በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በሚኖሩበት አገሮች ተሰባስበው የአገራቸውን ባህልና ትውፊት የሚያስተዋውቁበት መድረክ የማግኘት ዕድል እምብዛም ነው፡፡ በተለይ በባዕድ አገር ያፈሯቸውን ልጆች ኢትዮጵያዊ ባህልን እንዲያውቁ ማስቻል ፈታኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ አራተኛ ዓመቱን የያዘው ታላቅ የአፍሪካ ሩጫ ዓመታዊ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በተለይ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እየተዘወተረ መጥቷል፡፡
ከሕፃናት እስከ አዋቂ የሚካፈሉበት የታላቁ አፍሪካ ሩጫ ጥቅምት 5 ቀን 2015 ዓ.ም. በዋሽንግተን ዲሲ እንደሚከናወን አዘጋጁ አካል አስታውቋል፡፡
በዓመታዊ መርሐ ግብሩ ላይ በርካታ ኢትዮጵያውያን ኦሊምፒያኖችና የዓለም ሻምፒዮኖች በክብር እንግዳነት ሲሳተፉ የቆዩ ሲሆን፣ ዘንድሮም እንደሚካፈሉ አዘጋጁ ለሪፖርተር በላከው መረጃ አስታውቋል፡፡
በዝግጅቱ ላይ ከ20 በላይ ታዋቂ ኦሊምፒያኖችና የዓለም ሻምፒዮን የሆኑ የአገር ባለውለታዎች ተሳታፊዎችን ለማበረታታት የሚካፈሉ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ደራርቱ ቱሉ በክብር እንግድነት እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡
‹‹አብሮነት መሻል ነው›› በሚል መሪ ቃል የሚካሄደው ይህ ዝግጅት፣ ኢትዮጵያውያንን ማሰባሰብ፣ የመጀመርያው ትውልድ ልጆችን ከባህላቸው ጋር የበለጠ ማቀራረብና ለተለያዩ በጎ ሥራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ የሚከናወን እንደሆነ የታላቅ አፍሪካ ሩጫ ሥራ አስኪያጅ ጋሻው አበዛ (ዶ/ር) አስረድተዋል፡፡
በዚህ ዝግጅት በሺዎች የሚቆጠሩ የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉ ታውቋል።
ዓመታዊ ውድድሩን የደገፉና የዝግጅቱ የመጠሪያ አጋር በመሆን ዳሸን ባንክ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታዊ ዝግጅቶችን ለመደገፍ አጋርነቱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ሌላው አጋር አሌክሳንደሪያ ቶዮታ በዋና ተባባሪ ስፖንሰርነት ዝግጅቱን በዘላቂነት ለመደገፍ መስማማታቸውን ጋሻው (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
ሁለቱም አጋር ድርጅቶች የዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት የድርጅቶቻቸው ታማኝ ደንበኛ ሆነው ለረዥም ጊዜ በመቆየታቸው፣ ለእነሱ ድጋፋቸውን ለመግለጽና ምሥጋና ለማቅረብም የሩጫ ዝግጅቱን እንደ መድረክ በመጠቀም ለአንድ ዕድለኛ ተሳታፊ የ2022 ቶዮታ መኪና በውድድሩ አስተባባሪዎች በኩል ማሰናዳቱ ተጠቅሷል፡፡፡
በዝግጅቱ የሚመዘገቡና በዕለቱ ውድድሩን የሚያጠናቅቁ ተመዝጋቢዎች በሙሉ ሽልማት በሚያስገኘው ዕጣ ላይ የሚካተቱ ሲሆን፣ በውድድሩ ማጠናቀቂያ ላይ የመኪናው ዕድለኛ የሆነው ተሳታፊ በይፋ መድረኩ ላይ ይገለጻልም ተብሏል፡፡
‹‹የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ባንካችን ካሉት ቀዳሚ ደንበኞች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የዳያስፖራው ማኅበረሰብም የባንካችንን ተመራጭነት እያደገ በመጣው የደንበኞች ቁጥር አሳይቶናል፤» በማለት የዳሸን ባንክ ሲኒየር የዳያስፖራ ባንኪንግ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያስቻለው አልማው ገልጸዋል፡፡
ዳሸን ባንክም የማኅበረሰብ ግዴታውን ለመወጣት፣ እንደ ታላቅ አፍሪካ ሩጫ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስቡ ዝግጅቶችን በቀጣይነት በመደገፍ፣ ለዳያስፖራው ማኅበረሰብ ምሥጋናውን የሚገልጽበት አንዱ አጋጣሚ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
‹‹በተለይ ብሔራዊ እሴታችን የሆነውን ሩጫ እንደ መድረክ በመጠቀም በውጭ የሚኖሩ ወገኖቻችን ግንኙነት ማጠናከርና የባህል ልውውጥ ማድረግ አበክረን የምንድግፈው ነው፤›› ሲሉ አቶ ያስቻለው አክለዋል።
እንደ ሥራ አስኪያጁ አስተያየት ከሆነ፣ በቀጣይም ዳያስፖራውን ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንደሚተጋ፣ መሰል መድረኮችንም በዋና አጋርነት ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ሌላው የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ አቶ ያሬድ ማናለብህ፣ አፍሪካውያን በተለይ ኢትዮጵያውያን የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ የረዥም ዓመታት ደንበኞች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
‹‹ኢትዮጵያውያን ላሳዩን እምነትና የአሌክሳንደሪያ ቶዮታ ቤተሰብ በመሆናቸው በታላቅ አፍሪካ ሩጫ በኩል ለማመሥገንና ለመደገፍ በማሰብ አጋርነታችን ለማሳየት ወደናል፤›› በማለት አብራርተዋል፡፡
ባለፉት ሦስት ዓመታት ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያ አንጋፋዎች ማለትም ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ የዲባባ ቤተሰብ፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ብርሃኔ አደሬ፣ ስለሺ ስህን፣ ቁጥሬ ዱለቻና ሌሎችም በክብር እንግድነት ተገኝተውበታል። በዚህ የ5 ኪሎ ሜትር የቤተሰብ ሩጫ ለመካፈል ምዝገባው በአዘጋጆቹ ድረ ገጽና በይነ መረብ ላይ እንደሚካሄድ ተገልጿል።