Monday, May 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በመንፈስ የኩሽ ዘር ነኝ ክፍል ፪

በያሬድ ነጋሽ

የቀደመ ሰለሞናዊው ሥርወ መንግሥት ተገርስሶ በመርሐ ተክለሃይማኖት የአገው ወይም የዛጉዬ ሥርወ መንግሥት በመጣበት ወቅት አገሪቷ ከውስጥ ወደ ውጭ እንድታይ የተደረገበት፣ እጇ ላይ የነበረውንና ለዜጋዋ ምቹ ማዕድ መሆን የሚችለው የተዳፈነ የሀብት ብርሃን የገለጠችበት፣ ከ1262 ዓ.ም. በኋላ በይኩኖ አምላክ በኩል የሰለሞን ሥርወ መንግሥት ሲመለስ አገሪቱን ከውጪ ሆኖ ወደ ውስጥ የመመልከት አባዜው መልሶ ያቆጠቆጠበትና በእጇ ያለውም ሀብት ወደ ቀደመ ስውርነቱ የተመለሰበት ወቅት እንደነበር አምናለሁ፡፡

የሰለሞናዊው ሥርዓት የመንግሥት፣ የቤተ ክርስቲያን አወቃቀሩንም፣ የቅዱሳት ሥፍራውንም፣ የቅዱሳን ማጣቀሻውም፣ ሌላውንም ስናይ አካሉን ኢትዮጵያ አድርጎ መንፈሱ ኢየሩሳሌም የከተመ ነበር፡፡ የመንግሥት ዋነኛ ኃላፊነት የሆነውን ተቋማትን የመምራትና የማስተባበሩ ሒደት የኢትዮጵያን ቀደምት እሴቶችና አሰላሳዮችን ከውጪው ጋር አካቶ የተኬደበትና በስተመጨረሻ ሥልጣኑን በሰላም የመረካከብ ሒደት (ከነመውደቅ መነሳቱ) ከእነሱ በፊት ባልነበረ መልኩና ከእነሱም በኋላ ላይደገም ሆኖ በዛጉዬ ሥርወ መንግሥት ተከናውኗል።

ሲመዘግበው፣ በዚያ ጊዜ የቤት መሠረት ከጣሪያ እንዲጀምር ያደረጉበትን የሕንፃ ምሕንድስና ተመልክተው በመደነቃቸው ነው፡፡ የዛሬ ትውልድም ስለ ላሊበላ አስረዱ ብንባል የምንናገረውም ይህንኑ ነው፡፡ ስለሕንፃው ግንባታ የተጻፉ ታሪካዊ ምልከታዎችን ከተለያዩ ድርሳናት በተናጥል ተመልክተን፣ በመቀጠል ወጥ በሆነ መልኩ ለመሰብሰብ  እንሞክር።

‹‹ላሊበላ ከምድረ ግብፅ ተሰደው ለመጡት ሰዎች የሚጠጉበትና የሚያርፉበትን ሥፍራ ሰጣቸው፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ ከእነዚህ መካከል የእጅ ሥራ፣ ግንብ መገንባት፣ እንጨት መጥረብና ድንጋይ መውቀር የሚያውቁ መኖራቸውን በሰማ ጊዜ እያስጠራ ቢጠይቃቸው እርግጥ መሆኑን አስረዱ›› (የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ ዓደዋ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ በ1920 ዎቹ፣ ገጽ 30 እና 31)

‹‹እንደዚሁ አፄ ላሊበላ የጎደለውን ጥበብ የሚያውቅ ሠራተኛ እንዲልክ ለግብፅ ሡልጣን ልኮ አስመጥቶ ነበር። በቤተክርስቲያኑ ሥራ ከአፄ ላሊበላ ጋር ባለቤታቸው መስቀለ ክብራ፣ እንዲሁም ‹‹ዓበይተ ብጉና›› የሚባሉ ልዩ ልዩ የቤተመንግሥትና የቤተክህነት ሹማምንት መድከማቸው የማይቀር ነው። …አብያተ ክርስቲያኖቹ ሰለሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበልጥ፣ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን… የገድሉ ጸሐፊ ጽፏል›› (የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ አክሱም ዛጉዬ፣ በተክለጻዲቅ መኩሪያ፣ ገጽ 425 እና 426)፡፡

‹‹ሕንጻ ቤተክርስቲያኑን ዛሬ እንኳን የኢትዮጵያ ሕዝብ ከየአውራጃው እየተሰባሰቡ በየዓመቱ በመሄድ እንደ ኢየሩሳሌም አክብረው ይሳለሙታል›› (የኢትዮጵያ ታሪክ ከንግሥተ ሳባ እስከ ታላቁ ዓድዋ፣ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ በ1920ዎቹ፣ ገጽ 33)

ከላይ የተመለከትነው ዝርዝር የታሪክ ማስረጃ ተጠቃሎ የታሪካዊ ልቦለድ ለዛ ተላብሶ የተቀመጠው ‹‹ሐሰተኛው በእምነት ስም›› በተሰኘው የደራሲና ሐያሲ ዓለማየሁ ገላጋይ ሥራ ውስጥ ነው፡፡ ‹‹የመራ ወንድማማቾች ይባላሉ፣ ሴማዊያኑ ሰለሞናውያን ነገሥታት ተዳክመው የኩሽ ሥርወ መንግሥት ሲቋቋም በመጀመሪያው ንጉሥ በመራ ተክለሃይማኖት ስም የተመሠረቱ ነበሩ። ዓላማቸውም የባዕዱን ትውፊት አጥፍተው ነባሩን፣ የራሳችንን ሥነ ተረት በሕዝቡ መካከል ማቆም ነበር። …አዲስ አስተሳሰብ የሚያራምዱ ብቅ አሉ፡፡ ነባሩን ትውፊት በአዲሱ ክርስቲያናዊ አስተምሮ ውስጥ በመሰግሰግ፣ በተደባለቀ ሥነ ተረት ኢትዮጵያ የኢየሩሳሌምን ሥፍራ እንድትወርስ ማስቻል፡፡

ያ በአፄ ዘድንግል ጭንቅላቱን የተቆረጠው ጥቁር መሲህ የአዲሱ ድብልቅ አስተምሮ ተርጓሚ ነበር፡፡ ማኅበረ ላሊበላ ይባላሉ፡፡ የአፄ ላሊበላ ድጋፍ ስለነበራቸው ብዙ ሥራዎችን ሠርተዋል፡፡ የላሊበላ አብያተክርስቲያናት ሲታነጹ የራሳቸውን ነባር እምነት ምልክት ደባልቀዋል፡፡ ለምሳሌ የአቴቴ አድባር የፀሐይ መታቀፊያ በትር የሚወክለው ኦጃይቭ (ogive) ወይም ኦጊ ቅርጽ ቤተ ገብርኤልና ቤተ ጊዮርጊስን ጨምሮ መቀሰቻ ሆኖ እንዲገባ አድርገዋል። የመቀሰቻው ትርጉምና ሚናው የቤተ እምነቱ ዋስትና እስከመሆን የሚያደርሰው እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ የማኅበረ ላሊበላ እንቅስቃሴ የምድራዊትና የሰማያዊት ኢየሩሳሌም ትውፊት ወደ ኢትዮጵያ በማዞር ቤተ እምነቶቹን ለሁለት ከፍለው ሰይመዋል። የማኅበረ ላሊበላ ሥራ ተደጋጋፊ ሆኖ በሁሉም ረገድ ዓላማቸውን እንዲያሳካ ታስቦ የተከናወነ ነበር ማለት ይቻላል። ኪነ ሕንጻውን በትውፊት ደግፈውታል። ‹‹…ገድለ ቅዱስ ላሊበላ ወደ ቤተክርስቲያንህም የገሰገሰ ሁሉ ወደ መቃብሬ እንደገሰገሰ ይሆናል የሚል ቃልኪዳን ከኢየሱስ ለቅዱስ ላሊበላ ይተላለፋል፡፡ …ሥጋህ የተቀበረበት መቃብርህንም እጅ የነሳ ሥጋዬን የተቀበረባትን እጅ እንደነሳን ይሁን’ ይሄስ? ቀጥታ የኢየሩሳሌም ወራሽነት በሮሃ አካባቢ ተከናውኗል ማለት ይቻላል›› (ሐሰተኛው በእውነት ስም ገጽ 296-297)፡፡

በሁለተኝነት በሰላም የሥልጣን ብቻ ሳይሆን የስርወ መንግሥት ወይም የርዕዮተ ዓለም ሽግግር የተደረገበትን ሒደት ስናነሳ፣ ‹‹የኢትዮጵያን መንግሥት የወሰዳችሁት በማይገባ መልኩ ነውና አሁንም ለሚገባው ለይኩኖ አምላክ መልሱ›› በማለት በግልጽ ነገሩት፡፡ እርሱም መንፈሳዊ ሰው ስለሆነ የአቡነ ተክለሃይማኖትን ቃል እንዳይተላለፍ ፈርቶ እሺ እለቃለሁ፣ ነገር ግን የእኔ ዘመን ካበቃ በኋላ በውል ነው የምለቀው አላቸው (በጀምስ ብሩስ በተጻፈው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ስድስት ውሎችን አስቀምጧል)፡፡ አቡነ ተክለሃይማኖት ይህንን ውል አዋውለው መንግሥቱን ከላስታ ወደሸዋ፣ ከዛጉዬ ወደ ሰለሞናዊው ዘር፣ ከነአኩቶለአብ ወደ ይኩኖአምላክ እንዲዘዋወር አደረጉ ‹‹የኢትዮጵያ የአምስት ሺሕ ታሪክ ከኖኅ እስከ ኢሕአዴግ፣ መጽሐፍ 1፣ በፍሥሐ ያዜ ካሣ፣ ገጽ 220 -221)፡፡

ከዚህ በመነሳት ኢትዮጵያዊው መሲህ የሞተበት ምክንያት የማኅበረ ላሊበላ ውጥን መሆኑንና የንጉሡም የመቅላት ፍርድ አገሪቱን ከውጭ ወደ ውስጥ የመመልከት አባዜ እንደነበር እንረዳለን፡፡ የኢትዮጵያ ትንሳዔ የሚባል ሃይማኖት ቢመሠረት ኢየሱሱ ያ አንገቱ የተቀላው ኢትዮጵያዊው ጥቁር መሲህ ይሆን እንደነበር ጥርጥር የለውም፡፡

በአጠቃላይ በኢቦኒ መጽሔት ተቀንቅኖ ጥቁር ወጣቶች የተከተሉትም፣ በኢትዮጵያዊ መሲህ ይሁን በማኅበረ ላሊበላ የተከናወነው ውጥን አንድነቱን ስንመለከት፣ ከተፅዕኖ ተላቀን እኛን የሚመስል መንግሥታዊም ይሁን ሃይማኖታዊ አስተዳደር ይኑረን የሚል መሆኑ እንረዳለን፡፡ ልዩነቱ ደግሞ፣ ዛሬ ድረስ በጥቁር አፍሪካውያንና በካሪቢያን ወጣቶች የሚቀነቀነው ሐሳብ አንደኛ በተቋማዊ ቅርጽ ወይም በማኅበር ደረጃ ከመቅረብ ይልቅ የተናጠል አካሄድን መምረጣቸው አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ባሉ የጥቁር ሕዝብ መኖሪያዎች ውስጥ የትምህርት ሥርዓቱም ፊት ያዞረበት፣ የፖሊሲ ማዕቀፍ ድጋፍም ያላገኘና በመሪዎች ደረጃ ትኩረት የተነፈገው መሆኑ ነው፡፡ ሆኖም በአገው ሥርወ መንግሥቱ ወቅት የነበረው እንቅስቃሴ አንደኛ በማኅበር የተዋቀረ ነው፡፡ ሁለተኛውና ዋነኛው መንግሥታዊ ድጋፉ (የመንግሥት ዋነኛ ግብር የሆነው የማስተባበር ሥራ) የለውጥ ሐዋርያቱን ማዕከል ያደረገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዳግማዊ ኢየሩሳሌምን በኢትዮጵያ አምሳል ሲታነጽ አሻራቸውን እስኪያስቀምጡበት ድረስ ዕድል የሰጠ ነበር።

‹‹በፈረንሳይ አገር ከአብዮት በኋላ በ1790ዎቹ፣ በአገሪቱ በመከባበሩ ዕሴት ፈንታ እርስ በርስ መገዳደል ለመበራከቱና ባልተገባ መልኩ በደቦ ፍርድ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለመፈጸሙ (የወል እብደት ወይም Collective Madness ተብሎ ይጠሩታል) መነሻ ምክንያት፣ የቀደሞ አስተሳሰብ ሙሉ በሙሉ ስህተትና ኋላ ቀርነት ተደርጎ በመቁጠር ከሥሩ ነቅሎ በአዲስ ለመተካት በመሞከሩና ከትላንቱንም፣ ከአዲሱም ያልሆነ ትውልድ በመፈጠሩ ነው›› (Reflections on The Revolution in France፣ በኤድመንድ ቡርክ)፡፡

አዲስ ነገርን ልናስተናግድበት ስለሚገባው አስገዳጅ ምክንያትን፣ የመሠላል ዓይነት ምሳሌ አቅርበው ያስገነዘቡት እጓለ ገብረ ዮሐንስ ‹‹የመጀመሪያው ሳይረገጥ ሁለተኛው ላይ አይወጣም፣ የመጀመሪያው ላይ ግን ቆሞ መቅረት የሚፈልግ ስለሌለ ወደ ሁለተኛው ይሻገራል፡፡ ስለዚህ ወደላይ ለመውጣት የመጀመሪያውም የሁለተኛውም አስፈላጊ ናቸው፤››  (የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ)፡፡

