Saturday, May 18, 2024

ከሱዳን ትንኮሳ በስተጀርባ ማን አለ?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮ ሱዳን ድንበር ጉዳይ ከሰሞኑ ዳግም የውዝግብ ማዕከል ሆኖ ነው የሰነበተው፡፡ እሑድ ሰኔ 19 ቀን 2014 ዓ.ም. የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ያወጣው መግለጫ፣ ኢትዮጵያን ለሰባት ወታደሮችና ለአንድ ሲቪል ሞት ተጠያቂ ያደረገ ነበር፡፡ የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ከዚህም አልፎ ኢትዮጵያን ለማስፈራራት የሚዳዳውም ዓይነት ነበር፡፡

‹‹ለዜጎቻችን ሕልፈት የበቀል አፀፋ አለን›› ነበር ያለው የሱዳን ጦር በመግለጫው፡፡ ሱዳን በአንድ በኩል ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አቤት ማለቷ ቢነገርም፣ ከዚህ ጎን ለጎን ግን በኢትዮጵያ ላይ የብቀላ ዕርምጃ በመውሰድ በራሷ ፍትሕ ለማስፈን እንደምትፈልግ በግልጽ ስትናገር ተደምጣለች፡፡

የሱዳን ድንፋታ አጨብጫቢም አላጣም፡፡ ከካይሮ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታ አልሲሲ ለሱዳን ዜጎች ሕልፈት ሐዘናቸውን ሲገልጹም ተሰምቷል፡፡ በዚህ መሰሉ የግብፆች አይዞህ ባይነት ተበረታትተው በሚመስል ሁኔታ ሰኞ ዕለት ሱዳኖች በኢትዮጵያ ላይ ከባድ መሣሪያ ሲተኩሱ መዋላቸው ነው የተሰማው፡፡ የዓለም አቀፍ ሕግ መርሆዎችን ጥሳ ሱዳን የኢትዮጵያ ድንበርን በወረራ መያዟ ሳያንስ፣ ‹‹ሰባት ሰዎች ሞቱብኝ›› በሚል ሰበብ በከባድ መሣሪያ ተኩስ ትንኮሳ በማድረግ ላይ መሆኗ ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ የሱዳንን ክስ ውድቅ አድርጎታል:: የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መደበኛ የፀጥታ ኃይል በሱዳኖች ላይ አንዳችም ጥቃት አለማድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡ የሱዳን ጦር ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቆ በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ ሚሊሻዎች ጋር በከፈተው ግጭት የሰዎች ሞት መከሰቱን፣ ለዚህም ሐዘን የተሰማው መሆኑን ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ያመለክታል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ሁልጊዜም ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚገዛ ያመለከተው ይኼው መግለጫ፣ የሱዳን መንግሥት ሰሞነኛውን ግጭት ወደ ማቀጣጠል እንዳይገባ ነው ያሳሰበው፡፡

ይኼንን የኢትዮጵያ መንግሥት ውትወታም ሆነ ትዕግሥት የሱዳን መሪዎች ለመስማት ፈቃደኞች የሆኑ አይመስሉም፡፡ የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤቱና የጦሩ መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሀን ወደ አወዛጋቢው የአልፋሽቃ ድንበር መሄዳቸው ተዘግቧል፡፡ ጄኔራሉ ወደ እዚህ አካባቢ የመጡት በዚያ የሠፈረውን ጦራቸውን ለማበረታታትና በኢትዮጵያ ላይ የጀመረውን ትንኮሳ አጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግ መሆኑ ተነግሯል፡፡

ባልሰመረ የፖለቲካ ሽግግር ከኢትዮጵያ በከፋ የፖለቲካ ኢኮኖሚ ምስቅልቅል ውስጥ ወድቃ ስትዳክር የቆየችው ሱዳን፣ ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ እያደረገች ያለችውን ትንኮሳ ሌላ ገጽታ እያሰጣት ይገኛል፡፡ ‹‹ሱዳን የውስጥ ፖለቲካዋን መቼ በቅጡ አረጋግታ ነው ከኢትዮጵያ ጋር ፀብ ያለሽ በዳቦ የምትለው?›› የሚለው ብዙ ያጠያይቃል፡፡ ‹‹ሱዳን ማንን ከጀርባ ተማምና ነው ጥቃቱን የጀመረችው?›› ከሚለው ጥያቄ እኩል ደግሞ፣ ‹‹ጥቃቱን ወቅት ጠብቃ ክረምት ላይ ለምን ልትከፍት ቻለችም?›› የሚለው ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነው፡፡

‹‹አብደራፊ አካባቢ ሰው እንደሞተባቸው ተናግረዋል፡፡ በዚህ ንዴት ይመስላል አፀፋ እንመልሳለን ብለው በወረሩት አካባቢ ከባድ መሣሪያ ሲተኩሱ ውለዋል፡፡ እኔ የምገኘው ለአካባቢው ቅርብ በሆነ ገጠር ቢሆንም፣ እስካሁን ግን በጥቃታቸው የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አረጋግጫለሁ፤›› በማለት የአካባቢውን ሁኔታ የሚያውቁት አቶ ተስፉ የሺወንድም ናቸው፡፡ የሱዳንን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉትና ለረዥም ዓመታት በካርቱም የኖሩት አቶ ተስፉ፣ የሰሞኑ ትንኮሳ መነሻ ብዙም ግልጽ እንዳልሆነ ነው የጠቀሱት፡፡

ሱዳን ከሰሞኑ በኢትዮጵያ ላይ የፈጸመችው ትንኮሳ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ የታወጀ ከባድ ጦርነት አድርገው የቆጠሩት ብዙ ነበሩ፡፡ የተለያዩ የማኅበራዊ ትስስር ገጾች ተዋንያንና የመገናኛ ብዙኃን፣ ‹‹ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ጦርነት ከፈተች›› ብለው ወሬውን በሰፊው ተቀባብለውታል፡፡ ይሁን እንጂ በአካባቢው ካሉ የመረጃ ምንጮች ዘግይቶ እንደተሰማው፣ ሱዳኖች ሰኞ ዕለት በከባድ መሣሪያ በመተኮስ ትንኮሳ መፈጸማቸውን ከመጠቆም በቀር፣ በአካባቢው ጦርነት መጀመሩን የሚያረጋግጡ ሆነው አልተገኙም፡፡

የሱዳን ጦርና የኢትዮጵያ ኃይሎች ተፋጠው በሚገኙበት፣ ሱዳኖች ‹‹የእኔ ነው›› ብለው በጉልበት በያዙት የአልፋሽቃ የእርሻ መሬት አካባቢ ከወረራው በፊትም ሆነ በኋላ አለፍ ገደም እያለ ግጭት መከሰቱ የተለመደ ነው፡፡ ሰሞነኛውን ትንኮሳ ካለፉት የተለየ የሚያደርገው ወይም ከበድ ያለ ጦርነት ነው የሚያሰኘው ተጨባጭ መረጃ እስካሁን አልወጣም፡፡ ይሁን እንጂ ሱዳኖቹ ጉዳዩን የተመድ ፀጥታው ጥበቃ ምክር ቤት አጀንዳ ለማድረግ አቤቱታ ማስገባታቸውን፣ እንዲሁም ጉዳዩ በሱዳን፣ በግብፅና በዓረብ ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን እንዲሰጠው ያደረጉት ጥረት ብዙ የሚያጠያይቅ ነው ተብሏል፡፡ ሱዳኖቹ በኢትዮጵያ የወከሏቸውን አምባሳደር ወደ አገር ቤት መጥራታቸውና በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደርን ማብራሪያ እንጠይቃለን ማለታቸው ደግሞ ጉዳዩ የት ድረስ እንዲጋጋል እንደፈለጉ ያመለክታል፡፡

ትናንት ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ ሱዳን የተማረኩት ወታደሮቼን የኢትዮጵያ ጦር ገደለ ብላ ያሰማችው ክስ መሠረተ ቢስ ነው ሲል አስተባብሏል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ ግጭቱ ተከስቷል በተባለበት አካባቢ ሠራዊት አለመሰማራቱንም ነበር ያረጋገጠው፡፡

‹‹መንግሥት ትዕዛዝ ካዘዘ ግን በቂ ምክንያት ስላለን መከላከያችን እንደ ሽፍታ ተደብቆ ሳይሆን፣ እንደ መደበኛና ዘመናዊ ጦር በግልጽ፣ በታወቀና በታወጀ መልኩ በኃይል ከተያዘ ከግዛታችን አስወጥተን የኢትዮጵያን ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሚያስችል ሁለንተናዊ ቁመና እንዳለው ለመግለጽ እንወዳለን፤›› በማለት ነበር የመከላከያ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር (ኮሎኔል) ጌትነት አዳነ  የተናገሩት፡፡

ሉዓላዊ መሬቷ በሱዳን ተወሮ፣ ወራሪው አገር ጥቃት ከፍቶ፣ ተወራሪው አገር የምላሽ አፀፋ አልሰጠሁም የሚል መግለጫ መስጠቱ፣ በአንዳንዶች ዘንድ አሳማኝ አልነበረም፡፡ ሱዳኖች ድንበር ጥሰው በገቡበት ቀጣና አገር ለመጠበቅ የተሠለፈው ማነው ብቻ ሳይሆን፣ ለሱዳኖቹ እንደ አመጣጣቸው ምላሽ የሰጠው አካልም ማንነት ሲያጠያይቅ ነው የሰነበተው፡፡

ለሱዳኖች ሰሞነኛ ትንኮሳ ተመጣጣኝ አፀፋ በኢትዮጵያ በኩል መሰጠቱ ተነግሯል፡፡ የሱዳን ኃይሎች እንደ አመጣጣቸው ሁሉ ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ የሚያደርግ ተመጣጣኝ ምላሽ እንደተሰጣቸው ተሰምቷል፡፡ ሆኖም ከዚህ ይልቅ ከሱዳኖች ጀርባ የተሠለፈውን ኃይል በተመለከተ ከሁለቱም አቅጣጫ ተመሳሳይ ስም ሲነሳ ነው የታየው፡፡

ሱዳኖች በግብፆች አይዞህ ባይነት የሕወሓት ኃይልን በማሠለፍ ለትንኮሳው ተሰማርተዋል የሚለው ክስ፣ በመከላከያም ሆነ በአካባቢው ምንጮች ተደጋግሞ ተነስቷል፡፡ የሰሞኑ ጥቃት/ትንኮሳ ዋና ግብም የሕወሓቶችን በወልቃይት በኩል መተላለፊያ ኮሪደር የማስከፈት ብቻ ሳይሆን፣ የግብፅና የሱዳን ሦስተኛ ዙር የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሙሌት የማስተጓጎል ፍላጎት የተከተለ ነው በሚል እየተዘገበም ነው፡፡

ሪፖርተር ከጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ ከታማኝ የአካባቢው ምንጮች ባገኘው መረጃ መሠረት፣ ከሁለት ወራት በፊትም በዚሁ አወዛጋቢ የእርሻ ድንበር በኩል በሕወሓትና በሱዳኖች ቅንጅት ጥቃት ተከፍቶ እንደነበር አረጋግጧል፡፡ ረገም፣ መቻችና ዱግዲ በሚባሉ አካባቢዎች የትግራይ ክልል ጦርነት ሲጀምር ወደ ሱዳን ከዘለቀ የሕወሓት ኃይል የተውጣጣ ጦር ሱዳኖች ማስፈራቸውን እነዚሁ ምንጮች አረጋግጠዋል፡፡ መለስ፣ ሰዓረ፣ ወዘተ በሚል የብርጌድ ስሞች የተደራጀው ይህ በሱዳኖች የሚደገፍ የሕወሓት ኃይል ጥቃት ከፍቶ የነበረ ቢሆንም፣ በአካባቢው በሚንቀሳቀሱ የአማራ ሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት ጥቃቱ መክሸፉን ነው የመረጃ ምንጮቹ ያረጋገጡት፡፡ በወቅቱ በሱዳኖች የሚታገዘው ከሱዳን አቅጣጫ የሠፈረውን የሕወሓት ሠራዊት ከቆፈራቸው ሦስት ምሽጎች ሁለቱን ለቆ እንዲወጣ ቢገደድም፣ ነገር ግን በባህር ሸባብ አቅጣጫ ምሽጉን ሳይለቅ መቅረቱ ተሰምቷል፡፡ ይህ የሆነው ደግሞ በኢትዮጵያ ኃይሎች የተሰጠው አፀፋ ለጊዜው እንዲቆም በመደረጉ መሆኑን ነበር የመረጃ ምንጮቹ ያረጋገጡት፡፡

ለሰሞኑ የሱዳኖች ትንኮሳም የኢትዮጵያ ኃይሎች ተመጣጣኝ አፀፋ ሰጥተዋል ቢባልም፣ ሱዳኖች በወረራ ከያዙት የኢትዮጵያ ሉዓላዊ መሬት ሙሉ ለሙሉ ለቀው እንዲወጡ የሚያስገድድ ዕርምጃ ስለመወሰዱ ያረጋገጠ ወገን የለም፡፡

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹መንግሥት ትዕዛዝ ከሰጠኝ የአገሪቱን ሉዓላዊ ዳር ድንበር ለማስከበር ዝግጁ ነኝ፤›› የሚል አቋሙን ይፋ አድርጓል፡፡

አሁን ተጠባቂው ጉዳይ የመንግሥት ትዕዛዝ ከሆነ፣ መከላከያና ሌሎች የኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሎች የሱዳኖችን ትንኮሳ እንዲያስታግሱ መንግሥት ትዕዛዝ የሚሰጠው መቼ ነው? የሚለው ጥያቄ መነሳቱ የማይቀር ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለጉርብትናና ችግሮችን በሰላም ለመፍታት የሰጠው ዕድልና ሆደ ሰፊነት መልካም ቢሆንም፣ ነገር ግን በአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ የሚያሳየው ታጋሽነት ጥያቄ እያስነሳ ነው የሚገኘው፡፡ ሱዳኖች ሕወሓቶችን ከፊት አሠልፈውና ግብፆችን ከጀርባ አዝለው የጀመሩት ነው የተባለው ሰሞነኛው ትንኮሳ ተባብሶ ወደ ጦርነት ካደገ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተገቢውን አፀፋ ለመስጠት ቢዘጋጅ ይሻላል የሚለው ውትወታ እየበረታ ነው፡፡

የሰሞኑን የሱዳን ትንኮሳና እስከ ትናንት በአካባቢው የቀጠለውን ሁኔታ እንዲያስረዳ የተጠየቀው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ ሙሉዓለም ገብረ መድኅን፣ አካባቢው ወደ ተለመደ ሁኔታው መመለሱንና እንደሚወራው ጦርነት አለመኖሩን ነው የገለጸው፡፡

‹‹ሰኞ ጠዋት ረፋድ 4፡00 ሰዓት አካባቢ ሱዳኖቹ ጥቃቱን ጀመሩ፡፡ እስከ 6፡00 ሰዓት ከባድ መሣሪያ መተኮስ የቀጠሉ ቢሆንም ከሰዓት ዝናብ ነበረ፣ ጥቃቱም ቆሟል፤›› በማለት የተናገረው ሙሉዓለም፣ ጦርነት ከፈቱ የሚለው ወሬ ተጨባጭነት እንደሌለው አረገጋግጧል፡፡

የአካባቢውን የፖለቲካ ሁኔታ በቅርበት ሆኖ የሚከታተለው ሙሉዓለም እንደተናገረው፣ ሱዳኖቹ በወረራ ከዚህ በፊት ከተቆጣጠሩት ሌላ የያዙት ተጨማሪ መሬት የለም፡፡ እስከ ትናንት አመሻሽ በአካባቢው የተለየ ሁኔታ አለመፈጠሩን የጠቀሰው ሙሉዓለም፣ የሞቱት ሰባት ሰዎችም ድንበር ጥሰው በመግባት ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር ግጭት ለመፍጠር የሞከሩ የሱዳን ወታደሮችና የሕወሓት ታጣቂዎች መሆናቸው እንደተረጋገጠም ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡

ሰሞነኛው የሱዳኖች ትንኮሳ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ለመክፈት ባላቸው ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ገፊ ምክንያቶች የመጣ ሊሆን እንደሚችል አመልክቷል፡፡

‹‹እ.ኤ.አ. ሰኔ 30 ቀን 2022 በሱዳን ትልቅ የሠርቶ አደሮች ማኅበር ተቃውሞ ተጠርቷል፡፡ የአል ቡርሀን መንግሥት የትኩረት አቅጣጫ ለማስለወጥ በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት ሊከፍት ይችላል፡፡ የሱዳን የፖለቲካ ሽግግር ጊዜ ገደብ ለመጠናቀቅ ከመቃረቡ በተጨማሪ፣ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ኢትዮጵያ ለሦስተኛ ተከታታይ ዓመት የምትሞላበት ወቅትም ተቃርቧል፡፡ ግብፆች ሁሌም እንደሚያደርጉት ከሱዳን ጀርባ ሆነው የማደናቀፍ ሥራ መሥራታቸው የሚጠበቅ ነው፡፡ ሰሞነኛው የወለጋ ጭፍጨፋ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የፈጠረውን ውዝግብና ክፍተትንም እንደ አንድ ምቹ አጋጣሚ ሱዳንና ግብፅ ሊጠቀሙበት መፈለጋቸው አይቀርም፡፡ በሌላም በኩል ሕወሓት ወደ ድርድር ሲገባ ተጨማሪ መሬት ይዞ ጉልበቱንና ጫናውን ከፍ ለማድረግ ፍላጎቱ አለው፤›› ሲል የዘረዘረው ሙሉዓለም፣ የሰሞነኛውን ጥቃት ሊያስከትሉ ይችላሉ ያላቸውን መላምቶች አስቀምጧል፡፡

የሰሞኑን ጥቃት ምንነትና የአካባቢውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በቅጡ ያልተረዱ ሚዲያዎች፣ አጋጣሚውን የሁለት አገሮች ጦርነት ዳግም መጀመር አድርገው ማቅረባቸው ስህተት መሆኑን የጠቀሰው የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኛ ሙሉዓለም፣ በአካባቢው ሰላምና መደበኛ እንቅስቃሴ መመለሱን ነው ያረጋገጠው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -