Friday, May 24, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የግሉ ዘርፍ የሚገኝበትን ደረጃና ሚና የዳሰሰው የንግድ ምክር ቤቱ 75ኛ ዓመት የምሥረታ በዓል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የግል ዘርፍ የአንድ አገር ዋነኛ የኢኮኖሚ ዕድገት መሠረት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አበርክቶ እጅግ አነስተኛና ከሌሎች አገሮች አንፃርም ሲታይ እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ደረጃ ላይ የሚገኝ እንደሆነና ያሉበትም ችግሮች ብዙ መሆናቸውም ይጠቀሳል፡፡ የግሉ ክፍለ ኢኮኖሚ ለአገር ኢኮኖሚ አበርክቶው ከፍተኛ እንደሆነ ቢታወቅም የአስፈላጊነቱን ያህል እየታገዘ አለመሆኑና ኢኮኖሚው በአብዛኛው በመንግሥት እጅ ላይ ሆኖ ቀጥሏል የሚለው አመለካከት ጎልቶ ይወጣል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት 75ኛ ዓመት ክብረ በዓሉን አስመልክቶ ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይም ይኸው አመለካከት ተንፀባርቋል፡፡

የግሉ ዘርፍ የቱ ጋር ነው ያለው? የሚለውን መንደርደሪያ ጥያቄ በማስቀደም ያሉበትን ችግሮችና መፍትሔዎችን በተመለከተ ትናንት በተደረገው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙ ተናጋሪዎች የግሉ ዘርፍ ማደግ ያለበትን ያህል እንዳላደገ ገልጸዋል፡፡ ችግሩ የመንሥትና የራሱ የግሉ ዘርፍ ጭምር መሆኑን በንግግራቸውም የጠቀሱ አሉ፡፡  ወቅታዊውን የግል ዘርፍ ማነቆዎች በተመለከተ የመወያያ ሐሳብ ካቀረቡት ተናጋሪዎች መካከል የግሉን ዘርፍ በማማከር ሥራቸው የሚታወቁት አቶ አፈወርቅ ዮሐንስ፣ አንዱ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የግሉ ዘርፍ የመጣበት መንገድ ብዙ ውጣ ውረድ የነበረበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ ነው›› የሚለው መፈክር መነገር ከጀመረበት ካለፉት 30 ዓመታት ወዲህ በተግባር ለዕድገቱ የሚሆን ሥራ ተመሥርቷል የሚል እምነት የላቸውም፡፡ የግሉ ዘርፍ የአገር የኢኮኖሚ ዋልታ መሆኑ አጠራጣሪ እንዳልሆነ የጠቀሱት አቶ ዮሐንስ፣ መንግሥት ለግሉ ዘርፍ አስፈላጊውን ትኩረት ተሰጥቶታል ተብሎ እንደማይታመንም አብራርተዋል፡፡ የነበሩ በጎ ጎኖችና ለችግሩ መባባስ ያሉዋቸውን ምክንያቶችንም ጠቃቅሰዋል፡፡ 

መንግሥት ከግሉ ዘርፍ በሚሰብሰብ ታክስ የመኖሩን ያህል፣ የግሉን ዘርፍ ሊያሳድጉ የሚችሉ ፖሊሲዎች በመቅረጽ ረገድ ብዙ የሚቀረው መሆኑን የገለጹት ተናጋሪው አሁንም ይህ ክፍተት ጎልቶ የሚታይ እንደሆነ አመልክዋል፡፡ ፖሊሲዎች በአብዛኛው የሚወጡት በመንግሥት ነው፣ የግል ዘርፉ የተሳተፈባቸው ፖሊሲዎች እምብዛም አይታዩም ብለዋል፡፡ አሁንም የግሉ ዘርፉን እንቅስቃሴ በቂ ሁኔታ ሊያጎለብቱ የሚችሉ ተቋማት ካለመኖራቸውም በላይ በፖሊሲ ቀረፃ ዙሪያ ያለው ተሳትፎ አናሳ መሆኑ አንድ ችግር ሆኖ አሁንም ድረስ ዘልቋል ይላሉ፡፡  

ለግል ዘርፍ በጣም ከሚያስፈልጉ መሠረታዊያን አንዱ የሆነውን ፋይናንስ በሚገባ እያገኘ አለመሆኑን በምሳሌነት ጠቅሰው፣ ከዚህም ሌላ የገበያው ሁኔታ ግልጽ ሆኖ አለመገኘትና የመሳሰሉ ችግሮች የዘርፉ ማነቆ ሆነዋል፡፡ በመሠረተ ልማትና በገበያ ተሳስረው አቅማቸውን ማሳደግ የሚችሉበት ከባቢ እንደሌለም ተናግረዋል፡፡ በዓለም ላይ ካለው የግል ዘርፍ እንቅስቃሴ አንፃር ተወዳዳሪ መሆን የሚችልበት ጥራት ያለው ምርት ለማምረት የሚያስችል አቅም አለመኖር የግሉ ዘርፍ ተግዳሮቶች ሆነው አሁንም ድረስ መዝለቃቸውን አብራርተዋል፡፡ 

በብዛት ለማምረት የሚችሉት ግብዓት ውስንነት መኖሩ፣ እንዲሁም በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂ ለማንቀሳቀስ የሚያስችል አቅም አለመኖር የዚህ ዘርፍ ማነቆዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በቂ የሆነ ክህሎት የለም፣ የተመረተውንም ምርት በጊዜ ለዓለም ገበያ ለማቅረብ የሚደግፍ የፖሊሲ መሣሪያ አለመኖር የግሉ ዘርፍ የሚንቀሳቀስበት ምኅዳር ምቹ እንዳይሆን አድርጎታል ይላሉ፡፡ 

የማምረት አቅም የግል ዘርፉ ችግር እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ዮሐንስ፣ በመረጃ አሰጣጥ ረገድ ያለውንም ችግር ጠቅሰዋል፡፡ በቅርቡ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ማምረት ካለበት ወደ 49.2 በመቶ ማምረት ጀምሯል የሚለውን የመንግሥት ሰሞናዊ ሪፖርት በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ 

ይህ አኃዛዊ መረጃ በበቂ ጥናት የተደገፈ ስለመሆኑ ይጠራጠራሉ፡፡ ምክንያቱም በአብዛኛው ቦታ ለጥናት ሄደው ማየት የቻሉት በዚህን ያህል ደረጃ የሚንቀሳቀሱ አምራቾች አላጋጠማቸውም፡፡ ስለዚህ 49.2 በመቶ የሚለው መረጃ ለኢትዮጵያ ቅንጦት እንደሚመስላቸው ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም አምራቾቹ ብዙ እጥረት ያለባቸው በመሆኑ እዚህ የማምረት ደረጃ ላይ አልደረሱም ብለዋል፡፡ ሌላው በግሉ ዘርፍ እንደ ችግር ያነሱት ጉዳይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ጥቅም ላይ የዋለው ስልት ኋላ ቀር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በተለይ ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ የምንጠቀምበት መንገድ ፈፅሞ ስህተት›› ነው የሚሉት አቶ አፈወርቅ፣ በምሳሌነት የጠቀሱት ርካሽ የሰው ኃይል፣ የኤሌክትሪክ ዋጋ ዝቅተኛ ነው፣ ሰፊ መሬት ስላለ መሬት በቀላሉ ይገኛል፣ በማለት የሚደረገው የማስተዋወቅ ሥራ ተገቢ ነው ብለው አያምኑም፡፡ 

ርካሽ የሆነው ሠራተኛ የተማረ ነው ወይ? ርካሽ የተባለ የኤሌክትሪክ ኃይል በአግባቡ ይቀርባል ወይ? መሬትስ? የሚሉ ጥያቄዎች በአግባቡ ሲመለሱ እንደማይታይ ገልጸዋል፡፡ ሌላው አንድ ሀብት ሲመዘን ትልቁን መጠን የሚይዘው መሬት ነው፡፡ ባለሀብቱ ግን የመሬቱ ባለቤት አይደለም በማለት ያሉ ችግሮችን ዘርዝረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ምንም እንኳን በሮች እየተከፈቱ ቢሆንም፣ ፖሊሲዎች ከግሉ ዘርፍ ፍላጎት ጋር ተጣጥሞ እየወጡ አለመሆናቸውን ይተቻሉ፡፡ ገና መሬት የነኩ ነገሮች ስለሌሉ ብዙ ችግሮች መፍትሔ ያልተበጀላቸው በመሆኑ የግሉ ዘርፍ የኢኮኖሚው መሪ ነው በሚል መጠቀስ ከጀመረበት ካለፉት 30 ዓመታት ጀምሮ ያለውን እውነታ ከጎረቤት አገሮቻችን ጋር ቢነጻጸር በጣም ወደ ኋላ የቀረ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ 

አሁንም ቢሆን የግል ዘርፉ የሚታየው እንደ ዘራፊ እንደሆነ የጠቀሱት አቶ አፈወርቅ፣ ያለ ድካም ገንዘብ የሚያግበሰብስ እንጂ ሀብት ፈጣሪና ለብዙዎች መኖር ምክንያት እንደሆነ ተደርጎ የሚቆጠር የግል ዘርፍ አለመገንባቱን ጠቁመዋል፡፡ ስትራቴጂዎቹ፣ ፖሊሲዎቹና የመሳሰሉት ነገሮች ለግል ዘርፉ ዕድገት በሚመጥን መልኩ የተቀረፁ አለመሆን ደግሞ ዕድገቱ እንዲገታ ካደረጉት አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው በግሉ ዘርፍ ችግር ተብሎ የተጠቀሰው ሊስተካከልም እንደሚገባው የተመለከተው ጉዳይ የግሉ ዘርፍ ቢያንስ ባመነጨው ገቢ ተጠቃሚ እንዲሆን አለመቻሉ ነው፡፡ ከሚያመጣው የውጭ ምንዛሪ እንኳን የሚጠቀመው 20 በመቶውን ብቻ እንደሆነና ይህም ራሱ የፈጠረውን ሀብት መጠቀም የማይቻልበት ደረጃ ላይ እንዳደረሰው የሚያሳይ መሆኑን ጠቁመዋል። በዚህም ሳቢያ ዘርፉ ተጨማሪ ሀብት የማፍለቅ አቅሙን መጎዳቱንና እንዲህ ያሉ ክፍተቶች መታረም እንደሚኖርባቸው መክረዋል፡፡ በመሆኑም ስለ ግል ዘርፉ ዕድገት ሲታሰብ አሁንም ገና ብዙ መስተካከል ያለባቸው ነገሮች መኖራቸውን ነው፡፡ የንግድ ምክር ቤቶች አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች መንግሥትን መጎትጎት ይኖርባቸዋል ያሉት ሌላው ተናጋሪ ዓይናለም ዓባይነህ (ዶ/ር) ደግሞ በመረጃ ተደግፎ መንግሥትን መጎትጎት ያስፈልጋል፣ መንግሥት ሊሞገትበት የሚችሉ ብዙ ነጥቦች አሉም ይላሉ፡፡

ነገር ግን መንግሥትንም ዝም ብለን በደፈናው መውቀስ አንችልም የሚሉት ዓይናለም (ዶ/ር) ይህንንም ያሉበትን ምክንያት ሲገልጹ መንግሥት ባለፉት የልማት ዕቅዶች ውስጥ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶች ውስጥ የግሉ ዘርፍ በኢኮኖሚ ውስጥ መሪ ተዋንያን እንዲሆን አቅጣጫ አስቀምጧል ብለዋል፡፡ ከመንግሥት የሚጠበቀው ይህ መሆኑን፣ ነገር ግን በአግባቡ መሠራት ካልቻለ ውጤት ሊያመጣ እንደማይችል ገልጸዋል፡፡ ያለውን ችግር ለመቅረፍም እንደ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ ተቋማት በመረጃ ተደግፎ መሞገት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡ በተለይ የንግድ ምክር ቤት አካባቢ ያሉ ኃላፊዎች ይህንን መሥራት እንዳለባቸው የገለጹት ዓይናለም (ዶ/ር) የንግድና ዘርፍ ማኅበራትን ለማደራጀት የወጣን አዋጅ ለማሻሻል የሚወስደውን ጊዜ አስታውሰዋል፡፡ አዋጁ መሻሻል እንደሚገባው ሥራ ከተጀመረ ዓመታት የተቆጠሩ ቢሆንም መንግሥት ይህንን ያለማስፈጸሙ አንድ ችግር ሆኖ ይህ እንዲፈጸም መግፋት ከምክር ቤቱ የሚጠበቅ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ ስለዚህ መንግሥትን በምክንያት መሞገት ተገቢ ነው ይላሉ፡፡ 

የግል ዘርፉ ችግሮች ብለው የጠቀሱት ሌላው ጉዳይ በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ ግሉ ዘርፍ እንዲያድግ የሚደረጉ ሥራዎች አሉ በማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአደረጃጀት መንግሥት የንግዱ ኅብረተሰብ ተወካዮች ናቸው ተብለው፣ ከመንግሥት ጋር የሚደራደርና የሚነጋገሩ አሉ፡፡ ይህ መልክ መያዝ አለበት ብለው ያምናሉ፡፡  

‹‹ሸቀጣ ሸቀጦች ላይ ዋጋ ሲጨምር መንግሥት አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች ይህንን አደረጉ ይላል፤›› ያሉት ዓይናለም (ዶ/ር)፣ መንግሥት ራሱ እያደረገ ያለው ለምሳሌ የመሬት ሊዝ ጋር ተያይዞ ዋጋው ይህንን ያህል ከፍ አለ ሲባል፣ ይህ ነፃ ገበያ ነው ማለቱን በንፅፅር አቅርበዋል፡፡ ስለዚህ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መሞገቱ አስፈላጊ ነው ብቻ ሳይሆን በጥንካሬ ሊሠራበት የሚገባ ጉዳይ ነው ብለዋል።

በተናጋሪዎቹ እንደ መፍትሔ ከተጠቀሱ ሐሳቦች መካከል የግል ዘርፉ የሚቀረፁ ስትራቴጂዎችን ባለቤት እንዲሆን ማስቻል በዋናነት የተቀመጠ ነው፡፡ ሐሳቦችንም ማመንጨት ያለበት የግል ዘርፉ ነው የሚል እምነት ተንጸባርቋል።

በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ውስጥ ዘርፉ በጣም ወደ ኋላ የቀረበት ሁኔታ ላይ እንዳለ የገለጹት አቶ አፈወርቅ በዚህ ሁኔታ ደግሞ አገር ልታድግ እንደማትችል ተናጋሪዎቹ ያሰምሩበታል፡፡ መንግሥት ባስቀመጠው ፕላን መሠረት በ2030 የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ መካከለኛ ገቢ መግባት ካለበት የግሉ ዘርፉ የመሪነቱን ሚና መጫወት እንደሚኖርበት አቶ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡  

የግል ዘርፉ ሥራ ብዙ ትሩፋት ያለው መሆኑን ያመለከቱት ዓይናለም (ዶ/ር)፣ አንዳንድ ጊዜ የግሉ ዘርፍም ኃላፊነት መውሰድ አለበት ብለው ከጠቀሱት ውስጥ ደግሞ የንግድ ምክር ቤት አባል ሳይሆኑ፣ የሚያጭበረብሩ የሚሠርቁና መሰል ተግባራትን የሚፈጽሙ አካላትን ለማረም መሠራት የሚኖርበት መሆኑን ነው፡፡  

ከዚህም ሌላ የንግዱን ኅብረተሰብ የሚመለከት አዋጅ ሊወጣ መሆኑ ታውቆ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት የሚደረግ መሆኑ ሲገለጽ አዋጁን ለመሞገት የሚገኝ ጥቂት መሆኑን የገለጹት ዓይናለም (ዶ/ር)፣ ነገር ግን አዋጁ ከወጣ በኋላ ብሶት ማሰማት ተገቢ ያለመሆኑን በመጥቀስ እንዲህ ያሉ አካሄዶችም  መታረም እንደሚኖርባቸው ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡

ሌላው ተናጋሪ  የካዲስኮ ግሩፕ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሰልሃዲን ካሊፋ የግሉ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የግሉ ዘርፍ ጥንካሬንና ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹እኛ ጠንካራ ካልሆነንን መንግሥት የሚያወጣው ፖሊሲ ላይ እኛን የማይወክል ከሆነ ብሶታችንን የምናቀርብበት መንገድን ማጠናከር ያለብን እኛው እራሳችን ነን፤›› ብለዋል፡፡

በግል እንደሚመለከቱት ያሉ ችግሮችና ክፍተቶች ከድህነትና ከራሳችን የመነጨ ነው ብለው የሚያምኑ መሆኑን አቶ ሳላዲን ገልጸው፣ ችግሮችን መዘርዘር ብቻ መፍትሔ ሊያመጣ ይችላል ብለው አያምኑም፡፡ እሳቸው በአምራችነት፣ በአገልግሎት፣ በጤና፣ በሎጂስቲክና በተለያዩ ንግዶች ላይ ተሰማርተው የሠሩ መሆኑን የገለጹት፣ አቶ ሳላዲን ሁሉም ጋር የሚመለከቷቸው ችግሮች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ ነገር ግን እስካሁን መፍትሔ ያልተሰጣቸው መሆኑ ትልቅ ችግር ነው ብለዋል፡፡ 

ስለዚህ መፍትሔው ላይ ማተኮር ተገቢ ይሆናል ብለዋል፡፡ እነዚህ ችግሮች የማኔጅመንት፣ የኢኮኖሚና የሪሶርስ ችግሮች በመሆናቸው መፍትሔውም የግሉን ዘርፍ በማጠንከር የሚመጣ ነው ብለዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ ተቋማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከሙ መሄዳቸው ግልጽ ነው ያሉት አቶ ሳላዲን የግሉ ዘርፍ ተዋንያንም ችግሩን በማየት የመፍትሔ አካል መሆን አለባቸው በማለት መንግሥትም ሆነ የግል ዘርፉ የየራሱን ድርሻ ሊወጣ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች