Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉሞትና ጥቃቱ ለኢኮኖሚ ወይስ ለፖለቲካ ጥቅም?

ሞትና ጥቃቱ ለኢኮኖሚ ወይስ ለፖለቲካ ጥቅም?

ቀን:

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር)

መንደርደሪያና የጽሑፉ ዓላማ

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያዊ ላይ ግድያና ሞት መፈጸሙ ጎልቶ ይታያል፡፡ ለምን? በማን? በምን አመክንዮና ፍላጎት? እና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በሞቶቹና በጥቃቶቹ ዙሪያ ማንሳት፣ ማጥናትና መመርመር ተገቢ ነው፡፡ ታዲያ ይህ ሥራ ለአንዱ ቀላል፣ ለሌላው ደግሞ ውስብስብ ሆኖ መገኘቱ አይቀሬ ነው፡፡ ውስብስብነቱ የሚጀምረው በተለምዶ መንስዔዎቹ ከማይነጣጠሉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ፣ እንዲሁም የባህላዊ ዓውዶች ይዘት ላይ ከሚመሠረት ዕሳቤያዊ አቋም ነው፡፡ እኔ የእነዚህን ዓውዶች ያለመነጣጠል ዕሳቤን አልቀበልም፣ ይነጣጠላሉ፡፡ ኢኮኖሚው ከፖለቲካው ተነጥሎ መጠናት፣ መመርመርና መተቸት ይችላል፡፡ በዓውዳዊ ይዘት ቅደም ተከተል ማስቀመጥ ቢባልስ የትኛው ይቅደም? ወቅታዊ ዝንባሌዎችን ከተመለከትን አብዛኞቹ ፖለቲካ ይላሉ፡፡ የዘር፣ የጎጥ፣ የብሔር፣ የቋንቋ፣ የመጨቆን፣ የመገዛት፣ የመበዝበዝ፣ የትምክህተኝነት፣ የነፍጠኝነት፣ ወዘተ ስሜታዊ የሆኑ ሰዋዊ ይዘቶችን ለፖለቲካው ዓውድ ተቀዳሚ ትኩረት ማስገኛ ምክንያትና መነሻ አድርገውም ያቀርቡታል፡፡ እኔ የፖለቲካ ዓውድ ተቀዳሚነት ዕሳቤን አልቀበለውም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ሞቶችና ጥቃቶች ምክንያታቸውና መንስዔያቸው በዋነኛነት ፖለቲካ ከዚህም ጋር ዘር፣ ብሔር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ነው ብዬ አልቀበልም፡፡ የመግደልና የማጥቃት ድርጊቶቹ መነሻና ምክንያቶቻቸው ኢኮኖሚና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ከኢኮኖሚ ጉዳዮች መሀል ደግሞ ዋነኛው ‹‹ሀብት›› ነው፡፡ ሀብት ከሚባሉት ነገሮች መሀል ደግሞ ዋነኛው መሬትና መሬት በላይዋ (ውኃን ጨምሮ) እና በውስጧ (በማኅፀኗ) የያዘቻቸው ማዕድናትና ተዛማጅ ቁሶች ናቸው፡፡

- Advertisement -

ጥያቄው ታዲያ እነዚህን ተንተርሶ ማነው በቅድሚያ ለኢኮኖሚ ፍላጎቱና ተጠቃሚነት የኢትዮጵያን ሀብት ለማዋል ሲል፣ ፖለቲካና ሌሎች ዓውዶችን ሽፋን አድርጎ የሚንቀሳቀሰው? ይህን ለማድረግ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ከፀሐይ በታች ያለን ፍጡር፣ ቁስና የኃይል ምንጭ የሚጠቀመው? በገንዘብ የሚሆን ከሆነ ደግሞ በቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርፆ የሚተገብር፣ ኢትዮጵያውያንን እርስ በርሳቸው እንዲተራረዱና እንዲጫረሱ የሚያደርግ? የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ፣ ለመፍትሔያቸውም ጥናትና ምርምር ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ይህን መንደርደሪያ ተንተርሼ ጽሑፌን በሦስት ዓላማዎች ዙሪያ አዘጋጅቻለሁ፡፡

  1. ኢትዮጵያ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ ላይ በውጭ ኃይሎች እየታመሰች ነው፡፡ እነዚህም ናቸው ዋነኛ የወቅቱ የችግሮቻችን ምንጮች፡፡ እነዚህ ኃይሎች ለዘመናት በጦርነት ሊይዟት ያልቻሏትን አገር የፖለቲካ ባንዳዎችን በመግዛት የሀብት ብዝበዛ ጥቅማቸውን ለማስከበር ጠንክረው እየሠሩ እንዳሉ ለማስገንዘብ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን አገራዊ ችግራችንን በውጭ ኃይሎች ላይ ማላከክ አለመሆኑን ማወቅን ይሻል፡፡
  2. በዶላር ተገዝተው አገራችንን ለጥፋትና ለውጭ ኃይሎች ተበዝባዥነት ለመዳረግ የሚሠሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ምሁር ተብዬ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎች ከሴራና ክህደታዊ ተግባራቸው ታቅበው፣ ለኢትዮጵያ ዕድገትና ብልፅግና ከሕዝቧ ጋር እንዲንቀሳቀሱ ጥሪ ለማቅረብ ነው፡፡
  3. ሞትና ስቃያችን ቢበዛም ኢትዮጵያን በዘር፣ በጎሳ፣ በጎጠኝነት፣ በሃይማኖት፣ በገንዘብና ቁሳዊ ጥቅም የማይደለሉት የመከላከያና የፀጥታ አስጠባቂ ልጆቿ ለበርካታ ሺሕ ዘመናት ሳትፈርስ እንዳቆዩዋት ዛሬም እንዳትፈርስ፣ ወደፊትም የማትፈርስ አገር እንደሚያደርጓት ያለኝን እምነት ለማሳወቅ ነው፡፡

መሬትና ፖለቲካ

በተለያዩ ጊዜያት በጻፍኳቸው መጻሕፍትና ትምህርታዊ ጽሑፎች ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ሰላምና ደኅንነት፣ ሉዓላዊነቷን ለማስከበርና በማናቸውም ዓውድ ውስጥ ለሚደረግ ልማታዊ እንቅስቃሴ፣ የፖሊሲና የተቋማዊ (ኢንስቲትዩሽን) ማዕቀፍ ዋነኛና ወሳኙ ማጠንጠኛ መሬት ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ዛሬም በአገራችን ውስጥ እየተከሰቱ ያሉ ግድያዎችና ጥቃቶች መንስዔያቸው ከመሬት ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ ዛሬ የኢትዮጵያን መሬትና በላይዋና በውስጧ የያዘቻቸውን የውኃ፣ የማዕድንና ተዛማጅ ቁሳዊ ሀብቶች ለመጠቀም ሲሉ በአገራችን ውስጥ ግጭቶችን፣ ጦርነቶችንና ግድያዎችን የሚቆሰቁሱ፣ በገንዘብና በተለያየ ቁሳዊና ቴክኖሎጂያዊ መሣሪያዎች የሚደግፉ፣ ገዳይና አውዳሚ ኃይሎችን የሚያሠማሩ እነ ማን ናቸው? ብለን መጠየቅ ተገቢነት አለው፡፡ ፈጣን መላሾች ፖለቲከኞች ሊሉ ይችላሉ፡፡ ፖለቲከኞች ቢሆኑስ የትኞቹ? ኢትዮጵያውያን? አገራዊ ፖለቲከኞች? ወይስ ሌሎች፡፡

ዛሬ ካለን የፖለቲካ ዓውዳዊ ይዘት እንደምንወግነው የፖለቲካ ጎራ፣ ቡድን፣ ወይም ፓርቲ በአገራችን የሚታየውን የግድያና ጥቃት ዕርምጃ አንዱ ሌላውን ‹‹ያ እገሌ እኮ ነው››፣ ‹‹እነ እገሌ ናቸው›› ብሎ ጉዳዩን ዘር፣ ብሔር፣ ሃይማኖትና ቋንቋ አላብሶ፣ አገር በቀል የገዥው ወይም የተቃዋሚው ፖለቲከኞች ያደረጉት አድርጎ ለማቅረብ ይነሳል፡፡ ወይም የዚህ አካባቢ ጠባቦች፣ ዘረኞች፣ ነፍጠኞችና ትምክህተኞች ይሆናሉ ብሎ ግምታዊ ማብራሪያ ሊያቀርብ ይሞክራል፡፡ በእርግጥ ይህ ግምት ተጨባጭ ይዘትና አመክንዮ የለውም ባይባልም፣ ጥቅላዊ አገላለጹና ፍረጃው ግን ከፖለቲከኞች ቡድን ጎራ አንፃር ውስጣዊና ውጫዊ ይዘቱ መጠናትና መመርመር አለበት፡፡

የፖለቲከኞች ቡድን ሦስቱ ፖለቲከኞችና ወቅታዊ ይዘታቸው

በኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲከኞች የፈለገውን ያህል ቢፖተልኩ፣ በተለምዷዊ አረዳድ እገሌ ፖተለከ ማለት ዋሸ፣ ከዳ ማለት መሆኑን ይገንዘቡ፡፡ ሃይማኖታዊ ዕውቀትንና ክህሎትን ይዘው ቢሰብኩ፣ ቢፀልዩ፣ በተለያዩ መድረኮች ቢደሰኩሩ፣ ትንታግና አፍ አስጨባጭ ተናጋሪ ቢሆኑ፣ የተዋጣላቸው ጸሐፊዎች ሆነው ቢገኙ፣ ከሥልጣንና ከኃይል ብሎም ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸው አንፃር ዘርን፣ ጎጥን፣ ብሔርተኝነትን፣ ሃይማኖትን፣ ቋንቋን፣ ማኅበራዊ እሴቶችን፣ ወዘተ ተጠቅመው ቢደራጁና ቢንቀሳቀሱ፣ በጥቅሉ ሊከፈሉ የሚችሉት ግን በሦስት ጎራ ነው፡፡

ሦስቱን ጎራዎች በ2012 ዓ.ም. ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› በሚል ርዕስ ባሳተምኩት መጽሐፌ በምዕራፍ አምስት ውስጥ አብራርቼ አቅርቤያለሁ፡፡ ለዚህ ጽሑፍ መረዳት ያግዝ ዘንድ ደግሞ በአጭሩ በሚከተለው ይዘት አቅርቤያቸዋለሁ፡፡

በአገር ውስጥ የተደራጁ አገራዊ ፖለቲከኞች ለሀብት አስተዳደር (ሕዝብን ጨምሮ) ሥልጣንና ኃይለ ወንበር ለመጨበጥ የበቁ ወይም ለመብቃት የሚታገሉ ተብለው ለሁለት የሚከፈሉ ይሆናሉ፡፡ ሦስተኛው የፖለቲካ ጎራ መነሻውና ሥሪቱ አገራዊ ሳይሆን ውጫዊ ነው፡፡ መነሻው በአብዛኛው ከውጭ በተለይም ካደጉ ኢምፔሪያሊስት አገሮች ነው፡፡ የእነዚህ አገሮች ጥቅም አስፈጻሚ ተቋማትና አባሎቻቸው በታዳጊ አገሮች ውስጥ የፖለቲካ ባንዳዎችን መልምለውና አሠልጥነው በማደራጀት ያንቀሳቅሷቸዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የኢኮኖሚ ባንዳዎችን በመመልመልና በኢትዮጵያ የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በመሰግሰግ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች የእነሱን ጥቅም የሚያስከብሩ እንዲሆኑ ያደርጋሉ፡፡ በአጭሩ ለተግባቦት ቅለት ሦስተኛው ጎራ ‹‹የውጭ ኃይል›› ተብሎ ይጠቀሳል፡፡

የውጭ ኃይሎች ለሺሕ ዓመታት ኢትዮጵያን በጦርነት ለመያዝ አልቻሉም፡፡ ዛሬ ግን ሦስተኛውን የፖለቲከኞች ቡድን በማደራጀት፣ ለዚህም ‹‹ዶላርን ከፖለቲካ ባንዳዎች›› ጋር አጣምረው በመሣሪያነት በመጠቀም ኢትዮጵያን ከፋፍለው ሀብቷን ለመዝረፍ፣ አገሪቱም እንድትቀጭጭ፣ ቢቻልም እንድትፈርስ ጠንክረው እየሠሩ ነው፡፡ በርካቶች በውጭ ኃይሎች በሚመሩ ዓለም አቀፋዊ ብዝኃና የሁለትዮሽ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ እነዚህ ኃይሎች ኢትዮጵያን በዓለም ላይ ያላትን የጥቁር ሕዝቦች ጥንካሬ፣ የአዕምሯዊ ምጥቀት፣ የዕውቀት ምንጭነትና የሥራ ትጋት ተምሳሌትነት አዎንታዊ ቅቡልነቱ እንዲኮስስ ለማድረግ የሴራ ፕሮጀክት ቀረፃና ትግበራ እንደሚያደርጉ በ2013 ዓ.ም. ‹‹የምርጫ ሰሞን ፈተና›› በሚል ርዕስ በጻፍኩት ጽሑፍ ለማስገንዘብ ሞክሬአለሁ፡፡

በ2007 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ2015) በእንግሊዝኛ በጻፍኩትና ትኩረቱን በኢትዮጵያ አገራዊ ፖሊሲና ዕድገት ላይ ባደረገው መጽሐፌ ምዕራፍ 22 ኢትዮጵያ በመስቀለኛው መንገድ ላይ መሆኗን፣ በዚሁ መንገድ ላይ ገጥመውን ስላሉ ተግዳሮቶችና ችግሮች ከሰላሳ በላይ በሆኑ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ወቅታዊ ማስገንዘቢያዎችን አቅርቤአለሁ፡፡ በመጽሐፉ በንዑስ ክፍል 22.1.1 በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊና በባህላዊ፣ እንዲሁም በፖለቲካዊና በሃማኖታዊ አደረጃጀታችንና ሥሪታችን ላይ አካታችና ሁሉን በእኩልነት፣ አንዱ ሌላውን በማይጎዳና በማያገል ዓውዳዊ ቅኝት ላይ ተመሥርተን የዕድገትና የልማት እንቅስቃሴያችንን ካልመራነው፣ እንዴት የውጭ ኃይሎች ዘርን፣ ጎሳን፣ ሃይማኖትን፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ክፍተቶቻችንን ተጠቅመው ሊያጠፉን እንደሚሠሩ ለማሳሰብ ሞክሬአለሁ፡፡ ይህን ጉዳይ በ2007 ዓ.ም. መጽሐፌ ውስጥ አካትቼ ያቀረብኩት፣ ኢሕአዴግ ይፈርሳል ተብሎ በማይገመትበት በ2011 ዓ.ም.፣ እንደሆነውም ለሁለት ይከፈላል ተብሎ በማይታሰብበት፣ አልፎ ተርፎ ደግሞ ዛሬ ያለው የብልፅግና ፓርቲ ተቋቁሞ ሥልጣንና ኃይለ ወንበሩ ላይ ይቀመጣል ተብሎ በማይታለምበት ጊዜ መሆኑን ነው፡፡

በቅርቡ በሰሜኑ የአገራችን ክፍልም ሆነ ከሰሞኑን በምዕራብ ወለጋ የተከሰተው ዘግናኝ፣ ወንድም ወንድሙን፣ ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊን ኢሰብዓዊ በሆነ መንገድና ድርጊት የመግደሉ ክስተት አሳዛኝ መሆኑን ባውቅም፣ ቢያመኝም፣ እጠብቃቸውና እላቸው ከነበሩ ጉዳዮችና ሁኔታዎች አንፃር ግን አጉልቼ አልጮሁበትም፡፡ ምክንያቱም ለእነዚህ ድርጊቶች ቢሊዮን ሳይሆን ሚሊዮን ብርም አልወጣባቸውምና፡፡ በቀላሉም የተሸረቡ የሴራ ውጤቶች ናቸው ብዬም ስለምገምት ነው፡፡

በ2012 ዓ.ም. በጻፍኩት መጽሐፌ ውስጥ በንዑስ ክፍል 14.3 የውጭ ኃይሎች በቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ቀርፀው የአገሪቱን መንግሥት ለማኮላሸት እንደሚሠሩ፣ በአንድ ቀን የውሎ አበል የዶላር ክፍያ ወጣቱ እርስ በርሱ እንዲጋደል እንደሚያደርጉት፣ በተለይ ደግሞ በንዑስ ክፍል 14.3.3 ‹‹የውጭ ኃይሎች የ11ኛው ሰዓት ኢትዮጵያን የማፈራረስ አሻጥር›› በሚል ርዕስ የአሻጥሮችን ይዘትና አፈጻጸም ለማሳወቅ ሞክሬአለሁ፡፡ እነዚህ ዛሬ ላይ እውነት እየሆኑ ተከስተዋል፡፡ ዛሬም እነዚህንና መሰል ጉዳዮች ተገንዝበን ወደ አንድነታችን ተመልሰን፣ የአገራችንን ሀብት ኢትዮጵያዊያን በጋራ ተቀዳሚ እንድንሆን ከዘር፣ ከብሔርና ከጎጠኝነት ቅርቃር ውስጥ ካልወጣን የውጭዎቹ የጠነሰሱልን ሴራ ጉዳቱ የከፋ እንደሚሆን ጠቋሚ ናቸው፡፡ በተለይ በአዲስ የፖለቲካ ቅኝት ለሁሉም ነገር ‹‹እኔና የፖለቲካ አባሎቼ ብቻ ነን እምናውቅላችሁ›› የሚሉን ፖለቲከኞች እየበዙ ሲመጡ፣ ዛሬ የተያዝነው የጥፋት ጎዳና መጥፎ ውድመትና ስቃይ ያስከትልብናል፡፡ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ሕይወትም ያስቀጥፋል፡፡

ከላይ እንዳመላከትኩት የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ ‹‹አትፈርስም እንጂ›› በቢሊዮን በሚቆጠር ገንዘብ የሴራ ፕሮጀክት ቀርፀው እንደሚተገብሩ ለማስገንዘቤ፣ ከዚህ በፊት የጻፍኳቸው ጽሑፎቼና መጽሐፍቶቼ ዋቢ ናቸው፡፡ ካልተጠነቀቅንና ወደ እኛነታችን ካልተመለስን በቢሊዮን በሚቆጠር የገንዘብና የቁሳዊ ድጋፍ የሚተገበሩ ብዙ ሞቶች፣ ብዙ ግድያዎችን የሚያስከትሉ ሴራዎች አሉ ብዬ እገምታለሁ፡፡ እዚህ ላይ አንባብያን በ2012 ዓ.ም. በጻፍኩት መጽሐፍ በምዕራፍ 5፣ በንዑስ ክፍል 5.2.4 ‹‹ኢትዮጵያ እንደ ኮንጎ›› ብዬ ከጻፍኩት ማስገንዘቢያ ኢትዮጵያና ኢትዮጵውያን የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክና የሕዝቦቿ ሰቆቃ፣ መራቆትና መታረዝ፣ በተለያዩ ግዛቶቿ በመቶዎች በሚቆጠሩ የተደራጁና የታጠቁ ኃይሎች የመታመስና የመገደል ዕጣ ፈንታቸው ለእኛም እንደማይደርሰን ምን ያህል እርግጠኞች ነን? ብዬ ያቀረብኩትን ጥያቄ ለመመለስ ይቻለን ዘንድ እንድናጠና፣ እንድንመራመር፣ የሴራዎችን ጥልቀትና ስፋትም እንገምት ዘንድም አበክሬ እጠይቃለሁ፡፡

የውጭ ኃይሎች የመሬትና የማዕድናት ዝርፊያ

ኢትዮጵያ ዛሬ እየገጠማት ያለው የፖለቲካ ችግር አይደለም፡፡ የኢኮኖሚ በተለይ ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንጂ፡፡ ከ1940ዎቹ ጀምሮ በመሬት ዙሪያ በሚያጠነጥን የፖለቲካ ችግር ኢትዮጵያ በውጭ ኃይሎች ሴራና ተንኮል እየታመሰች፣ ልጆቿ እርስ በርስ እየተጋደሉ እዚህ ደርሰዋል፡፡ በእነ ጄኔራል መንግሥቱ ንዋይ የተመራው የ1950ዎቹ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በተለያዩ ጸሐፍት የተለያየ ማብራሪያ ቢቀርብለትም፣ በአንዳንዶች በገርማሜ ንዋይ ኮሙዩኒስታዊ አስተሳሰብ የተቃኘ የሀብት መደላደል ፍትሐዊ ጥያቄ ይዘት እንደነበረው ሊገለጽ ቢሞከርም፣ በዋነኛነት ይህ ሰው በምዕራባውያን የመሬትና የማዕድናት መበዝበዝ ሴራ ውስጥ ገብቶ የቀሰቀሰው ጉዳይ እንደነበር የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ መፈንቅለ መንግሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ በመሬት ይዞታ ላይ ሊወስዱት ከነበረው የፖሊሲ ማሻሻያና ትግበራ ጋር የተገናኘ ጉዳይ እንደነበርም መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

በንጉሡ ዕሳቤ በ1945 ዓ.ም. የመሬት አዋጅን ሥራ ላይ በማዋል፣ የመሬት ጭሰኝነትን ከአገራችን ጨርሶ ለማስወገድ፣ አዋጁንም ተግባራዊ ለማድረግ፣ ሰፊ የልማት ፕሮጀክት ተቀርፆ ወደ ትግበራ የተሄደበት አቅጣጫ ለመፈንቅለ መንግሥቱ መንስዔ መሆኑን ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት በ2012 ዓ.ም. ‹‹ሕይወቴ…›› በሚል ርዕስ በጻፉት መጽሐፍ በዝርዝር አስረድተውናል፡፡ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው ለአዋጁ ተፈጻሚነት መሪዎች የነበሩትን እነ ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊን ያስገደለ ነበር፡፡ ለዚህ ሴራ ዋነኞቹ አስተባባሪዎች የምዕራባውያን የአደጉ አገሮች መንግሥታት አምባሳደሮች መሆናቸውን፣ ከፕሮጀክቱ አስፈጻሚዎች አንዱ ሊሆኑ ከነበሩት ከደጃዝማች ወልደ ሰማዕት መጽሐፍ በተለይ በምዕራፍ ዘጠኝ በሰፊው መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል፡፡

ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መመሥረት ጋር ተያይዞ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም በምዕራቡ ኢምፔሪያሊስት አገሮች ከተማሩ ‹‹ምሁር›› ተብዬዎች መሀል እየመለመሉ፣ የአገራችንን መሬትና በውስጧ የያዘችውን ሀብት ተጠቃሚ ያደርጓቸው ዘንድ በገንዘብና በተንደላቀቀ ኑሮ ዘዬ በማማለል እንደ መሣሪያነት እየተጠቀሙባቸው ይገኛሉ፡፡ ዛሬም እነዚህን መሰሎችን በገዥም ሆነ በተቃዋሚ የፖለቲካ ቡድኖች ጎራ ውስጥ ሰግስገው ዘርን፣ ጎሳን፣ ብሔርን፣ ቋንቋን፣ ሃይማኖትን፣ ወዘተ ሽፋን አድርገው ለራሳቸው ጥቅም ማስከበሪያ ሰዋዊ መሣሪያ አድርገዋቸዋል፡፡ በረብጣ ዶላር ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ ክፍያ በተለያዩ መንግሥታዊ፣ ሕዝባዊ፣ ዓለም አቀፋዊ፣ እንዲሁም በግል ዘርፍ ተቋማት ውስጥ አሠማርተው ለኢትዮጵያ መዳከም፣ ለኢኮኖሚና ለማኅበራዊ ብሎም ለባህላዊና ሃይማኖታዊ የሀብት ክምችቶች መውደም የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎችን የእኩይ ሥራቸው መሣሪያዎች አድርገው እየተጠቀሙባቸው ነው፡፡

በእነዚህ ባንዳዎች በሚሠሩ ሴራዎች ኢትዮጵያዊ ኢትዮጵያዊን ሲገድል ጉዳዩ የዘር፣ የጎሳ፣ የብሔር፣ የሃይማኖት እንዲመስልም ይደረጋል፡፡ ጉዳዩ ግን ከመሬት ጋር የተያያዘ፣ በዋነኛነት ይህንን ሀብት ለውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንዲሆን ከሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ለውጭዎቹ ጥቅም ማግኘት ደንቃራ ይሆናሉ ተብለው የሚገመቱ ዜጎችን በዘር ፈርጆ ካሉበትና ከሠፈሩበት አካባቢ የማስለቀቅና የማሳደድ ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የውጭዎቹ በኢንቨስተርነት ስም መሬትን በተለይ በጥናት የሚያውቋቸውን የማዕድናትና የከበሩ ድንጋዮች ሥፍራዎችን ለመያዝ ሥር እየሰደዱ ይገኛሉ፡፡

የኬንያ መሪ የነበሩት ጆሞ ኬንያታ በአንድ ወቅት ቅኝ ገዥዎች መጽሐፍ ቅዱስ ሰጥተውን ወደ ላይ አንጋጠን ስንፀልይ፣ እነሱ መሬታችንን ዘርፈው ጨረሱት እንዳሉት ሁሉ፣ ዛሬ ኢትዮጵያን በፖለቲካ ትርክት ሳቢያ እንዲገዳደሉ እያደረጉ፣ የውጭዎቹ በኢንቨስተርነት ስም መሬታችንና የማዕድን ሀብታችንን ባለቤትነት በእጃቸው ለማስገባት ለ12ኛው ሰዓት ሩብ ጉዳይ ላይ የደረሱ ይመስላል፡፡

የሚዲያውና የፖለቲካው ቅኝት

የውጭ ኃይሎች የኢኮኖሚ የበላይነትን ለመያዝ ያግዛቸው ዘንድ ሚዲያውንም በመሣሪያነት ይጠቀማሉ፡፡ የኢትዮጵያ የዛሬ ችግሮቿ ዋነኛ ጠንሳሾችና ደጋሾች የውጭ ኃይሎች ስለመሆናቸው፣ አጀንዳውም ኢኮኖሚያዊ ስለመሆኑ ለማስገንዘብ እኔም ሆንኩ እኔን መሰሎች ያደረግነውን ጥረት መደበኛውም ሆነ ኢመደበኛው የሚዲያ ተቋማት ሊያዳፍኑት ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡ ችግሮቻችን ሁሉ ፖለቲካዊ መስለው እንዲታዩ የሚተገበር ሴራ እንዳለም እንድጠረጥር አድርጎኛል፡፡

የውጭዎቹ ለእኛ አዛኝ ዕርዳታና ድጋፍ ሰጪ፣ ሰብዓዊ ልግስና ያላቸው ቸር ፍጡሮች እንደሆኑ ተደርገው እንዲታዩም በሚዲያው እየታገዙ ነው፡፡ ኢትዮጵውያን ከተኛንበት ነቅተን፣ ዋነኛ የችግሮቻችን መንስዔዎች የውጭ ኃይሎች መሆናቸውን ማወቅና መገንዘብ አለብን፡፡ የእነዚህ ኃይሎች ዋነኛ የሴራ መሣሪያዎች ደግሞ ትውልደ ኢትዮጵውያን የሆኑ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎችና ኪራይ ሰብሳቢዎች፣ በእነዚህም ቀጥተኛም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የተደራጁ የሚዲያ ተቋማት እንደሚገኙበት፣ ቢያንስ መገመት ይገባል፡፡ የፖለቲካ ኪራይ ሰብሰቢ ማለት ፖለቲከኞች ያላቸውን የፖለቲካ ሥልጣንና የኃይል ግንኙነት ተጠቅመው መንግሥትንና የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ብልፅግናቸው ማዋል ነው (ከፍራንሲስ ፉከያማ እ.ኤ.አ. በ2011 መጽሐፉ ገጽ 141)፡፡

ኢምፔሪያሊዝምና ዴሞክራሲ

ያደጉ ኢምፔሪያሊስት መንግሥታት የታዳጊ አገሮች ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲኖራቸው ለማድረግ የሚጥሩና የሚሹ ሳይሆን ለኢኮኖሚ ጥቅማቸው፣ በኢትዮጵያም መሬትና ተጓዳኝ ሀብቷን መዝረፍ፣ ሕዝቡን በቁጥርም ሆነ በይዘት አመንምነው ከተቻላቸውም በሌሎች አገሮች እንዳደረጉት ጨርሰው መኖር ነው፡፡ ይህ ታሪካዊ ተሞክሯቸው ነው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ አሜሪካን ኢንዲያንስ ዝርያዎች እንዲጠፉ እየተደረገ ነው፡፡ በደቡብ አፍሪካ ነጮቹ በኋላ ራሳቸውን አፍሪካነርስ ያሉት ወደ እዚያች ምድር ከመምጣታቸው በፊት የነበሩትን ነባር ሕዝቦች (ኮሆሺያኖች) እንዲጠፉ አድርገዋል፡፡

የኢምፔሪያሊስት አገሮች መንግሥታትና የእነሱ ጉዳይ አስፈጻሚዎች የሆኑት እንደ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የመሳሰሉት፣ ለታዳጊ አገሮች የሚያሰሙት የመልካም አስተዳደር ጩኸት ፖለቲካዊ የማስመሰያ ትርክት ነው፡፡ ለእነሱ ዴሞክራሲ የኳስ ጨዋታቸው ‹‹ኳስ›› መጠሪያ ስም ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎች፣ በተለይ ደግሞ ከ1940ዎቹ ጀምሮ እየመለመሏቸው የመጡትና ዛሬ በዳያስፖራ ስም ጭምር በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ወደ አገር እንዲመለሱ ያደረጓቸው አብዛኞቹ የዚህ ጨዋታ አባላት ናቸው፡፡ በዚህ ዙሪያ ዝርዝር ነገሮች እዚህ ጽሑፍ ውስጥ ለማቅረብ የቦታ ጥበት አለ፡፡ ከዚህ በፊት በጻፍኳቸው መጽሐፎቼ ውስጥ ግን ስላብራራኋቸው፣ ማንበብ ለምትፈልጉ በ2012 ‹‹ኢኮኖሚው ሦስቱ ፖለቲከኞችና ፖሊሲ›› ብዬ ከጻፍኩት መጽሐፍ የሚከተሉትን ንዑስ ክፍሎች ቢያነቡ እመክራለሁ፡፡ ከምዕራፍ አንድ ዴሞክራሲ እንደ ኳስ፣ ኢትዮጵያ እንደ ኳስ ሜዳ፣ ልሂቃን፣ ሙያተኞችና ምሁራን ምንና ምን ናቸው፡፡ ከምዕራፍ አምስት የምዕራቡ ካፒታሊዝምና የታዳጊ አገሮች መበዝበዝ፣ ኢትዮጵያ እንደ ኮንጎ፣ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና ሲአይኤ፣ የፖለቲከኞች ክፍፍል፣ ዳያስፖራውና ፖሊሲ፣ ብሔርተኝነት፣ በርቀት ቅኝ የመግዛት ሴራና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች አፍራሽ ተልዕኮ፡፡ ከምዕራፍ አሥራ አራት ኪራይ ሰብሳቢነትና አሻጥር የሚለውን፣ በ2013 ዓ.ም. ‹‹ኮርፖራቶክራሲ…›› በሚል ርዕስ ከጻፍኩት መጽሐፍ ደግሞ ቅኝና በርቀት በሥውር ቅኝ መገዛት፣ የመሪዎችና የውጭ ኃይሎች ተዛምዶ፣ በውጭ ኃይሎች የሚመራ ኢኮኖሚ ብልፅግና አያመጣም፡፡ የውጭ ኃይሎችን ለልማት መጠቀምና ሰብዓዊ ካፒታል ሙያተኞች፣ የሙያ ማኅበራትና የኢኮኖሚ ባንዳ ንዑስ ክፍሎችን፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪ ሪፖርተር ጋዜጣ ካወጣቸው የርዕሰ አንቀጽ ጽሑፎቹ መሀል የሚከተሉትን ኢትዮጵውያን ደጋግመው እንዲያጠኗቸውና እንዲወያዩባቸው እመክራለሁ፡፡ በእሑድ ዕትሙ ሚያዝያ 20 ቀን 2011 ዓ.ም. በርዕሰ አንቀጹ ‹‹ለአገር የማይፈይድ ዕውቀት ዕርባና የለውም›› በሚል ከጻፈው መሀል የሚከተሉትን በድጋሚ ቢያጠኗቸው፡፡

‹‹. . . ሚሊዮኖች በረሃብ እየተሰቃዩ፣ ከእጅ ወደ አፍ በሆነ የሰቆቃ ኑሮ መከራ እያዩ፣ በመጠለያ ችግር እየተቆራመዱ፣ የአገሪቱ ምሁራንና ልሂቃን ለአገርና ለሕዝብ ማበርከት ያለባቸውን አስተዋጽኦ ዘንግተው መፍትሔ አልባና የሰለቸ የፖለቲካ ዲስኩር ላይ ተጥደዋል፡፡ ከትምህርት ማዕድ የተቋደሱት ዕውቀት ለአገር ፋይዳ ከሌለው፣ የትምህርት ካባ ደርቦ መንጎማለል ምን ያደርጋል? ለዘመናት ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ድህነትንና ኋላቀርነትን ማስወገድ ያልቻሉ ምሁራን ከንቱ ወሬ ምን ያደርጋል? . . .  የገበዩት ዕውቀት እየባከነ አገር እየተጎዳች ነው፡፡ . . . ለኢትዮጵያ አንድም አስተዋጽኦ ሳይኖራቸው ሊያፈርሷት ግን እንቅልፍ ያጣሉ፡፡ . . . ለእነሱ በጣም ቀላሉ ሥራ ቀውስ ፈጥሮ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ ነው፡፡ . . . ለአገር ህልውና ደንታ የሌላቸው ምሁራን ተብዬዎች ምን ይፈይዳሉ? . . . በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ የሙያ መስኮች ሠልጥነናል የሚሉ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ደሃ አገር ውስጥ መኖራቸውን እስኪረሱ ድረስ ማኅበራዊ ሚዲያ ውስጥ መሽገው ለአገር የማይጠቅም ነገር ሲያቦኩ ውለው ያድራሉ፡፡ . . . የሚረጩት መርዝ በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ፣ እነዚህ ፋይዳ ቢሶች በዚህ ከቀጠሉ የአገር ዕጣ ፈንታ ያሳስባል፡፡ . . . በአጠቃላይ አገርን በሚያጠፉ ከንቱ ድርጊቶች ውስጥ የተሰማሩ ምሁራንና ልሂቃን ተብዬዎች ዕውቀታቸው ለጥፋት እየዋለ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ለአገር ፋይዳ የሌለው ዕውቀት ደግሞ ዕርባና ቢስ መሆኑን ይረዱ!፡፡

በየካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. በርዕሰ አንቀጹ ‹‹ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የግድ ነው!›› በሚል ከጻፈው መሀል የሚከተሉትን በድጋሜ ቢያጠኗቸው ለዛሬዪቱ ኢትዮጵያ የወደፊት ጉዞ መያዝ የሚገባዎትን መስመር በሚገባ ያመላክትዎታል፡፡

‹‹. . . ኢትዮጵያ ከተለያዩ አቅጣጫዎች በምዕራባውያን ኃይሎች ከፍተኛ ጫና እየተደረገባት ነው፡፡ በሁሉም ዲፕሎማሲያዊ ግንባሮች እየተደረገ ያለው ጫና በውስጣዊ አንድነትና ጥንካሬ እንዲረግብ ካልተደረገ፣ በተለያዩ ማዕቀቦች በማሽመድመድ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተን አደጋ ማጋጠሙ አይቀሬ ነው፡፡ . . .ጭቆናና በደልን አሜን ብሎ ለመቀበል አሻፈረኝ የሚል መንፈስ የፈጠረውና የሥነ ልቦና ፈውስ የሆነው የዓድዋ ድል በዘመኑ የነበሩ ኃያላን ቅኝ ገዥዎችን ከማሳፈሩም በላይ፣ ቅኝ ተገዥዎችን ለትግል ያነሳሳ ታላቅ ተምሳሌነት ነበር፡፡ ለዚህም ነው ከዓድዋ ድል ማግሥት ጀምሮ በተለይ የምዕራባውያን ቅኝ ገዥዎች ይህንን የአይበገሬነት መንፈስ ለመስበር ሲያሴሩ የነበሩት፡፡ ለዚህ ዓላማ ስኬት ደግሞ ኢትዮጵያን በተለያዩ ፈርጆች ማጎሳቆል፣ ደካማ ጎኖቿን እያነፈነፉ ማሳፈር፣ የረሃብና የኋላቀርነት ተምሳሌት ማድረግ. . .፣ የውስጥ ተላላኪዎችን በማደራጀት፣ የማንነትና የእምነት ልዩነቶችን በማጋጋል፣ አንድነትን መሸርሸር፣ እርስ በርስ ማባላትና የመሳሰሉ ሴራዎችን ፈጽመዋል፡፡ በዚህ ወቅት ምዕራባውያንና ታሪካዊ ጠላቶች ከየአቅጣጫው ችግር እየፈጠሩ አንድ መሆን አለመቻል የሚያስከትለው መዘዝ ከሚታሰበው በላይ ነው፡፡ ‹‹. . . በኢትዮጵውያን ላይ በምዕራባውያን እየተደገሰ ያለውን ሴራ በአንድነት ማምከን ያስፈልጋል፡፡ . . . ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ኃላፊነት መሆን አለበት!››፡፡

ማጠቃለያ

በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገሮች ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችና ሴረኞች በድጋሚ እንዲገነዘቡት የምሻው በሪፖርተር ጋዜጣ ከሚያዝያ 23 እና 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በሁለት ተከታታይ ክፍሎች ለኅትመት ያበቃሁት ጽሑፌ ውስጥ የሰጠኋቸው ሦስት የዕሳቤ ማዕቀፎች፣ ለዚህኛው ጽሑፌም ማጠቃላያነት ያላቸውን ጠቃሚነትና አንድምታ ነው፡፡ ሦስቱ ዕሳቤዎችም እንደሚከተለው በማጠቃለያ ምክረ ሐሳብ ማጠንጠኛነት ቀርበዋል፡፡

  1. የአንድ ‹‹ሰው›› የሆነ ኢትዮጵያዊ ሞት ከማናቸውም በላይ ያመኛል፣ ያሳዝነኛል፡፡ ግን ሺሕ አይደለም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መስዋዕት ሆነውም ኢትዮጵያ አትፈርስም፣ ትኖራለች፡፡
  2. ምንም እንኳ የቅርብ ጊዜ ግድያዎችና ጥቃቶች ዘግናኝና አሰቃቂ ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ ሰላምና ደኅንነት ከማኅፀኗ በወጡ የዘር፣ የሃይማኖት፣ የብሔር፣ የፖለቲካ ቡድን ወገንተኝነት በሌላቸው የመከላከያና የፀጥታ ኃይል ልጆቿ ይጠበቃል፡፡
  3. የውጭ ኃይሎችን በሚያስፈልገው መንገድ ሁሉ ታግሎ አደብና ሥርዓት በማስያዝ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት፣ በአገራዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ዕውቀት፣ ጥበብና አስተምህሮ ለሀብቶቿ አስተዳዳሪና መሪ መንግሥት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ይህ እንቅስቃሴም አግላይ ያልሆነ፣ ከዓለም ኅብረተሰብ ጋር ተወዳዳሪ የሆነች፣ በሁለንተናዊ ዓውዳዊ ይዘቷ የበለፀገች አገር ያደርጋታል፡፡ ለዚህም በዴሞክራሲ ስም አገርን ለውጭ ኃይሎች መሸጥ እንዲቆም ወይም እንዲከስም እውነተኛ የኢትዮጵያ ልጆች በኅብረትና በአንድነት ይነሳሉ፡፡ በሒደትም በዘር፣ በጎሳ፣ በጎጠኝነት፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ ወዘተ ጥላ ሥር ሆነው ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ባንዳዎችን በቅድሚያ በማስተማርና አባታዊ ምክር በመስጠት አደብ ማስገዛት፣ አስፈላጊ ከሆነም በፈረጠመና ሕዝባዊ ቅቡልነት ባለው የሥልጣንና የኃይል ጫና አገራዊ መስመር መያዛቸው አይቀሬ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው demesec2006@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...