Tuesday, September 26, 2023

የኢትዮጵያና ሱዳን መሪዎች በናይሮቢ ተገናኝተው መከሩ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በድንበር ግጭት ውዝግብ ውሰጥ የሚገኙት አገሮች፣ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ሌተናል ጄኔራል አዱልፈታህ አል ቡርሐን በኬንያ ናይሮቢ ከተማ ተገናኝተው ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

ሁለቱ መሪዎች ሰኔ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. ናይሮቢ በተጀመረው 39ኛው የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት (የኢጋድ) ልዩ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን በወቅታዊ ቀጣናዊና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቻው በጻፉት አጭር መልዕክት ‹‹ሁለቱ አገሮች በሰላማዊ መንገድ ሊሠሩባቸው የሚችሉ በርካታ የትብብር መሠረቶች እንዳሏቸው አረጋግጠናል፤›› ብለዋል።

‹‹ያለን ትስስር ከየትኛውም መከፋፈል የሚበልጥ ነው፡፡ ሁለታችንም ያልተፈቱ ቀዳሚ ጉዳዮችን በሰላማዊ መንገድ በውይይት ለመፍታት ቁርጠኝነታችንን ገልጸናል፤›› ሲሉም በጽሑፋቸው አስቀምጠዋል፡፡

ሁለቱ አገሮች በድንበር ይገባኛል ጥያቄና በዓባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የህዳሴው ግድብ ምክንያት ግንኙነታቸው እየሻከረ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ሱዳን ‹‹ትኩረታችንን ወደ ሰሜኑ ጦርነት ስናደርግ ዘላቂ መፍትሔ እስኪሰጠው ድረስ የምናከብረውን ስምምነት በመጣስ ኢትዮጵያ ላይ ወረራ አድርጋለች፤›› ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ አቶ ደመቀ፣ ሱዳን በወረራ በያዘቻቸው የኢትዮጵያ ግዛቶች፣ የሕዝብ ስብጥርን ለመቀየር እየሠራች መሆኑን ጠቅሰው፣ የተወሰደው የኢትዮጵያ ግዛት ‹‹በየትኛውም መመዘኛ›› ይመለሳል ሲሉ ለምክር ቤቱ ተናግረው ነበር፡፡

ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበትና የይገባኛል ጥያቄ በቀረበባቸው የድንበር አካባቢዎች በተከሰተ ግጭት ሰባት የሱዳን ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ በሁለቱ አገሮች መካከል ውጥረት ተፈጥሮ ነበር፡፡

ሱዳን በኢትዮጵያ ሠራዊት ተገድለውብኛል ባለቻቸው ወታደሮቿ ምክንያት ተቃውሞዋን ለመግለጽ በአዲስ አበባ የሚገኙትን መልዕክተኛዋን ወደ  ካርቱም ጠርታ እንደነበር ተዘግቧል፡፡

በዚህም ሳቢያ የኢጋድ ዋና ጸሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ወደ ሱዳን አቅንተው ከጄኔራል አል ቡርሐን ጋር በመነጋገር፣ ሁለቱ አገሮች ለድንበር ውዝግቡ ዘላቂ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ እንዲፈልጉ ጥሪ አቅርበው ነበር፡፡

በናይሮቢው የኢጋድ ጉባዔ በቀጣናው ያሉ የሰላምና ደኅንነት እንዲሁም ድርቅና ሌሎች ችግሮችን በጋራ ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ውይይት የሚደረግበት መሆኑን ወርቅነህ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -