Wednesday, September 27, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዕልቂቱ መቼ ነው የሚቆመው?

አሁንም በወለጋ ዕልቂቱ ቀጥሏል፡፡ በወለጋ ምድር በኦነግ ሸኔ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች በማንነታቸው ምክንያት መጨፍጨፋቸው፣ አሁንም እንደ ተራ ወሬ እየተሰማ ነው፡፡ በየጊዜው የሚሰማው ተመሳሳይ ጭፍጨፋ መቼ ነው የሚያበቃው? ከምሥራቅ ወለጋ ወደ ምዕራብ ወለጋ፣ ከዚያም አሁን ደግሞ ወደ ቄለም ወለጋ የተስፋፋውን ጭፍጨፋ መንግሥት ለማስቆም ያልቻለበት ምክንያት ምንድነው? ሁኔታው በዚህ ከቀጠለስ ማቆሚያው የት ነው? ጭፍጨፋው ተጠናክሮ እየቀጠለ ሲሄድ የሚፈጠረው መረር ያለ ቅራኔ የሚወልደው ትንቅንቅ፣ ለእርስ በርስ ጦርነት መከሰት ምክንያት ሊሆን አይችልም ወይ? የኦሮሚያ ክልልም ሆነ የፌዴራል መንግሥት ተቀናጅተው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍትሔ መስጠት ካልቻሉ የሚከተለው ምንድነው? ወለጋ ውስጥ የተንሰራፋው ኦነግ ሸኔ በተደጋጋሚ አከርካሪውን እየተመታ ነው ቢባልም፣ አሁን እየታየ ያለው አደገኛ እንቅስቃሴው ለአገር አደጋ መደቀኑን ነው ሥጋት የሚያጭረው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የተለያዩ ባለሥልጣናት ኦነግ ሸኔ በደረሰበት ምት እየሸሸ ነው የሞት ሞቱን ግድያ የሚፈጽመው ይላሉ፡፡

ኦነግ ሸኔ ንፁኃንን በማንነታቸው ምክንያት እየጨፈጨፈ ያለው፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ አጋሮቹ ትብብር ለመሆኑ ከበቂ በላይ ምልክቶች አሉ፡፡ ከጥቃት የተረፉ ወገኖችም በግልጽ የሚናገሩት ይህንን እውነታ ነው፡፡ መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነት አለበት ሲባል ለማለት ያህል የሚነገር አይደለም፡፡ መንግሥት የሕዝብ ደኅንነት ለመጠበቅና ከጥቃት ለመከላከል መከላከያ፣ ፖሊስ፣ ደኅንነትና የተለያዩ የፀጥታ ኃይሎች አሉት፡፡ እነዚህን አካላት በተገቢው መንገድ አሰማርቶ ኢትዮጵያውያንን በማንነታቸው ምክንያት የሚጨፈጭፉ ኃይሎችን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስቆም ካልቻለ፣ የኢትዮጵያ ህልውና ታይቶና ተሰምቶ ለማይታወቅ አደጋ ይጋለጣል፡፡ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሰላሟ እየደፈረሰና መረጋጋት እየራቃት ነው፡፡ ሕዝብና መንግሥት ተቀናጅተው መሥራት ከቻሉ ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰላም ማስፈን አያቅትም፡፡ በተለይ ሆን ተብሎ በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት የሚፈጸምባቸው ወገኖች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተቀናጅተው ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ ትጥቅ ቢሰጣቸው፣ እንደተባለው በደረሰበት ምት እየሸሸ ነው ጥቃት የሚፈጽመው የሚባለው ኦነግ ሸኔ የጅምላ ፍጅት ለማካሄድ አይችልም፡፡

በዚህ መንገድ ተጠቂዎችን ማሳተፍ ከተቻለ የጉዳቱን መጠን መቀነስ ብቻ ሳይሆን፣ በአገር ላይ የተቃጣውን አደጋም መቀልበስ ይቻላል፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ባለፈው ሳምንት በሰጠው መግለጫ በቄለም ወለጋ፣ በምዕራብ ወለጋና በሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞኖች የሚገኙ ወረዳዎች በመንግሥት የተቀናጀ የፀጥታ ኃይሎች ሥር መግባታቸው ተገልጾ ነበር፡፡ ኦነግ ሸኔ ተቆጣጥሯቸው የነበሩ አካባቢዎችም የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና ሚሊሻ በቅንጅት ባደረጉት ዘመቻ እንደያዟቸው ተነግሮ ነበር፡፡ በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ጭፍጨፋ የፈጸሙ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎችም መደምሰሳቸው መገለጹ አይዘነጋም፡፡ በዚህን ያህል ደረጃ ዘመቻ የተካሄደበት ኦነግ ሸኔ በቄለም ወለጋ እንደገና ጭፍጨፋ ፈጸመ ተብሎ ሲነገር ያስደነግጣል፡፡ ችግሩ ምንድነው ያስብላል፡፡ በተጨማሪም እየሸሸ በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆኖ ንፁኃንን ፈጀ ሲባል ለመቀበል ያስቸግራል፡፡ መንግሥት እዚያ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በፍጥነት በቁጥጥር ሥር አውሎ ሰላም ማስፈን ካልቻለ፣ በየጊዜው ብቅ እያለ የሚሰጠውን መግለጫ ለመቀበል ይከብዳል፡፡

ቀደም ሲል በሶማሌ ክልል ውስጥ የነበረውን አደገኛ ጥቃትና ሽብር መሰል ድርጊት በማስቆም ሰላም ማስፈን እንደተቻለው፣ በኦሮሚያ በተለይም በወለጋ ውስጥ ተመሳሳይ ሥራ ለማከናወን ለምን አልተቻለም ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው፡፡ የፖለቲካ ሳይንስ ሊቃውንት ከሚስማሙባቸው ጉዳዮች አንዱ ለሽብር ወይም ለጥቃት መስፋፋት ምክንያቱ፣ ደካማ የመንግሥት አስተዳደር መኖርና በጥቃቱ ውስጥ የሚሳተፉ አካላት ውስጡ መመሸጋቸው ነው፡፡ በተለይ በአርብቶ አደሮች አካባቢ ከሚፈጠሩ የውኃና የግጦሽ ግጭቶች በተጨማሪ፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች ውስጥ ማንነትን መነሻ ያደረጉ ጥላቻዎችን በመፈብረክ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ይሆናሉ፡፡ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶችም ሆኑ ጥቃቶች ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ደካማ የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ የተሰገሰጉ የተለያዩ ዓላማዎችን በውክልና የሚያራምዱ ኃይሎች፣ በብዙ ሺሕ ለሚቆጠሩ ንፁኃን ዕልቂት ምክንያት ሆነዋል፡፡ አሁንም በወለጋ የተለያዩ ሥፍራዎች በቀናት ልዩነት ውስጥ እየተስተዋሉ ያሉ ግድያዎችና ጭፍጨፋዎች፣ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ሰዎች ጭምር የሚታገዙ ለመሆናቸው ብዙ ተብሎበታል፡፡ መንግሥት የውስጡን መዋቅር ሳያፀዳ የፈለገውን ያህል ዘመቻ ቢከፍት ውጤቱ ትርፍ የለውም፡፡

ሌላው ከፍተኛ ትኩረት የሚያስፈልገው ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያ ከሱዳንና ከግብፅ ጋር በታላቁ የህዳሴ ግድብ ምክንያት የገባችበት እሰጥ አገባ፣ ሌሎች የውጭ ኃይሎች ወደ አካባቢው ጥቅማቸውን አስልተው እንዲዘልቁ በር እየከፈተላቸው ነው፡፡ በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደተሞከረው ኢትዮጵያውያን ተጠናክረው የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ማጠናቀቅ ከቻሉ፣ ግብፅ በአካባቢው የሚኖራት የበላይነት ስለሚያከትምለት ኢትዮጵያውያንን እርስ በርስ ማጣላት አንዱ ተመራጭ ዘዴ ነው፡፡ ሱዳን ምንም እንኳ የህዳሴ ግድቡ በጎርፍ ከመጥለቅለቅ እንደሚታደጋትና በውኃ አቅርቦቷ ላይ ምንም ችግር እንደማይፈጥርባት በማስታወቅ ከኢትዮጵያ ጎን በመሠለፍ ትታወቅ የነበረ ቢሆንም፣ ከኦማር አል በሽር መንግሥት ውደቀት በኋላ የሥልጣኑን ልጓም የጨበጠው ወታደራዊ ኃይል የግብፅ ተላላኪ በመሆን በድንበር አካባቢ ወረራ በማካሄድ ክህደት መፈጸሙ አይዘነጋም፡፡ በግብፅ የሚዘወረው የዓረብ ሊግና ሌሎችም ተቀናጅተው የግብፅን መሰሪ ፍላጎት እየደገፉ ነው፡፡ በዚህ የልብ ልብ የተሰማት ግብፅ ኢትዮጵያ ውስጥ ተላላኪዎችን በመጠቀም ኢትዮጵያውያንን ለመከፋፈል፣ አረመኔያዊ ድርጊቶች እንዲከናወኑ በማድረግ ላይ ለመሆኗ መጠርጠር ይገባል፡፡ የአረመኔያዊ ድርጊቱ ተዋናዮችም የመንግሥት መዋቅር ውስጥ አልሰረጉም ማለት አይቻልም፡፡

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ይህንን ሁሉ ሴራ በመረዳት፣ አገራቸው ከገባችበት ማጥ ውስጥ ጎትተው የማውጣት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የመጀመሪያው ኃላፊነት መንግሥት ውስጡን በሚገባ አፅድቶ የአገርና የሕዝብ ደኅንነት እንዲያስጠብቅ ጫና ማሳደር ነው፡፡ መንግሥት እየተልፈሰፈሰ መዋቅሩ አገር በሚያጠፉ መሰሪዎች የሚወረር ከሆነ፣ እንኳንስ ሕዝብና አገርን ሊጠብቅ ለራሱም ህልውና ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የኢትዮጵያ ህልውና በአስተማማኝነት እንዲቀጥል መንግሥት በሚፈለግበት ቁመና ላይ እንዲገኝ መገደድ አለበት፡፡ አገር የሚመራው በሕግ የበላይነት ሥር በመሆኑ መንግሥት በተገቢው መንገድ ሕግና ሥርዓት ያስከብር፡፡ ሕግና ሥርዓት የማይከበርበት አገር የሥርዓተ አልበኞች መፈንጫ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው ሁለተኛ ጉዳይ ኢትዮጵያውያንን በብሔር፣ በእምነትና በሌሎች ልዩነቶች በመከፋፈል በሕዝብና በመንግሥት መካከል መተማመን እንዳይኖር ለማድረግ በውስጥና በውጭ ሴራዎች ይጎነጎናሉ፡፡ መንግሥት ለቅራኔ በር ከሚከፍቱ አጓጉል ድርጊቶች መታቀብ አለበት፡፡ ሰዎች በነፃነት ሐሳባቸውን በመግለጻቸው ምክንያት ከመንገድ ላይ አፍኖ ያልታወቀ ሥፍራ ማሰር ሕገወጥነት ነው፡፡ ዜጎችን በማንነታቸው ምክንያት ማጥቃት፣ መበደልና መብታቸውን መንፈግ ተገቢ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ ጉዳይ ያገባኛል ያለ ሁሉ ተሳትፎው ሊበረታታ ይገባል፡፡ ለቅራኔ መነሻ ሊሆኑ የሚችሉ ድርጊቶች በሙሉ ይወገዱ፡፡ ጥቃትንና ጭፍጨፋን በተባበረ ክንድ ማቆም የሚቻለው በዚህ መንገድ ብቻ ነው፡፡ እስከዚያው ግን የአሁኑ ዕልቂት መቼ ነው የሚቆመው ብሎ መነጋገርም ግድ ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...

ማን በማን ላይ ተስፋ ይኑረው?

በአንድነት ኃይሉ ችግሮቻችንን ለይተን ካወቅን መፍትሔውንና ተስፋ የምናደርግበትን ማወቅ እንችላለን፡፡...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...