Wednesday, November 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በተወሰነላቸው ቀናት በማይደርሱ ነዳጅ ጫኝ ተሽከርካሪዎች ላይ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የፍርድ ቤት ውሳኔ ሳይኖር ‹‹ይወረሳል›› መባሉ አጠያያ ሆኗል

ከጂቡቲ ተነስተው በአራት ቀናት ወደ አዲስ አበባ የማይደርሱ የነዳጅ ጫኝ ቦቴ መኪኖች እስከመወረስ ድረስ ዕርምጃ እየወሰደ መሆኑን መንግሥት በተደጋጋሚ እየገለጸ ሲሆን፣ አንዳንድ ቦቴዎችም ነዳጅ ጭነው ለረዥም ጊዜ ተደብቀው መገኘታቸው ተገልጿል።

ከሰሞኑ በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች እየተስተዋለ ላለው የነዳጅ እጥረት እንደ ምክንያት ተደርጎ የተቆጠረው፣ የነዳጅ ድጎማ ዛሬ ሰኔ 29 ቀን 2014 ዓ.ም. ስለሚጀመር በሚፈጠረው የዋጋ ልዩነት ተጠቃሚ ለመሆን እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ መኪኖች እየተደበቁና መዳረሻቸው ላይ በጊዜ አለመድረሳቸው ምክንያት በማድረግ፣ የአዲስ አበባና የክልል ንግድ ቢሮዎች በርካታ መኪኖችን እየወረሱ እንደሆነ እየተገለጸ ይገኛል።

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እስካሁን 12 የነዳጅ ጫኝ ቦቴዎችን እንደወረሰ የገለጸ ሲሆን፣ በማከልም ቦቴዎቹ የነዳጅ እጥረት እንዲከሰትና የመንግሥትን መመርያና ደንብ በመጣስ ወደ ከተማ እንዳይገቡ የተደረጉ መሆናቸውን አክሎ በመግለጫው አሳውቋል። የቢሮው ምክትል ኃላፊን አቶ መስፍን አሰፋ በተወረሱት የነዳጅ ቦቴዎች ውስጥ የነበረው ነዳጅ በተለያዩ ማደያዎች በኩል መከፋፈላቸውን ገልጸዋል።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሳህረላ አብደላ በትናንትናው ዕለት ከንግድና ቀጠናዎች ትስስር ሚኒስትሩ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ ጋር በመሆን በሰጡት መግለጫ ላይ እንደገለጹት፣ ‹‹ለዚህ የመንግሥት ዕርምጃ ዋነኛ ምክንያት እየሆነ ያለው፣ በነጋዴዎችና በባለመኪኖች እየተስተዋለ ለመጣው ያላግባብ የማከማቸት ተግባር ነው።

ይህም ውሳኔ ቦቴዎችን ወደ ትክክለኛ አሠራር እያስገባ እንደሆነ የገለጹ ሲሆን፣ ከነዳጅ ኩባንያዎች ጀምሮ እስከ ክልል ንግድ ቢሮዎች ድረስ አሠራሩ የተደገፈና ለውጥ እያመጣ እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። ‹‹አሁንም ቢሆን አዲስ አበባ ገብቶም በየሠፈሩ የመደበቅ ሁኔታ አለ፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሳህረላ ገልጸዋል።

ሆኖም ግን የመኪኖቹም ሆነ የጫኑትን ነዳጅ አወራረስን ያላግባብነትና ጉዞውም ከታሰበው አራት ቀናት በላይ ሊወስድ እንደሚችል የተለያዩ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አካላት ያስረዳሉ።

ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገና ቢሮው ከሰኔ 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ዕለት ጀምሮ ከወረሳቸው ቦቴዎች ውስጥ አንደኛው የእሱ እንደሆነ የሚገልጽ አንድ የቦቴ መኪና ባለንብረት የእሱ መኪና ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ላይ ነዳጁን ከጂቡቲ ቀድቶ የጨረሰ መሆኑን ገልጾ፣ የተለያዩ መውጫ ዶክመንቶችን በነጋታው ጠዋት እስኪያስጨርስ እዚያው በማደሩ እንደ አንድ ቀን የተቆጠረበት መሆኑን ያስረዳል።

በነጋታው አፋር ደርሶ ሰመራ ላይ በሌትር 20 ሳንቲም ነዳጅ የሚቀንስ በመሆኑ፣ እዚያ ነዳጅ ለመቅዳት ባደረገው ጥረትና ባጋጠመው ሠልፍ ምክንያት ሾፌሩ እዚያው ማሳለፉን ያስረዳል። ለሁለት ቀናት በጉዞ አሳልፎ ሰኔ 16 ቀን በጠዋት አዲስ አበባ ቢገባም፣ በድንገት ተግባራዊ በሆነው በዚህ አሠራር ምክንያት አምስት ቀናት የፈጀ ነው በሚል ሊወሰድበት ችሏል።

‹‹የሾፌርን ዕረፍት፣ የመንገዱን ደኅንነት፣ በመንገድ ላይ የሚቀዳ ነዳጅ አለመኖርን፣ በጂቡቲ ውስጥ ነዳጅ ማታ ላይ በመቀዳቱ አዳሩን እንደ አንድ ቀን በመቆጠሩና በርካታ ተያያዥ ምክያቶች መሠረት፣ ከአምስት ቀናት በፊት መድረስ የማይቻል ነው፤›› ሲሉ እኚህ የቦቴ መኪና ባለቤት ያስረዳሉ። ሁሉም ነገር የሚሳካ ከሆነ ግን እንደሚታሰበው በሦስት ቀናት መድረስ እንደማያስቸግርም አክለው ገልጸዋል።

የንግድ ቢሮው ቦቴ መኪኖችን በሚወርስበት ጊዜ የጫኑትን ነዳጅ በተለያዩ ነዳጅ ማደያዎች ላይ እንደሚያራግፍ የገለጸ ሲሆን፣ ሪፖርተር እንዳጣራው ከሆነም ነዳጁ ላልተጫነለት የነዳጅ ድርጅትም ሊሆን እንደሚችል ተገንዝቧል። ቦቴ መኪናው የተወረሰበት ግለሰብም የናሽናል ኦይል ካምፓኒ (ኖክ) ሲሆን የተራገፈውም በቶታል ማደያ ውስጥ ነበር።

በተደረገው ክርክር ቦቴው ለባለቤቱ የተመለሰ ቢሆንም፣ ስለተራገፈው ነዳጅ ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም። ከባለፈው ሳምንት እሑድ ጀምሮ ተወረሱ ከተባሉት ቦቴ መኮኖች ውስጥ በፈቃደኝነት በተለየው ነዳጅ ማደያ ውስጥ ነዳጃቸውን ያራገፉ ባለንብረቶች በድርድር ቦቴዎቻቸው እየተመለሱላቸው ሲሆን፣ በነዳጅ ድርጅቶቻቸው ከታቀደላቸው ማደያ ውጪ አናራግፍም ያሉት ግን እስካሁን በፖሊስ ጥበቃ እንደቆሙ ተሰምቷል።

እንደ ሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል አስተያየት፣ የነዳጅ ኩባንያዎቹ በራሳቸው ቦቴዎች ከሆነ ነዳጁን ያመላለሱትና እሱንም ለሕገወጥ ተግባር ካዋሉት በንግድ ፈቃድ አዋጁ መሠረት በሕገወጥ ንግድ ተግባር ላይ የዋለውን ዕቃ ጨምሮ [ነዳጁን] መውረስ ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ውሳኔ የአስተዳደራዊ ይሁን የፍርድ ቤት ውሳኔ አከራካሪ ነገር ነው። እንደ አቶ ዮሐንስ አስተያየት በአስተዳደራዊ ውሳኔ እንደዚህ ዓይነት ትልቅ ውርስ ላይ መወሰን አስቸጋሪ ነው።

‹‹ከሕገወጥ ሥራ ጋር በተያያዘ የውርስ ውሳኔ የማስተላለፍ የፍርድ ቤት ኃላፊነት ነው፤›› ሲሉ አቶ ዮሐንስ አስረድተዋል።

ሆኖም አብዛኛውን ነዳጅ አመላላሾች ኩባንያዎች ሳይሆኑ የቦቴ መኪና ባለንብረቶች በመሆናቸው፣ እንደ ሁለቱ አካላት ድርድርና ነዳጁን ወደ ተፈለገበት ቦታ በተወሰነ ጊዜ ገደብ አደርሰዋለው ብለው በመነጋገር የሚደረግ የማመላለስ ሥራ ይሆናል። ቢሆንም ግን ይህ አመላላሽ ከነዳጅ ኩባንያው ተገቢውን ውል ገብቶና ክፍያም አግኝቶ ስለሠራ፣ ኩባንያዎቹ ከሚፈጠረው የመዘግየት ተግባር ተካፋይ እንደሚሆኑ አቶ ዮሐንስ ይገልጻሉ። ከአቅማቸው በላይ የሆነ ጉዳይ ከሆነ ግን ወዲያውኑ ማሳወቅ እንዳለባቸው አስረድተዋል።

ኩባንያዎቹ ከዚህ የመወረስ ዕርምጃ መጀመር በፊት መንገድ ላይ ችግር ቢያጋጥማቸው፣ ተሽከርካሪዎቹ ሲበላሹባቸው፣ ጂቡቲ ላይ ምንም ቢገጥማቸው ለባለሥልጣኑ ሪፖርት የማያደርጉ ሲሆን፣ ካሁን በኋላ ባለው አሠራር ግን ይህን የማድረግ ግዴታ እንዳለባቸውና አሊያም ሕግን የማስከበር ዕርምጃ ባለሥልጣኑ እንደሚወስድ ወ/ሮ ሳህረላ በመግለጫው አንስተዋል።

እንደ ዋና ዳይሬክተሯ፣ መንግሥት በዚህ ዓመት ላለፉት 11 ወራት ብቻ በነዳጅ ድጎማ 146 ቢሊዮን ብር አውጥቷል።

ነዳጅ አዳዮችም በበኩላቸው ወደ እነሱ የሚመጣው ነዳጅ በጊዜ መድረስ አለመድረሱን ማሳወቅ እንዳለባቸው አሠራሩ የሚገልጽ ሲሆን፣ ለእነሱ ነዳጅ የሚያመጣው ቦቴ መኪና ከጂቡቲ ከመነሳቱ ጀምሮ ከአምስተኛው ቀን በኋላ ለማራገፍ ከመጣ፣ ማደያዎቹ ሳያራግፉ ለንግድ ቢሮው ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ይህን ካላደረጉም ተጠያቂ ይሆናሉ። 

የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር ቦርድ አባልና የነዳጅ ማደያ ባለቤት የሆኑት አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹በወሬ ደረጃ ከመስማት በስተቀር ለእነሱ በሥርዓቱ የደረሳቸው የአሠራር መመርያ የለም፤›› ብለዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች