Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናለደን ውጤቶች የተሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ሊገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ማሳጣቱ ተነገረ

ለደን ውጤቶች የተሰጠው ዝቅተኛ ትኩረት ሊገኝ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ ማሳጣቱ ተነገረ

ቀን:

በኢትዮጵያ የደን ውጤቶች ለሚባሉት ዕጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤና ሌሎችም የወጪ ንግድ ምርቶች የተሰጠው አነስተኛ ትኩረት፣ ከዘርፉ የሚገባውን የውጭ ምንዛሪ  እንዳይገኝ አድርጎታል ተባለ፡፡

ከአገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች የሚገኘውን ምርት ሰብስቦና በጥራት አዘጋጅቶ ለውጭ ገበያ የሚያቀርበው የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከዘርፉ የማይናቅ ገቢ ለአገሪቱ ቢያስገኝም፣ ምርቱ በኮንትሮባንድ ከአገር መውጣቱ፣ ለተፈጥሮ ሀብቱ በተሰጠው አነስተኛ ትከረት ሳቢያ፣ ያጋጠመው አገራዊ የምርት መቀነስ ዋነኞቹ ማነቆዎች ናቸው ተብሏል፡፡

ምንም እንኳን ምርቱን የግል ዘርፍ ላኪዎች ለውጭ ገበያ ቢያቀርቡትም ኮርፖሬሽኑ አንድ የአገልግሎት ክንፉ በሆነው የዕጣን፣ የሙጫ፣ የከርቤና የአበክድ ሽያጭ በ2013 የበጀት ዓመት ከ900 ሺሕ ዶላር በላይ፣ በ2014 ዓ.ም. ዘጠኝ ወራት ደግሞ ከ670 ሺሕ ዶላር በላይ ገቢ አግኝቷል፡፡

- Advertisement -

በ2012 ዓ.ም. ኮርፖሬሽኑ ከዘርፉ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ 747 ሺሕ ዶላር የነበረ ሲሆን፣ በአንፃሩ በ2011 የበጀት ዓመት 1.1 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱ አኃዛዊ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

ክንውኑ ካነሰባቸው ምክንያቶች መካከል በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በፀጥታ ችግር የተፈጥሮ ሙጫ ምርት በቀላሉ በድንበር አካባቢ በሕገወጥ መንገድ መውጣቱ ተጠቃሽ መሆኑን ኮርፖሬሽኑ አስታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እንዳለ ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ600 ሺሕ ዶላር በላይ ዋጋ ያላቸው የደን ውጤቶች ለውጭ ገበያ ቀርበዋል፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ የቀረበው ምርት 2,000 ሺሕ ኩንታል ያህል ነው ያሉት አቶ እንዳለ፣ ከ4,300 ኩንታል በላይ ኤክስፖርት መሆን የሚችሉ የተለያዩ የደን ውጤቶች በዚህ ወቅት በአዳማ የማዘጋጃና የማከማቻ ማዕከል እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ምርቱ በኮንትሮባንድ ከአገር ውጪ በከፍተኛ መጠን የሚወጣ በመሆኑ መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት ሊሠራበት እንደሚገባ የተናገሩት አቶ እንዳለ፣ የኮንትሮባንድ ንግዱ እንዳለ ሆኖ በተለይ በዘንድሮ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተከሰተው ድርቅ ለምርቱ አቅርቦት መቀነስ አንዱ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የደን ውጤቶቹ በአብዛኛው የሚሰበሰቡት ከትግራይ፣ ከአማራ፣ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ከኦሮሚያና ከሶማሌ ክልሎች ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ እነዚህን ምርቶች የሚሰበስበው በራሱ ማምረቻ፣ በዘርፉ ከተሰማሩ ማኅበራትና ግለሰቦች በግዥ መልክ መሆኑ ተገልጾ፣ በጠቅላላው አገሪቱን ባጋጠማት ድርቅና ሰው ሠራሽ በሆነው የፀጥታ ችግር ወደ ኮርፖሬሽኑ ማዕከል የሚመጣው ምርት ቀንሷል ተብሏል፡፡

‹‹ከኮንትሮባንድ አኳያ ዘርፉ በአገር ደረጃ የግብይት ሥርዓት የለውም፣ በተለይ የደን ውጤቶችን ማንኛውም ፈቃድ ያለው ኤክስፖርተር ነው ወደ ውጭ የሚልከው፣ ይህንን ችግር ለመቆጣጠር ፌዴራል ፖሊስና ጉምሩክ ኮሚሽን በጋራ የተቻላቸውን  ጥረት እያደረጉ ነው፤›› በማለት የተናገሩት አቶ እንዳለ፣ የጎረቤት አገሮች በሆኑት  የሶማሌ አዋሳኝና ሌሎች አገሮች ድንበሮች ምርቱ የሚሸጥበት ዋጋ በጣም ከፍተኛ መሆኑን፣ ክልሎች ለዘርፉ የሚሰጡት ትኩረት በጣም አናሳ መሆኑ የሚፈለገውን ያህል ውጤት እንዳይገኝ ካደረጉት ችግሮች ዋነኞቹ ናቸው ብለዋል፡፡

የአዳማ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ ያሉትን ደንበኞች እስካሁን ይዞ የቆየው አብዛኛው የሰበሰባቸው ምርቶች ከሁለትና ሦስት ዓመት በፊት የተሰበሰቡ በመሆናቸው ምክንያት ነው፡፡ በዘርፉ ላይ ትልቅ የመንግሥት ድጋፍ የሚያስፈልግ መሆኑን አያይዘው አስረድተዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ወደ ውጭ አዘጋጅቶ የሚልካቸው የተፈጥሮ ደን ውጤቶች መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው የሚሉት አቶ እንዳለ፣ ምክንያቱ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብቱ የተሰጠው ትከረት እየቀነሰ በመሆኑ ነው፡፡

የምርቱ ምንጭ የሆነውን ደን ለመንከባከብ ያለው እንቅስቃሴ በጣም አናሳ ስለሆነ የደን ሽፋን መቀነሱ ተጠባቂ ነው ያሉት አቶ እንዳለ፣ ባለውም ሀብት ላይ ብዙ ተዋናዮች ስለበዙበት ምርቱ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ፣ አገሪቱም ወደ ውጭ የምትልከው መጠን በሚፈለገው ልክ ያላደገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ደኑ በሚገኝባቸው ክልሎች በኅብረተሰቡ ዘንድ የገበያ ትስስር መፍጠር ወይም ወጣቶች ተደራጅተው ምርቱን እንዲያመርቱ በማድረግ፣ የኤክስፖርት ሥራውን ደግሞ በኮርፖሬሽኑ በኩል እንዲከናወን ለማድረግ ከክልሎች ጋር ሥራዎች መጀመራቸው ተገልጿል፡፡       

በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚሰበስበው የዕጣን ምርት ውስጥ ከ90 ከመቶ በላይ የሚሆነው ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ነው፡፡ የውጭ ገበያው የሚፈልጋቸው የዕጣን፣ የሙጫ፣ የከርቤና አበክድ ምርቶች ለመድኃኒት፣ ለጨርቃ ጨርቅ፣ ለምግብ፣ ለመጠጥ፣ ለኮስሞቲክስ (ሽቶና ሌሎችም) ለቀለምና ለመሳሰሉ ፋብሪካዎች ግብዓትነት ይውላሉ፡፡ በተለይም እነዚህ ምርቶች በብዛት ለተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ፣ ጀርመን፣ አሜሪካ፣ ቡልጋሪያ፣ ግሪክ፣ ቱኒዚያ፣ ቻይና፣ ቬትናም፣ የመንና ሆላንድ ገበያ ውስጥ የሚቀርቡ መሆናቸው ታውቋል፡፡

ለአገር ውስጥ ፍጆታ የሚውለው ዕጣን በተለምዶ ለመዓዛማ ጭስ አገልግሎት የሚውለው ሲሆን፣ ይህም በማበጠር ወቅት በዝቅተኛ ደረጃ የሚወጣው የምርቱ አንዱ ክፍል ነው፡፡

በተያያዘም የግብርና ሚኒስቴር በተያዘው ሳምንት መጀመሪያ የዕጣንና የሙጫ አመራረት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመደገፍ፣ የመዓዛማ ዘይቶች ማጣሪያ በመትከል እሴት በመጨመርና የምርት ጥራት በማሻሻል የገበያ ትስስር ተግዳሮቶችን በመፍታት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ማሳደግ እንደሚቻል የሚያመላክት የባለድርሻ አካላት የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የጥናት ውጤቶች እንደሚያመለክቱት የቆላማ አካባቢዎች የአርሶና የአርብቶ አደሮችን ኑሮ ለማሻሻልና የገቢ ምንጭ ለማስፋት በአካባቢዎቹ ያለውን የተፈጥሮ ሀብት ውጤት የሆነው የዕጣንና የሙጫ አመራረት በማዘመንና እሴት በመጨመር፣ መዓዛማ ዘይቶች በማምረት፣ የገበያ ትስስር ተግዳሮቶችን በመፍታት፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝት አሳድጎ ለአገር ኢኮኖሚ ተጨማሪ ገቢ ማስገኘት እንደሚቻል ተመክሮበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...