Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልሲንቄን ለዓለም ለማስተዋወቅ የታተመው መጽሐፍ

ሲንቄን ለዓለም ለማስተዋወቅ የታተመው መጽሐፍ

ቀን:

በኦሮሞ ማኅበረሰብ ዘንድ የሴቶች ሚና በከፍተኛ ደረጃ የሚገለጽበት ‹‹ሲንቄ/ሲቆ›› የሚባለው ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት ነው፡፡ በዓለም አቀፉ የባህል ተቋም ዩኔስኮ በሰው ልጆች ወካይ ቅርስነት በተመዘገበው የገዳ ባህላዊ ሥርዓት ውስጥ አንዱ ሲንቄ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የግጭት መፍቻ፣ የጾታዊ ጥቃት መከላከያ፣ የሴቶች የሰላም በትር በመባል የምትታወቀውን ተምሳሌታዊ የሲንቄ/ሲቆ ባህላዊ ሥርዓት ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ በሴቶች የሚከናወነው የግጭት አፈታት ሥርዓት መሆኑም ስለ ትውፊቱ የሚገልጸው ጥናታዊ ጽሑፍ ይገልጻል፡፡

ስለዚሁ የሴቶች ባህላዊ የግጭት አፈታት ሥርዓት፣ የኦሮሞ ሴቶች የእርቅና የሰላም ተምሳሌት ስለሆነው ሲንቄ ትውፊት የሚያወሳ በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ የምርምር መጽሐፍ፣ ዓምና በታኅሣሥ 2013 ዓ.ም. በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እና በኦሮሚያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ አማካይነት ታትሞ መመረቁ ይታወሳል፡፡

ይህንኑ የኦሮሞ ሴቶች የዕርቅና የሰላም ተምሳሌት በሆነው ሲንቄ/ሲቆ ትውፊት ላይ ያተኮረ የምርምር መጽሐፍ በውጩው ዓለም እንዲታወቅ ለማድረግ ሁለቱ አካላት በመተባበር በእንግሊዝኛ ተተርጉሞ እንዲታተም አድርገውታል፡፡

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴርና የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በጋራ መጽሐፉን ያሳተሙት ‹‹THE ESSENCE OF SINQE/SIQQO CULTURAL SYSTEM AND ITS ROLE IN THE OROMO COMMUNITY›› በሚል ርዕስ ቀርቧል፡፡

መጽሐፉ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ሲመረቅ የተገኙት የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ቀጄላ መርዳሳ፣ ሲንቄ ሴቶች ነፃነታቸውንና መብታቸውን የሚያስከብሩበት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት የሚሸከሙበት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ባህላዊ ሥርዓት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ ሲንቄ ያሉ ባህሎችን በዘመናዊ ትምህርት ውስጥ በማካተት ለትውልዱ ማሳወቅ እንደሚገባ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ የብሔረሰቦችን ባህልና ቋንቋ ለማጥናት፣ ለመንከባከብና ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም ሳይገልጹ አላለፉም።

የምርምር ተቋማትም ባህላዊ እሴቶችን በማጥናት አገራዊ ፋይዳቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም በመናገር ጭምር፡፡

‹‹ሲንቄ ለሰላምና ለግጭት አፈታት ሴትን የማብቃት ምልክት ሆኖ የሚያገለግል ልዩ ሥርዓት ነው፤›› ያሉት የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)፣ በኢትዮጵያ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን በማረጋገጥ የሴቶችን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብትና ጥቅም የሚያስከብሩ ተቋማት ሊበረታቱ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የዩኔስኮ ተወካይ የሆኑት አቶ ጌቱ አሰፋ ደግሞ በኦሮሞ ማኅበረሰብ የገዳ ሥርዓት ውስጥ ሲንቄ ለሰላም የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው በማይዳሰሱ ቅርሶች ላይ ተመዝግቦ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንዳለ ተናግረዋል።

መጽሐፉ  የተዘጋጀው የሲንቄ ሥርዓት በስፋት በሚተገበርባቸው በኦሮሚያ አራት ዞኖች ጥናት በማካሄድ መሆኑን ከአዘጋጆቹ አንዷ ተናግረዋል፡፡

ሲንቄ ሲገለጽ

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የአማርኛ ዕትሙን ዓምና ሲያስመርቅ ስለ ሲንቄ ምንነት በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደሚከተለው ገልጾ ነበር፡፡

የሲንቄ/ሲቆ ባህላዊ ሥርዓት ሴቶች በስፋት በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያላቸውን ሚና እና ትኩረት የሚያሳዩበት የገዳ ሥርዓት ሲመሠረት አብሮ የተመሠረተ ነው፡፡

የገዳ ሥርዓት ሲመሠረት ለአባ ገዳው ‹‹ሎጋ ቦኩ እና ከለቻ›› ለሴቷ ደግሞ ‹‹ሲንቄ፣ ጫንጮ እና ጭጮ›› በተለያዩ ክብረ በዓላትና ውሳኔ በሚሰጡበት ቦታዎች ላይ እንዲጠቀሙበት የገዳ ሥርዓቱ ደንግጓል፡፡

ሲንቄ/ሲቆ ‹‹ሀሮሬሳ›› ከሚባልና ከሌሎች ከማይነቅዙ ከተመረጡ የዛፍ ዓይነቶች ተቆርጣ የምትዘጋጅ ቀጥ ያለችና ያልተጣመመች ዘንግ/ በትር ስትሆን፣ የጋብቻ ዕለት እናት ለምትድራት ልጇ የምትሰጣት እስከ ዕለተ ሞቷ የማትለያት የክብር መገለጫ ስጦታዋ ናት፡፡

ይህች የሰላም ጦር የሚዋጉባት ሳይሆን ክብራቸውን የሚያስጠብቁባት፣ ሰላምን የሚያወርዱባት፣ ፈጠነው የሚለምኑባት፣ አባ ገዳዎች ሲሾና ወንዶች ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ ድል እንዲቀናቸው የሚመርቁባት፣ ጋብቻንና ጉዲፈቻን ሕጋዊ የሚያደርጉባት፣ ሥልጣን የሚጋሩባትና ሀብት የሚያገኙባት፣ ከገዳ ሥርዓት ጋር ተያይዛ የምትሄድ ለሴቷ ተብላ የተደነገገች በሴቶች ብቻ የምትከናወን ባህላዊ ሥርዓት ናት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...