Thursday, October 6, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  [ክቡር ሚኒስትሩ አመሻሽ ላይ ድካም ተጫጭኗቸው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በሐዘን ስሜት ውስጥ ሆነው ተቀበሏቸው]

  • ምን ሆነሻል ዛሬ?
  • ምንም አልሆንኩም፣ ይልቅ አረፍ በል የደከመህ ትመስላለህ። 
  • አዎ፣ ቀኑን ሙሉ ጉብኝት ላይ ነበር የዋልኩት። 
  • ምን ስትጎበኝ? 
  • በዘመናዊ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎች እንዲደራጁ የተደረጉትን ተቋማት ስንጎበኝ ነበር ዛሬ። 
  • አይ…
  • ምነው? እንዴት ያለ የለውጥ ሥራ መሰለሽ የተመለከትነው፣ በነገራችን ላይ…
  • እ…
  • እነዚህን ተቋማት የምንገነባው ኢትዮጵያን ሊያፈርሱ ከሚፈልጉ ኃይሎች ለመከላከል ነው።
  • ምን ዋጋ አለው? 
  • እንዴት? 
  • እየሆነ ያለው ተቃራኒው ነዋ፡፡
  • እመኚኝ እየለፋን ያለነው አገራችንን በሰላም ለማቆየት ብቻ አይደለም። 
  • እ… ሌላ ለምንድነው?
  • የበለፀገችና ሰላማዊት ኢትዮጵያን ለልጆቻችን ለማውረስ ነው።
  • ስለየትኛው አገር ነው የምታወራው?
  • ስለእኛ ነዋ?
  • ጨቅላ ሕፃናት እኮ በጥይት እየተገደሉ ነው፡፡ 
  • እሱ ያሳዝናል፣ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን ይስጣቸው።
  • ቤተሰቦቻቸው? በአንድ ሌሊት ሙሉ ቤተሰብ እያለቀ እኮ ነው፡፡ 
  • እመኚኝ፡፡
  • ምኑን ልመንህ?
  • እመኚኝ፣ ይህ መከራ ሊያበረታን ነው የመጣው፡፡
  • ምነው እቴ? አሁንስ አበዛኸው፡፡ 
  • እንዴት?
  • ይሁን ብዬ ብሰማህ ሊያበረታን ነው የመጣው ትላለህ ጭራሽ?
  • እመኚኝ ስልሽ? 
  • ለምን ብዬ ነው የማምንህ? እውነታውን እያየሁት?
  • ምንድነው እውነታው? 
  • እውነታውማ አንተ ከምትለው ተቃራኒ ነው። 
  • ተቃራኒ ማለት?
  • መከራው እያበረታችሁ አይደለም፡፡
  • እ…?
  • እየበረታባችሁ ነው፡፡
  • ምን…?
  • ከመበርታትም አልፎ…
  • እ…
  • እያርበተበታችሁ ነው። 
  • እንዴት? 
  • የማኅበረሰቡን ሥቃይ ሊያበረታን ነው ከማለት የበለጠ ምን መርበትበት አለ?

  [ክቡር ሚኒስትሩ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ ጸሐፊያቸው ሞባይሏን እየተመለከተች ሰትስቅ አገኟት]

  • በጠዋት ምን የሚያስቅ ነገር አግኝተሽ ነው? 
  • ውይ ገብተዋል እንዴ ክቡር ሚኒስትር? 
  • ምንድነው እንደዚያ ሲያፍለቀልቅሽ የነበረው?
  • ወድጄ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
  • እንዴት?
  • ወደው አይስቁ ሆኖብኝ ነው።
  • በምን ምክንያት?
  • ፌስቡክ ላይ የሚቀለደውን አይቼ ነው ክቡር ሚኒስትር። 
  • ስለምንድነው የሚቀለደው?
  • አይ… ይቅርብዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡
  • ለምን?
  • ግዴለዎትም ይቅርብዎት ክቡር ሚኒስትር፡፡ 
  • ለምን? ጉዳዩ እኔን የሚመለከት ነው እንዴ? 
  • ምን በወጣዎት፣ ቢሆንም ግን…
  • ቢሆንም ምን?
  • ብዙ አይርቅም፡፡
  • ማለት?
  • ስለአማካሪዎት ነው እየተቀለደ ያለው፡፡
  • እንዴት? በምን ምክንያት?
  • ለሚዲያ በሰጡት ኢንተርቪው ነው ክቡር ሚኒስትር።
  • ምን ብሎ ነው?
  • ለገጠመን የኑሮ ውድነት ችግር የመፍትሔ ሐሳብ አቅርበው ነው።
  • ምን እንዳለ ለምን አትነግሪኝም?
  • ክቡር ሚኒስትር እንዲያው ቢቀርብዎት ይሻላል ብዬ እኮ ነው፡፡
  • ለኑሮ ውድነቱ ምን ዓይነት መፍትሔ አቀረበ? ለምን አትነግሪኝም?
  • ሸማቹ ከጠባቂነት ተላቆ የተወደደበትን ምርት ሊያመርት ይገባል የሚል መፍትሔ ነው የሰጡት።
  • እ…
  • ይቅርብዎት ያልኩት እኮ ለዚህ ነበር ክቡር ሚኒስትር?
  • ሌላ የተናገረው ነገር አለ? 
  • ሸማቹ መንግሥት ዋጋ እንዲያረጋጋለት ከመጠበቅ ይልቅ፣ የተወደደበትን ምርት ራሱ ማምረትና የመፍትሔው አካል መሆን አለበት ብለዋል። 
  • ታዲያ አንቺን ያሳቀሽ ምንድነው? 
  • እ…
  • መንግሥትም የሚያምነበት መፍትሔ እኮ ነው፡፡
  • መንግሥት ያመነበት ነው?!
  • በትክክል፡፡
  • አይ… ሳቅ ከንቱ፡፡
  • ምን አልሽ?
  • አሁን ነዋ ማዘን፡፡
  • ለምን? 
  • እንዴት ለምን ይባላል ክቡር ሚኒስትር?
  • እንዴ… ለምን አይባልም?
  • እንዴት ሆኖ ነው ሸማቹ የተወደደበትን የሚያመርተው? ስንቱን ነው የሚያመርተው? ምን ላይ ነው የሚያመርተው? 
  • በመንግሥት ደረጃ የጀመርነው የጓሮ አትክልት ምርት ውጤት ብትመለከቺ እንደዚህ አትይም ነበር። 
  • እሱማ በመንግሥት ጓሮ ነው። 
  • ማኅበረሰቡም በየጓሮው፣ በየደጃፉ ይህንን ቢያደርግ ችግሩን በቀላሉ መፍታት ይቻላል። 
  • የአዲስ አበባ ነዋሪ ምን ደጃፍ አለው? የምን ጓሮ አለው?
  • እህ… እሱም አለ ለካ? አየሽ እሱን አላሰብንበትም። 
  • ለነገሩ ማኅበረሰቡም የዋዛ አይደለም ክቡር ሚኒስትር።
  • እንዴት?
  • ደጃፍ የሌላቸውም ማምረት አለባቸው እያለ ነው ማኅበረሰቡ።
  • ምን?
  • ደጃፍ! 

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  አገር የሚገቡ የግል ዕቃዎችን በሚገድበው መመርያ ምክንያት በርካታ ንብረቶች በጉምሩክ መያዛቸው ተገለጸ

  በአየር መንገድ ተጓዦች ወደ አገር የሚገቡትን የግል መገልገያ ዕቃዎች...

  ባንኮች እንዲዋሀዱ እስከ ማስገደድ ሊገባ እንደሚችል ብሔራዊ ባንክ ጠቆመ

  በአሁኑ ወቅት የባንኮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ችግር የሚሆንና የውጭ...

  የተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅን የሚተካ ረቂቅ ተዘጋጀ

  ከቫት ነፃ የነበረው የኤሌክትሪክ ኃይል ገደብ ተቀመጠለት የገንዘብ ሚኒስቴር ከሃያ...

  የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ንግግሩን ለማስጀመር ያቀረበውን ጥሪ መንግስት ተቀበለ

  የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ንግግሩን ለማስጀመር ያቀረበውን ጥሪ መንግስት ተቀበለ

  የአፍሪካ ሕብረት በፌደራል መንግስትና በህወሃት መካከል የሰላም ንግግር እንዲጀመር...