Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊእየጨመረ የመጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

እየጨመረ የመጣውን የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ኅብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ቀን:

ኅብረተሰቡ በመዘናጋትና የመከላከያ መንገዶች ትግበራን በመቀነሱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እንደገና እየጨመረ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቁት፣ በቫይረሱ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነስ ኅብረተሰቡ በመዘናጋት የመከላከያ መንገዶች እንዳይተገብር አድርጓል፡፡

ኮቪድ-19 ባለው ተለዋዋጭ ባህሪ ምክንያት በተለያዩ ጊዜያት ከፍ ዝቅ እያለ የኅብረተሰቡን ጤና እየጎዳ እንደሚገኝ የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ዕድሜያቸው ከ12 እና ከዚያ በላይ ለሆኑ፣ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግና የመከላከል አቅም ለማጠናከር ከሰኔ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በተሰጠው ሦስተኛው ዙር የኮቪድ-19 ክትባት ዘመቻ እስካሁን ድረስ ከ22 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተከትበዋል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

አሁንም በአገር አቀፍ ደረጃ የተፈናቃዮችና ስደተኞች ጣቢያዎችን ጨምሮ በሁሉም አካባቢዎች ክትባቱ እየተሰጠ ስለሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ እንዲከተቡ አሳስበዋል።  

በኮቪድ-19 ተይዘው በፅኑ ሕክምና ክፍል ዕርዳታ እያገኙ ያሉ ወገኖች መኖራቸውን የገለጹት ዳይሬክተሩ ክረምቱን ተከትሎ ኮቪድ-19ን ጨምሮ በንፅህና ጉድለት ሊመጡ የሚችሉ ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል ኅብረተሰቡ የግልና የአካባቢውን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡

የሃይማኖት ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና መላው የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮቪድ-19ን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ክትባቱን ከመከተብ በተጨማሪ ያለመሰልቸት የመከላከያ መንገዶችን መተግበር እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

እስካለፈው ሳምንት ድረስ 42.6 ሚሊዮን ሰዎች ቢያንስ የመጀመርያ ዶዝ የተከተቡ ሲሆን፣ 36.3 ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ በሙሉ መከተባቸውን ሳይገልጹ አላለፉም።

በተያያዘ ዜና ኮርያ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ወረርሽኞች መከላከል ዙሪያ ያላትን ልምድ ማካፈል እንደምትፈልግ ማስታወቋን የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡ ኮርያ ፍላጎቷን የገለጸችው ኢትዮጵያ በጤና ዙሪያ ያሉባት ክፍተቶችን የሚያመለክቱ ጥናቶችና የፕሮጀክት ፕሮፖዛሎች በቀረቡበት መድረክ ላይ ነው፡፡

የኮርያ ፋውንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሔልዝ ኬር ፕሬዚዳንት ኪም ጃንግ ያፕ ኮቪድ-19 ወረርሽኝን በተመለከተ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሠሩ ሥራዎችና የተገኙ ለውጦች እንዲሁም ያጋጠሙ ችግሮችና መልካም አጋጣሚዎች ላይ ገለጻ አቅርበዋል፡፡

 ኮርያ በኮቪድ-19 እና በሌሎች ወረርሽኞች መከላከል ዙሪያ ያላትን ልምድ ማካፈል ትፈልጋለች ያሉት ኪም፣ ወረርሽኙ በጤና ላይ ብቻ ሳይሆን በኅብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም እነዚህን ጉዳዮችን ለመፍታት የጤና ሥርዓት በመዘርጋትና ስትራቴጂዎችን በመንደፍ ተባብሮ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በማንሳትም በኮቪድም ሆነ በሌሎች የጤና ክፍተቶች ላይ ድጋፍ ለማድረግና አብሮ ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በጤና ሚኒስቴር የብሔራዊ የኮቪድ-19 ከፍተኛ አማካሪ መብራቱ መሰቦ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመመከት አጋር ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላትን በማስተባበርና ኅብረተሰቡን በማሳተፍ በርካታ ሥራዎች መሠራታቸውን  ጠቁመዋል፡፡  በቀጣይም በሽታውን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ክትባት በመስጠት፣ በምርመራና በማከም ላይ በማተኮር ይሠራል ብለዋል፡፡

የእናቶችና ሕፃናት ጤና ላይ የተገኙ ስኬቶች መኖራቸውን የገለጹት የጤና ሚኒስትር አማካሪ ዳንኤል ገብረሚካኤል (ዶ/ር)፣ የጨቅላ ሕፃናት ሞትና የመቀንጨር ችግር እንዲሁም የተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ ያለውን ጫና ለመፍታት የተለያዩ ስትራቴጂዎችን በመከተል በቅንጅት እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

የኮርያ ፋውንዴሽን ፎር ኢንተርናሽናል ሔልዝ ኬር ከጤና ሚኒስቴርና ገንዘብ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በእናቶችና ሕፃናት ጤና፣ በጤና መድን፣ በሕክምና መሣሪያዎችና ግብዓቶች አቅርቦት፣ የሕክምና ባለሙያዎች አቅም ግንባታ ሥራዎችን ሲሠራና ሲደግፍ የቆየ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