች የሚያስቀምጡዋቸው መሥፈርቶች ይኖራሉ፡፡

ብሔራዊ ውትድርና በጦርነት ጊዜ ሳይሆን በሰላም ጊዜ ተዘጋጅቶ ወደፊት ከሚመጣ አደጋና ጦርነት (Potential Threat) መዘጋጀት ነው፡፡ በብሔራዊ ውትድርና የሠለጠኑ ዜጎች አገሪቱ አደጋ በሚያጋጥማት ጊዜ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ አንዲት አገር በሰላም ጊዜ ለጦርነት ዜጎቿን በትጥቅና (ዘመኑን በዋጁ) በስንቅ ካዘጋጀች ማንም ተነስቶ (የውዐና የውስጥ) አገርን ለማፈራረስ ሕዝቦችን ለአደጋ ማጋለጥ አይችልም፡፡

በአገራችን ‹‹አያያዙን አይቶ ጭብጦውን ቀማው›› እና ‹‹ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ›› የሚሉ ብሒሎች ለዚህ ዝግጅት ወሳኝ ማስረጃ ናቸው፡፡ በመሆኑም አሁን ከገባንበት የእርስ በእርስ ጦርነት አምላካችን በፍጥነት ያውጣንና በሰላም ጊዜ ተተግብሮ ሰላማዊ አገር፣ የታፈረችና የተፈራች አገር እንድትኖረን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ያስፈልጋል የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡

የውዴታ ግዴታ ውትድርና ዓለም አቀፋዊ ታሪክ

የውትድርና አገልግሎት ከጥንት ጀምሮ የዜጎች አገራዊ ግዴታ ሆኖ ሲሠራበት የቆየ አገልግሎት ነው፡፡ በጥንት ግሪክ ወጣት ወንዶች በሚኖሩበት የከተማ ግዛት ከሚሊሻነት ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የጦር መኮንነት ለረዥም ዓመታት ማገልገል ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ በጥንታዊ ሮማ በግዴታ በሚገባበት ውትድርና መሳተፍ እንደ ልዩ ክብር ይቆጠር ነበር፡፡ ስለሆነም ዕድሜያቸው ከ17 እስከ 60 የሆናቸው ወንድ ሮማውያን ያለ ምንም ክፍያ ያገለግሉ ነበር፡፡ በግዳጅ ላይ እያሉ ሕገወጥ ድርጊት መፈጸምና ግዴታን አለመወጣት በእስርና ንብረቱን በመውረስ ይቀጣ ነበር፡፡ ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ከሁለተኛው ምዕተ ዓመት በኋላ በሚሊሻ የተደራጁት በባለሙያና ደመወዝ በሚከፈላቸው ወታደሮች ተተክተዋል፡፡

በመካከለኛው ዘመን አካባቢ (In the Middle Ages) የጦር መሣሪያዎች ውድ በሆኑበት ጊዜ የወታደሮች ቁጥር ያንስና አመራሩ ይጠነክራል፣ አምባገነንነት ይሰፍናል፣ የጦር መሣሪያዎች ሲረክሱ ደግሞ የጦር ሠራዊቱ ቁጥር ጨምሮ አመራሩ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል፡፡ ደሃ አገሮች በሚያደራጁዋቸው ሚሊሻና ወታደሮች ይተማመናሉ፣ የአገራቸውንም ሰላም ያስጠብቃሉ፡፡

ዓለም አቀፋዊ የግዳጅ አገልግሎት በመጀመሪያ የተዋወቀው በ16ኛው ክፍለ ዘመን በጣሊያናዊው የፖለቲካ ፈላስፋ፣ የታሪክ ምሁሩና የመንግሥት ባለሥልጣኑ በኒኮሎ ማኪያቬሊ ነው፡፡ የስዊዘርላንድ ሠራዊት ሙሉ በሙሉ በግዳጅ የተመሠረተ ነበር፡፡ በ18ኛው ክፍለ ዘመን በግዳጅ የሚሳተፉት ደሃዎች ሲሆኑ፣ ማባባያና አንዳንድ ስጦታዎች እንደ መመልመያ መሥፈርት ይጠቀሙ ነበር፡፡

በአውሮፓ ብሔራዊ ውትድርና ዘመናዊ ሆኖ የተነሳው በፈረንሣይ አብዮት ጊዜ ሲሆን፣ በወቅቱ ዓለም አቀፋዊ ወታደርነት በእኩልነትና በወንድማማችነት መርህ (The Principles of Equality and Fraternity) የተመሠረተው የሪፐብሊኩ ግዴታና አገርን የማስቀጠል አስፈላጊነት ስለታመነበት ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በነሐሴ 1793 ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 25 ዓመት የሆናቸው ዜጎች በጦር ሠራዊት የመሳተፍ ግዴታ እንዲኖርባቸው ሕግ ፀደቀ፡፡ ዜጎች በየአካባቢያቸው እንዲመዘገቡ ሆኖ ለወጣቶች ቅድሚያ ሲሰጥ ሌሎች ግን እንደ አስፈላጊነታቸው ነበር የሚመዘገቡት፡፡

ፈረንሣይ ከኦስትሪያ ጋር በነበራት ጦርነት ዋዜማ (እ.ኤ.አ. 1796) ዓለም አቀፋዊ የውትድርና አገልግሎትን ተቋማዊ በማድረግ በሠራዊቱ የሚቀላቀሉ ወንድ ዘማቾችን ከ20 እስከ 25 ዓመት ያላቸውን የሠራዊቱ አባላት በደረጃ በመክፈል፣ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 21 ዓመት የሆናቸው የመጀመሪያ ደረጃ እንዲይዙ ሲደረግ ሌሎቹ ሲፈለጉ እንዲቀላቀሉ ሆነዋል፡፡ እነዚህ በብሔራዊ ውትድርና የተሠማሩ ሠራዊቶች ታላቁ ፖሊዮ በተሳተፈባቸው ጦርነቶች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1800 እስከ 1813 የተሳተፉ የሠራዊት ብዛት 2.6 ሚሊዮን ነበሩ፡፡

በ1808 በፐርሺያ ዓለም አቀፋዊ ውትድርናን ተቋማዊ በማድረግ በማኅበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ከፍ ማድረግና መደበኛ ደመወዝ ክፍያ ተጀምሯል፡፡ ሁሉም ወጣት የሠራዊቱ አባላትም ከሥልጠና በኋላ ለውስን ጊዜ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ በ19ኛ ክፍለ ዘመን መጨረሻ በዓለም ኃያላን ከሚባሉ አገሮች መካከል በታላቋ ብሪታንያና ከአሜሪካ ውጪ ያሉ አገሮች የግዴታ ውትድርናን በሰላም ጊዜ ይተገብሩ ነበር፡፡

ነገር ግን የውትድርና ሳይንስ ዘመናዊነትን እየተላበሰ መምጣት፣ የጦር መሣሪያዎችም በከፍተኛ ቴክኖሎጂ መመረትና መሣሪያዎቹን ለመጠቀም ዕውቀት በማስፈለጉ የግዳጅ ውትድርና በግዳጅ ትምህርት ተተካ፡፡ በዚህም ብሔራዊ ውትድርና ሁሉንም ወጣቶች ማቀፍ አልቻለም፡፡

በ20ኛው ክፍለ ዘመን አገሮች ለጦርነት ጥቃት በሚጋለጡበት ወቅት በጦርነቱ አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ኢንዱስትሪዎች የጦርነት መሣሪያዎችን እንዲያመርቱና በቴክኒክ ብቃታቸው ከፍ ያሉ ሠራዊቶችን ለማሠልጠን ተገደዋል፡፡ በዚህም በ1930ዎቹ ጀርመን፣ ጃፓንና የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከፍተኛ የሆነ የጦር መሣሪያ እሽቅድምድም ውስጥ ገብተዋል፡፡

በአሜሪካ በግዳጅ የሚደረግ የውትድርና አገልግሎት በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት በነበረችበት ወቅት በነበረው ልማድ በሚሊሻነት ነው፡፡ ሁሉም አቅማቸው የሚፈቅድ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 60 የሆኑ ወንድ ዜጎች በግዳጅ እንዲሳተፉ ይደረግና የጦር መሣሪያ ባለቤት እንዲሆኑ ይገደዱ ነበር፡፡ ወደ ውትድርና የሚገቡ ዜጎች በፈቃደኝነትና አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች ቃል ተገብቶላቸው ነው፡፡ በዘመቻ ጥሪ ወቅት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወዶ ዘማቾች ቢገኙ በየግዛቱ ያሉ ወንድ ዜጎች (ትዳር ከመሠረቱ፣ የመንግሥት ሥልጣን ካላቸውና ከመምህራን ውጪ) በሎተሪ ዕጣ አሠራር እንዲቀላቀሉ ይገደዱ ነበር፡፡

እ.ኤ.አ. በየካቲት 1778 የአሜሪካ አብዮት ጊዜ ጦሩ በከፍተኛ ሠራዊት ዕጥረት በመጠቃቱ ኮንግረሱ ለሁሉም ግዛቶች ሠራዊት እንዲዋጣ የሚያስገድድ ሕግ አውጥቶ ነበር፡፡ በዚህም ግዛቶቹ የተጣለባቸውን ኮታ ለማሟላት የግዳጅም ልመና አካሄዱ፡፡ በ1792 የወጣው የሚሊሻ ሕግ ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 45 ለሚደርሱ ነጭ አሜሪካውያን የውትድርና አገልግሎትን በግዳጅ እንዲቀላቀሉ አስገድዷል፡፡

በአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት (American Civil War 1861-1865) ብዙ ግዛቶች የግዳጅ ውትድርናን ትተው በውዴታ ሠራዊት ማዋቀር ጀመሩ፡፡ በ1863 የወደቀው የግዴታ ውትድርና ሕግ ለፕሬዚዳንቱ ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 45 የሆናቸው ወንዶችን ለማዋቀር ሥልጣን የሰጠው ቢሆንም፣ በስፋት በተሠራጨው ተቃውሞ  ውትድርናን በፈቃደኝነት የሚቀላቀሉ በመብዛታቸው ሥልጣኑን መጠቀም አልተቻለም፡፡

በአንደኛው የዓለም ጦርነት (1914-1918) ታላላቆቹ ኃያላን አገሮች ጦርነቱን የተቀላቀሉት በውትድርና የግዳጅ አገልግሎት በገቡ ሠራዊቶች ነው፡፡ ታላቋ ብሪታንያ እስከ 1916 ድረስ በወዶ ገብ ሠራዊቶች ስትገለገል ቆይታ በቀጣይ በግዴታ ውትድርና ውስጥ ገብታለች፡፡ አሜሪካ ደግሞ በ1917 ያፀደቀቸውን የምርጫ አገልግሎት ሕግ በመጠቀም ወደ ጦርነቱ ገብታለች፡፡

በሁለቱ የዓለም ጦርነቶች መካከል ከታላቋ ብሪታንያና ከአሜሪካ በቀር በሌሎች አገሮች ዓለም አቀፋዊ ወታደርነትን ቀጥለውበት ነበር፡፡ ጀርመን በቨርሴይልስ ስምምነት ወታደሮችን ከመመልመልና ከመጠቀም እንድታቆም ብትታገድም፣ በግንቦት 1935 ግን ሥርዓቱን በድጋሚ ወደ ትግበራ አውላዋለች፡፡

ታላቋ ብሪታንያም በግንቦት 1939 የግዴታ ውትድርና እና በሰላም ጊዜ ውትድርናን አሠልጥኖ የማሰማራት ሕግን ያፀደቀችና የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ሲቀሰቀስ፣ ዕድሜያቸው ከ18-41 የሆናቸውን ወንድ ዜጎች ተጠቅማለች፡፡ በግንቦት 1940 ደግሞ ፓርላማው የአስቸኳይ የመከላከያ ኃይል ሕግን አፅድቆ በአገሪቱ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ሀብቶቻቸውንና የሰው ኃይል ሀብቶቻቸውን ለአገር መከላከያ ጥቅም እንዲያውሉ አድርገዋል፡፡

በአሜሪካ በሰላም ጊዜ ዜጎችን ለውትድርና መመልመልና ማሠልጠን፣ እንዲሁም በተመረጡ ዘርፎች አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ የተበሠረው በመስከረም 1940 ሲሆን፣ ጃፓን ፐርልርበርን ባጠቃች በስድስተኛው ቀን ሕጉ ላይ ተጨማሪ አንቀጾች ተጨምረውበት ሰፍቷል፡፡

በ1948 በፕሬዚዳንት ሃሪ ትሩማን በሰላም ጊዜ ዓለም አቀፋዊ ውትድርና ሥልጠና ለማቋቋም ቢያቅዱም ኮንግረሱ ግን የተመረጡ የውትድርና አገልግሎት ሕግን የጦር ሠራዊቱን ጥንካሬ በሚጠብቅ መልኩ በ1948 አፀደቀ፡፡ ይህ ሕግ በ1950 የተሻረ ሲሆን፣ በሐምሌ 1951 በኮሪያ ጦርነት ጊዜ እንዲተገበር ሆኗል፡፡ በየጊዜውም እየተሻሻለ በቬትናም ጦርነት ጊዜ ሠራዊት የተደራጀው በዚሁ ዘዴ ነው፡፡

ማጠቃለያ

አገራችን ኢትዮጵያ ካላት ታሪካዊ፣ ተፈጥሮአዊና ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥና አስፈላጊነት፣ እንዲሁም ታሪካዊ ጠላቶች አንፃር የውስጥና የውጭ፣ እንዲሁም የሩቅም ሆነ የቅርብ ጠላቶች ያሉና በተለያየ ፈተናዎች ለዘመናት ሰላሟ መናጋቱ ይታወሳል፡፡

እነዚህን ፈተናዎች ከፈጣሪ ዕርዳታ ጋርና ዜጎቿ ለአገራቸውና ለነፃነታቸው ባላቸው ፍቅር በድል ተወጥታዋለች፡፡ በሁሉም ጦርነቶች ወታደሮቿ አስቀድመው የተዘጋጁ ሳይሆኑ፣ ለጦርነቱ ተብለው የተመለመሉና እጅግ በሚገርም ወኔ የሠለጠኑ ናቸው፡፡

በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ አገርም ለዜጎቿ፣ እንዲሁም ለአፍሪካ ወንድሞቻችን የነፃነት ዓርማ እንደ መሆኗ ጠንካራ፣ ዘመናዊና የማይበገር መከላከያ ሠራዊት ሊኖራት ስለሚገባ የሚመለከታቸው አካላት በስፋትና በጥልቀት አስበውበት፣ አገራዊ ምክክር ተደርጎበት ዜጎች በውዴታ ግዴታ የሚሳተፉበት ብሔራዊ ውትድርና ሊጀመር ይገባል፡፡

በሰሜን አሜሪካ፣ በደብብ አሜሪካ፣ በአውሮፓና በእስያ ብዙ አገሮች የግዴታ ውዴታ ውትድርና አገልግሎትን የሚተገብሩ ሲሆን፣ ሰላማቸውም በተሻለ ሁኔታ ይገኛል፡፡ በተቃራኒው በየጊዜው በመፈንቅለ መንግሥትና የእርስ በርስ ጦርነት የምትታመሰው አኅጉራችን አፍሪካ ከሞሮኮና ከግብፅ ውጪ የውዴታ ግዴታ ውትድርናን የሚተገብሩ አገሮች የሉም (ላገኝ አልቻልኩም)፡፡ ስለዚህም በአገራችን ብቻ ሳይሆን በአኅጉራችንም የውዴታ ግዴታ ውትድርና ሊተገበር ይገባል፡፡

የውዴታ ግዴታ ውትድርና አገልግሎት በተለያዩ አገሮች

በአፍሪካ

  1. ግብፅ

በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታ ሲሆን መሥፈርቶችን ማግኘት አልቻልኩም፡፡

  1. ሞሮኮ

ወንድ ሞሮኮአውያን ለ18 ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታ ነው፡፡

ሌሎች አፍሪካ አገሮች

አገራችንን ጨምሮ ሴራሊዮን፣ ኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ዚምባብዌ፣ ዛምቢያ ውትድርና በግዴታ የሚገቡበት ሳይሆን በውዴታና በጦርነት ጊዜ በክተት የሚገቡበት ነው፡፡

አውሮፓ

  1. ግሪክ

ሁሉም ግሪካውያን ወንዶች በውትድርና አገልግሎት ለ19 ወራት ማገልገል ግዴታ ነው፡፡ ሴቶች በውትድርና አገልግሎት የሚሳተፉት በፈቃደኝነትና በተወሰኑ የጦሩ ቅርንጫፎች ነው፡፡

  1. ጣልያን

ወንድ ጣሊያናውያን የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን በግዴታ የሚቀላለቀሉ ሲሆን፣ እስከ አሥር ዓመት ለሚቆይ ጊዜም ያገለግላሉ፡፡

  1. ዩክሬን

ዕድሜያቸው 18 እና ከዚያ በላይ የሆናቸው ወንዶች በውትድርና አገልግሎት የመሳተፍ ግዴታ ሲኖርባቸው፣ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ያጠናቀቁ ለአንድ ዓመትና ያላጠናቀቁ ደግሞ ለአንድ ዓመት ተኩል ያገለግላሉ፡፡

  1. አልባንያ

ዕድሜያቸው 19 ዓመት የሆናቸው አልባናውያን ለ12 ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

  1. ኦስትሪያ

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 50 የሆናቸው ወንዶች ለስድስት ወራት በብሔራዊ ውትድርና የማገልገል ግዴታ አለባቸው፡፡

  1. ቡልጋሪያ

ዕድሜያቸው ከ19 ዓመት በላይ የሆናቸው ቡልጋሪያውያን ለዘጠኝ ወራት የማገልገል ግዴታ ሲኖርባቸው፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት አንዱ መሥፈርት ነው፡፡

  1. ክሮሺያ

ከ19 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች የአሥር ወራት የብሔራዊ ውትድርና ግዳጅ ይፈጽማሉ፡፡

  1. ዴንማርክ

ከ19 እስከ 25 ዓመት የሆናቸው ወንዶች ለአራት ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

  1. ላቲቪያ

ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ዜጎች ለአንድ ዓመት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

  1. ኖርዌይ

ከ19 ዓመት በላይ የሆናቸው ኖርዌጂያን በባህር ኃይል ለ15 ወራትና በምድር ጦር ለ12 ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

እስያ

  1. እስራኤል

ወንድ እስራኤላውያን ዕድሜያቸው 18 ዓመት ሲደርስ ከሥልጠና በኋላ ለሦስት ዓመት የሚዘልቅ የውትድርና አገልግሎት መስጠት ግዴታ ሲሆን፣ ያላገቡ ሴት እስራኤላውያን ለሁለት ዓመት ማገልገል ግዴታ ነው፡፡ በአገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ገብቶ ለመማር የውዴታ ውዴታ ውትድርና አገልግሎትን መፈጸም ግዴታ ነው፡፡

የውትድርና አገልግሎት እስከ 55 ዓመት ሲቆይ በዓመት ቢያንስ ለ45 ቀናት ማገልገል ይጠበቅባቸዋል፡፡

  1. ኳታር

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን ያላጠናቀቁ ወንዶች ብሔራዊ ውትድርናን የመቀላቀልና የማገልገል ግዴታ አለባቸው፡፡

  1. ኢራን

ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ኢራናውያን ለሁለት ዓመት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

  1. ላኦስ

ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ላኦሳውያን ለ18 ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መሳተፍ ግዴታቸው ነው፡፡

ደቡብ አሜሪካ

  1. ፔሩ

ዕድሜያቸው ከ20 እስከ 25 ዓመት የሆናቸው ወንድ ፔሩያውያን ለሁለት ዓመት የሚቆይ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎትን የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡

  1. ቺሊ

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 19 ዓመት ያላቸው ወንድ ቺሊያውን በምድር ጦር ለአንድ ዓመትና በባህር ኃይል ለሁለት ዓመት ያገለግላሉ፡፡

  1. ኮሎምቢያ

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸው ወንዶች ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ የውትድርና አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡

  1. ጓቲማላ

ዕድሜያቸው ከ18 እስከ 50 የሆኑ ወንዶች ከ24 እስከ 30 ወራት በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው፡፡

ሰሜን አሜሪካ

  1. ሜክሲኮ

ዕድሜያቸው 18 ዓመትና በላይ የሆኑ ወንድ ሜክሲኮአውያን በብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት መስጠት ቢኖርባቸውም በአግባቡ እየተተገበረ ግን አይደለም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው  ewnetabrham@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...