Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርአርዓያነት ያለው በጎ ተግባር ከፈጸሙ ጎረቤታማቾች ልንማር የሚገባን

አርዓያነት ያለው በጎ ተግባር ከፈጸሙ ጎረቤታማቾች ልንማር የሚገባን

ቀን:

ሠፈሩ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 02 በጀሞ አካባቢ ቦስኮ ከሚባለው የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሙያ ማሠልጠኛ ማዕከል ቅጥር ግቢ ጀርባ ነው፡፡ ነዋሪዎቹ እንደየአቅማቸው የየራሳቸውን ቤቶች ሠርተውም ሆነ ገዝተው በሠፈሩ መኖር ከጀመሩ ዓመታት ሆኗቸዋል፡፡

በአካባቢው የነዋሪዎቹ ቁጥር እየጨመረ ቤቶቹም እየበዙ ሲመጡ በአንፃሩ ጎረቤት ከጎረቤት በመተዋወቅ የማኅበራዊ ሕይወታቸውም እንዲሁ ከመቀራረብና ከመግባባት ባለፈ የበለጠ ሊያድግ በመቻሉ፣ እነሆ ለሌሎች አርዓያነት ያለው በጎ ሥራ በመሥራታቸው ድርጊታቸው ከሚያሳድረው ትምህርት ሰጪነቱ ረገድ በዚህ መልኩ ተጽፎ ሊቀርብ ችሏል፡፡

ጉዳዩ እንዲህ ነው፡- በሠፈሩ እነዚህ ቤቶች በአብዛኛው ግንባታቸው ተጠናቆ ባለቤቶቻቸው ሳይገቡባቸው በነበሩት ረዥም ዓመታት በአካባቢው የነበሩ ትንንሽና ትልልቅ ንብረቶችን በግንባታ ላይ የነበሩ ቤቶች ለሥራው የሚጠቀሙባቸውን ዕቃዎችን በመጠበቅ ኃላፊነት ላይ የተሰማራ ስሙ ጉታ ቀጄላ የተባለ ዕድሜው በ40ዎቹ ውስጥ የሚገኝ ሁለገብ ችሎታ ያለውና ከምንም በላይ የነበረው ታዛዥነት፣ ታማኝነትና ቅንነቱ በጊዜው የቤታቸውን ግንባታ ጨርሰው መኖር የጀመሩትንም ሆነ ያላጠናቀቁትን ቀልብ የገዛ ነበር፡፡

- Advertisement -

ጉታ በመኖሩ ይላሉ ነዋሪዎቹ፣ የሠፈር ውኃ መስመር ቢበላሽ፣ የኤሌክትሪክ ገመድ ተበጥሶ አደጋ ያደርሳል ወይም በአካባቢው ላይ ችግር ይፈጠራል እንዲሁም ሠፈርተኛ ያልሆኑ ሰዎች ተገኝተው ዕቃ ያነሳሉ የሚል ቅንጣት ሥጋት እንዳልነበራቸውና እሱ ንቁ ሆኖ ሠፈሩን ከመጠበቁ በተጨማሪ በባህሪው ትንሽ ትልቅ ሳይል ለሁሉም ነዋሪዎች በአክብሮትና በፍቅር በመታዘዝና በማገልገል የሠፈሩን መሠረተ ልማት በሚችለው መልኩ እንዲሟላ የበኩሉን ያላሰለሰ ጥረት ያደርግ እንደነበረ ሁሉም ነዋሪ ይመሰክራል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ታዞ የልብን የሚያደርሰው ሲጠሩት አቤት ሲልኩት ወዴት በማለት ለሠፈሩ ሁለገብ አገልጋይ የነበረው ጉታ፣ በአንድ በዚሁ ሠፈር ነዋሪ በሆነ ሰው ለሥራ ወደ ሌላ ቦታ ተወስዶ ሳለ በቅርብ ርቀት ላይ በነበረ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ተይዞ ለጽኑ አደጋ ተዳረገ፡፡ በዚሁ ምክንያት በመሞትና በመኖር ውስጥ የነበረው ጉታ የደረሰበት አደጋ አስደንጋጭና ያልተጠበቀ ነበረና ሁኔታውን በሰሙት ነዋሪዎቹ ሁሉ ላይ ከፍተኛ መደናገጥን ሲፈጥር በተለይ ደግሞ ለሥራ የወሰደውን ሰው ያሳዘነና ያስለቀሰም ሲሆን፣ በአደጋው ምክንያት የጉታ አንድ ዓይኑ ማየት ስለተሳነውና ጉታም ፍፁም ራሱን በመሳቱ በቅርብ ወደ ሚገኝ ሆስፒታል እንዲወሰድ ተደረገ፡፡

ጉታ በነዋሪው ውስጥ ለዓመታት ባሳየው መልካም ታዛዥነቱ፣ ታማኝነቱና ቀናነቱ ብሎም ሁለገብ ችሎታው የተነሳ የተወደደና የተከበረም በመሆኑ የደረሰበትን አሳዛኝ አደጋ ለመስማት ጊዜ ያልፈጀም ከመሆኑ ባሻገር ሁሉም ከእንባና ከልባዊ ሐዘኑ በተጨማሪ ለጉታ ምን እናድርግ? ምንስ ነው ሊደረግለት የሚገባው? በማለት ኮሚቴ አቋቁሞ መነጋገር ተጀመረ፡፡ ኮሚቴው ጉታን በዘለቄታ ማገዝ በምን መልኩ ሊሆን እንደሚገባ አውጥቶና አውርዶ በማሰብ ከፊሉ የማስተባበሩን ሥራ በአንድ ወገን ሲያካሂድ፣ በሌላ ወገን ደግሞ ምንድነው ለጉታ ዘለቄታዊ ሕይወት ሊያኖረው የሚችለው የሚለውን ሐሳብ በማብላላት ነበር አንድ ውሳኔ ላይ የተደረሰው፡፡

‹‹መታዘዝ ከሰነፍ መስዋዕትነት ይበልጣል››  እንዲሉ ለዓመታት የሠፈሩ ጠባቂና ታዛዥ ዘርፈ ብዙ ባለሙያ ለነበረው ጉታ ቀጄላና በእሱ ተባራሪ ገቢ ትተዳደር ለነበረችው ባለቤቱ በሚገርምና ዛሬ እንዲህ አርዓያነታቸው በትምህርት ሰጪነቱ ሊቀርብ የቻለው ጎረቤታማቾች ‹‹ድር ቢያብር አንበሳ ያስር›› እንደተባለው ምን ሊገዛለት እንደሚገባ አጥንቶ ባቀረበው ኮሚቴ አማካይነት፣ የህንድ አገር ሥሪት የሆነች የ2021 ጄቢሲ ሞዴል ባጃጅ በጉታ ቀጄላ ስም በብር 320,000 የተገዛች ሲሆን፣ ከግዥው የተረፈውን ገንዘብ ብር 55,000 ደግሞ በእጁ አስረክበውታል፡፡

ትሁቱና ሁሌም ለነዋሪው ሠፈርተኛ አክብሮት ያለው ጉታ ከሁሉም ሰዎች ባየው ልባዊ መረባረብና ከፍተኛ ዕርዳታ ‹‹እኔ ምን አደረኩላቸውና ነው?›› በዚህ የኑሮ ውድነት ወቅት ይኼን የመሰለ ፍፁም ያልጠበኩትን ዕርዳታ ያደረጉልኝ በማለት እኔ ብድራቸውን ለመክፈል አቅም የለኝም፡፡ ብድራቸውን እሱ እግዚአብሔር ይክፈላቸው በማለት አደጋው ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ሕይወቱን በመታደጉ ዙሪያ ለሕክምና ከማድረሱ ጀምሮ በአለርት ሆስፒታል ዕርዳታ እንዲያገኝ ላደረጉትና ከትንሽ እስከ ትልቅ ገንዘብ ላዋጡት፣ ሁኔታውን ላስተባበሩት የኮሚቴ አባላት ልባዊ ምስጋናውን በራሱና በቤተሰቡ ስም አቅርቧል፡፡  

ውድ ይህንን በቅርቡ የተከናውነውን የመልካምነት መልዕክት አንባቢ ድንገተኛ አደጋ መቼና እንዴት እንደሚደርስብን አይታወቅም፡፡ ይሁንና ሁሌም በተሰማራንበት የሥራ መስክ በጨዋነት፣ በታዛዥነትና በታታሪነት እስከሠራን ድረስ ታማኝነታችን ራሱ ይከፍለናል፡፡ ከጉታ ሁለገብ አገልጋይነት፣ ታማኝነትና ጥንካሬ ተወዳጅነትን ከሠፈሩ ነዋሪዎች ደግሞ ፍቅርና ፈጥኖ ደራሽነትን ልንማር ችለናል፡፡

ፈጣሪ ለጉታ ቀጄላ ሙሉ ጤንነትን እንዲሰጠው በነዋሪዎቹም ውስጥ ፍቅርና መተባበሩ ዘመን እንዲሻገር እመኛለሁ፡፡

(ግርማ ባህሩ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...