በጋዜጣችሁ ግንቦት 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕትም የአፈር ማዳበሪያን በተመለከተ ከግብርና ሚኒስቴር የአፈር ለምነት ዳይሬክቶሬት የተገኘውን መረጃ በመዘገብ የፊት ለፊት ገጽ ዜና ሆኖ መቅረቡ ይታወሳል፡፡
በቅድሚያ የኑሮ ውድነትና የሰላም ጉዳይ የዚች አገርና ሕዝብ የዚህ ዘመን የህልውና አጀንዳ እንደመሆናቸው፣ ጋዜጣው የግብርና ምርታማነት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን በመገንዘብ ጉዳዩን ዋነኛ ዜና አድርጎ መዘገቡና የመሥሪያ ቤቱ ኃላፊም ለሰጡት ዝርዝር መረጃ ያለንን አድናቆት መግለጽ እንወዳለን፡፡
በዘገባው እንደተገለጸው በአገሪቱ ከሚገኘው ወደ 15 ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን መታረስ የሚችል መሬት ውስጥ ወደ 5.6 ሚሊዮን ወይም 43 በመቶ አካባቢ የሚሆነው በአሲድ የተጠቃና በዚህም ምክንያት ግማሽ ያህሉ ማለትም ከ50 በመቶ በላይ ምርት ሊሰጥ የማይችል ቀሪው ግማሽ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ምርት የማይሰጥ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
ይህንን ጉዳይ በአኃዝ ለማስረዳት ይቻል ዘንድ የአገሪቱን አማካይ የስንዴ ምርት በሔክታር 25 ኩንታል የሆነውን ወስደን ብናይ ሙሉ በሙሉ በተጠቃው 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ምንም ምርት የማይሰጥ በመሆኑ በዓመት 70 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የማምረት ዕድል ሲያጣ፣ ቀሪው በ50 በመቶ ያህል የተጠቃው 2.8 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ደግሞ 35 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ የማምረት አቅም አጥቷል ማለት ነው፡፡ በድምሩ በአፈር አሲዳማነት ምክንያት በዓመት ከመቶ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ የማምረት ዕድል ታጥቷል ማለት ይቻላል፡፡ በገንዘብ ቢተመን ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ የሆነ ምርት ማጣት ማለት ነው፡፡ በአንፃሩ ግን 5.6 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ለማከም የሚያስፈልገው ኖራ ዋጋ ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ አይሆንም፡፡ አንድ ጊዜ የተጨመረ ኖራ ለሦስት ዓመት እንደሚያገለግል ታሳቢ ሲደረግ ደግሞ 200 ቢሊዮን ብር የሚያወጣ ስንዴ ለማምረት ለኖራ የሚወጣው ገንዘብ ከ13 ቢሊዮን ብር ያነሰ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታትና በአሲድ የተጠቃሚ መሬትን ከኖራ ድንጋይ ማዕድን በሚመረተው የኖራ ምርት በማከም መሬቱን ወደ ምርታማነት ከመቀየርም በላይ በእጥፍ እንዲያመርት ማድረግ እንደሚቻል በመግለጽ፣ ነገር ግን ይህንን የኖራ ምርት ለመግዛት ቢያንስ በዚህ ዓመት ለመግዛት ለታቀደው ኖራ ከመንግሥት ሊመደብ የሚገባው ወደ 800 ሚሊዮን ብር ባለመመደቡ ግዥው ሊፈጸምና ለአርሶ አደሩ መቅረብ በሚገባው ጊዜ ሊቀርብ እንዳልቻለ በዘገባችሁ ተመልክቷል፡፡ አያይዘውም ከተጠቃሚው መሬት ስፋትና ብዛት አኳያ የሚፈለገው የኖራ ምርት ከፍተኛ መሆኑንና ይህም ፍላጎት አሁን ባሉት የግል አምራቾችና በመንግሥት የማምረቻ ፋብሪካዎች አቅም ሊሸፈን እንደማይችል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በተጨማሪም የመሬትን ምራታማነት ለመጨመር የሚያገለግለው ሌላኛው ከውጭ አገር ተገዝቶ የሚገባው የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ የመግዣ ዋጋው ከአራት እጥፍ በላይ በማደጉም ጭምር በዚህ ዓመት በተመሳሳይ የበጀት እጥረት መከሰቱንና የተፈለገውን ያህል መግዛትና ማቅረብ እንዳልተቻለም በኃላፊው ከተጠቀሱት በላይ፣ ቀደም ሲልም በተለያየ መንገድ በመንግሥት በኩል ሲገለጽ ቆይቷል፡፡
እንደሚታወቀው የዋጋ ንረትንና የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍ ዋነኛውና የመጀመርያ መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደመሆኑ፣ የግብርና ምርትን የማሳደግ ዕርምጃ ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ የማያጠያይቅ ሆኖ ሳለ፣ የበጀት እጥረት ለዚያውም ደግሞ የ800 ሚሊዮን ብር በጀት እጥረት ምክንያት ሆኖ መቅረቡ ያለፉት 15 ቀናት የብዙዎች መነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል፡፡
ስለሆነም የጉዳዩ ዋነኛ ርዕስ መሆንና አነጋጋሪነቱ የሚጠበቅ የመሆኑን ያህል፣ ሌሎች ሊታወቁ የሚገባቸውና ከዛሬው አነጋጋሪ በጀት ጋር በተያያዘም ሆነ ከዚያ ባሻገር ከትናንት አፈጻጸምና ከወደፊት አካሄድ አንፃር ግንዛቤ ሊወሰድባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ ብለን እናምናለን፡፡
- አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ቴክኖሎጂ ከረዥም ጊዜ ጀምሮ ከብራዚል እስከ ቻይና በዓለም የታወቀና ጥቅም ላይ ሲውል የነበረ ቢሆንም፣ የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ ከአሥር ዓመታት በላይ ምርምር ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ሰፋ ወዳለ የተግባር ሙከራ እ.ኢት.አ ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ገብቷል፡፡
- ይኸውም አሲዳማነትን ለማከም በአልካሊን የበለፀገውንና (በኬሚካል ይዘቱና ስሙ ካልሲየም ካርቦኔት) የተባለውን የላይም ስቶን ማዕድን በመጠቀም ሲሆን፣ ይህም በኢትዮጵያ ከሰሜን አዲራት በምሥራቅ ኢትዮጵያና በዓባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢዎች (ሙገር፣ ጀማ) ወዘተ. በከፍተኛ ክምችት የሚገኘው የኖራ ድንጋይ ተብሎ የሚጠራው ማዕድን ነው፡፡
- ይህንን የግብርና ኖራ ለማረም ደግሞ አንዲት ሳንቲም የውጭ ምንዛሪ የማያስፈልግ ከመሆኑም በላይ፣ ጥሬ ዕቃውን ጠንክረው ለሠሩ የአገር ውስጥ እንደ ልብ የሚገኝና በአመራረት የተወሳሰበ ቴክኖሎጂ የማይፈልግ፣ ሙሉ ለሙሉ ኦርጋኒክ ከመሆኑ ሌላ የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው የተፈጥሮ ግብዓት ነው፡፡
- አሲዳማነቱ በኖራ የታከመና የተስተካከለ የእርሻ አፈር የሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ፍላጎቱ በግማሽ የሚቀንስ በመሆኑ፣ ለሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በውጭ ምንዛሪ ሊወጣ ይችል የነበረውን ገንዘብ ብቻ ሳይሆን የውጭ ምንዛሪ የሚያድን ሀብት ነው፡፡
- ይህ ኦርጋኒክና ርካሽ የአገር ሀብት፣ በአንድ ሔክታር ሊገኝ የሚችለውን ምርት ከእጥፍ በላይ በመጨመርና ከውጭ የሚመጣውን ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ በእጥፍ በመቀነስ ከዋጋ አኳያ ሊሰጥ የሚችለው ግልጽ ጥቅም ባሻገር፣ የአርቲፊሻል ማዳበሪያን አጠቃቀም በመቀነስ ሊከሰት የሚችለውን የጎንዮሽ ጉዳት ፍፁም የሆነ የመከላከል ውጤት ያለው ነው፡፡ ታዲያ ቢያንስ ከውጭ ለሚገባው አርቲፊሻል ማዳበሪያ ከተመደበው ገንዘብ ውስጥ የተወሰነ ያህል በመመደብ አጠቃላይ ወጪውንም ሆነ የመሬቱን የምርታማነት አፈጻጸም በማሳደግ ሊኖር የሚችለውን ውጤት እንደምንመዘገብ እንዳልተቻለ አነጋጋሪ ነው፡፡
- በመሠረቱ ይህ በየትኛውም ዓለም ከጥንት ጀምሮ የሚታወቅ ዘዴ እንደመሆኑ ለምርምር አሥር ዓመት መጨረስ ያልነበረበት ሲሆን፣ ተግባራዊ መሆን ከጀመረበት ጊዜ በኋላ ደግሞ ተገቢውን በጀት ካለመመደብ ጀምሮ፣ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በጀት በተመደበባቸው የ2012 እና 2013 ዓመታትም ከግዥና የአቅርቦት አፈጻጸም ችግር (ድክመት) ጋር በተያያዘ የተመደበውን ገንዘብ ጥቅም ላይ ሳይውል የቀረበት አጋጣሚ እንደነበር ደግሞ ሊታወቅ ይገባል፡፡
- ይህ ብቻም አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ የዚህን ፕሮጀክት አስፈላጊነት በቅጡ የተገነዘቡ እንደ ዓለም ባንክና የጀርመን ተራድኦ (GIZ) የመሳሰሉ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ረዘም ካለ ጊዜ ጀምሮ ፕሮጀክቱን ለመደገፍ እያሳዩ ያሉትን ፍላጎት ወደ ተግባር ለመቀየር የሚያስችል ተቋማዊና መዋቅራዊ ብቃት ማሳየት ቀርቶ የሚመደቡትንም ገንዘብ ጥቅም ላይ ማዋል ሳይቻል ተመላሽ የሆኑባቸው አጋጣሚዎች ታይተዋል፡፡
- በሌላ በኩል የግብርና ሚኒስትሩ ኃላፊ እንደገለጹት የዚህ ግብርና ኖራ ፍላጎቱ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ በአሁኑ ወቅት ከአሥር በላይ አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሲሆን፣ ብዙዎቹም ይህንኑ ፍላጎት በማጥናት ከባንክ ብድር በመውሰድ ጭምር ባለፉት ሁለት ዓመታት በከፍተኛ የማስፋፋት ሥራ ላይ ተጠምደው ቢያሳልፉም የሽያጭና የገቢ አፈጻጸማቸው ግን በፍላጎት አሊያም በአቅርቦት ችግር ሳይሆን ከላይ በተገለጸው ከፌዴራል እስከ ክልል የሚገኙ የግብርና ቢሮዎች ደካማ የግዥ አፈጻጸምና ቢያንስ ለጊዜው ልንገልጸው የማንችለውና በማንፈልገው የተዝረከረከና (ከአገር ውስጡ ይልቅ ኢምፖርትን የመምረጥ ጭምር) ግዴሽ የቢሮክራሲ አሠራር አምራቾቹም፣ መንግሥትም፣ ግብረ ሰናይ ድርጅቶቹና አርሶ አደሮቹም፣ … እናም ኢትዮጵያ ምንም ሳትሠራ ጊዜያቶች በከንቱ አልፈዋል፣ ዛሬም እያለፉ ነው፡፡
- ሌላው የተከበሩ የግብርና ኃላፊው የነገሩንና ለጉዳዩ ቅርብ የሆንን አካላት እንደምናውቀው መንግሥት የላይም ማምረቻ ፋብሪካዎችን በየቦታው (እስካሁን ባለን መረጃ በኦሮሚያ ጉደርና በአማራ ደጀን አካባቢ) ተክሎ ኖራን ለአርሶ አደሩ ለማቅረብ እየሞከረ መሆኑን ነው፡፡ ይህ መንገድ ከመንግሥት የኢኮኖሚ ፖሊሲና ከውጤታማነት አኳያ ምን ያህል ያስኬዳል? የሚለው ወደፊት ራሱን በቻለ ርዕስ የሚታይ ሆኖ እስካሁን ግን በዚህ ረገድም እንደተጠቀውና እንደሚጠበቀው ይህ ነው የተባለ አፈጻጸም ያላሳየ መሆኑም ሊሰመርበት ይገባል፡፡
- በመጨረሻና በማጠቃለያው፣ የዚች አገርና የዚህ ዘመን ትውልድ በሁለት መሠረታዊ የህልውና ጥያቄዎች ማለትም በኑሮ ውድነትና በሰላም አጀንዳዎች ተወጥሮ በሚገኝበት በዚህ ወቅት መንግሥት በተለይም በከፍተኛው የመንግሥት አካል ከዚህ አጣብቂኝ ለመውጣት የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ በተለይም ደግሞ በተለያየ የመንግሥት፣ የቢዝነስ፣ የሲቪልና የአካዴሚክ ኃይል ላይ ያለውን ልዩ ተሳትፎ፣ አመራርና አስተዋጽኦ ይጠብቃል፣ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አጠቃላይ ግንዛቤ ተነስተን ወደዚህ አጀንዳ ስንመጣ የኑሮ ውድነትን ችግር ለመቅረፍ ዋነኛውና የመጀመርያው መፍትሔ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ መሆኑን በመገንዘብ የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የዚህ የኖራ አጠቃቀም ቴክኖሎጂ አስፈላጊነትና ወሳኝነት ባለፈው በተካሄደው የብልፅግና ጉባዔ ቃል በቃል ተናግረውትና መመርያ ሰጥተውበት እያለ እንደምን ሊዳከምና ከዚህ ግባ በማይባል የገንዘብ መጠን በበጀት እጥረት እየተባለና እንዲያውም ከመንግሥት ሌላ ፕሮጀክት ጋር እየተነፃፀረ መቅረቡ ከዜጎች አንፃር ትክልል የመሆኑን ያህል፣ ከመንግሥት አንፃር ደግሞ እንደ ተቋም ከሚመለከታቸው የግብርናና የመሳሰሉት ተቋሞች ተገቢውን ምላሽ እንዲሁም በግልጽ ከተከበሩ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለተግባራዊነቱ ትኩረት እንደሚሰጡበትና ክትትል እንደሚያደርጉበት እንጠብቃለን፡፡
(ከላይም አምራች ድርጀቶች)