Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከራስ ዳሽን ግርጌ ሊታነፅ የታሰበው የቅዱስ ያሬድ የልህቀት ማዕከል

ከራስ ዳሽን ግርጌ ሊታነፅ የታሰበው የቅዱስ ያሬድ የልህቀት ማዕከል

ቀን:

ኢትዮጵያዊው ቅዱስ ያሬድ ባስተማረበትና በመጨረሻም በተሰወረበት በደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም የቅዱስ ያሬድን አስተምህሮ የሚዘክር የልህቀት ማዕከል ለመሥራት የተመረጠው የኪነ ሕንፃ ዲዛይን ይፋ ሆኗል፡፡  

አገራዊውን የኪነ ሕንፃ ዕውቀት መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ አርክቴክቶች ማኅበር የውድድር መሥፈርት መሠረት በስካይላይን አርክቴክትስ ኤንድ ኢንጂነርስ የተሠራው የቅዱስ ያሬድ የምርምርና የልህቀት ማዕከል ዲዛይን ግንባታው የሚከናወነው በሰሜን ጎንደር ራስ ዳሽን ተራራ ግርጌ ላይ እንደሆነ የሕንፃው ዲዛይን ይፋ በተደረገበት ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. ተገልጿል፡፡

የበርካቶች መሰል ፕሮጀክቶችን ዲዛይን ከነደፈው ስካይላይን አርክቴክትስ ኤንድ ኢንጂነርስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ የተገኙት አርክቴክት መኮንን ወርቁ እንዳሉት፣ ዲዛይኑ የተሠራው ከቅዱስ ያሬድ ሕይወት ታሪክናን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን ትውፊት መነሻ በማድረግ ነው፡፡

- Advertisement -

‹‹የቅዱስ ያሬድ ነፀብራቅ ነው›› የተባለው ዲዛይን ግንባታ ከራስ ዳሸን ተራራ ግርጌ፣ ከቀዝቃዛውና መውጣትና መውረድ ከሚጠይቀው ሥፍራ በስድስት ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ ግንባታውም ሦስት ቢሊዮን ብር ይፈጃል ተብሏል፡፡

የአብነት ትምህርት ቤት፣ የጥናትና ምርምር ማዕከል፣ የሙዚየምና ቤተ መጻሕፍት፣ አገራዊ የማህሌት ትዕይንት የሚቀርብበት መድረክ፣ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃ፣ የሊቃውንትና መነኮሳት ማረፊያ በሕንፃ ግንባታ ፕሮጀክቱ ከተካተቱት ይገኙበታል፡፡

ማዕከሉና ሙዚየሙ የሚገነባበት ሥፍራ የራስ ዳሽን ተራራና የስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አቅራቢያ በመሆኑ ለቱሪስት መስህብነት እንዲውል ያስችለዋልም ተብሏል።

ግንባታውን ለማጠናቀቅ ከአምስት እስከ ሰባት ዓመታት እንደሚወስድና ለተገለጸው ለፕሮጀክቱ የሚውለውም ገንዘብ ከተለያዩ አካላት ይሰበሰባል ተብሏል፡፡ 

የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም በሰሜን ጎንደር ዞን በበየዳ ወረዳ ይገኛል፡፡ ይህ ሥፍራ ቅዱስ ያሬድ (ከ505 እስከ 751 ዓ.ም.) በኢትዮጵያ ምድር በቅድስና በኖረበት ዘመን አምስቱን ዓበይት ድርሰቶችና የዜማ ዓይነቶች ከደረሰ በኋላ የተሰወረበት ሥፍራ መሆኑን ገድሉና በእሱ ዙሪያ የተጻፉ ድርሳናት እንደሚያሳዩ የቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት የዓብይ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ ያሬድ መርሄ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ የደረሳቸው መጻሕፍት ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ ዝማሬና መዋሥዕት እንዲሁም አንቀጸ ብርሃን በመባል ይታወቃሉ፡፡ የነገረ ትርጓሜ ዕውቀቱ ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል። ድጓ የተባለውና ለሥርዓተ አምልኮ የተዘጋጀው ድርሰቱ መሠረቱን ያደረገው በአራቱ የኢትዮጵያ ወቅቶች ክረምት እና መፀው፣ ሐጋይ (በጋ) እና ፀደይ ላይ ነው፡፡

 እነዚህ ድርሰቶች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ከመሆናቸው ባሻገር የቅዱስ ያሬድ ጥልቅ የፍልስፍና፣ የተፈጥሮ ሳይንስ፣ የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የክዋኔ ጥበብና የሥነ ውበት ንድፈ ሐሳብና የጥበብ መጻሕፍት ናቸው፡፡

እንደ አቶ ያሬድ ሥፍራው የግንባታ ቁሳቁስ ለማመላለስ አስቸጋሪ በመሆኑ መንገዱ እንዲሠራ ጠይቀዋል፡፡ የመንገዱ ችግር ከተፈታ ግንባታው በ2015 ዓ.ም. መስከረም ላይ ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የፕሮጀክቱ ዓላማ

የደብረ ሐዊ ቅዱስ ያሬድ አንድነት ገዳም ፕሮጀክት ዓላማ ለኢትዮጵያ ምልከት የሆነውንና ኢትዮጵያዊነትን በጥበብ ያነፀና እና ያቀና የጥበብ አባት አብነት አድርጎ አስተምህሮውን ማስረፅ ነው፡፡

በዚህ ሒደት ኢትዮጵያና የቀደመውን ወርቃማ ዘመን ትሩፋት እየፈተፈተች የዛሬውን መልከ ብዙና ፈርጀ ብዙ ዝብርቅርቅ ፍላጎትና አስተሳሰብ እያረቀች በጥበብና ዕውቀት ኢትዮጵያን ለመሥራት ትጠቀምበታለች፡፡ በዚህ ምክንያት ፕሮጀክቱ በኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባለቤትነትም ቢመዘገብም ሀብትነቱ ለአገርና ለሕዝብ ነው፡፡

በፕሮጀክቱ ከሚታነፁ ተቋማት በዋነኝነት ለቅዱስ ያሬድ ወጥ አስተምህሮ፣ ለማህሌት አገልግሎት፣ ትንግርት የሆኑ ታላላቅ የጥበብ ሥራዎቹ የሚመጥንና ለሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ናሙና ሊሆን የሚችል ይዘትና ቅርፅ ያለው ቤተ ክርስቲያን በስሙ ማነፅ ይገኝበታል፡፡

የቅዱስ ያሬድ አምስቱን ዜማና የዜማ ድርሰቶቹን ጨምሮ አጠቃላይ ሥራዎቹን መሠረት አድርጎ የታሪክ፣ የፍልስፍና፣ የሥነ ውበትና የክዋኔ ጥበብ ጥናትና ምርምር ሊካሄድበት የሚችል የልህቀት ማዕከልም የግንባታው አካል ነው፡፡

በመላ ኢትዮጵያ የሚገኙና ጉባዔ ዘርግተው ደቀ መዛሙርት የሚያስተምሩ የአብነት ትምህርት ቤቶች ዕውቀታቸውን የሚያጠናቅቁበትና የሚመረቁበት የአምስቱ ጽዋትወ ዜማ ምስክር ጉባዔ ቤት የሚገነባም ይሆናል፡፡

የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች፣ የወግ ቁሶችና ቅርሶች እንክብካቤ የሚደረግበት፣ የሚጠበቅበትና ለጥናትና ለምርምር፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር በአንድ ሥፍራ የሚደራጅበት ሙዚየምና ቤተ መጻሕፍትም እንደሚገነባ የዓብይ ኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ያሬድ መርሄ በመድረኩ ላይ ተናግረዋል፡፡

ቅዱስ ያሬድ ማነው?

የዘር ሐረጉ ከአክሱም ካህናት ወገን የሚመዘዘው ቅዱስ ያሬድ ሚያዝያ 5 ቀን 505 ዓ.ም. ከአባቱ ይስሐቅና ከእናቱ ታውክሊያ በአክሱም ከተማ ተወለደ፡፡ አባቱ በልጅነቱ በመሞቱ ምክንያት እናቱ በአክሱም ጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ያስተምር ወደነበረው ወንድሟ ጌዴዎን ዘንድ እንዲማር ወስዳ ሰጠችው፡፡

ይሁን እንጂ ሕፃኑ ያሬድ ትምህርት አልገባው ስላለው አጎቱ ጌዴዎን በጨንገር ይገርፈዋል፡፡ በዚህ የተነሳ ሽሽቶ ሲሄድ ደክሞት ከክሬዋህ ዛፍ ሥር ያርፋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዛፍ ለመውጣት ስድስት ጊዜ ወድቆ በሰባተኛው ከአናት ወጥቶ ፍሬውን ለመምጠጥ ከቻለው ትል ፅናት ተምሮ ወደ አጎቱ እንደተመለሰና በቤተ ቀጢን ትምህርቱን እንደቀጠለ መጻሕፍት ይዘክራሉ፡፡ ከዚህ በኋላ ቅዱስ ያሬድ በአካል ሥጋ ወደ ሰማይ እንደተነጠቀና ከመላዕክት በቀጸለው ዜማ ተመሥርቶ የተለያዩ ዜማዎችና የዜማ መጻሕፍትን እንደደረሰ ድርሳናት ያትታሉ፡፡

መጽሐፈ ስንክሳር የተባለው ታላቅ መጽሐፍ የግንቦት 11 ቀን ንባብ ላይ እንደተገለጸው፣ ቅዱስ ያሬድ እንደ ሰማያዊው ሱራፌል  የመላዕክትን ዝማሬ ተምሮ የተለያዩ ዝማሬዎችን እንደዘመረ፣ የዜማ መሠረት የሆኑ ግዕዝ፣ ዕዝል፣ አራራይ ስልቶችን እንደፈጠረ እንዲሁም ከድርሰቶቹ ባሻገር ስምንት የዜማ ምልክቶች (ኖታዎች) ፈጥሯል፡፡

 

 በኋላም በምናኔ መኖር በመፈለጉ ከአክሱም ተነስቶ ተከዜ ወንዝን በመሻገር በተለያዩ ሥፍራዎች በርካታ ደቀ መዛሙርትን እያስተማረና ድርሰቶቹንም እየጻፈ መዳረሻውን በሰሜን ጎንደር ጸለምት ዋሻ አድርጎ በእዚያው ለረዥም ዘመናት እንዳስተማረና የመጨረሻው የሆነውን ድርሰቱን እንደጻፈ ይነገራል፡፡ በዚሁ ዋሻ ዕድሜውን ሙሉ በምናኔና በቅድስና ኖሯል፡፡

ከስድስተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድ ያበረከተላትን አምስቱን ጸዋትወ ዜማና የዜማ ድርሰቶቹን በአብነት ትምህርት ቤት ወንበር ዘርግታ ጉባዔ አቁማ እያስፋፋች በርካታ ሊቃውንትን በእግሩ እየተካች አስተምህሮቱን አስፋፍታለች፣ አስቀጥላለች፡፡ አበርክቶዉን፣ ትውፊቱን ጠብቃና አክብራ ለአምልኮ ሥርዓት ማስፈጸሚያና አገልግሎት በሰፊው አውላ እየተጠቀመችበት ትገኛለች፡፡

ቅዱስ ያሬድ በዚህም ዓለምን ባስደመመ የዜማ ስጦታውና ሥርዓቷ ተከብራና ገዝፋ ከአራቱ ማዕዘናት በሚጎርፉ ጎብኚዎችና አጥኚዎች እየተጎበኘች ትወደስበታለች፡፡ በዝማሬና በሽብሸባ ተውበው ካህናት የሚያገለግሉባቸው ታላላቅ የአደባባይ በዓሎቿም በዓለም የማይዳሰሱ ድንቃ ድንቅ ቅርሶች ለማስመዝገብ በቅታለች፡፡

ለቅዱስ ያሬድ መታሰቢያ እንዲሆኑ ቤተ ክርስቲያን በስሙ ከመታነፁ ባሻገር በአክሱም ከተማ የነገረ መለኮት ከፍተኛ ተቋም ያለ ሲሆን፣ በአዲስ አበባም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር የሚገኘው የሙዚቃ ትምህርት ቤት በስሙ ይጠራል፡፡ እንዲሁም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ጣቢያ መካከል ያለው መንገድም ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ ‹‹የቅዱስ ያሬድ መንገድ›› በመባል ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...