የኢትዮጵያን ዛሬ የደረስንበትን ውጥንቅጥ የወል ዕብደት (collective madness) በሚል ከመበየን አንስቶ፣ ለውጥንቅጡ መንስዔ የሆነው ጉዳይ፣ ከፈረንሣይ አብዮት ማግስት ጋር ተያይዞ ከተነሳው ሐሳብ አያፈነግጥም፡፡ መፍትሔው ደግሞ ሊቁ እጓለ እንዳሉት፡- ታዲያ የዛጉዬ ነባሩን አጽንቶ፣ አዲሱን በመጨመር የማዋሃድ መንፈስና የሃይማኖት አባት ወይም የሽማግሌ ክብሩ ጣፋጩን ሥልጣን አሳልፎ እስኪሰጥ ሲያደርሰው ያየንበት መንገድ ዛሬ ለተመለከትነው የወል እብደት ከመከሰቱ በፊት ከሩቁ ይታደገን አልነበር? በፀባዩ ነባሩን ሳይነካ፣ አዲሱንም ተቀብሎ ያዋህድ አልነበር? የኩሽ ባህልን ከክርስትናው አስማምቷልና አዲሱን የፕሮቴስታንት አስተሳሰብ ለመቀበል ሳያንገራግር፣ ነገር ግን ነባሩ ክርስትና ክርስትና እንዳልሆነ ሳይሰማው ከኦርቶዶክሳዊ አስተሳሰብ ጋር ብቻ ሳይሆን ከሌሎች ጥንታዊ አስተሳሰቦች ላይ ጨምሮ አያዋህደውም ነበር? ይታመንበትም አይታመንበትም በቅዱሳኑ ላይ የሚሳለቅ፣ አርበኛውን የሚያጣጥል አዲስ ሐሳብ ቀርፎ አይጥልልንም ነበር? የቅዱሳን (በእስልምናውም ከሽርክ በማይቆጠር መንገድ ዕውቅና ያላቸው ቅዱሳን አያሌ ናቸው) እና የአርበኝነት ታሪክ ሰዎች ለዓለማዊ ሕይወታቸውም ላመኑበት ነገር የሚከፈለውን መስዋትነትና ጽናት ያስገነዝበናልና ወደ ትምህርት ሥርዓቱ ከማምጣት ወደኋላ ይሉ ነበር? በየሃይማኖት ሥፍራ የሚገኙ ጥንታዊ የብራና ድርሳናት ሥራቸው እንዲማስና በዚህ መሠረት የሕክምናው፣ የትምህርት፣ የሳይንስና ሌሎች ዘርፋት እንዲዋቀሩ፣ የመድረሳው፣ የቄስ ትምህርት ቤቱ፣ የባህላዊው ሽምግልናው ተሞክሯቸው ተቀምሮ በዘመናዊ የትምህርትና የፍትሕ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ያስገድዱስ አልነበር? አገሬው በአገሩ ልሳንና መሣሪያ በመዘመር አያመሠግንም ነበር? የቅዱሳኑን ታሪክ ሰብስቦ 82ኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አድርገው ከመጨመር ይቦዝኑ ነበር? እንደውም በየዘመኑ ቅዱሳን መፍራታቸው ስለማይቀር ታሪካቸው እየተጨመረ የሚታደስ መጽሐፍ ቅዱስን ለማሰናዳት ዓይናቸውን ያሹ ነበር? ከእነሱ በቀር በኢትዮጵያ ውስጥ በእስክርቢቶ፣ በወረቀትና በሃይማኖት አባትና የአገር ሽማግሌ ሥልጣን የለቀቀ ማነው? የዛሬ ፖለቲከኞች መናከስና ጦር መስበቅ የመንፈሳዊ አባትና የአገር ሽማግሌ ግርማና ፋይዳ ለመረዳት መንፈሳዊ ኃይል ተገፈን፣ ግብዝ ሆነን ቆመን እንጂ እንደ አቡነ ተክለሃይማኖት ላሉ ሌሎች የሃይማኖት አባቶች (በየትኛውም ሃይማኖት) ይሁን ለአገር ሽማግሌዎች ያዳግት ነበር? ይህስ ለዛጉዌው መንፈስ ይሳነው ነበር?

የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ዛሬ ላይ በዓረቡ ዓለም ባህል ማጌጡና ልቡ ከኢትዮጵያ የመሸፈቱ መነሻ ‹‹ኢትዮጵያዊ ሆነን ከመንግሥታቱ በርካታ የዜግነት መብታችን መነፈጋችን ነው›› የሚል ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ከባህል ተኳርፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ የሸማ አልባሳትና እንጀራ የሙስሊም ባህል አይደለም እስከማለት የደረሱም፣ በኢትዮጵያ ኢስላማዊ መንግሥት እስካልተመሠረተ ድረስ አንረካም ያሉትንም አይተናል፡፡ የዛጉዌው መንፈስ ከኢየሩሳሌም መጥቶ መንፈሱን ግን እዚያው ያደረገውን ክርስትና ከሸፈተበት ተመልሶ ከአገራዊ አስተሳሰብ ጋር ለማስታረቅ ሞክረዋልና ለሙስሊሙ ቅራኔ መፍትሔ አበጅቶ ልቡን ወደ አገሩ ይመልስልን ነበር፡፡ በኢትዮጵያውያን የባህል ልብስ ጀለብያ፣ ጥምጣምና የመስገጃ ምንጣፍ አዘጋጅቶ ሲያመልክ እንመለከት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ሙስሊሙና ክርስቲያኑን የሚያስማማ አንድ የሥነ ምግባር ሰነድና የእምነት ተከታዮቹን ወጣቶች በአንድ ጉባዔ አሰናድቶ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያኑ ሁሉ በአገር ግንባታውም የየራሳችንን ሐሳብ በአንድ ላይ እንድናሳርፍ ሜዳውን ያመቻች ነበር።

ሐሳባቸው በኢትዮጵያ ውስጥ የሚስተዋሉትን የመክሸፍ ሥጋቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ይታደጋል፡፡ በአገራችን በሦስት ዓይነት መልኩ አሰላሳይ ሲከሽፍ ተመልክተናል፡፡ በ17ኛው ክፍለ ዘመን የነበረውና በአካል ባይተዋወቁም ከዘመኑ ከነበረው ዴካርት ጋር የተነጻጸረው ዘርዓያዕቆብ (ወርቄ) አምስቱም ስሜት ህዋሳቶቼ እውነታው ላይ አላደረሱኝም ያለውን ሐሳብ ለማንሸራሸርና በልቦናው ለመመርመር የቤተመንግሥትና የቤተክህነት ፍላጻውን ፈርቶ ለማሰብ የተገደደው በዋሻ ተሸሽጎ ነበር፡፡  ሐሳቡ እንኳን ጥሩ ወይም መጥፎ የሚለው እንዳለ ሆኖ ስለሱ ታሪክ እንኳን ያወቅነው ከተጣለበት ባነሱት ግለሰቦች አማካይነት ነበር፡፡ ዛሬ የፖለቲካ፣ የሃይማኖቱንና የማኅበረሰቡ ፍላጻ ፍራቻ ወይም የማሰቢያ ሥፍራ በመነፈጋቸው ጥግ ይዘው ለማሰብ የተገደዱ አያሌ ናቸው፡፡ የጥናት ሰነድ አዘጋጅተው ወደ አገር ተመልሰው የመተግበሪያ ወይም በቤተ ሙከራ አስመስክረው ለአገር ጥቅም እንዲውል የማድረጉ ሒደት የተዘጋባቸው አያሌ ፕሮፌሰሮች ይገኛሉ፡፡ የአገው መንግሥት መንፈስ ለዚህ መላ አለው፡፡ ጉዳዩ የሊቃውንቱ ሐሳብ ልክ ነው፣ አይደለም የሚለው ላይ ሳይሆን፣ ልክ ቆዳ ለፍቶ መልክ ያለው ጫማን እንደሚሠራ ሁሉ ሊቃውንቱ ሐሳባቸውን የሚያለፉበት የፋብሪካ አምሳል መድረክ አዘጋጅቶ ሐሳቦቹ ለፍተው መልኳ የተዋበ አገር መገንባቱ ላይ የሚያደርሰውን መልክ ማሲያዝ ያውቁበት ነበር።

ሌላው ዋሻ ሳይገቡ በግልጽ ምዕናባቸውን ያሳዩን አያሌ ሊቃውንት ሥፍራ አጥተው በፌዝና በዋዛ ዘመናቸውን እንዲገፉ ተገደዋል፡፡ አለቃ ገብረሃና ተገኝ ደስታ በፌዝ ብናውቃቸውም ትልቅ የቤተክርስቲያን ሊቅ እንደሆኑና በርካታ አበርክቶ እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በቅኔያቸው የምድሩን ጨርሰው ‹‹ጠላታችሁን ውደዱ ትላለህ፣ አንተ ግን ጠላትህን ሲኦል ትከታለህ›› እስከማለት እንደደረሱም አድምጠናል፡፡ በተለይ የአለቃ ዓይነት ሐሳብ ያላቸው ሊቃውንት ማስተባበሩን ለሚያውቅበት ዛጉዌ ተስማሚ ናቸው፡፡

አንድ የቅኔ ተማሪያቸው ወደ አለቃ መጥቶ ‹‹የኔታ የክርስቶስ መቃብር ወደሆነው ጎሎጎታ ልሄድ ተነስቼ፣ የመጣሁት ልሰናበቶት ነው›› ይላቸዋል፡፡ እሳቸውም ‹‹ባለፈው ቅዱስ ሥጋውን ተቀበልኩ አላልከኝም እንዴ›› ይሉታል ‹‹አዎን›› ዳቆኑ መለሰ፡፡ አለቃ ሆዱን ገልጠው ሳሙት፡፡ ይህም ማለት ‹‹ከቆረብክ መቃብሩማ አንተነህ፡፡ ከአንተ ቢያልፍ ደግሞ እዚሁ ላሊበላ ጎሎጎታ አለልህ›› እንደማለት መሆኑን ስንረዳ የዛጉዌው መንፈስ እንደሰፈነባቸው እናያለን፡፡ ሆኖም አለቃ ወደ ቤተክህነት ማስጠጋት ይቅርና ሳይገደሉ በሕይወት የታደጓቸውም በዘመናቸው የነበሩ ነገሥታት ናቸው፡፡ እኛም የምናውቀው ከገንቢ አገራዊ ሐሳባቸው ይልቅ በፌዛቸው ነው፡፡ የሕይወት ታሪካቸውም ቢሆን ‹‹አለቃ ገብረሃናና አስቂኝ ቀልዶቻቸው›› በሚል በአረፈዓይኔ ሐጎስ በተጻፈች 80 ገጽ መጽሐፍ ተወስና የምትገኝ ናት፡፡ አያሌ አለቃ ገብረሃናዎች ተገቢውን ሥፍራ በማጣታቸው ያለንበት ዘመን ድረስ ሲከሽፉ ተመልክተናል፡፡

ኢትዮጵያዊ  ለአገሩ ሲያስብ የሚጠብቀውን ውጣ ውረድና መጨረሻ ለማሳየት አቤ ጉበኛ ‹‹አልወለድም›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ በመላው አገሩ የዴሞክራሲ ቅንጣቶች ተዳርሰው ለማየት የወደደ አንድ የ54 ዓመት ሰው ባደረገው ትግል እንደ እብድ፤ ኋላም እንደ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ሞት ይፈረድበታል:: ኋላ ግን ሞቱ አገር ለቆ በመውጣት እንዲቀየርለት አማራጭ ቢቀርብለትም ስለ መላው አገሩ ነፃነት እንጂ ራሱን ነፃ ለማውጣት እንዳልታገለ በመግለፅ በአገሩ የሞቱን ፅዋ ለመቅመስ ሲመርጥ ያሳየናል፡፡ ያኛው የአገዎቹ መንፈስ ለዚህ የሚሆን ማርከሻ መድኃኒት ነበረው።

በአጠቃላይ ትላት ይሁን ነገ የምዕናብ ነገሥታቶቼ ከ1143 እስከ 1262 ዓ.ም. የነበሩትን ኩሾች መንፈስ የተዋረሱ ናቸው፡፡ በመንፈስም የኩሽ ዘር ነኝ።

እናቶች ጠላ ሲነፍስበት፣ ኃይሉን፣ መዓዛውንና መልኩን ሲያጣ ‹‹ማላስ›› ብለው በሚጠሩት መፍትሔያቸው አማካይነት ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርጉታል፡፡ የነፈሰበትን ጠላ ላይ፣ በኃይሉ በመልኩና በመዓዛው ሁነኛ የሆነ ድፍድፍ አምጥተው ያልሱታል ወይም ያዋዙታል፡፡ በዚህ መንገድ ወደቀደመ ኃይሉ መልኩና መዓዛው እንዲመለስ ያደርጉታል፡፡ ኃይሉን፣ መልኩንና መዓዛውን ላጣው ኢትዮጵያዊነትና በውጤቱም ለተፈጠረው የወል እብደት የዛጉዌ ሥርወ መንግሥት አስተዳደር ድፍድፍ ጋር ልናልሰው ወይም ልናዋዛውና ወደነባር ይዞታው ልንመልሰው ይገባናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው habeshaw2022@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles