Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአገሪቱን ኢኮኖሚ እያደቀቀ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድና መፍትሔዎቹ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች የሚካሄዱ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳውና ችግሩም አሳሳቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ መሆኑ እየተገለጸ ነው፡፡ 

ከሕገወጥ ንግድና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሰሞኑን በተካሄደ የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለጸው የአገር ውስጥም ሆነ የውጭ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎች አገሪቱን ኢንዱስትሪ አልባ ወደ ማድረግ እያሸጋገረ መሆኑን ጭምር የሚያመለክት ነው፡፡ 

በውይይት መድረኩ ተናጋሪ ከነበሩ ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆኑት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ ግንኙነትና ስምምነት ዳይሬክተር አቶ ሙሴ ምንዳዬ ከገቢና ወጪ ንግድ ጋር የተያዘው ሕገወጥ ንግድ አሳሳቢ የሚባል መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

የችግሩን ግዝፈት ለማመለከት ምሳሌ ያደረጉት የቁም ከብት የወጪ ንግድን ነው፡፡ ሁለት ሚሊዮን የሚሆን የቀንድ ከብት በሕጋዊ መንገድ ኤክስፖርት ከተደረገ 20 ሚሊዮን የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ እንደሚሄድ ጥናቶች የሚያመለክቱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከቀንድ ከብት ሌላ የጥራጥሬ ምርቶችም በሕገወጥ መንገድ ከአገር እየወጡ ሲሆን፣ በገቢ ምርቶች ረገድም አብዛኞቹ የኢንዱስትሪ ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር እንደሚገቡ፣ በዚህም ሳቢያ የአገር ውስጥ አምራቾች እየተጎዱ እንደሆነ አቶ ሙሴ ጠቁመዋል። በመሆኑም ችግሩ አሳሳቢና ፈጣን መፍትሔ የሚያሻው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በመድረኩ ሌላ ተናጋሪ የነበሩት የማክሮ ኢኮኖሚው ባለሙያው አቶ አሚን አብደላ በበኩላቸው የሕገወጥ ንግድ የተለየዩ መገለጫዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰው አገሪቷ በሕገወጥ መንገድ በሚደረጉ ንግዶችና በገንዘብ ዝውውር ያጣችው የሀብት መጠን ከዓመት ዓመት እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ 

ኢትዮጵያ በአምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ 70 ቢሊዮን ዶላር በደረሰኝ ማጭበርበር እንደምታጣ ጥናቶች ያመላክታሉ ያሉት አቶ አሚን ይህም ከገቢና ወጪ ንግድ ሒደት ጋር ተያይዞ ዋጋን አሳንሶና ከፍ አድርጎ በማቅረብ በሚፈጸም ማጭበርበርና ገንዘብን በሕገወጥ መንገድ ከአገር በማሸሽ (በካፒታል ፍላይት) የሚታጣ እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የሳይበር (የበይነመረብ) ግብይትን በመጠቀም መንግሥት የማያውቃቸው ንግዶች እየተካሄዱ መሆኑን የተናገሩት የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ተደማምረው በአሁኑ ወቅት የሕገወጥ ንግዱ በሕጋዊ መንገድ ከሚካሄደው እየበለጠ መሄዱን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ በኮንትሮባንድ የሚገባውና የሚወጣው ብዛት ያለው ሲሆን በአንፃሩ ተያዘ የሚባለው ግን አነስተኛ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ 

የኮንትሮባንድ ንግድን የሚመለከት ጥናት ለማድረግ በተንቀሳቀሱበት ወቅት ቁጥጥሩ ጥቃቅን ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩር፣ ሦስት አራት ሸሚዝ ደርበው ለማለፍ በሚሞክሩት ላይ የሚበረታ መሆኑን እንዳስተዋሉ ተናግረዋል። በኮንቴነር የሚተላለፈውን ዋናውን የኮንትሮባንድ ንግድ ትኩረት እንዳላገኘና የኮንትሮባንድ ቁጥጥር ሥራው ችግር ያለበት መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣናና ኮሜሳ ውስጥ ብትገባ የአገር ውሰጥ ኢንዱስትሪዎች ይጎዳሉ የሚል ሥጋት እንደነበራቸው መለስ ብለው ያስታወሱት አቶ አሚን፣ አሁን ግን ኢትዮጵያን ኢንዱስትሪ አልባ ሊያደርጋት የሚችለው ትልቁ ሥጋት ኮንትሮባንድ እንደሆነ በመግለጽ የችግሩን አሳሳቢነት አመላክተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ በሚገቡ ተመሳሳይ ምርቶች ጋር መወዳደር አቅቷቸው እየተዘጉ መሆኑን ያስረዱት አቶ አሚን ኮንትሮባንድ በሁሉም ዘርፍ እየተስፋፋ መሄዱ በግልጽ እየታየ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ኮንትሮባንድ ከኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎችና ከመሳሰሉት አልፎ ወሳኝ የሚባሉ መድኃኒቶች ሳይቀር በኮንትሮባንድ እየገቡ መሆኑ ችግሩን ኢኮኖሚያዊ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ እያደረገው እንደሆነ፣ ጉዳቱም ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ወደ ማዳረስ እየተሸጋገረ መሆኑን አመልክተዋል።

አሁን ላይ በሕጋዊ መንገድ ከሚላከው የወጪ ንግድ ምርት ይልቅ በተለይ በአንዳንድ ዘርፍ ላይ በሕገወጥ መንገድ የሚገባው እየባሰ መምጣቱ ትልቅ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ አሚን፣ ይህም ሰዎች ሕጋዊ ሥነ ሥርዓትን ከመከተል ወደ ሕገወጥነት እያመዘኑ መሆኑን እንደሚያሳይ ገልጸዋል፡፡ 

በተለያዩ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖ የሚያመርተው የአገር ውስጥ አምራች በኮንትሮባንድ በሚገባውና በተሻለ ጥራትና በዝቅተኛ ዋጋ መሀል ከተማ ላይ እየተሸጠ በሚገኘው ምርት እየተንኮታኮተ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የአገር ውስጥ አምራች ጉዳት ውስጥ እየወደቀ ከሆነ በአገራዊ ኢኮኖሚው ላይም እያረፈ ያለው ተፅዕኖ ቀላል አይደለም ማለት እንደሆነ፣ በዚህ ሒደት መንግሥት ከፍተኛ የሚባል የታክስ ገቢ እያጣ መሆኑን ባለሙያው በማብራሪያቸው አመልክተዋል፡፡ 

የሕገወጥ መንገድ እንቅስቃሴ ሌላው መገለጫ ገንዘብ ከአገር ማሸሽ (ካፒታል ፍላይት) እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አሚን የኢትዮጵያ ካፒታል ፍላይት ከፍሪካ ከፍተኛው የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱንም ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም በባንክና በጥቁር ገበያው መካከል ያለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ልዩነት አንዱ ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አንድ ዶላር በባንክ 52 ብር ሲመነዘር፣ በጥቁር ገበያ ከ82 ብር በላይ ደርሷል፡፡ እንደየአገሩ ሁኔታም የምንዛሪ ዋጋው እንደሚለያይ የጠቆሙት የኢኮኖሚ ባለሙያው በቱርክ ላይ አንድ ዶላር 110 ብር ይመነዘራል መባሉን መስማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የግል ዘርፍ ከሕገወጥ ንግድ ጋር በተያያዘ ምን ተሳትፎ አለው? ምንስ ይጎዳዋል ምንስ ይጠቅመዋል? እንዲሁም ምንስ መደረግ አለበት በሚሉት ጭብጦች ላይ ማብራሪያ የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ዮሐንስ ወልደ ገብርኤል ደግሞ ሕገጥ ንግድ ሕገወጥ ዕቃዎችን ብቻ የሚመለከት ሳይሆን የሞራል ደረጃ መገለጫም እንደሆነ ይገለጻሉ።

