በኢትዮጵያ ያሉ ተደራራቢ ሕጎችና ድንጋጌዎች የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት ሳቢነት እየገደበና የግል ዘርፉን በእጅጉ እየፈተነ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ሰሞኑን በተደረገ የውይይት መድረክ ላይ የኢትዮጵያን የንግድና ኢኮኖሚ ዘርፍ ለማስተዳደር የወጡ የተለያዩ ሕጎችና ደንቦች ተደራራቢ መሆን አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ ተመልክቷል፡፡
በአገሪቱ የወጡና ሥራ ላይ የዋሉ አንዳንድ ሕጎች ድርብርብ ግዴታዎችን የሚጥሉ በመሆናቸው ለሙስና የተጋለጠ አሠራር እንዲፈጠር በር የከፈቱ መሆኑን በውይይት መድረኩ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ምሁራን ገልጸዋል፡፡ ችግር ፈጣሪ የሆኑ ሕጎችን ለማሻሻል የተደረጉ ጥረቶች ቢኖሩም፣ በጥቅል ሲታይ ግን የኢትዮጵያ ድንጋጌዎች አሁንም ብዙ መሻሻል የሚኖርባቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ደካማ የማስፈጸም አቅም የችግሩ አንድ አካል ስለመሆኑ በዚሁ መድረክ ላይ ተወስቷል፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም የግል ዘርፉንና አጠቃላይ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለማስተዳደር የወጡ ሕጎች እየፈጠሩ ያለውን ተፅዕኖ በተመለከተ በውይይት መድረኩ ላይ አጭር የውይይት ጽሑፍ ካቀረቡት መካከል የሕግ ምሁሩ አቶ ምሕረት አብ ልዑል አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ የኢትዮጵያ ገበያ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት መሆኑን፣ ይህ ደግሞ ብዙ ተፅዕኖዎችን በማስከተል ላይ ነው። አንድ የውጭ ኩባንያ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ሲያስብ ስለአገሪቱ የንግድ እንቅስቃሴ ከባቢ ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን እንደሚያጠና፣ በዚህ ረግድም የእሳቸው ተቋም ባደረገው ጥናት የኢትዮጵያ ገበያ ከፍተኛ ቁጥጥር የሚበዛበት፣ በኢትዮጵያ ሁሉም ነገር በሕግ የታጠረ መሆኑን፣ በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ገበያ አስቸጋሪ እንዳደረገው ይገልጻሉ፡፡
ለምሳሌ ያነሱት የፋይናንስ ዘርፉን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያለው ቁጥጥር ውስብስብ ያለ፣ ከሌላው የተለየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በአንድ መድረክ ላይ ከአንድ የኬንያ ባለሙያ ጋር በመሆን ገለጻ ለማድረግ ዕድል ባገኙበት ወቅት የተገነዘቡት የኬንያ የፋይናንስ ዘርፍ ላይ ያለው ከፍተኛ ቁጥጥር በሕገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ከማጠብ (መኒ ላውንደሪንግ) እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ ከመደገፍ (ፋይናንሲንግ ቴረሪዝም) ሥጋቶችን ከመቆጣጠር ጋር ብቻ የተቆራኘ መሆኑን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን በጣም ብዙ ጉዳዮችን በሕግ የማጠር ልምድ በመኖሩ የፋይናንስ ዘርፉ ላይ ያለው ቁጥጥር ውስብስብ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የገበያ ሁኔታ ቁጥጥር የበዛበት በመሆኑ ኢንቨስትመንትን የመሳብና በቀላሉ ቢዝነስ ለመሥራት የሚያስችል እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ይህ እጅግ ቁጥጥር የበዛበት የንግድ አሠራር ቀልጣፋ ካልሆነ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ሲገናኝ ደግሞ ነገሩን የከፋ እንደሚያደርገው አቶ ምሕረት አብ አክለዋል፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ የመንግሥት ሠራተኞች ጋር የአገልጋይነት ስሜት የለም፡፡ ይህ ደግሞ ሕጎች በአግባቡ እንዳይሠሩ ከማድረጉም በላይ ችግሩን ያባብሰዋል ብለዋል፡፡ ተገልጋይ የማያውቃቸው ሕጎች መኖራውን፣ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለሙስና ተጋላጭ እንደሚደርግ የገለጹት አቶ ምሕረት አብ፣ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት ወይም ቀላል የንግድ አሠራር ሥርዓት ለመፍጠር ቁጥጥር ላይ መሠረት የማድረግ አካሄድ መቀነስ እንዳለበት መክረዋል፡፡ ይህም ቀላልና ቀልጣፋ የንግድ አሠራርን ለመፍጠር መንግሥት ምን መደረግ እንዳለበት ለመመክር አዘጋጅቶች በነበረው መድረክ እንደ መፍትሔ የቀረበ ሐሳብ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የሕግጋቱ ብዛት ካልተቀነሰ ሙስና መሥራት ለሚፈልግ ሰው ሁሉ የተመቻቸ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ገልጸዋል፡፡ ከወቅታዊው የመንግሥት የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አንፃርም አለ ያሉትን ክፍተት ያነሱት አቶ ምሕረት አብ፣ ይህ የኢኮኖሚ ዘርፍ ማሻሻያ ፕሮግራም እንደተፈለገው በውጭ ኩባንያዎች ዘንድ የሚጋብዝ ሆኖ አለመገኘቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህንንም ተቋማቸው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ማረጋገጥ መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት የተቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት ኢትዮጵያን ምቹ የኢንቨስትመንት መዳረሻ ለማድረግ ከታሰበ፣ በተለይ በተዘረጋው ውስብስብ የቁጥጥር ሥርዓት ላይ አሁንም ብዙ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
በዕለቱ ሌላው ተናጋሪ የነበሩት የሕግ ምሁር ፈቃዱ ጴጥሮስ (ረዳት ፕሮፌሰር) ደግሞ፣ ያለፉት አምስትና ስድስት ዓመታት በቁጥጥር ሥርዓቱ ላይ ብዙ ማሻሻያዎች ለማድረግ መሞከሩን ይገልጻሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም አንዱ ከሁለት ዓመታት በፊት የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት ሕግ መውጣቱን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ የሕግ ማሻሻያ ያልተገባ የሕግ ቁጥጥርን ለማቅለል ወሳኝ የሚባል ማሻሻያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌላው እንደ ማሻሻያ የሚታየው መንግሥት ከግል ዘርፉ ጋር በቀጥታ ፐብሊክ ፕራይቬት ዲያሎግ ፎረም (የግልና የመንግሥት የውይይት መድረክ) እንዲኖር በማድረግ አንዳንድ አላሠራ ያሉ ሕግጋቶችን ለማሻሻል መሞከሩ ነው፡፡ በሦስተኛነት የጠቀሱት ደግሞ ‹‹ኢዝ ኦፍ ዱይንግ ቢዝነስ›› ማሻሻያን ነው፡፡ እነዚህ ሦስት ወሳኝ የሪፎርም እንቅስቃሴዎች ናቸው ብለው የሚያምኑት አቶ ጴጥሮስ፣ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ ወሳኝ ከሚባሉ አዋጆች አንዱ ለመሆኑ ማሳያ ያሉትን ማብራሪም አክለዋል፡፡ ይህ አዋጅ እንደ ወሳኝ ጉዳይ የሚታየው ኢትዮጵያ ውስጥ የመንግሥት ተቋማት መመርያ ሲያወጡ ምን ዓይነት ሥርዓት መከተል እንዳለባቸው አስገዳጅ አድርጎ ያስቀመጠ አዋጅ በመሆኑ ነው፡፡ የመንግሥት ተቋማት መመርያ ሲያወጡ ምን ዓይነት ሥርዓት መከተል እንዳለባቸው አስገዳጅ አድርጎ አስቀምጧል፡፡ ስለዚህ ማንኛውም የመንግሥት ተቋማት መመርያ ሲያወጡ የሚመለከታቸውን አካላት አስቀድሞ ማሳወቅና ማወያየት እንዳለባቸው የሚያስገድድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ተቋማት መመርያ ከማውጣታቸው በፊት በረቂቁ ላይ ባለድርሻ አካላት በጽሑፍ አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል መሰጠት ያለባቸው ሲሆን፣ መመርያው ከመጽደቁ በፊትም ረቂቅ መመርያውን ለፍትሕ ሚኒስቴር አዋጁ መላክ እንዳለባቸው የሚደነግግ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ መመርያው ከመፅደቁ በፊት የፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት ማካተት አስገዳጅ እንዲሆን መደረጉንም ጠቅሰዋል። ይህ የተደረገውም የሚወጡት መመርያዎችና ሕጎች ጥራት ያላቸው እንዲሆኑና ከሌሎች ሕጎች ጋር የሚጋጩ እንዳይሆኑ ለማረጋገጥ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ መመርያዎቹ ከወጡ በኋላም ኅብረተሰቡ እንዲያውቃቸው ድረ ገጽ ላይ መቀመጥ እንዳለባቸውና ማንም እነዚህን መመርያዎች ፈልጎ ማጣት የሌለበት እንደሆነ በዚሁ ሕግ በአስገዳጅነት መደንገጉን አስረድተዋል።
ነገር ግን ይህ ወሳኝ የሚባል አዋጅ በአግባቡ እየተተገበረ አለመሆኑን የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ይህንንም በተጨባጭ ያሳያል ያሉት ፍትሕ ሚኒስቴር ከቀናት በፊት ያወጣውን ጥናት ነው፡፡ በዚህ ፍትሕ ሚኒስቴር ጥናት መሠረት የገንዘብ፣ የጤና፣ የገቢዎች ሚኒስትሮችና የጉምሩክ ኮሚሽን ይህንን አዋጅ ተግባራዊ እያደረጉ አለመሆኑ ይፋ መደረጉን ጠቅሰዋል። ስለሆነም ሕጉ ቢወጣም እየተተገበረ እንዳልሆነ ገልጸዋል። ሌላው ማብራሪያ የሰጡበት ጉዳይ የግል ዘርፉና የመንግሥት ምክክርን የሚመለከት ነው፡፡ ይህ አሠራር የግል ዘርፉና መንግሥት በቀጥታ የሚገናኙበትና በርካታ መልካም ሥራዎችና የተገኙበት መድረክ ቢሆንም የሚታሰብለትን ያህል ውጤት ያመጣ እንዳልሆነም ጠቁመዋል፡፡
የእኚሁ ጽሑፍ አቅራቢው ሌላው ማብራሪያ ‹‹ኢዝ ኦፍ ዱይንግ ቢዝነስ››ን (የተቀላጠፈ የንግድ አሠራርን) ይመለከታል፡፡ ይህ የአገራትን የንግድ አሠራር ምቹነት የዓለም ባንክ የሚለካበትና የ189 አገሮችን የንግድ አሠራር በየዓመቱ ደረጃ የሚያወጣበት አሠራር እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡ በዚህ የዓለም ባንክ መመዘኛ ኢትዮጵያ ለረዥም ጊዜ ከ150ኛ በታች ያለውን ደረጃ እንደምታገኝ የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ይህንንም ለማሻሻል መንግሥት ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸው የሚመሩት አሥር የመንግሥት ተቋማት ኃላፊዎች የሚሳተፉበት የሪፎርም ኮሚቴ እንደነበር ጠቅሰው፣ ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ የወጣው የንግድ ሕግ የረዥም ጊዜ ሥራ ቢሆንም፣ እንዲፈጥንና እንዲፀድቅ የተደረገው በዚህ ሪፎርም አማካይነት መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህ የሪፎርም ሥራ የንግድ ምዝገባ ሥርዓቱን በቴክኖሎጂ የተደገፈና ወደ ተቋማት በአካል መሄድን ሳይጠይቅ በበይነ መረብ የንግድ ምዝገባ እንዲካሄድ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ቀልጣፋ የንግድ አሠራርን ከመተግበር አኳያ እጅግ በርካታ ማሻሻያዎችና ማስተካከያዎች በመደረጋቸውን ይህም ኢትዮጵያን በዓለም ባንክ መመዘኛ የነበራትን ደረጃ በማሻሻል ከ100 በታች ያደርጋል ተብሎ ታምኖበት ውጤቱ እየተጠበቀ ሳለ የዓለም ባንክ ይህንን መመዘኛ (ወርልድ ዱይንግ ቢዝነስ) ማስቀረቱን ተናግረዋል፡፡ ብዙ ተለፍቶ ከተሠራ በኋላ መመዘኛው ቀሪ መሆኑ ቢያሳዝንም፣ ብዙ ድንጋጌዎችና አሠራሮች እንዲሻሻሉ ዕድል መስጠቱ ደግሞ በመልካም ጎኑ የሚታይ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያን ሕግጋቶች በተመለከተ በመልካም የሚታዩ ብለው አቶ ምሕረት ከተቀሷቸው ውስጥ ደግሞ አዲስ ኢንቨስትመንት ኮድ መዘጋጀቱና የንግድ ሕጉ እንዲሻሻል መደረጉን በዋናነት ገልጸዋል፡፡ ሌላው ከኢንቨስትመንት አንፃር ኢትዮጵያ 1958 የኒዮርክ ኮንቬንሽንን ተቀብላ የአገር ውስጥ ሕግ አካል ማድረጓ ሲሆን፣ ይህም ከ20 እስከ 25 ለሚደርሱ ዓመታት በማመንታት የዘገየ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ አሁን ይህንን መቀበሏ ሊጠቀስ የሚገባው መልካም ተግባር መሆኑንም ተጠቅሰዋል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንቶች ሲመጡ ከሚጠይቋቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ዓለም አቀፋዊ ስምምነቶች የሚዳኙበት የሕግ ሥርዓት መኖሩ አለመኖሩን ከመሆኑ አንፃር ኢትዮጵያ ይህንን ዓለም አቀፍ ሕግ በስተመጨረሻ ተቀብላ ማፅደቋ መልካም እንደሆነ አንስተዋል፡፡
የግል ዘርፉ ላይ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ብዙ ችግሮች እንዳሉ የገለጹት አቶ ፈቃዱ፣ ሥር ነቀል የሆነ የቁጥጥር ሥርዓት ማሻሻያ ማምጣት የሚቻለው በብዙ አገሮች ተሞክሮ ውጤታማ የሆነውን የቁጥጥር ተፅዕኖ የሚገመግም (ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት) ራሱን የቻለ አካል በመንግሥት ሥር ሆኖ እንዲቋቋም ሲደረግ ነው ይላሉ፡፡ ይህም በመንግሥት ጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ወይም የፕሬዚዳንት ጽሕፈት ቤት በሚደራጅ ሕጎች ከመውጣታቸው በፊት አስቀድሞ ተፅዕኗቸውን ገምግሞ መጥፎ ሕጎች እንዳይወጡ የሚደረጉበት አሠራር ይፈጥራል፡፡ ይህንን ብዙ አገሮች ተግባራዊ እያደረጉ መሆኑን የገለጹ አቶ ፈቃዱ በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ እኛ አገር የአሠራር ሥነ ሥርዓት ሕግ ከወጣ በኋላ፣ ሕጉን የሚያወጣ አካል የሚመለከታቸውን ጠርቶ አወያይቶ ሐሳባቸውን አካቶ ያወጣዋል፡፡ ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት ግን እያንዳንዱ ተቋም በተናጠል ሳይሆን ማንኛውም ተቋም ሕግ ከማውጣቱ በፊት ማዕከላዊ ወደ ሆነው አካል ይልካል፡፡ ያ ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት አድርጎ ገምግሞ ኳሊቲ እንዲጠበቅ ያደርጋል፡፡ ይህ ማለት ራሱን የቻለ የሙሉ ጊዜ የሰው ኃይል ያለው አንድ የተደራጀ ማዕከል ይኖራል ማለት ነው፡፡ ይህም ባለሙያዎች ያሉት ለምሳሌ ሶሻሊስቶች፣ ኢኮኖሚስቶችና የታሪክ ሰዎች የሕግ ባለሙያዎች ያሉበት ማለት ነው፡፡ ይህ ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት በአፍሪካ እንደ ሞርሼስ፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ሴኔጋል፣ ኡጋንዳና ዛምቢያ ተግባራዊ እያደረጉት ያለ ፕሮግራም በመሆኑ ኢትዮጵያም ይህንን አሠራር ብትከተል መልካም መሆኑን አቶ ፈቃዱ ገልጸዋል፡፡
ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት ከመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የምክክር መድረክ (ፒፒዲ) ጋር ስናነፃፅረው ዋናው ልዩነት ፒፒዲ ችግሮች ከተፈጠሩ በኋላ ወይም አስቸጋሪ ሕጎች ከወጡ በኋላ ያንን ማስተካከያ ነው፡፡ ሬጉላቶሪ ኢምፓክት አሰስመንት ግን እንዳይደረግ አስቀድሞ ሕጉ ጥራቱን እንዲጠብቅ የሚያደርግ ሥርዓት በመሆኑ ይህንን መተግበር ጠቃሚ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ሌላው የመፍትሔ ሐሳብ ብለው ያቀረበት፣ ‹‹ሬጉላቶሪ ግሎታይን›› የሚባል አሠራርን ነው፡፡ አሁን ልክ እንደ እኛ አገር የግል ዘርፉ በጣም ሲጨነቅ፣ አላሠራ ሲል መንግሥት አንድ ፕሮጀክት ይፈጥርና ያሉትን ሕጎች በሙሉ ሰብስቦ ሁሉንም አጥንቶ ከዚህ ውስጥ የሚያስፈልገውን ሕግ እየቆራረጡ መጣል ማለት ነው፡፡
በዚህ አሠራር እያንዳንዱ ሬጉሌሽን ያለው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሬጉሌሽናቸው በሙሉ ተሰብስቦ አንድ ላይ ኢንቨንተሪ ይደረጋሉ፡፡ የማስረዳት ኃላፊነት ያለበት የመንግሥት አካል ይህ ሬጉሌሽን ያስፈልጋል የሚለውን ማስረዳት አለበት፡፡ ይህንን ማሳመን ካልቻለ ሬጉሌሽኑ ይሰረዛል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ አሠራር ሌላው መፍትሔ ሊሆን ይችላል የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡
‹‹ሬጉላቶሪ ግሎታይን›› ግምቱ የሚነሳው ሬጉሌሽኑ አያስፈልግም ከሚል ነው፡፡ ያስፈልጋል የሚል መጥቶ ይህ ሬጉሌሼን የሚያስከትለው ወጪ ይህ ነው፣ የሚያስገኘው ጥቅም ይህ ነው ብሎ ማስረዳትና ማሳመን አለበት፡፡ ጥቅሙ የማያሳምን ከሆነ ሬጉሌሽኑ ተቆርጦ ይጣላል ማለት ነው፡፡ ይህ አሠራር ብዙ ጊዜ እስከ ሁለት ዓመት የሚወስድ መሆኑን የገለጹት ጥናት አቅራቢው፣ አንዳንድ አገሮች ይህንን ተግባራዊ አድርገው ብዙ ሥር ነቀል ሬጉላቶሪ ሪፎርም አምጥተዋል፡፡ እነዚህን ሁለት አማራጮች መንግሥት ቢተገብር ጥሩ ነው ብለው እንደሚያምኑ አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡
የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት አዋጅ መውጣቱ ጥሩ ጅምር ነው ብለው የሚያምኑት መንግሥት ወይም ሕግ የሚያወጡ አካላትም በደንብ አንቆ የሚይዝ በመሆኑ ያሉትን መልካም ዕድሎች በአግባቡ መጠቀም ተገቢ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ነገር ግን ያሉት ሕግጋት አሁንም ሊሻሻሉ የሚገቡ ስለመሆኑ አመልክተዋል፡፡
ሌላው አቶ ፈቃዱ እንደ መልካም ያነሱት ሕግጋት ደግሞ ሕግ መውጣቱ ነው፡፡ ይህ ሕግ የግል ዘርፉንም የሚመለከት ነው፡፡ በ2013 ዓ.ም. ላይ የወጡ ብዙ የግል ዘርፉን የሚመለከቱ የፀረ ሙስና ሕጎች አሉ፡፡ በፋይናንስ ዘርፉ ሊብራላይዜሽን የሚደረግ መሆኑ መገለጹም አበረታች ነው ብለውታል፡፡ ከዚህ አንፃር አፈጻጸም ላይ ችግር ቢኖርም የመንግሥትም ፍላጎት ጠንካራ ነው፡፡ በአንፃሩ እንደ ተግዳሮት ያነሱት ነጥብ ደግሞ የጠንካራ አስፈጻሚ ዕጦትን ነው፡፡ የትኛውም ሬጉላቶሪ ፕሮግራም የቱንም ያህል ቢሻሻል ጠንካራ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም ያስፈልጋል፡፡ ሲቪል ሰርቪሱ ጠንካራ ካልሆነ ዞሮ ዞሮ ፈጻሚው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ያለ ሰው ነውና ችግር ይኖራል፡፡ መንግሥት በቅርቡ እንደገለጸው፣ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩ ሲቪል ሰርቪስ ውስጥ የተሰገሰጉ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የያዙ ሰዎች አሉ ብሎ ተናግሯልና ይህ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ ይህ ካልተለወጠ ከፍተኛ ተግዳሮት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ ችግሩ ካልተፈታ ደግሞ የትኛውም ሪፎርም ውጤታማ ሊሆን አይችልም በማለት ሥጋታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