Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚታዩ የኦዲትና የሕግ ጥሰቶች በጥናት መመለስ አለባቸው›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌደራል ዋና ኦዲተር

ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የኦዲት ዘርፍ ምክትል ዋና ኦዲተር ከዚህ ቀደም በዋልታ ኢንፎርሜሽን፣ በበገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ እንዲሁም በዚሁ የዋና ኦዲተር ተቋም ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ተመድብ ሠርተዋል፡፡ የቀድሞው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ በ2013 ዓ.ም. በጡረታ ከተሰናበቱ በኋላ ከአንድ ዓመት በላይ ተቋሙን በበላይነት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ ግንቦት 26 ቀን 2014 ዓ.ም.  በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና ኦዲተር ሆነው ተሾመዋል፡፡ ወ/ሮ መሠረት አዲሱን ኃላፊነትና አጠቃላይ የኦዲት ሥራን በተመለከተ ሲሳይ ሳህሉ ጋር ያደረጉት ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡– ከዚህ ቀደም በዋልታ ኢንፎርሜሽን፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን እንዲሁም በዚሁ የዋና ኦዲተር ተቋም ለበርካታ ዓመታት በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ተመድበው ሠርተዋል፡፡ አሁን ደግሞ በቅርቡ የፌደራል ዋና ኦዲተር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተሹመዋል፡፡  ስላለፉበት የሥራ ጉዞና ስለ አዲሱ ኃላፊነት ይንገሩን?

ወ/ሮ መሠረት፡ጥሩ እንግዲህ፡፡ እኔ የመጀመሪያ ዲግሪዬ በአካውንቲንግ ስለሆነ እንደመታደል ሆኖ እስካሁን የሠራሁባቸው ተቋማት ከፋይናንስና ኦዲት ጋር የተገናኙ ናቸው፡፡ ፋይናንስና አስተዳደር፣ ጠቅላላ አገልግሎት ኃላፊ፣ እንዲሁም የፋይናንስ ዋና ክፍል ሆኜ በእነዚህ ዘርፎች ሠርቻለሁ፡፡ ስለዚህ ወደዚህ ተቋም ስመጣ ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ነገር ግን ዋናው ልምዴን መነሻ አድርጌ ወደዚህ ሥራ ስቀላቀል ራሴን የበለጠ በሥራው ለማሳደግና የአሁኑ ሥራም ሙሉ የኦዲት ሥራ በመሆኑና የራሱ የሆነ ዓለም አቀፍ መስፈርቶች ያሉት በመሆኑ እነሱን የግድ ማንበብና ማወቅ ነበረብኝ፡፡ ከእኔ በፊት በወቅቱ የነበሩት ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶም፣ እኔ ለዚህ ደረጃ እንድበቃ አስተዋጽኦ አድርገውልኛል ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላ በኩል ይህን ኃላፊነት ስቀበል ባለፉት አምስት ዓመታት ከአቶ ገመቹ ጋር በመሥራቴ በጣም ዕድለኛ ነኝ፡፡ ስለዚህ የነበረውን ሁኔታ ከሥር ከሥር በመከታተተል አቶ ገመቹም እየረዱኝ እዚህ ለመድረስ ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ የበለጠ ደግሞ አቶ ገመቹ ከዚህ ተቋም በጡረታ ከወጡበት ጊዜ ጀምሮ ለአንድ ዓመት ከአራት ወር ይህን ተቋም ብቻዬን ነበር የመራሁት፡፡ በዚህ ሒደት ብቻዬን የመራሁትን ተቋም ኃላፊነትና ሹመት ለመቀበል አልተቸገርኩም፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ከአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ምንም ሳይጎድል በተለይም ቀድሞ ከነበረው አፈጻጸም ምንም ባልጎደለ መልኩ ሥራዎችን በአግባቡ በነበሩበት ሒደት ማስቀጠል ችያለሁ፡፡ እንዲያውም ከዚህ ቀደም የምንታማባቸውን የአቅም ግንባታ ዘርፍ እስከ ክልል ድረስ ወርደን በርካታ ሥራዎችን ሠርተናል፡፡ ስለዚህ ለእኔ ያለፈው አንድ ዓመት የሥራ ጊዜ እንደ ጥሩ አጋጣሚ ያየሁትና ምናልባት ወደዚህ ሹመት እንድበቃ ያደረገኝ ያንን መሥራቴ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ ይህን ተቋም የመሩት ወንዶች ነበሩ፡፡ አሁን ላይ የመጀመሪያ ሴት ዋና ኦዲተር ሆነዋል፡፡ ይህን ሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቀበሉ ምን ተሰማዎት?

ወ/ሮ መሠረት፡በመሠረቱ ይህ ለእኔ ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከለውጥ በኋላ የመጣው መንግሥት ለሴቶች ልዩ ትኩረት ሰጥቷል ብዬ ነው የማስበው፡፡ አሁን የመንግሥት ካቢኔዎችን ስታይ አብዛኞዎቹ ሴቶች ናቸው፡፡ ከዚህ በፊት ባልተለመደ ሁኔታ ወደ ዴሞክራሲ ተቋማትም ስትሄድ ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ ዋና ኦዲተር፣ ምርጫ ቦርድ ሴቶች ነን፡፡ በሥራችንም ውጤታማ ነን፡፡ ስለዚህ ሴቶች በመሆናችን ለሥራው የበለጠ ጥሩ አጋጣሚ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ ለሴቶች ተፈጥሮ የሰጠችን ፀጋ አለ እሱን ጨምረን ወደ ኃላፊነት ስንወጣ ጥሩ መሥራት እንችላለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– ዋና ኦዲተር የአገር ሀብት እንዳይባክን የሚሠራው ሥራ በትልቁ የሚታይ ነው፡፡ እርስዎ የዋና ኦዲተርን የሥራ ድርሻ እንዴት ይገመግሙታል?

ወ/ሮ መሠረት፡በነገራችን ላይ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ትልቅ ሚና አለው፡፡ ትልቅም ኃላፊነት የተሰጠው ተቋምም ነው፡፡ በፓርላማው የፀደቀን በጀት ትክክለኛነቱን የሚያረጋግጠው ይህ ተቋም ነው፡፡ ሕግና ሥርዓቱን ተከትሎ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ አንፃር እኛ ሥራ ባንሠራ አሁን ከምናየውና ከሚባክነው ሀብት የበለጠ የአገር ሀብት ይባክናል፡፡ ብዙ ነገሮችን እያስተካከልን ነው፡፡ ከጊዜ ወደጊዜ ለውጥ ያመጡ ተቋማቶች አሉ፡፡ ለውጥ የማያሳዩ ተቋማትም አሉ፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን በድምሩ ስታየው ያን ያህል ላያረካህ ይችላል፡፡ እንደ ተቋም ስትሄድ ግን ለውጥ ያመጡ ተቋማት አሉ፡፡ እና ይህ ተቋም እንደ መሥሪያ ቤት ያላግባብ የሚመዘብረውን ሀብት ማስቀረት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ከዚህ በፊት መመርያ የሌላቸው መሥሪያ ቤቶች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ ወደ ከፍተኛ ተቋማት ስትሄድ የውስጥ ገቢ እንደመጣ ያለአሠራር ነበር የሚሰበሰበው፡፡ ይህ ገቢ የሚሰበሰበው ከመንግሥት ተቋም እንጂ የግል ድርጅት አይደለም፡፡ ወጪ እንኳን ሲወጣ ተመዝግቦ በመመርያ ነው መውጣት ያለበት፡፡ እኛም ይኼን አሠራር የግኝት አካል ስላደረግነው አሁን ላይ በሕግና ሥርዓት እንዲመራ አድርገነዋል፡፡ በሌላ በኩል ተመን የሌላቸው ክፍያዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ ክፍያዎች ዝም ብለው የሚባክኑ ነበሩ፡፡ ይህንንም አሠራር ሕግና ሥርዓት ይዞ እንዲመራ አድርገናል፡፡ እንደገና በክዋኔ ኦዲት ረገድ የነዳጅ አጠቃቀምን በተመለከተ በደርግ ጊዜ የወጣ አሠራር በኦዲት ሪፖርት ተገኝቶ አዲስ መመርያ ወጥቶለት በሕግና ሥርዓት በአግባቡ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግበት አድርገናል፡፡ ስለዚህ እኛ ባንሠራ ኖሮ የሀብት ብክነቱና ጥፋቱ ከዚህ የበለጠ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡

ሪፖርተር፡- የተቋማችሁ ገለልተኝነትና በተቋሙ ላይ የሚደርሱ ጣልቃ ገብነቶች ምን ይመስላል?

ወ/ሮ መሠረት፡የሚገርምህ ይህ ተቋም ባለፈው ጋምቢያ ላይ 26 አባል አገሮች ያሉበት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተናጋሪ አገሮች ስብስብ ውስጥ፣ የተቋም ገለልተኝነታቸውን ካረጋገጡ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት አንዱ ነው፡፡ ገለልተኛ ሲባል ከምን ይጀምራል መሰለህ ከበጀት ይጀምራል፣ በጀታችን ቀጥታ በፓርላማው ነው፡፡ የሠራተኛ አስተዳደር እኛ ከሲቪል ሰርቪስ ውጪ ነን፡፡ የራሳችን ደንብ አለን፡፡ መረጃ የማግኘት መብት አለን፡፡ ለመንግሥት ወሳኝ ተቋም የሚባሉት እንደ ዋና ኦዲተርና ጠቅላይ ፍርድ ቤት በማንም መናወጥ የሌለባቸው ተቋማት ናቸው ተብሎ ነው የሚታሰበው፡፡ ነፃና ገለልተኛ ሆነው መቋቋም አለባቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የእኛ ተቋም ከሥራ አስፈጻሚ ተፅዕኖ በጣም ነፃ ነን ማለት ይቻላል፡፡ እርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ አደረጃጀቱ ነፃ ነው፡፡ ምንም ዓይነት ተፅዕኖ የለበትም፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ምን ይላሉ መሰለህ፣ አዋጅ ውስጥ ያሉትን ጉዳዮች ሕገ መንግሥት ላይ አካቷቸው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም አዋጅ መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር ይሻራል፣ ሕገ መንግሥት ግን አይሻርም፡፡ ወደፊት ምናልባት ሕገ መንግሥቱ ሲሻሻል የምናስገባቸው ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ያምሆኖ ግን በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 101 ላይ የተቋቋመ የፌደራል ዋና ኦዲተር ነፃና ገለልተኛ፣ ትክክለኛ በሆነ መንገድ እየተንቀሳቀሰ ያለና ሌሎች እኛን በሚገመግሙ አካላትም የተረጋገጠ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡– በዚህኛው የመንግሥት ምሥረታና የፓርላማ አደረጃጀት የፓርላማው የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተቃዋሚ ፓርቲ እንዲመራ ተደርጓል ፡፡ ይህ በመሆኑ ለዋና ኦዲተር ምን የተለየ አበርክቶ ይዞ መጣ? ምንስ ዕገዛ ያደርጋል?

ወ/ሮ መሠረት፡ እኛን ጠቅሞናል፡፡ አሁን እኔ ጠቅሞኛል፡፡ ቢያንስ በዕቅድ ከያዝናቸው የመስክ ምልከታ ውጪ 26 ጉዳዮችን ፈጽሟል፡፡ አሁን ይህ ሲደረግ ደግሞ ዝምብሎ ስብሰባ አይደለም፡፡ አያንዳንዱ ባለድርሻ አካል ባለበት ከፍትሕ ሚኒስቴር፣ ከፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከግዥ ኤጀንሲና ከሌሎች ይመጣል፡፡ አሁን ከመመርያና ከበጀት ዓመት ጋር ችግር ሲፈጠር፣ ገንዘብ ሚኒስቴር የቤት ሥራ ይሰጠዋል፡፡ ወንጀል ነክ የሆኑ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ደግሞ ለፍትሕ ሚኒስቴርና ለፀረ ሙስና ኮሚሽን ኃላፊነት ይሰጣል፡፡ ይህ አሠራር በዚህ ዓመት ያየነው ነው፡፡ እስካሁን አልነበረም፡፡ እኔ ከዚህ በፊትም ነበርኩ እንሰባሰባለን፣ አቅጣጫ ይሰጣል፡፡ ከዚህ በኋላ እነሱ የሰጡትን የድርጊት መርሐ ግብር ዘወር ብሎ አይከታተልም፡፡ እኛ ከቀድሞው ቋሚ ኮሚቴ ጋር ይህን ገምግመን ነበር፡፡ ለአዲሶቹም ይህ የነበረው አሠራር እንዳይቀጥል አስገንዝበን ነው የጀመርነው፡፡ አዲሶቹ ሲጀምሩ መብታቸውና ግዴታቸው ምንድነው የሚለውን የሌሎችን አገሮች ተሞክሮ አሠልጥነን ነው፡፡ የጀመርነው፡፡ በተጨማሪም የባለፈውን ኮሚቴ ጠንካራና ደካማ ጎን ነግረንና አሳይተናቸው ነው ወደ ሥራ የገባነው፡፡ በዚህ ረገድ አሁን ያለው ጥሩ የሚባል ክትትል ነው በዚሁ ከቀጠለ ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፍትሕ ሚኒስቴርም ሆነ ሌሎች የራሳቸውን የቤት ሥራ ይዘው ነው የሚወጡት፡፡ በዚህኛው ፓርላማ እኔ ከመጣሁ ለመጀመያ ጊዜ ያየሁት ገንዘብ ሚኒስቴር 39 ተቋማትን በተለያየ መልኩ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡ ድሮ እኮ አይደለም ገንዘቡ ‹‹ስማችን እንደዚህ ሆነ›› ብለው ይጠይቁን የነበሩ ተቋማት ነበሩ፡፡ ስለዚህ ይህ ለእኛ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ በሚቀጥለው ሥራቸውን በሚገባ ካላከናወኑ ዕርምጃው ይቀጥላል፡፡ እኛ ግን የመንግሥት ተቋማት እንዲቀጡ ሳይሆን ተቋማት ከችግር ወጥተው ግልጽ የሆነ የበጀት አጠቃቀም እንዲኖራቸው በሚል ነው፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ዋና ኦዲተር ዕገዛ ጥሩ የፋይናንስና የክዋኔ ኦዲተር ሪፖርት ይዘው እንዲመጡ በሚል ነው ትኩረት ይዘን የምንንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡- ስለዚህ ቋሚ ኮሚቴው በተቃዋሚ ፓርቲዎች መያዙ አቅም ፈጥሮላችኋል ማለት ነው?

ወ/ሮ መሠትረት፡አዎ አቅም ፈጥሮአል፡፡ መንግሥትም ሕጉንና ዓለም አቀፍ ተሞክሮን ተከትሎ ነው ሹመቱን የሰጠው፡፡

ሪፖርተር፡– የመንግሥት ተቋማት ለኦዲት ሪፖርት ያላቸው ተገዥነት ምን ይመስላል? የትኞቹ ተቋማት ላይስ ክፍተት ይበዛል?  

ወ/ሮ መሠረት፡የኦዲት ግኝት የሚገኝባቸው ተቋማት ደረጃ ይለያያል እንጂ ሁሉም ጋር ችግሩ አለ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ደረጃ አለው፡፡ በዝቶ የሚታየው በሪፖርት ወቅት እንደተገለጸው የዩኒቨርሲቲው ነው፡፡ እንግዲህ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በርካታ የሕግ ጥሰቶች አሉ፡፡ መሠረታዊ መፍትሔ ነው ብዬ የማየው በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ግን ከባህሪያቸው አንፃር ታይቶ በጥናት መመለስ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም ከዓመት ዓመት ከኦዲት ግኝት የማይወጡበት ችግር ምንድነው የሚለው ራሱን የቻለ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ በተለይም ትክክለኛ የሆነና የእነሱን ባህሪ ታሳቢ ባደረገ መልኩ በጥናት የተደገፈ መመርያ ሊወጣላቸው ይገባል እንጂ፣ በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ችግሩ አይሻሻልም፡፡ ለዚህ የሚሆነው ችግሩ ምንድነው ብሎ ማጥናትና መሠረታዊ የሆነ መፍሔ ያስፈልጋል፡፡

ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ

ሪፖርተር፡- ተቋማት ለኦዲት ሪፖርት ያላቸው ተገዥነትስ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ መሠትረት፡በነገራችን ላይ አንዳንዶቹ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ትኩረት አይሰጡም፡፡ ሪፖርቱ የት እንዳለ የማያውቁ ተቋማት አሉ፡፡ እኛ ሪፖርት ለማድመጥ ስንሰበሰብ ሪፖርት አልደረሰንም ብለው እኛ የምንልክላቸው ተቋማት አሉ፡፡ ይኼ እኔ በጣም ያሳዝነኛል፡፡ እኛ ኦዲት ስናደርግ ሀብት እያፈሰስን ነው፡፡ ለሠራተኞች ደመወዝና አበል እየከፈልን ነው የምናሠራው፡፡ ስለዚህ ያንን ስንሠራ ዓላማችን ሪፖርት መሥራት ብቻ አይደለም፡፡ ተቋማቱ ከሪፖርት ተነስተው አሠራራቸውን እንዲፈትሹና እንዲያስተካክሉ ነው፡፡ የእኛ ኦዲት በናሙና ነው የሚሠራው፡፡ ይህ ማለት ተቋማቱ ከናሙና ኦዲቱ ተነስተው አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉና ከችግራቸው እንዲወጡ ነው፡፡ ነገር ግን የኦዲት ሪፖርቱን በበጎ ጎን የሚያዩት አሉ፡፡ ዘወር ብለው የማያዩትም አሉ፡፡ እንደየ አመራሩ ጥንካሬና ድክመት ይወሰናል፡፡ ጠንካራ አመራሮች መሥራያ ቤታቸውን ለውጠውበታል፡፡ የተለወጡም አሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ዘወር ብለው አያዩትም፡፡ ከአሁን በኋላ ግን ይኼ ነገር ይቀጥላል ብዬ አላስብም፡፡ መንግሥትም ትኩረት ይሰጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ ባለፈው የመንግሥት ምሥረታ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እንዲሁም ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ ሌብነትን እንጠየፋለን ሲሉ ንግግር አድርገው ነበር፡፡ ስለዚህ በዚህ ይቀጥላል ብዬ አላስብም፡፡ ከዚህ ተነስተው ማስተካከያ ይወስዳሉ ብዬ አስባለሁ፡፡ ዘንድሮ እስካሁን የማናውቀው ተሰብሳቢ ሒሳብ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ተመላሽ ተሰብስቧል፡፡ ይህ ገንዘብ የመጀመሪያው የመሪዎቹ ንግግር ተፅዕኖም ሊሆን ይችላል፡፡ የቋሚ ኮሚቴውም ክትትልና ቁጥጥር ሊሆን ይችላል፡፡ እኛ ተመልሷል ያልነውን ያህል እንኳን ባይመለስ እስካሁን ከ15 በመቶ አልፎ የማያውቀው ተመላሽ አሁን በዚህ ዓመት ወደ 40 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ ይህ አሠራር ተጠናክሮ ከቀጠለ ውጤት ያመጣል፡፡ ስለዚህ ተቋማት የዕቅዳቸው አካል ካደረጉት ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡

ሪፖርተር፡– በኦዲት ሪፖርት ወቅት የሚቀርቡ የተለያዩ ዓይነት ግኝቶች ይሰማሉ፡፡ እናንተ ከምታገ˜ቸው ግኝቶች ውስጥ ግርምት የሚያጭርባችሁ ግኝት አለ? እንዴት ብሎ ነው የኦዲት ክፍተት የሚፈጠረው? በግምገማችሁ ያያችሁት ካለ?

ወ/ሮ መሠረት፡አንዳንዶቹ ታች ካሉት የሒሳብ ባለሙያዎች ከብቃት ጋር በተገናኘ የሚከሰቱ መሠረታዊ ችግሮች ናቸው፡፡ ነገር ግን ሁሉም የኦዲት ግኝት ለእኛ አስገራሚ ነው፡፡ እያንዳንዱ ሒሳብ በምን እንደሚመራና እንዴት መሠራት እንዳለበት መርህና መመርያ ተቀምጦለታል፡፡ አሁን ብዙ ጊዜ የሚገጥመን ከግዥ ጋር የሚገናኝ ጥሰት ነው፡፡ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት የግዥ መመርያ አለው፡፡ ማንኛውም ግዥ የመንግሥትን የግዠ መርሆዎች ተከትሎ መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ የመሥሪያ ቤቱ ትልቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ተነስቶ የመሥሪያ ቤት ኃላፊነት ከሆነ በዓመቱ ሊሠራቸው ያቀዳቸውን ተልዕኮዎች መሠረት ያደረጉ ዕቅዶችን ማቀድ አለበት እነዚህ ዕቅዶች መቼ መቼ መፈጸም አለባቸው ብሎ ማስቀመጥ አለበት፡፡ በዚህ ዕቅድ ከተመራ እያንዳንዱ ዕቅድ እንደየገንዘቡ መጠን በተቀመጠለት የግዥ ሕጎች መሄድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ይኼ ስለማይሆን አንዳንዴ የግዥ ዕቅድ የሌለው ተቋም እናገኛለን፡፡ ዕቅድ ሳይኖራቸው ግዥ ይፈጽማሉ፡፡ ለምን ከዕቅድ ውጪ ግዥ ይፈጽማሉ የሚለው ለእኛ አግራሞት ይፈጥራል፡፡ እነሱ እኮ በመመርያ መሠረት ሔደው በአጋጣሚ ችግር ሲፈጠር፣ እኛ እንደሰው እንረዳቸዋለን፡፡ ምክንያቱም ኦዲተር ስለሆን የተገኘውን ሁሉ የኦዲት ግኝት አናደርግም፡፡ ተቋማቱ ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ እንረዳለን፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ እንደምንጠብቀው አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አላሠራ ያላችሁ ጉዳይ አለ?

ወ/ሮ መሠረት፡አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች የእኛ ኦዲተሮች ለኦዲት ሥራ ቢሮ ስጡን ሲሉ ቢሮ የለንም ይላሉ፡፡ ነገር ግን እነዚህ መሥሪያ ቤቶች ቢሮ እንሰጥም ማለት አይችሉም፡፡ ነገር ግን እኛ እየተቸገርን ነው፡፡ በጀቱን ሲወስድ አንድ ተቋም ለኦዲተር ቢሮ ማዘጋጀት አለበት፡፡ ቢሮ የለንም የሚል መልስ የኦዲት ሥራችንን ያስተጓጉልብናል፡፡ ሌላው ደግሞ ሰነድ ሲጠየቁ የማያቀርቡ አሉ፡፡ ሰነድ የለም ይሉና መጨረሻ ከኃላፊዎቹ ጋር የመውጫ ስብሰባ ሲደረግ እንደገና ይኼው ሰነድ አለ ብለው የደበቁትን ሰነድ ያቀርባሉ፡፡ ይህ በጣም የሚገርም ነው፡፡ ኦዲተሮች ልከን ሁለትና ሦስት ወራት ቆይተው ሰነድ የለንም ይላሉ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የእኛ ተቋም ለጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ባለመስጠት የኦዲት ሥራችን ያጓትቱብናል፡፡ ኦዲት ስንሠራ ዝቅተኛ፣ መለስተኛ፣ ከፍተኛ ተብሎ ለመጨረስ የተቀመጠ ሰዓት አለ፡፡ ነገር ግን መረጃ ባለማቅረባቸው ሥራችን እያጓተቱብን ነው፡፡ ጉዳዩ ቀርቶ ላይቀር ሰነድ ባለማቅረባቸው ኦዲት ሳናደረግ የምንወጣባቸው መሥሪያ ቤቶች አሉ፡፡ የተሰበሰበ ገንዘብ አለ ወጪም አለ፡፡ ነገር ግን ለዚህ ገንዘብ ማስረጃ የሚሆን አስፈላጊ ሰነድ ስላላቀረቡ አላየናቸውም፡፡ ይኼ የሕግ ጥሰት ነው፡፡ እንደዚህ ማድረግም አይችሉም፡፡  

ሪፖርተር፡– ኦዲት ለማድረግ ስትሄዱ ቢሮ የሚከለክሉትንና ሰነድ የማያቀርቡትን ምንድነው የምታደርጓቸው?

ወ/ሮ መሠረት፡እኛ ይህን ሪፖርት በወቅቱ የማይዘጉትንና ቢሮ አንሰጥም ያሉትን ለገንዘብ ሚኒስትሩ ለፓርማውም እንጽፋለን፡፡ ከዚህ ተነስቶ ዕርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ የሰነድ ጉዳይ ግን ሊዘገይ ይችላል እንጂ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ነገር ግን የእኛን ጊዜ ይጎትትብናል፡፡ ባለፈው ለምሳሌ ሪፖርት በወቅቱ ያልዘጉትን ለፍትሕ ሚኒስቴር ጽፈን እንዲዘጉ ተደርገዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የእናንተን የኦዲት ሪፖርት ተከትሎ የፓርላማው ዕገዛ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ መሠረት፡በቀድሞው የፓርላማ ዘመን እኛ አቅርበን እንመለሳለን፡፡ የሚደረገውም ክትትል ጠንካራ አልነበረም፡፡ አሁን ግን ለውጥ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተቃዋሚ ፓርቲ መሆኑ በራሱ ዓለም አቀፍ ተሞክሮውም እንዲህ ስለሚያሳይ ማለት ነው፡፡ አሁን ለምሳሌ በየዓመቱ የኦዲት ውይይት እናደርግባቸዋለን ብለን የያዝናቸውን ሁሉንም አድርገናል፡፡ ባለፉት ቀናት ጨርሰናል ይኼ አንዱ ስኬት ነው፡፡ ለእያንዳንዱ የኦዲት ሪፖርት ውይይት ላይ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የራሱን የቤት ሥራ እየተወጣ ነው እየሄደ ያለው፡፡ ከዚያ ተነስተን ደግሞ ቀጣይ ክትትል አለ፡፡ ግብረ መልስም ይሰጣል በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ምን ላይ ደረሳችሁ ተብሎ ዕርምጃ ይወሰዳል ማለት ነው፡፡ ፓርላማውም ሊያደርግ የሚችለው ችግሩን ለይቶ ለፍትሕ ሚኒስቴር ከማቅረብ ውጪ ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ነገር ግን ምናልባት ሹመት በሚሰጥበት ጊዜ የራሳቸው አሠራር ያላቸው ይመስለኛል፣ ለኃላፊነት ሲሰጥ የሚቀርብባቸው ግምገማ ያለ ይመስለኛል፡፡ አሁን በዚህ ዓመት ያለው አብዛኛው አመራር አዳዲስ ነው፡፡ ሪፖርትም የማያወጡት በዚያ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ ለመጠየቅም ትቸገራለህ፡፡ ስለዚህ በሚቀጥለው ግን እነዚህ አመራሮች ከአምናው ካልተማሩ ባሉበት ይቀጥላሉ ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- በአንዳንድ ተቋማት ኃላፊዎች ሲቀያየሩና በእነዚህ ተቋማት ለተፈጠሩ ችግሮች እኔ አይመለከተኝም፣ በቀድሞ ጊዜያት በነበሩ ኃላፊዎች የተፈጸሙ ናቸው፣ የሚሉ ምላሾች እንዳሉ አልፎ አልፎ ይደመጣሉ፡፡ ይህ ግን ትክክለኛ አሠራር ነው?

ወ/ሮ መሠረት፡አይባልም፡፡ በነገርህ ላይ አንድ ተቋም ላይ ስትሾም መልካሙንም መጥፎውንም ነገር ይዘህ ነው የምትቀጥለው፡፡ ይኼ የግለሰቦች የአረዳድ ችግር ነው እንጂ አንድን ተቋም ስትቀበል ድክመቱንም ጥንካሬውንም ይዘህ ነው፡፡ ጥንካሬውን ተቀብለህ ትጎለብታለህ፡፡ ክፍተቱን ደግሞ አርመህ ታስተካክላለህ እንጂ እኔን አይመለከተኝም አትልም፡፡ እንዲህ የሚል ሰው ካለ በጣም ስህተትም ክልክል ነው ምክንያቱም አንዳንድ በሳል አመራሮች ወደ አዲስ ተቋም ሲሄዱ፣ ያን ተቋም ያለውን ጠንካራና ደካማ ጎን ለይተው በዕቅዳቸውና በድርጊት መርሐ ግብራቸው፣ በስትራቴጂና ዓመታዊ ዕቅዳቸው አካተው ያለውን ችግር ከመመርያ ጋር ወይስ ከአቅም ጋር የተያያዘ ነው የሚለውን በግልጽ ለይተው ያነሳሉ፡፡ ብዙ ጊዜ ለምሳሌ ኦዲት መነሻ አለው አንዱ ከአቅም ጋር ወይም ከሕግና መመርያ ችግር ሊሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ ተቋምን የሚረከብ አካል መመርያ የሌለውን በመመርያ እንዲገዛ፣ ሕግ ጥሰት ያለበትን ደግሞ ሕግን ተከትሎ እንዲሠራ በማድረግ፣ በየደረጃቸው ተጠያቂ የሚሆነውን ተጠያቂ በማድረግ አቅም በመፍጠር፣ ክፍተት ያለበትን ደግሞ እሱን በማሠልጠንና በማስተካከል መቀጠል ይችላሉ እንጂ ተቋሙን ሲቀላቀል ‹‹ይኼ የባለፈው ነው›› የሚል ከሆነ ሲጀመር ሥልጣኑንም መቀበል የለበትም ብዬ ነው የማስበው፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ሥልጣን ሲረከቡ ዕዳውንም ሀብቱንም ነው እኮ የተቀበሉት፡፡ እሳቸው ከመጡ ወዲህ እንኳ እያከናወኑት ያለው ሥራ የባለፈውን ዕዳ ለመክፈል አይደል? ስለዚህ በተዋረድም እንደዚያ ነው መደረግ ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡– የዋና ኦዲተርን ሪፖርት ሲያቀርቡ የመንግሥት የበላይ ኃላፊዎች በምርክ ቤቱ ባለመገኘታቸው ቅሬታ አስነስቷል፣ በፓርላማው ኃላፊዎች ተጠርተው አለመገኘታቸው ምን አንድምታ አለው?

ወ/ሮ መሠረት፡እሱን እንግዲህ ፓርላማው ነው ራሱ መጠየቅ ያለበት፡፡ በነገርህ ላይ በፓርላማው ገደብ የሌለበት ሪፖርት ከሚያቀርቡ ተቋማት ውስጥ የዋና ኦዲተርና የጠቅላይ ሚኒስቴር ሪፖርት ነው፡፡ ምክንያም ሁሉንም የፌዴራል ተቋማት ሪፖርት ስለሆነ ገደብ የለውም፡፡ እንደሌላው ተቋም 16 ገጽ ወይም ይህን ያህል ደቂቃ አንባልም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩና ዋና ኦዲተር ገደብ የለባቸውም የሚለው የፓርላማው የአሠራር ደንብ ላይ አለ፡፡ በዚህ የምክር ቤት ደንብም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጪ ሁሉም መገኘት አለባቸው ይላል፡፡ ይህን መጠየቅ ያለበት ፓርላማው ነው፡፡ እንደኛ ሁለም የመንግሥት ተቋማት ቀርበው ማሳወቅና ማዳመጥ አለባቸው፡፡ የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ ምንም እንኳን ቀድመን ለሁሉም የምንልክ ቢሆንም፣ ነገር ግን ምንድንው የሚነሳው ጉዳይ የሚለውን ቀርበው ማዳመጥ አለባቸው፡፡  

ሪፖርተር፡- የኦዲት ሪፖርትን በተመለከተ ከሁሉም ተቋማት በተለይ ደግሞ ፍትሕ ሚኒስቴር፣ ፀረ ሙስናና መሰል ተቋማት ምን እንዲያደርጉላችሁ ነው የምትጠብቁት?

ወ/ሮ መሠረት፡አንዱና ዋናው እኛ ሪፖርታችን ለሚመለከታቸው አካላት ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለንዘብ ሚኒስቴርም፣ ይሁን ለሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን እንሰጣለን፡፡ ስለዚህ ሪፖርቱን በጥሞና ማንበብና እኛ የሰጠናቸውን ምክረ ሐሳቦች በመመልከት፣ በተለይ በሕግ ተመላሽ መሆን ያለበትን ተመላሽ እንዲሆን፣ ማስተካከያ ማድረግ ያለበትን ማስተካከያ እንዲያደርግ ሁሉም የሚመለከታቸውን ወስደው መሥራት አለባቸው፡፡ አንዳንዶቹ እኛ ሠርተን ከጨረስን በኋላ እንደ አዲስ እንደገና ሠርተን እንድንሰጣቸው ይፈልጋሉ፡፡ ነገር ግን እኛ በናሙና መሠረት አድርገን የምንሠራ በመሆኑ ከሰጠነው ምክረ ሐሳብ በመነሳት መጠየቅ ያለበት አካል መጠየቅ አለበት ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት በሕግ አግባብ መጠየቅ ያለበት አካል መጠየቅ አለበት፡፡ ከዚህ በላይ ግን የሁሉም ተቋማት ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ይህን የተመደበ በጀት በአግባቡ እየተቆጣጠረ እንዲጠቀም ኃላፊነት አለበት፡፡ ከዚህ ካለፈ ነው የሌላው ዕገዛ የሚያስፈልገው፣ ይህ ማለት አንድ ተቋም የማይፈጽመውን እነዚህ ተቋማት ይቆጣጠሯቸዋል ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት የኦዲት ሪፖርቱን መነሻ አድርጎ በአስተዳደር ጉዳይ መጠየቅ ያለበት በአስተዳደራዊ፣ በወንጀል መጠየቅ ያለበትን በወንጀል እንዲጠየቅና ከዚያ አልፎ ጠለቅ ያለ ምርመራ የሚያስፈልግውን ደግሞ እኛ ጋር መጥተው እኛ እናግዛቸዋለን ማለት ነው፡፡ እኛ የምናደርገው የናሙና ኦዲት የተቋማት ሲስተም መሥራት አለመሥራት ለማየት እንጂ እንደ ልዩ ኦዲት ከሀ እስከ ፐ አንሠራም፡፡

ሪፖርተር፡- ኦዲት ሪፖርት ሠርታችሁ ለፓርላማው ከላካችሁ በኋላ ምን ዓይነት ክትትል ታደርጋላችሁ?

ወ/ሮ መሠረት፡እኛ ክትትል አለን፡፡ በተለይ የፋይናንስ ሒደቱን በየዓመቱ እንከታተላለን፡፡ ይህ ማለት ከቀደመው ዓመት እየተደመረ የሚመጣውን እየለየን ዕርምጃ የተወሰደበትን እየተውን ያልተወሰደበት ደግሞ እየተደመረ ይቀጥላል ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በቀጣይ ከእርስዎ የዋና ኦዲተር ዘመን ምን እንጠብቅ?

ወ/ሮ መሠረት፡ከኦዲት ሥራ ጋር በተገናኝ እንግዲህ እኛ የምንሠራው ዓለም አቀፍ መሥፈርትን መሠረት አድርገን ነው፡፡ እሱን ተከትለን ጥራት ያለው የኦዲት ሪፖርት ማቅረብ እንፈልጋለን፡፡ የመንግሥት በጀት ላልታሰበለት ዓላማ እንዳይውል ከባድ ኃላፊነት ስለተሰጠው የኦዲት ባለሙያን በአግባቡ በማነጽ የበለጠ ሥራ በውጤታማነት እንሠራለን፡፡ ይህን መሠረት አድርገን ለመንግሥት ትልቅ ግብዓት በመስጠት ዕገዛ እናደርጋለን ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡– በመጨረሻ ሊሉን የሚፈልጉት ነገር አለ?

ወ/ሮ መሠረት፡ እንግዲህ ከዚህ ቀደም ስመጣ ጀምሮ የረዱኝን የቀድሞው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹን በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ በሁሉም ረገድ እንድጎለብት ላደረጉልኝ ዕገዛና ለዚህ እንድበቃ የእሳቸው አስተዋጽኦ ስላለበትና የተቋሙ ሠራተኞች በተለይ ባለፈው ከአንድ ዓመት በላይ የኦዲት ሥራ ላይ ክፍተት እንዳይፈጠር ላደረጉት አስተዋጽኦ ትልቅ ምስጋና አለኝ፡፡

ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች


ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ግጭቶች በሰብዓዊ ዕርዳታ ሥራዎቻችን ላይ የሚያሳድሩትን አሉታዊ ተፅዕኖና እየተከሰተ ያለውን ሥቃይ እያየን ነው›› ሆላንደር ሆላንደር፣ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት የኢትዮጵያና የጂቡቲ ዋና...

ከበርካታ የአፍሪካ አገሮች መካከል ኢትዮጵያ ለአሜሪካ የቅርብ ወዳጅ እንደሆነች ይነገርላታል፡፡ ክፍለ ዘመንን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ሰሞኑን ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የጀመሩበትን 120ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸውን...

‹‹በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚኖሩንን እንቅስቃሴዎች ሊያግዙ የሚችሉ ተቋማት ያስፈልጉናል›› ገመቹ ዋቅቶላ (ዶ/ር)፣ የአይ ካፒታል አፍሪካ ኢንስቲትዩት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያንና የምሥራቅ አፍሪካን የፋይናንስ ተቋማት መሠረት በማድረግ በየዓመቱ የሚካሄደው የምሥራቅ አፍሪካ የፋይናንስ ጉባዔ፣ በበርካታ አጀንዳዎች አማካይነት በተለይ ለፖሊሲ አውጪዎች ግብዓቶችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጎን...

‹‹ኢትዮጵያ ብዙ ፈተና እየገጠማት ቢሆንም ከፈተናው ውስጥ ቀስ እያልን እንወጣለን ብዬ አስባለሁ›› ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥት ለውጥ መካሄዱን ተከትሎ  በቀደሙት ጊዜያት ከተቋማዊ ስሙ ባለፈ በሚያከናውናቸው ተግባራት፣ ተቋሙን ይመሩት በነበሩ ኮሚሽነሮች፣ እንዲሁም በአጠቃላይ ተቋማዊ ባህሪው ከአስፈጻሚው...