የሕገወጥ ንግዱ መነሻ ሞራል የጎደላቸው ነጋዴዎች በምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የሚፈጥሩት ሰው ሠራሽ የሆነ የአቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም መሆኑን አቶ ዮሐንስ ይጠቅሳሉ፡፡ እነዚህ ነጋዴዎች ሕጋዊ ነጋዴዎችም ሊሆኑ ይችላሉ ያሉት አቶ ዮሐንስ በአንድ አካባቢ የፍላጎትና የአቅርቦት አለመመጣጣን እንዲፈጠር አድርገው በሌላ በኩል አቅርቦቶችን ለማሟላት በኮንትሮባንድ ንግድ ውስጥ በመሳተፍ የተሻለ ጥቅም የሚያገኙበት ሁኔታ እየፈጠሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ፍላጎት ኖሮ የምርት አቅርቦት ሲጓደል ሸማች ዕቃውን ስለማግኘቱ እንጂ በሕገወጥ መንገድ የገባ ስለመሆኑ ወይም ስለዋጋው እንደማይጨነቅ ገልጸዋል። ይህ ዓይነቱን ሁኔታ በመፍጠር ሕገወጥ ንግዶች እየተበራከቱ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፣ በዚህ ውስጥም ሙሰኛ ባለሥልጣኖች ተሳትፎ እንዳላቸው አመልክተዋል። ሙሰኛ ባለሥልጣናት የሚሰጡት ድጋፍና ሽፋን ችግሩን እያባባሰው ነው ብለዋል፡፡ በፈቃድ አሰጣጥ ላይ፣ በድንበር ጥበቃ ላይ፣ በግብር አከፋፈልና የመሳሰሉት ላይ የሚታየውን ችግር የሚፈጥሩት ሙሰኛ ባለሥልጣናት እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ እነዚህ ባለሥልጣናት በሚፈጥሩት የተመቻቸ ሁኔታ ሕገወጥና ኢሞራላዊ ንግዶች እየተስፋፋ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ሕገወጥም ሆነ ኢሞራላዊ ድርጊቶችን የሚቆጣጠረው መንግሥት በመሆኑ፣ መንግሥት ታማኝነት ባለቸው፣ ከሙስና በፀዱና አቅም ባላቸው ባለሥልጣናት መደራጀት አለበት ብለዋል። ይህ ካልሆነ ሕገወጥ ተግባራት በቀላሉ እንዲስፋፋ ዕድል የሚሰጥ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ሌላው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት በዕቃዎች ላይ የሚጣሉ ከፍተኛ የታሪፍ ጫናዎች እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ዮሐንስ፣ ይህ ጫና ሕገወጥና ኢሞራላዊ ነጋዴዎችን ወደ ኮንትሮባንድ ንግድ እንዲገቡ የሚገፋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ሙሴ በበኩላቸው ለሕገወጥ ንግድ መስፋፋት በዋነኝነት የሚጠቀሰው በድንበሮች አካባቢ ያለው የማኔጅመንት ችግር እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹እውነት ለመናገር በጣም በሙስና የተዘፈቀ የጠረፍ አካባቢ አስተዳደር ነው ያለን፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፤›› በማለት ይህንን መፍታት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

ለሕገወጥ ንግዱ መስፋፋት ሌላው ምክንያት ተደርጎ በአቶ ሙሴ የተለገጸው ጉዳይ በአንድ ወደብ ላይ የተመሠረተው አገልግሎትና አማራጭ ተብለው የሚታሰቡት ወደቦች በአብዛኛው ለሕገወጥ ንግድ የተጋለጡ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በርበራ ወደብ በሕጋዊ መንገድ የሚመጣው ምርት በጣም ውስን እንደሆነና አብዛኛው በሕገወጥ መንገድ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ለዚህም በጎረቤት አገሮች ያለው ሰላም ጥሩ አለመሆን እንዲሁም በንግድ ስምምነት አለመታሠራችን ሕገወጥ ንግዱ እንዲሰፋ አድርጓል፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

ከኬንያ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት እንደሌለ የጠቆሙት አቶ ሙሴ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ንግድን መሠረት ያደረገ ስምምነት (ስፔሻል ስታተስ አግሪመንት) ቢኖርም እየተተገበረ ባለመሆኑ ለችግሩ መስፋፋት ሊጠቀስ የሚችል አንድ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ 

በተመሳሳይ ከሶማልያ ጋር ምንም ዓይነት ስምምነት አለመኖሩ፣ በአጠቃላይ መሬት ላይ የወረደ ሕጋዊ ስምምነት ከአገሮቹ ጋር አለመደረጉ ሕገወጥ ንግዱን መቆጣጠር ከባድ እንዳደረገው የአቶ ሙሴ ማብራሪያ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ የድንበር አስተዳደርም ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነፃፀር በጣም ደከም ያለ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሙሴ የኬንያን ልምድ ከኢትዮጵያ የተሻለ ሆኖ መገኘቱን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ የኮንትሮባንድ ንግዱን በተገቢው ደረጃ ለመቆጣጠር አዳጋች አድርገዋል ተብለው ከተጠቀሱት ሌሎች ችግሮች መካከል የኢትዮጵያ ድንበር ሥፋትና የመሠረተ ልማት ውስንነት ይገኙበታል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ለዚህ ችግር መፍትሔ ለመስጠት የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ መሆኑን አቶ ሙሴ ገልጸው፣ በዋናነት ግን ችግሩን በቋሚነት ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት ከመፍጠር ይልቅ በዘመቻ መልክ የሚካሄድ ሰሞነኛ ተግባር መሆኑ ትልቅ ችግር እንደፈጠረ ገልጸዋል። 

ችግሩን ለመፍታት ከጽሑፍ አቅራቢዎቹ ከተሰነዘሩ ሐሳቦች መካከል አቶ አሚን ንግድ ሚኒስቴር ከተቋቋመ ጊዜ አንስቶ በየት በኩል ኮንትሮባንድ እንደሚገባ እየታወቀ ለዚህ መፍትሔ አለመስጠቱ በመሆኑ አንዱ መፍትሔ የመንግሥት ቁርጠኝነት ነው ብለዋል፡፡ ሙስና ኮንትሮባንድና ሕገወጥ ንግድ የተቆራኙ በመሆናቸው ይህን መዋጋት እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

እንደ አቶ አሚን ገለጻ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር ሌላው መፍትሔ የሚሆነው ኢንሳና ቴሌኮሙዩኒኬሽንን በመጠቀም የቁጥጥር ሥራ መሥራት ነው፡፡ ሕገወጥ የገንዘብና እያንዳንዱ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በአገር ውስጥም ይሁን የውጭ አጋር ስላለው ይህንን ያመቻቸው ማነው ብሎ ተገቢውን ዕርምጃ መውሰድ ይገባል ብለዋል፡፡ 

አሁን እየታየ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪ የሚጠይቅ ባይሆን ኖሮ አገሪቱ በኮንትሮባንድ ምርቶች ልትጥለቀለቅ ትችል እንደነበርም አንሰተዋል።

ሕገወጥነትን ለመቆጣጠር ትልቁ ችግር በኬላዎች አካባቢ የሚታዩ ሕገወጥ ተግባራት በመሆናቸው በእነዚህ ኬላዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መደረግ ይኖርበታል ብለው የጠቀሱት አንድ ኮንትሮባንድ አንድ ኬላ አልፎ ቢመጣና ሁለተኛው ላይ ቢያዝ በመጀመርያው ኬላ ላይ ያሉትን ተጠያቂ በማድረግ ዕርምጃ መወሰድ መፍትሔ ያመጣል ብለዋል፡፡ ይህንን ለማለት የደፈሩት የትኛውን ኬላ ላሳልፍልህ የሚባል ድርድር ስለመኖሩ በመስማታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በየኬላው ቡና ለማሳለፍ ገንዘብ የሚከፈል መሆኑንና እንደ ኬላው ዓይነት የሚከፈለው የገንዘብ መጠን የሚለያይ ስለመሆኑ የጠቆሙት አቶ አሚን፣ አንድ የኮንትሮባንድ ዕቃ ከየት ተነስቶ የት እንደደረሰ እንዲሁም አልፎ ሲመጣ ያሳለፈን ኬላ ተጠያቂ የሚያደረግ ሥርዓት መዘርጋት ችግሩን ሊያቃልል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ነገሮች የታወቁ ናቸውና ለችግሩ መፍትሔ የሚሆነው ግን የመንግሥት ቁርጠኛነት እንደሆነ ጽሑፍ አቅራቢዎቹ ይስማማሉ፡፡ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ሲገባም ሆነ ሲወጣ ሕገወጥ መንገድ መከተል አገሪቷ ያቀደችውን የልማት ዕቅድ የሚያሰነካክል በመሆኑ ችግሩ ትኩረት ሊሰጠው ይገባልም ተብሏል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች