Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፈቃዳቸው ተሰርዟል የተባሉ ማዕድን ላኪዎች ከነገ ጀምሮ ሥራቸውን ይቀጥላሉ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከፊ ጎልድና ፖሊ ጂሲኤል ፈቃዳቸው ለአንድ ወር ተራዘመ

ከሳምንት በፊት በማዕድን ሚኒስትሩ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ፈቃዳቸው መሰረዙ ይፋ የተደረገው 850 ማዕድን ላኪዎች እንደ አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ከሚኒስቴሩ መውሰድ በመጀመራቸው፣ ከሰኞ ሰኔ 27 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ማዕድን መላክ እንደሚጀምሩ የማዕድን ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ማዕድን ላኪዎቹ አዲስ የብቃት ማረጋገጫ ሲወስዱ ከዚህ በፊት ሲጠየቁ የነበሩትን እንደ የማዕድን መለያ መሣሪያ፣ የቢሮ ኪራይና በዘርፉ ላይ ልምድ ያለው ጂኦሎጂስትና የመሳሰሉትን ቅድመ ሁኔታዎች እንደማይጠየቁ ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ ሚኒስትሩ ታከለ (ኢንጂነር) ከወርቅ ውጪ ያሉት የማዕድን ላኪዎች የብቃት ማረጋገጫ ለማግኘት የሚያስፈልጋቸው ሙሉ ስማቸውንና በዓመት ውስጥ ሊልኩ ያቀዱትን የማዕድን መጠን ማስመዝገብ ብቻ መሆኑን፣ ዓርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ከላኪዎቹ ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት ገልጸዋል፡፡

ላኪዎቹ ከዚህ ቀደም ይልኩ የነበሩትን የማዕድን መጠን በወር ከፋፍለው በዓመት ድምሩን ያሳውቁና አፈጻጸማቸውንም በዓመት ለሚኒስቴሩ ያቀርቡ ነበር፡፡ አሁን ግን አፈጻጸማቸውን በየሦስት ወራት ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይኼንን በማሟላትም ካለፈው ሳምንት ሰኞ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ከ100 በላይ ላኪዎች አዲስ የብቃት ማረጋገጫ መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ሚኒስቴሩ ባለፈቃዶች ማዕድን ሲልኩ ያጋጥማቸውን የአሠራር ሒደቶች ላይ ማሻሻያ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ ከዚህ ቀደም ባለፈቃዶቹ የሚልኩት ማዕድን ደረጃና መሸጫ ዋጋ ይወሰንላቸው የነበረው በሚኒስቴሩ ሲሆን፣ አሁን ይኼ አሠራር ቀርቶ የግብይት ሥርዓቱ በገበያው ዋጋ እንዲመራ ተወስኖላቸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ላኪዎች የሚያመጡት ማዕድን በሚኒስቴሩ ደረጃ ወጥቶለትና ዋጋው ተወስኖ ከታሸገ በኋላ፣ ወደ ኤርፖርት የሚጓጓዘው በላኪዎቹ ሳይሆን በሚኒስቴሩ ነበር፡፡ ማዕድን አውጪዎች ማዕድናቸው ከታሸገ በኋላ ሚኒስቴሩ ዘንድ ጥለው ሲሄዱ፣ ሊጠፋ ይችላል የሚል ሥጋት ይገጥማቸው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

አሁን ይኼ አሠራር ተነስቶ ላኪዎቹ ማዕድኑ ከታሸገ በኋላ ራሳቸው እንዲወስዱት፣ ሚኒስቴሩም ኤርፖርት በሚመድባቸው ባለሙያዎች ብቻ ታይቶ እንዲያልፍ እንደተደረገ ታከለ (ኢንጂነር) ተናግረዋል፡፡

ሚኒስትሩ ሰኔ 15 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ 972 በማዕድን ምርመራ ምርትና ኤክስፖርት የተሰማሩ ድርጅቶችን ፈቃድ መሰረዙን አስታውቀው ነበር፡፡ ከ972 ባለፈቃዶች ውስጥ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት የማዕድን ላኪዎች ሲሆኑ፣ ፈቃዳቸው ተሰርዟል የተባሉት 850 ላኪዎች ነበሩ፡፡

ሚኒስቴሩ የማዕድን ላኪዎቹ ፈቃድ የተሰረዘበትን ምክንያት ሲገልጽ፣ ፈቃዳቸውን ሽፋን በማድረግ በሕገወጥ የማዕድናት ግብይት ላይ መሳተፋቸውን በዋነኛ ምክንያትነት ጠቅሷል፡፡

ይሁንና ይኼ በተገለጸ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ላኪዎቹ ማዕድን ለመላክ የሚያስፈልጋቸውን የብቃት ማረጋገጫ ከሚኒስቴሩ መውሰድ ጀምረዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ ኃላፊ፣ ላኪዎቹ ፈቃዳቸው ሲሰረዝ በማዕድን መላክ ሒደት ላይ የነበሩ እንዳሉ ገልጸው፣ በዚህም ምክንያት በአዲስ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ማዕድን እንዲልኩ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስትሩ ዓርብ ዕለት ከላኪዎቹ ጋር በነበራቸው ውይይት ላይ ስለፈቃድ መሰረዝ ጉዳይ ሲናገሩ፣ ‹‹ሪፎርም ስለሆነ አንዳንዱን ካንስል እያደረጉ፣ አንዳንዱን እየሰረዙ፣ አንዳንዱን ደግሞ እየደለሉ ካልሆነ በስተቀር አይመጣም፤›› ብለዋል፡፡

ማዕድን ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት በነበረው መግለጫ የ850 ላኪዎች ፈቃድ መሰረዙን ቢገልጽም፣ ሪፖርተር በውይይቱ ላይ ያነጋገራቸው ማዕድን ላኪዎች ከመግለጫው በፊትም ሆነ በኋላ ፈቃዳቸው መሰረዙን የሚገልጽ ደብዳቤ እንዳልደረሳቸው አስታውቀዋል፡፡ ላኪዎቹ የማዕድን ላኪነት ፈቃድ የወሰዱት አሁን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከሚባለው መሥሪያ ቤት መሆኑን ገልጸው፣ ፈቃዳቸው የመሰረዙ ጉዳይ በማዕድን ሚኒስቴር መገለጹ ግርታ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል፡፡

ጥር 2014 ዓ.ም. በነጋሪት ጋዜጣ የታተመው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባር መወሰኛ አዋጅ፣ በአንቀጽ 23 ንዑስ አንቀጽ አንድ የማዕድን ሚኒስቴርን ሥልጣንና ተግባራት ዘርዝሯል፡፡ የዚህ ንዑስ አንቀጽ ላይ ሚኒስቴሩ በማዕድን፣ በጂኦተርማል፣ በነዳጅና በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ልማት ለሚሰማሩ፣ እንዲሁም የማዕድን ግብዓቶችን ተጠቅመው የኢንዱስትሪ ውጤቶችን ለሚያመርቱ ባለሀብቶች ፈቃድ እንደሚሰጥ ከመግለጽ ውጪ፣ በሚኒስቴሩ ስለሚሰጥ የማዕድን ላኪነት ፈቃድ አልተጠቀሰም፡፡

ይሁንና ላኪዎቹ እንደሚገልጹት፣ በሚኒስቴሩ የሚሰጣቸው የላኪነት ብቃት ማረጋገጫ ከተሰረዘ ማዕድን ለመላክ አይችሉም፡፡ አሁን ከሚኒስቴሩ እንደ አዲስ እያወጡ ያሉትም ይኼንን ማረጋገጫ ነው፡፡

ከሳምንት በፊት በነበረው መግለጫ በምሥራቅ ወለጋ በቱሉ ካፒ የሚገኘውን የወርቅ ክምችት ለማወጣት ፈቃድ የተሰጠው የብሪታኒያው ከፊ ጎልድና በኦጋዴን የተገኘውን የተፈጥሮ ጋዝ ለማልማት ፈቃድ የተሰጠው የቻይናው ፖሊ ጂሲኤል ኩባንያዎችን ጉዳይ ተነስቶ ነበር፡፡ መግለጫውን የሰጡት ታከለ (ኢንጂነር)፣ ኩባንያዎቹ የካፒታላቸውን 30 በመቶ በዝግ አካውንት እንዳላስቀመጡ ገልጸው፣ እስከ ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ይኼንን ካላደረጉ ፈቃዳቸው እንደሚሰረዝ አስታውቀዋል፡፡

ይሁንና ሚኒስቴሩ ዓርብ ሰኔ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ለሁለቱ ኩባንያዎች በጻፈው ደብዳቤ፣ የሁለቱን ኩባንያዎች ፈቃድ በአንድ ወር አራዝሟል፡፡

ሪፖርተር የተመለከተው ደብዳቤ እንደሚያሳየው፣ ከፊ ጎልድ ፈቃዱ የተራዘመለት ኩባንያው ማስገባት የነበረበትን የካፒታል ድርሻ ለማግኘት ያደረጋቸውን ሙከራዎችና ያለውን የፋይናንስ አቅም ገልጾ ለሚኒስቴሩ የጻፈውን ደብዳቤ ተከትሎ ነው፡፡ ከፊ ይኼንን ካፒታል ወደ ብሔራዊ ባንክ እስኪያስገባ ድረስም ቀነ ገደቡ በ30 ቀናት እንደተራዘመለት በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡

ለቻይናው ፖሊ ጂሲኤል የተጻፈው ደብዳቤ ደግሞ ቀነ ገደቡ የተራዘመለት ኩባንያው ያለውን የፋይናንስ አቅም ለማሳየት ለሚኒስቴሩ ያስገባቸውን ሰነዶች ምክንያት ሲሆን፣ ማዕድን ሚኒስቴር እነዚህን ሰነዶች መርምሮ ውሳኔ እስኪያሳልፍ ድረስ 30 ቀናት መጨመራቸው ተገልጿል፡፡

ይሁንና ሚኒስቴሩ ለሁለቱም ኩባንያዎች በጻፈው ደብዳቤ ቀነ ገደብ መራዘሙ፣ በቀጣይ ውሳኔው የኩባንያዎቹን ፈቃድ መሰረዝ አይችልም ማለት እንዳልሆነ አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች