Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናከቡና የሚገኘውን ዓመታዊ ገቢ በአምስት ዓመታት ውስጥ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል

ከቡና የሚገኘውን ዓመታዊ ገቢ በአምስት ዓመታት ውስጥ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ታቅዷል

ቀን:

ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ የደረሰውን የአገሪቱን ዓመታዊ የቡና ሽያጭ ገቢ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ ግብ መቀመጡን፣ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡

በቡናና ሻይ ባለሥልጣን ቴክኖሰርቭ በተባለ የጥናት ተቋምና በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ድጋፍ የተዘጋጀውን የቡና የ15 ዓመት ስትራቴጂ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የተዘጋጀው ስትራቴጂ ከምርት እስከ ግብይት ያለውን የአገሪቱን የቡና አሁናዊ እንቅስቃሴና በቀጣይ ዓመታት ከዘርፉ ሊገኝ የሚችለውን ውጤት የሚያመላክት መሆኑ ተገልጿል፡፡

በቡናና ሻይ ባለሥልጣን የግብዓት አቅርቦትና ጥራት ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ገዛኸኝ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከዚህ ቀደም በሥራ ላይ የነበረ ስትራቴጂ ቢኖርም፣ ከአጠቃላይ ግብርና ጋር ተዳብሎ ሲሠራበት ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም አቀፍ ሁኔታ አስገዳጅ በመሆኑ፣ ለቡና ራሱን የቻለ የቡና ስትራቴጂ ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል ብለዋል፡፡

- Advertisement -

አቶ ብርሃኑ የቡና ስትራቴጂው የዘርፉን ችግሮች በመለየት፣ በቀጣይ ዓመታት ሊደረስባቸው ይገባል ተብሎ ታሳቢ የተደረጉትን ግቦች ማካተቱን ገልጸዋል፡፡

የ15 ዓመት ስትራቴጂው በሦስት ምዕራፎች የተከፈለ ሲሆን፣ ስድስት ዓምዶች (ፒላሮች) አሉት፡፡ ምርምር (ሪሰርች)፣ ልማትና ኤክስቴንሺን፣ ምርት ዝግጅት፣ እሴት ጭማሮ፣ ግብይት፣ እንዲሁም ቀደም ሲል የተገለጹትን ለማስፈጸም የሚያስችለው የተቋማት አደረጃጀት የሚሉት ናቸው፡፡

ከስትራቴጂው ዓምዶች አንዱ የሆነው ልማት ሲታይ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በሔክታር የሚገኘው የቡና ምርት ከዓለም ጋር ሲገናኝ በጣም ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ካልተቻለ ሌሎቹን የስትራቴጂው ዓምዶች ማሳካት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡ ስለሆነም የተዘጋጀው ስትራቴጂ
ምርትን በተመለከተ አጽንኦት መስጠቱን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

በስትራቴጂው ከተቀመጡ ግቦች ውስጥ ከቡና ኤክስፖርት አገሪቱ ከአምስት ዓመታት በኋላ ዓመታዊ ገቢዋ 4.6 ቢሊዮን ዶላር ይደርሳል የሚል ዕቅድ የተቀመጠ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ አርሶ አደሩ ጋር የሚደርሰው ገቢ 3.6 ቢሊዮን ዶላር (80 በመቶ) ይሆናል የሚል ይገኝበታል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን በሦስት ምዕራፎች በተተለመው የ15 ዓመት ስትራቴጂ፣  በዚህ ወቅት ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን 470 ሺሕ ሜትሪክ ቶን ቡና ወደ 1.26 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን ለማድረስ እንደሚያግዝ ተገልጿል።

በዚህ ወቅት ከአንድ ሔክታር የሚገኘው የቡና ምርት ሰባት ኩንታል ሲሆን፣ እስከ 15 ዓመት ባለው የስትራቴጂው ትግበራ ጊዜ ውስጥ ከአንድ ሔክታር ማሳ 11.6 ኩንታል ወይም 1.1 ሜትሪክ ቶን ይገኛል የሚል ግብ ተቀምጧል ተብሏል፡፡

የተዘጋጀው ስትራቴጂ በዚህ ወቅት ይፋ ይደረግ እንጂ ከላዩ ላይ እየተቀነሰ ተግባራዊ መደረግ የጀመሩ የተለያዩ ተግባራት ሁለት ዓመታት ማስቆጠራቸውን፣ ኮቪድና የተለያዩ ምክንያቶች ስትራቴጂው በተዘጋጀበት ወቅት ይፋ እንዳይደረግ ዕክል ሆነው መቆየታቸውን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በተጠናቀቀው ሳምንት መጨረሻ የ15 ዓመት የቡና ስትራቴጂውን ይፋ ሲያደርግ ንግግር ያደረጉት የቡናና ሻይ ባለሥልጣን የገበያ ልማትና ቁጥጥር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሻፊ ዑመር፣ የተዘጋጀው የቡና የ15 ዓመት ስትራቴጂ  ዋና ዓላማ የኢትዮጵያን የቡና የወጪ ንግድ ገቢ ማሳደግና ከ85 በመቶ በላይ ምርት የሚያበረክቱትን በሚሊዮን የሚቆጠሩ አነስተኛ አርሶ አደሮች ገቢ ማሳደግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ስትራቴጂው ከምርምር፣ ከምርትና ኤክስቴንሽን፣ ከእሴት ጭማሪ፣ ከዝግጅትና ማቀነባበር፣ ከግብይትና የቡናን ዘርፍ ከማጠናከር ጋር የሚጣጣም በመሆኑ በአግባቡ ከተተገበረ ለሁሉም የዘርፉ ተዋናዮች የላቀ ጠቀሜታ እንደሚኖረው፣ እንዲሁም በርካታ ሥራዎችን ለማከናወን እንደሚያስችል አቶ ሻፊ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...