Monday, May 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሕገወጥ የትምባሆ ምርት የገበያውን 62.7 በመቶ ተቆጣጥሯል ተባለ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ ከሚሸጠው የትምባሆ ምርት ውስጥ 62.7 በመቶ የሚሆነው በሕገወጥ መንገድ በሚገቡ የሲጋራ ምርቶች መሆኑንና ይህም መንግሥትን በዓመት ከ4.5 ቢሊዮን ብር በላይ እያሳጠ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአገሪቱን ብቸኛው የትምባሆ ፋብሪካን የገዛው የጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል እንዳስታወቀው ሕገወጥ የሲጋራ ንግድ ኩባንያውን እየተፈታተነ ከመሆኑም በላይ በሕገወጥ መንገድ የሚገባው ሲጋራ የገበያ ድርሻ ከዓመት ዓመት እየጨመረ መጥቷል፡፡

በሕገወጥ ንግድ በተለያዩ ዘርፎች እያስከተለ ያለውን ከፍተኛ ጉዳት በተመለከተ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝተው ማብራሪያ የሰጡት የጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል ተወካይ ወ/ሮ ሰላም ሳህሉ እንደገለጹት እ.ኤ.አ. በ2012 በሕገወጥ ሲጋራ የተሸፈነው የአገሪቱ ገበያ 38 በመቶ ነበር፡፡ ይህ መጠን በ2015 ወደ 44 በመቶ እንዲሁም በ2020 ደግሞ ወደ 51.1 በመቶ ከፍ ማለቱን ገልጸዋል፡፡ በ2021 በተደረገ ጥናት ደግሞ  በሕገወጥ የሲጋራ ንገድ የገበያ ድርሻ 62.7 በመቶ ሊደርስ መቻሉን ገልጸዋል፡፡ 

ይህም የአገሪቱ የሲጋራ ገበያን ያጥለቀለቀው በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባ ምርት መሆኑን የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡ በኩባንያውም ሆነ በመንግሥት ከሚታወቁት ስድስት ዓይነት የሲጋራ ምርቶች ሌላ ከ70 በላይ የሚሆኑ ሕገወጥ የሲጋራ ምርቶች በኢትዮጵያ ገበያ ውስጥ እንደ ልብ እየተቸበቸቡ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ይህም ሆኖ ግን ናሽናል ቶባኮ ከሕገወጥ የሲጋራ ገበያ በተረፈው የ37 በመቶ የገበያ ድርሻው ብቻ ለመንግሥት በዓመት 2.5 ቢሊዮን ብር ታክስ በመክፈል ከከፍተኛ የአገሪቱ ግብር ከፋዮች መካከል አንዱ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የኩባንያው የገበያ ድርሻው በየዓመቱ በማሽቆልቆሉ ምክንያት ተጎጂ የሆነው ኩባንያው ብቻ ሳይሆን አገርና መንግሥትም መሆኑን የጠቀሱት ወ/ሮ ሰላማዊት በዚሁ ሕገወጥ ተግባር መንግሥት በዓመት 4.5 ቢሊዮን ብር እያሳጣው መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ችግሩ የኩባንያውን አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየፈተነ በመሆኑ በየጊዜው የሠራተኞችን ቁጥር ለመቀነስ እየተገደደ መሆኑንም ወ/ሮ ሰላማዊት ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ 

በሕገወጥ ንግዶች ትልቁ ተጠቂ የቶባኮ ኢንዱስትሪ እንደሆነ ያመለከቱት ጽሑፍ አቅራቢዋ ይህ ኢንዱስትሪ ድጋፍ ሳይሆን ከፍተኛ ቁጥጥር የሚደረግበት ዘርፍ በመሆኑ ሕገወጥ የትምባሆ ምርት ንግድ ሕጋዊ የሆነውን አምራች ምን ያህል እንደጎዳውና አሳሳቢ ደረጃ ለይ እንደሆነ ለማስገንዘብ እንዳልተቻለ አመልክተዋል።

ሕገወጥ የሲጋራ ንግድ ዓለም አቀፋዊ ችግር ሲሆን፣ በዓለም ላይ ከሚሸጡ አሥር ሲጋራዎች አንዱ በሕገወጥ መንገድ የሚሸጥ ነው፡፡ ይሄ ማለት የሲጋራ ኩባንያዎች ከ40 እስከ 50 ቢሊዮን ዶላር በዓመት የሚያጡ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡ 

ብዙ ጊዜ የሕገወጥ ሲጋራ ንግድ ላይ የሚሳተፉት የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች እንደሆኑ የጠቀሱት ወ/ሮ ሰላማዊት፣ በተለይ ሽብርተኛ የሚባሉ ቡድኖች የሚተዳደሩት በሕገወጥ የሲጋራ ንግድ እንደሆነና ከነዚህም መካከል ኢትዮጵያ በምትገኝበት ቀጣና አልሸባብ ተጠቃሽ እንደሆነ ገልጸዋል።

በኮንትሮባንድ፣ አስመስሎ በመሥራትና ርካሽ የሆኑ ሲጋራዎችን ወደ አገር በሕገወጥ መንገድ ማስገባት ተስፋፍቶ የቀጠለ በመሆኑ ጉዳቱ በሕጋዊው የትምባሆ አምራች ኢንደስትሪ ላይ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ጠቅሰዋል። በአብዛኛው በሕገወጥ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ምርቶች የሚመጡት ከዩናይትድ ዓረብ ኤምሬትስ፣ ከየመንና ከኬንያ መሆኑም ተገልጿል። ሕገወጥ የትምባሆ ምርቶቹ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡትም በሶማሌ ላንድና በጂቡቲ ድንበር በኩል መሆኑን የወ/ሮ ሰላማዊት ገልጸዋል፡፡

‹‹እንደ ግል ኩባንያ ትልቁ ውድድራችን ከሕገወጥ ሲጋራ ጋር ነው፤›› ሲሉ ወ/ሮ ሰላማዊት ሁኔታውን ገልጸውታል። ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል በ2016/17 የኢትዮጵያ ትንባሆ ሞኖፖልን ሲገዛ የሞኖፖል (በብቸኝነት የማምረት) መብቱም አብሮ የተሸጠለት እንደሆነ ያስታወሱት ተናጋሪዋ ይህም የሲጋራ ምርትን ለመቆጣጠር በአንድ ድርጅት ቢመረት የተሻለ እንደሆነ ታምኖበት የተወሰደ ዕርምጃ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ ነገር ግን ከኩባንያቸው ቁጥጥር ውጭ የሆኑ ከ70 እና 80 በላይ ዓይነት የሲጋራ ምርቶች በሕገወጥ መንገድ ገበያ ላይ መገኘታቸው ለኩባንያው የተሰጠው መብት ባልተገባ መልኩ በኮንትሮባንዲስቶች እጅ እንደወደቀ ያሳያል ብለዋል፡፡ 

‹‹እኛ ሞራል ኖሮን ስለ ጤና ማውራት ባንችልም ግን በሕገወጥ መንገድ የሚገቡ ምርቶች ጉዳት እያስከተሉ ነው፤›› ያሉት ወ/ሮ ሰላማዊት ሕገወጥ ነጋዴዎቹ  አምርተው ከሚሸጡበት ዋጋ ከሦስት አራተኛ ባነሰ ዋጋ እሸጡ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም ሕጋዊው ኩባንያ ተጎጂ ሆኗል ብለዋል። 

በተለይም ኩባንያ በቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የገባ ስለሆነ መንግሥት ችግራቸውን እንዲመለከት፣ መንግሥትና የግል ዘርፉ አይጥና ድመት ሳይሆኑ በመነጋገር ችግሮችን ሊፈቱ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡ ‹‹ሁላችንም ለአንድ አገር ነው የምንሠራው፤›› በማለትም ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የወጡ ኩባንያዎችን በተመለከተ የመንግሥት ግዴታውን እየተወጣ አይደለም ብለዋል፡፡

ጃፓን ቶባኮ ኢንተርናሽናል በ2016/17 የኢትዮጵያ ትምባሆ ሞኖፖልን ከፍተኛውን ሼር በመግዛት ወደ ግል የተዛወረ ሲሆን፣ ለሽያጩ የተከፈለው አንድ ቢሊዮን ዶላር ሲከናወን በነበረው የመንግሥት ድርጅቶች ፕራይቬታይዜሽን ከፍተኛ ወጪ የወጣበት ኩባንያ ተደርጎም ይጠቀሳል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት 929 ቋሚ ሠራተኞች ያሉት ሲሆን፣ በትምባሆ ቅጠል በሚመረትባቸው የእርሻ ሥራዎች ላይ ደግሞ ከሰባት እስከ አሥር ሺሕ የሚደርሱ ሠራተኞች ተጠቃሚ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ለሲጋራ ምርቱ የሚሆኑ ግብዓቶችን የሚያመርትባቸው ስድስት እርሻዎች እንዳሉትም የኩባንያው መረጃ ያመልክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች