Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቧልት ብቻ!

ከፒያሳ ወደ መገናኛ ልንጓዝ ነው። “የስሜቴ ጌታ የዕድሌ ባለቤት፣ የምወዳትን ልጅ አርግልኝ ጎረቤት” ይላል ለዛው የማይነጥፈው ድምፃዊ መስፍን አበበ ነፍሱን ይማረውና፡፡ ተሳፋሪዎች በስሜት ይወዘወዛሉ። “ዋ ሰው መሆን!” ይላል አጠገቤ የተሰየመ ወጣት። “ምኑን ዓይተኸው ደግሞ በዚህ ዕድሜህ? ባይሆን በእኛ ያምራል…” ይሉታል ከጀርባችን የተሰየሙ ጎበጥ ያሉ አዛውንት። “ደግሞ ብለን ብለን በሚያምርብንና በማያምርብን እንጣላ?” ሲላቸው በአንገታቸው እየተወዛወዙ በዝምታ አለፉት። ይኼኔ አዝማቹን ጨርሶ መስፍን ቀጥሏል። “ወይ አንተ አሞራ ና ተላከኝና ዋ ብሎ መለየት ባንተ ያምራልና” ይላል። ተሳፋሪዎች ከአዝማቹ እኩል በአቤት አቤት ይወዛወዛሉ፡፡ በሐሳብ የነጎዱት ፈዘው ተቀምጠዋል። “የዘንድሮ ነገር የተገላቢጦሽ፣ አህያ ወደ አደን ውሻ ወደ ግጦሽ፣ የዘንድሮ ጉዴን እኔ ምን አውቃለሁ፣ እንዲሁ በሆዴ እብሰለሰላለሁ…” ሲል “መብሰልሰልስ ቢሉህ መብሰልሰል ነው እንዴ?” ይላሉ አዛውንቱ አቀንቃኙን በአካል እንደሚያናግሩ ሁሉ። ወይ ትዝታ!

ከሚናገረው የማይናገረው በዝቷል። አዛውንቱና ያ አጠገቤ የተቀመጠ ወጣት እየቆያዩ የዘፈኑን ግጥም ተከትለው አንድ አንድ ይባላሉ። ደርሶ ሆድ የሚብሰው ሰው አየኝ አላየኝ ሳይል በዓይኑ ያቀረረ ዕንባውን አንኳሎ ሲያበቃ፣ ‹‹ሶፍት ይዛችኋል?” ብሎ አጠገቡ ያሉትን ይጠይቃል። ‘አልያዝንም’ የሚለው ሲበዛ ሲያልፍ ሲያገድም ከእኔም ከእሷም ከእሱም በተነካካበት ወዛም መዳፉ ጉንጩን ይጠርጋል። ይኼን በሰያፍ ያስተዋሉት አዛውንት ቀና ሳይሉ ዘወር ሳይሉ፣ “አይዞህ ወንድ ልጅ ዋጥ ነው…” ይላሉ። ማን ለማን፣ ለምን፣ በምን ምክንያት እንደሚናገር ዓይኑን መቆጣጠር አቅቶት እንደሚያነባና በምን ምክንያት እንደሚስቅ ግራ ያጋባል። መንገድ የሁሉም ነውና ዛሬም በትናንትናው ጎዳና በተዳከመ፣ በተሰላቸ፣ በተበራታ፣ ተስፋ በሰነቀ ዝብርቅርቅ የስሜት ምት ተሰባስቧል። መንገድ ሁሉን እንደ ቅኝቱና እንደ ዜማው እያገጣጠመ ደግሞም እያሸዋወደ ያስጉዘዋል። እነሆ ወደፊት!

ሙዚቃው አልቆ ሬዲዮኑ ከኢንተርኔት የተቃረመ መረጃውን ይረጫል። ይኼኔ አንዱ መጨረሻ የተቀመጠ ወጣት፣ “ኢንተርኔት እየሠራ እንዴ?” ብሎ ጠየቀ። “ኢንተርኔቱማ ይሠራል ጭንቅላታችን ነው እንጂ አልሠራ ያለው…” ትለዋለች ከጎኑ የተሰየመች ቆንጆ። “እንዴ እንደዚያማ አይባልም…” ይላታል። “እንዴት አይባልም? ሰው ማሰብ እስከሚችለው ድረስ {ተማረም አልተማረም} ማሰብ የሚያቅተው ፍጡር አይደለም። ሰላም፣ ፍቅር፣ ደግነት፣ እርስ በርስ መተሳሰብ በተፈጥሮ በልቦናችን ያሉ አስተሳሰቦች ናቸው። ታዲያ ከዚህ ውጪ ሲሆን ሰው ምን ሊባል ነው?” ስትለው፣ “ልክ ነሽ፣ ግን ልቦና የሚባል ነገር አለ። እስከ ዛሬ ይኼ ልቦና የሚባል ነገር መቀመጫው የት እንደሆነ አልታወቀም። ጭንቅላት ውስጥ ይሁን ደም ሥር ውስጥ ተስማምቶ የሚነግረን ጠፍቷል። ታዲያ ይኼ ልቦና የሚባል ነገር ፍቅር፣ ሰላም፣ መረዳዳት ብቻ ሳይሆን የሚያመነጨው እልህ፣ ቂም፣ በቀል፣ ዕብሪተኝነት፣ ጥላቻና መሰል እኩይ ዕሳቤዎችም አለው። ጭንቅላት ሥራው የፈቀዱለትን ማቀነባበር ነው እንጂ ሥራ ፈታ ማለትማ አበቃ ማለት እኮ ነው…” ይላታል። አይ ትንተና!

“ዋትኤቨር!” ትለዋለች። ይኼኔ አዛውንቱ ገልመጥ ብለው ወደኋላ እያዩ፣ “ቅዱሱ መጽሐፍም የሰው ልብ ውስጡ በእጅጉ ክፉ ነው ይላል እኮ? ምን ዙሪያ ጥምጥም ያስኬዳችኋል?” ብለው ከራሳቸው ጋር ማውራት ሲቀጥሉ፣ “ልብ ብቻውን ምን ዋጋ አለው? ከፋ ለማ ምን ያመጣል?” አላቸው ያ ወጣት። ነገረ ሥራው አልዋጥላቸው እንዳለ ነው። “እኮ ምን ልትል ነው?” ሲሉት፣ “ዘመን ካላገዘው ማለቴ ነው። አንዳንድ ዘመን አለ የሰላም፣ የተድላ፣ የፍቅር። አንዳንድ ዘመን ደግሞ አለ ሳይወዱ በግድ ነገር ሠርቶ ለነገር አሿሪ አሳልፎ እየሰጠ በአጭር የሚቀጭ…” ሲላቸው፣ “አሁን እውነት አወራህ…” ብለው ፈገግ አሉ። ‘አንዳንድ ዘመን አለ ምን ቢያምጡ ሳቅ የማይወለድበት’ ያለው ደራሲ ማን ነበር? ማን አስታውሶ!

