Saturday, May 18, 2024

በካምፕ በሚገኙ የትግራይ ተወላጆች ላይ ወረርሽኝ መሰል በሽታ መከሰቱን ኢሰመኮ አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአፋር ክልል ሰመራና አጋቲና ካምፕ በሚገኙና የእንቅስቃሴ ገደብ በተጣለባቸው የትግራይ ተወላጆች ላይ ለሕይወት መጥፋት ጭምር ምክንያት የሆነ ወረርሽኝ መሰል በሽታ መከሰቱን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡

ኢሰመኮ በተለይ ሕጻናት ላይ ጎልቶ የወጣው ይኼ ተላላፊ በሽታ ወደ አዋቂዎችም እየተዛመተ መሆኑን አስታውቆ፣ በአሁኑ ሰዓት በክልሉ ካለው ሙቀት አንጻር በካምፑ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ሕይወት አደጋ ላይ መውደቁን ገልጿል፡፡ ነዋሪዎቹ ወረርሽኝ ባለበት በእነዚህ ካምፖች ውስጥ ሕክምና በተገቢው መንገድ ሳያገኙ እንዳይንቀሳቀሱም ገደብ ተጥሎባቸው መያዛቸው ኮሚሽኑን በእጅጉ እንዳሳሰበው በኢሰመኮ የአፋር፣ የትግራይ፣ የአዲስ አበባና የፌዴራል የክትትልና ምርመራ ሪጅናል ዳይሬክተር ሰላማዊት ግርማይ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ዳይሬክተሯ፣ ‹‹ፍራሽ የለም፡፡ ጆንያ ላይ ነው የሚያድሩት፡፡ ብዛታቸው እንዲጨናነቁ አድርጓቸዋል፣  እናትና አባት ተለያይተው መሆናቸውም የአዕምሮ ጭንቀት ይፈጥራል፤›› በማለት ሁኔታውን አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ የተከሰተውን ወረርሽኝ መሰል በሽታ ለማከም የሚያስችል በቂ የሕክምና አቅርቦት አለመኖሩን የገለጹት ሰላማዊት፣ ካምፕ ውስጥ ሕክምና ቢኖርም በቂ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ወደ ሌሎች ተቋማት ሄደው መታከም ያለባቸው ሕመምተኞችም ጭምር የእንቅስቃሴ ዕገዳ የተጣለባቸው መሆኑ፣ ነገሩን አሳሳቢ እንዳደረገው አስታውቀዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለጻ በአፋር ክልል ነዋሪ የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የሆኑት ከስምንት ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ወደ ካምፑ የመጡት ከታኅሳስ ወር አንስቶ ነው፡፡ ነዋሪቹ ወደ ካምፖቹ ሲመጡ ደኅንነታቸውን ማስጠበቅና በወንጀል የሚፈለጉም መኖራቸው በምክንያትነት መጠቀሱን አስረድተዋል፡፡ ይሁንና ነዋሪዎቹ እንዳይወጡ ዕገዳ ተጥሎባቸዋል፡፡

ኢሰመኮ ከግንቦት 15 እስከ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. በሁለቱ ካምፖች ላይ ያደረገውን ክትትል አስመልክቶ ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ በሰመራ ካምፕ ብቻ በበሽታ ሕይወታቸው ያለፉ ሰዎች ስለመኖራቸው መረዳቱን አስታውቋል፡፡

ኢሰመኮም በመግለጫው ካምፑ ውስጥ በወሊድ ወቅት ልጅ የሞተባት እናት መኖሯን፣ ቤተሰቦቿ የአዕምሮ መረበሽ ደርሶባታል በሚል በሰንሰለት አስረው ያስቀመጧት ወጣት ሴት፣ እስከ አሥር የሚደርሱ ከባድ ቁስል ያለባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ከነዋሪዎች መስማቱን አስታውቋል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) በካምፑ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎችን ሁኔታ፣ ‹‹በመጠለያ ጣቢያ ስም የተፈጸመ፣ በብሔር ማንነት ላይ የተመሠረተ ሕገወጥና የዘፈቀደ እስር›› በማለት የጠሩት ሲሆን ነዋሪዎቹ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -