Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየአስፈጻሚዎች የዕቅድ አወጣጥ ችግር ማነቆ የሆኑባቸው የስታዲየም ግንባታዎች

የአስፈጻሚዎች የዕቅድ አወጣጥ ችግር ማነቆ የሆኑባቸው የስታዲየም ግንባታዎች

ቀን:

የአማካሪው ኤምኤች ኢንጂነሪንግ ድርሻና ግዴታስ ምንድነው?

በአሁኑ ወቅት በቢሊዮን ብር የሚገመት በጀት ፈሶባቸው ካልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል፣ በክልል ከተሞች ‹‹ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ›› በሚል ሽፋን የተጀመሩ የስታዲየም ግንባታዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ግንባታዎቹ ዘመናዊና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን አካተው በተያዘላቸው ጊዜ ሰሌዳ መሠረት ማለትም የዓለም አቀፍ ተቋማትን ዝቅተኛ መሥፈርት አሟልተው መገንባት እንዳለባቸው የብዙ አገሮች ተሞክሮ ያሳያል፡፡

በርካታ አገሮች የስታዲየም ግንባታዎቻቸውን በዚህ ረገድ እንዲከናወን ሲያደርጉ፣ እንዴት አትርፈው ስፖርቱም ሆነ ኢኮኖሚያቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ አሥልተውና አቅደው እንደሆነ ማሳያዎችን መመልከት ይቻላል፡፡ ታዲያ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው በተቃራኒው መሆኑ ለምን ማስባሉ አልቀረም፡፡

- Advertisement -

ለዚህ አባባል ማጠናከሪያ የሚሆነው ደግሞ፣ አኅጉራዊው የእግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል የሆነው ካፍ፣ በኢትዮጵያ ስታዲየም የሚመስሉ ግን ደግሞ አንድን ስታዲየም ‹‹ስታዲየም›› ሊያስብሉ የሚችሉ ውስጣዊና ውጫዊ ቅድመ ሁኔታዎች ያልተሟሉላቸው ናቸው በሚል እስካሁን ዕውቅና አልሰጣቸውም፡፡

በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ተገንብቶ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ፣ ከእግር ኳስና አትሌቲክስ ባሻገር የፈረስ ጉግስን ጨምሮ ኮንሰርቶችና ሃይማኖታዊ ዝግጅቶችን ሲያስተናግድ የቆየው የአዲስ አበባ ስታዲየም፣ የመጫወቻ ሜዳው፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎቹ፣ መፀዳጃ ቤቶቹ (የወንዶችና የሴቶች)፣ የሚዲያ ክፍሎች፣ የክብር እንግዶች ክፍልና የኤሌክትሪክና የሳኒተሪ ሥራዎችን በማካተት ዕድሳት እንዲደረግለት ካፍ ማዘዙን ተከትሎ በዕድሳት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡

የስታድየሙ ዕድሳት ከአንድ ዓመት በፊት መቼና በምን ያህል ጊዜ እንደሚጠናቀቅ ቀጠሮ ተይዞለት የነበረው፣ የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጨረሻውን የጨዋታ መርሐ ግብር እንደሚያስተናግድ ነበር፡፡ ይሁንና መንግሥት ለዘርፉ በአስፈጻሚነት የሚያስቀምጣቸው ባለሥልጣኖች በተለይም ከዕቅድ ጋር ተያይዞ ምን ያህሉን ተግብረዋል፣ የቀረውስ የሚለውን አስልቶ ኃላፊነት ወስዶ የሚጠይቅና የሚያስጠይቅ ተቋም እምብዛም በመሆኑ፣ የአዲስ አበባ ስታዲየም አሁን በያዘው ቁመና ዕድሳቱ ተጠናቆ በቀጣዩ የውድድር ዓመት የሚጠበቅበትን ግልጋሎት ለመስጠቱ እርግጠኛ ባለመሆን የሚጠይቁ አልጠፉም፡፡

በእርግጥ ከሰሞኑ ምዕራብ አፍሪካዊቷ የእግር ኳስ አገር አይቮሪኮስት በሚቀጥለው ዓመት ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በጎረቤት አገር ማላዊ ስታዲየም የግብፅ አቻውን 2 ለ 0 ማሸነፉን ተከትሎ፣ ብሔራዊ ቡድኑ በመስከረም ወር (2015) ኢትዮጵያ ከጊኒ ጋር የምታደርገውን ሦስተኛ የማጣሪያ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም እንድታደርግ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳ በተሳተፉበት ስታዲየሙን ሳር የማልበስ ሥራ እየተከናወነ መሆኑ መመልከት ተችሏል፡፡

የሳር ተከላው በተጀመረበት ዕለቱ የባህልና ስፖርት ሚኒስትሩ ቀጄላ መርዳሳና ሚኒስትር ዴኤታው መስፍን ቸርነትን (አምባሳደር) ጨምሮ የግንባታው ተቋራጭና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጃራ ተሳትፎ እንደነበራቸው ታዝበናል፡፡ ይሁንና ሳሩ ካፍ ካስቀመጠው ስታንዳርድ አኳያ ጥራቱ ምን ያህል እንደሆነ አቶ ኢሳያስ ጅራን ጨምሮ አንዳንድ ሙያተኞች ለተቋራጩ ጥያቄ አቅርበውላቸውም ነበር፡፡ የተቋራጩ ኃላፊም ‹‹የሳሩን ዓይነትና የጥራት ደረጃ በሚመለከት ሙያው የለኝም፤›› በማለት መናገራቸው ተሰምቷል፡፡

በሌላ በኩል ከአዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላ ሒደትና የስታንዳርድ ጉዳይ ጥያቄ እየሆነ ባለበት ማግስት፣ ሚኒስትሩ ቦሌ አካባቢ በግንባታ ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲየም፣ ሁለተኛው የግንባታ ምዕራፍ ምን ያህል እየተፋጠነ እንደሚገኝ የገለጹበት አግባብና መሬት ካለው እውነታ ጋር ተደማምሮ ሰሞነኛ መነጋሪያ መሆኑ አልቀረም፡፡

አነጋጋሪው ጉዳይ ደግሞ ሚኒስትሩ ስለ አደይ አበባ ስታዲየም ሒደት ከመግለጻቸው ከሁለት ቀን በፊት ሚኒስትር ዴኤታው ለመንግሥታዊው ሚዲያ የሚከተለውን ብለው ነበር፡- ‹‹የአደይ አበባ ስታዲየም ምዕራፍ ሁለት ግንባታ፣ ተቋራጩ የቻይናው ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጂነሪንግ ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ በሚጠይቁ የግንባታ ዕቃዎች መነሻነት፣ ድርጅቱ የዋጋ ማስተካከያ ጥያቄ በማቅረቡ የግንባታ መስተጓጎል አጋጥሟል፡፡ ያጋጠመንን የውጭ ምንዛሪ እጥረት በተመለከተም መንግሥት ዲፕሎማሲያዊ ውይይቶችን እያደረገ ነው፡፡››

በዚህ የተነሳ በሚኒስቴሩ የሚገኙና ስማቸው እንዳይጠቀስ የሚፈልጉት ባለሙያዎች ‹‹ማንን እንመን?›› በማለት በዕቅድ የማይመሩ አስፈጻሚዎች ለስፖርት መሠረተ ልማቱ ምን ያህል ማነቆ መሆናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡

እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ሲቀጥሉ፣ በአገሪቱ ግንባታቸው ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ የተጀመሩ በርካታ ስታዲየሞች ቢኖሩም፣ እስካሁን አንዳቸውም ዘመኑ የሚጠይቀውን ውስጣዊና ውጫዊ የስታዲየም ይዘት እንዲሁም ስታንዳርድ አሟልተው ባለመጠናቀቃቸው ለአገልግሎት ብቁ እንዳልሆኑ ያስረዳሉ፡፡

ለዚህ ሁሉ የሀብት ብክነት የመንግሥት አስፈጻሚዎች ክፍተትና ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው ወይ ከሚለው በተጨማሪ፣ ቦሌ አካባቢ በመገንባት ላይ የሚገኘውን አደይ አበባ ስታዲየምን ጨምሮ የባህር ዳር፣ የሐዋሳና የነቀምት ዓለም አቀፍ ስታዲየሞችና ሌሎችንም ትልልቅ የግንባታ ፕሮጀክቶችን በአማካሪነት የሚከታተለው ኤምኤች ኢንጂነሪንግ የተሰኘው ድርጅት እስካሁን ባለው ኃላፊነቱና ግዴታው ምን እንደሆነ የሚጠይቅ አካል መጥፋቱ በራሱ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸው ነው ባለሙያዎቹ የሚያክሉት፡፡

ሌሎችም የዘርፉ ሙያተኞች አማካሪ ድርጅቱን በሚመለከት ሲናገሩ፣ ‹‹ኤምኤች ኢንጂነሪንግ የተጠቀሱትን ስታዲየሞች ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማማከር እየሠራ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የስታዲየም ግንባታዎች በተለይም በአሁኑ ወቅት ግንባታዎች በሌሎች አገሮች እንደሚታየው ከሆነ፣ በምን ዓይነት ይዘትና ቅርፅ እንዲሁም የግንባታ ቁሳቁስ እንደሚከናወኑ ይጠፋዋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ እንዴት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ እንኳ ስታዲየም ዘመኑን እንዲዋጅ ተደርጎ ግንባታው እንዲከናወን ሙያዊ የማማከር ግዴታውን መወጣት ያልቻለው? በዚህ ረገድስ ከስታዲየም የግንባታ ስታንዳርድ ጋር ተያይዞ ጥያቄዎች ሲነሱ ለምንድነው የኤምኤች ኢንጂነሪንግ ስም ሲጠቀስ የማይደመጠው?›› ይላሉ፡፡ ከዚሁ ጉዳይ ጋር ተያይዞ የኤምኤች ኢንጂነሪንግ ኃላፊዎች ምላሽና አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ  ያደረግነው  ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...