ጉዟችን ቀጥሏል። አሁን ደግሞ ቀልባችን ሦስተኛው ረድፍ ላይ ወደ ተሰየሙት ወጣቶች ሸፍቷል። “ተረረም… ተረረም… ኧረ እንዲያው ተረረም…’ የተዘፈነው ላንቺ ነው አይደል?” ይላታል ልዕልት መሳይዋን ወጣት በቀኟ የተሰየመው። “ሰምቼው አላውቅም…” ትለዋለች ኮስተር ብላ። “እንዴ? እሱን ካልሰማሽማ ጆሮሽን እስካሁን ተጠቅመሽበት አታውቂም ማለት ነው። ‘አንቺ ልጅ አንቺ ልጅ የቬኑስ እመቤት፣ በምድር የማትገኝ አንቺ ነሽ በእኔ ቤት…” ብሎ በዜማ አንጎራጉሮ ሲያበቃ አፍጥጦ ያያታል። “አሁን በአንተ ቤት ጀንጅነህ ሞተሃል…” መሽኮርመም ጀምራለች። “ሥራ የሚያስጀምረኝ ሳጣ ምን ላድርግ ብለሽ ነው?” ሲላት ከጎኔ፣ “ምን ዓይነቱ ፋራ ነው፣ ገና ከአሁኑ ሥራ የለኝም ብሎ ይጀምራል እንዴ? አትሰማውም በቃ ከዚህ በኋላ…” ይላል። ይኼን የማይሰማው ‘ጀንጃኝ’ ነኝ ባይ መተርተሩን ቀጥሏል። “እኔ ምልሽ? ለምን እኔና አንቺ አንደራጅም?” ይላታል። “እንዴ? ምን ለመሥራት?” ትጠይቃለች በግንባሯ ፀዳል ዓይን የምታባርረው ቆንጆ። “ሥራ ይጠፋል ደግሞ? ዋናው እኔና አንቺ መደራጀታችን ነው፣ ከዚያ ዕድላችንን መሞከር ነው። ከሆነልን ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ እንሠራለን። ካልሆነልን ትውልድ እንተካለን…” ሲላት ከት ብላ ሳቀች። አዛውንቱ ሊናደዱ ፈልገው ሳይናደዱ፣ ሊቆጡ ፈልገው የሚከተለውን መገመት ከብዷቸው፣ “ሆ…ሆ…” አሉ በረጅሙ። ልጅት ለአመል ያሳየችውን ግንባር መከስከስ ትታ፣ “ቆይ አንተ እንዴት እስካሁን ተደራጅቶ ሥራ መሥራት ትዝ ሳይልህ ኖሮ አሁን አሰብከው?” ስትለው፣ “ምን ላድርግ አንቺን የመሰሉ ወርቀ ዘቦዎች ታክሲ መጠቀም አቆሙ…” ብሎ እጇን ይዞ ከአንገት በላይ ሳቀ። ጊዜና ታክሲ ከአንገት በላይ አነጋግሮ ይኼው እንዲህ ከአንገት በላይ ያሳስቃል። ምን ማለት ይቻላል!

ደግሞ ትንሽ እንደተጓዝን ዓይኑን በጨው ባጠበው ወጣት ጋባዥነት በሻይ መጠጣት ሰበብ ያቺ የፀዳል ክንፍ አብራው ወረደች። ገና ከመውረዳቸው አጀብ ባዩ በዛ። “ወይ ዘንድሮ፣ እንዲህ እየፈራሁ ቆሜ ልቅር? ምን አለ አምላኬ ወይ ድፍረት ብትሰጠኝ ወይ ወደ ጭልፊትነት በሆነ ምትሃት ብትለውጠኝ?” አለ መጨረሻ ወንበር ላይ አንዱ። “ሆኖ መገኘት እንጂ መለዋወጥ መቼ ከበደን ዘንድሮ? በተቀመጡበት መገኘት አልችል ብለን አይደል እንዴ ባስቀመጥነው ሥፍራ የምናጣው ነገር የበዛው…” ሲል ጋቢና የተሰየመ፣ “እስቲ ተረጋጋ፣ የተጨባበጠ ሁሉ ይጣመራል ያለህ ማነው?” አሉ አዛውንቱ። “ኧረ ተውኝ አባት፣ ብቻ አንዴ ላግባና ከዚያ የመጣው ይምጣ…” ይላል ያ ብቸኝነት የሰለቸው። “እንዴት ያለ ጊዜ ነው እናንተ? እናንተ ልጆች ምንድነው የሆናችሁት? ፍቺ ይኼን ያህል ቅልል ያለባችሁ ምን ነክቷችሁ ነው? የገነቡትን መናድስ፣ የደከሙበትን ማፍረስ እንዲህ ከጥፍራችሁ ቆሻሻ አልቆጥር ብላችሁ የከፋችሁትስ ምን ቢለክፋችሁ ነው?” ብለው እየተገረሙ አፋቸውን ሲይዙ ወጣቱ ብቻውን ያወራል። “በነገራችን ላይ ሰሞኑን ያም እየደወለ፣ ያም እየጠራኝ የሚለኝ ተፋታሁ ሆኗል። አይገርምህም?” የሚለኝ ያ ዝምታ የማያውቅ ከጎኔ የተሰየመ ወጣት ነው። ይኼኔ “አስገባው” ብሎ ወያላው ታክሲዋን አስቆማትና አንድ ጎልማሳ ገባ። ወያላው “ሳበው!” ከማለቱ ጎልማሳው፣ “ይኼው ስበን ስበን በጥሰን አረፍነው፣ ከዚህ በላይ ምኑ ይሳባል?” ብሎ ቀላቅሎ ጨዋታውን አቆረፈደው። ለነገሩ ምን ያልቆረፈደ አለ? ምንስ ያልተቀላቀለ አለ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። መንገዱ በተሽከርካሪዎች ተጨናንቋል። ሁሉም አሽከርካሪ ጥሩምባው ላይ ለሽ ብሎ የተጋደመ ይመስል መንገዱ በእሪታ ናኝቷል። “አይለቁንም እንዴ? ወይስ መብራቱ ‘ስታክ’ አደረገ?” ወያላው ሾፌሩን ያናግራል። “ምን ‘ስታክ’ ያላደረገ ነገር አለ?” ይላል ዝምተኛው ሾፈራችን። “በቃ እዚህ ጋ እናውርዳቸዋ?” ወያላው አንዴ ወደ እኛ አንዴ ወደ ሾፌሩ እያየ ለውሳኔ ቸኩሎ ይቁነጠነጣል። “እንዴ? እዚህ መንገድ መሀል ልታወርደን? ነውር አይደለም እንዴ?” አዛውንቱ ተቆጡት። “ታዲያ አረንጓዴው መብራት አልበራ አለ እኮ? በእግራችሁ ብታዘግሙ ለእናንተም ጤና ነው…” ሲላቸው፣ “መሀል መንገድ ዘርግፈኸን ነው ስለጤና የምታወራው?” ብሎ ከመጨረሻ ወንበር አንዱ ጮኸ። “እኔ ምን ላድርግ መብራቱ ነው እኮ። እንቢ ካላችሁ የሚያስገድዳችሁ የለም…” ወያላው ማጉተምተም ሲጀምር ጎልማሳው፣ “እሱ ምን ያድርግ ብላችሁ ነው? የታየውን መፍትሔ ነው ያቀረበው። ይህችንስ ማን አየብን። መፍትሔ ማጣታችን ሳያንስ መፍትሔ ሲገኝም አላዳምጥ እያልን ችግር መደራረብ በበኩሌ ታክቶኛል። እኔን አውርደኝ…” ብሎ ወረደ። ቀስ በቀስ አንዱ አንዱን እያየ ዱብ ዱብ አለ። ቢያንስ ስድስት ሰዎች ያህል እንደ ወረዱ የትራፊክ ፖሊስ መጥቶ ያስተናብር ጀመር። ይኼን መብራቱን አልፈን ጥቂት ተጉዘን ስናበቃ ታክሲያችን ጥጓን ያዘች። ወያላው “መጨረሻ!” ብሎ በሩን ከፈተው። “ከጨረስከውማ ቆይተህ ነበር…” እያሉ ተሳፋሪዎች ወረዱ። ‹‹እየተያየን አንግባባ፣ እየተደማመጥን አንስማማ፣ ከፒያሳ እስከ መገናኛ ቧልት ብቻ፡፡ ዓይንና ጆሮ ተሸክመን ባዶ…›› እያለ ወርደን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት