የአደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን ለማከናወን የቻይናው ድርጅት የጠየቀው የግንባታውን ሦስት እጥፍ ክፍያ ተቀባይነት አለማግኘቱን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በቻይና ኮንስትራክሽንና ዲዛይን ኮርፖሬሽን የሚገነባው አደይ አበባ ስታዲየም ግንባታን ለማከናወን በዓለም አቀፍ ገበያ የግንባታ ዕቃዎች በመጨመሩ የዋጋ ማስተካከያ ተጠይቋል ፡፡
ድርጅቱ የጠየቀው ዋጋ ከሁለት እስከ ሦስት እጥፍ ተጨማሪ እንዲከፈለው ሲሆን፣ ይህን መክፈል ማለት የግንባታውን ውል እንደ አዲስ መፈረም ስለሆነ አግባብ አይደለም ሲሉ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ቀጀላ መርዳሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹ድርጅቱ ማቅረብ የሚገባው የዓለም አቀፍ ገበያ በሚጠይቀው ዋጋ መሠረት እንጂ ያልተሰላ ዋጋ ማቅረብ አይችልም፡፡ በተጨማሪም በወቅቱ በተካተቱ የግንባታ ዕቃዎች ላይ በሙሉ ማስተካከያ ከተደረገላቸው መካተት የማይገባቸው ዕቃዎች ሊካተቱ ይችላሉ፤›› ሲሉ አቶ ቀጀላ ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም ይህንን ጉዳይ ከገንዘብ ሚኒስትር ጋር በመሆን ለድርጅቱ ማስታወቁን ገልጸው እስከ ሦስት እጥፍ የተጠየቀውን ማስተካከያ መቀበል ሕገወጥ ነው ብለዋል፡፡
ከድርጅቱ ጋር እየተደረገ ያለው ንግግር በርካታ ቴክኒካል ጉዳይ ያለበት ነው፡፡
በመሆኑም ድርጅቱ አትራፊ ስለሆነ የኢትዮጵያ መንግሥት በደንብ በመከራከር የአገርን ጥቅም በማስጠበቅ ያለአግባብ ወጪ እንዳይወጣ ማደረግ እንደሚገባ አቶ ቀጀላ ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት መክፈል ከሚችለው በላይ የውጭ ምንዛሪ በመጠየቁ ኢኤምኤች በተባለ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱን የሚወክለው አማካሪ ድርጅት አማካይነት ምክክር እየተደረገ ነው፡፡
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግባትን ተከትሎ የዓለም አቀፍ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ በመጨመሩ ምክንያት የአደይ አበባ ስታዲየም ኮንትራክተሮች በአዲሱ የገበያ ዋጋ ተስተካክሎ እንዲከፈላቸው የጠየቁት የተጋነነ ዋጋ በመሆኑ ተስተካክሎ እንዲያቀርብ ተደርጓል፡፡
በዓለም አቀፍና አገራዊ ምክንያቶች የተነሳ በኮንስትራክሽን ግብዓቶች ላይ የተፈጠረን የዋጋ ንረት ለማስተካከል ሲባል፣ ውላቸው ላይ የዋጋ ማስተካከያን ያላካተቱ የመንግሥት የግንባታ ፕሮጀክቶች፣ ከኮንትራክተሮች ጋር ያለውን ውል ለማሻሻል በወጣው መመርያ መሠረት ይሠራል ተብሏል፡፡
እንደ አቶ ቀጀላ ገለጻ ባለፉት ዓመታት በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በአገር ውስጥም ከፍተኛ የዋጋ ንረት መታየቱን ገልጸዋል፡፡
እንደ ሲሚንቶ፣ ብረት፣ ነዳጅ፣ ሴራሚክና የመሳሰሉ ስምንት ዋነኛ ግብዓቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ ማስተካከያ የሚደረግባቸው የግንባታ ዕቃዎች ናቸው፡፡
የዋጋ ማስተካከያው ተሠርቶ እስከሚቀርብ ድረስ ግንባታው ሥራ አቁሟል የሚለው መረጃ ሐሰት መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ ግንባታው ቀስ በቀስም ቢሆንም እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ከስድስት ዓመት በፊት በ2.47 ቢሊየን ብር ሊገነባ የታቀደው ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም ግንባታ በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል፡፡ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ሲጀመር በነበረበት ወቅት ኮቪድ-19 በመግባቱና ለድርጅቱ የሚከፈል የቅድመ ክፍያ የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ ባለመከፈሉ እንዲዘገይ አድርጎት ነበር፡፡