Saturday, May 18, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየኢራንና አሜሪካ የኑክሌር ውይይት የኢራንን ነዳጅ ዘይት ለዓለም ገበያ ያበቃ ይሆን?

የኢራንና አሜሪካ የኑክሌር ውይይት የኢራንን ነዳጅ ዘይት ለዓለም ገበያ ያበቃ ይሆን?

ቀን:

ኢራን ‹‹ኃይል ለማመንጨት አበለፅገዋለሁ›› የምትለው ዩራኒየም ለኑክሌር ጦር መሣሪያ ሊውል ይችላል በሚል በኢራን ላይ ሥጋት የገባቸው ኃያላን አገሮች፣ ኢራንን በስምምነት ያሰሩት እ.ኤ.አ. በ2015 ነበር፡፡

ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ስትፈተን የቆየችው ኢራንም ከስምምነቱ በኋላ የተጣሉት የኢኮኖሚ ማዕቀቦች በመነሳታቸው ዓለም አቀፉ ንግዷን አጣጡፋ ነበር፡፡

አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያና እንግሊዝ በወቅቱ ከኢራን ጋር በገቡት ስምምነት መሠረት፣ ኢራን የዩራኒየም ማበልፀጊያ ተቋሟ በዓለም አቶሚክ ኤጀንሲ ቁጥጥር እንዲደረግበት፣ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችቷም 3.67 በመቶ እንዳይበልጥ ያገደም ነበር፡፡

- Advertisement -

ይህ መጠን ለሰላማዊ ኢንዱስትሪ ብቻ የሚያገለግል ቢሆንም፣ ኢራን ይህንን ገደብ በመጣስ ከ4.5 በመቶ በላይ የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት የያዘችው አሜሪካ ስምምነቱን በተናጠል ካፈረሰችበት እ.ኤ.አ. ከ2018 ወዲህ ነው፡፡

ኢራን በ2015 የኑክሌር ስምምነቱን ከስድስቱ አገሮች ጋር ስታደርግ፣ ተጥለውባት የነበሩ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች ተነስተውላት የነበረ ቢሆንም፣ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በተናጠል ስምምነቱን አፍርሰው ጠንካራ የተባለውን የኢኮኖሚ ማዕቀብም ኢራን ላይ ማሳለፋቸው ይታወሳል፡፡

የኢራንና አሜሪካ የኑክሌር ውይይት የኢራንን ነዳጅ ዘይት ለዓለም ገበያ ያበቃ ይሆን? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ኢራን ለሰላማዊ ኢንዱስትሪ የማውለው ነው የምትለው የዩራኒየም ማበልፀጊያ (ሚድል ኢስት ሞኒተር)

የዩራኒየም ማብላያ ጣቢያዋ ለሰላማዊ አገልግሎት ብቻ እንደሚውል ስትናገር የከረመችው ኢራን፣ አሜሪካ ከስምምነቱ ራሷን ካገለለች ወደህ የዩራኒየም ክምችት መጠኗን ያሳደገች ሲሆን፣ ይህንን ለመቀልበስ ቀሪዎቹ የስምምነቱ አባል አገሮች ብዙ ጥረዋል፡፡

አሜሪካንና ኢራንንም ለማግባባት እንዲሁም፣ አሜሪካ ማዕቀቡን እንዳትጥል ለማድረግ ደክመዋል፡፡ ሆኖም የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሳለፉትን የተናጠል ውሳኔ ማስቀረት አልተቻላቸውም፡፡  

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ዕልባት አደርግበታለሁ ብለው ቃል ከገቡት አጀንዳ አንዱ የነበረው ደግሞ የኢራንን የኑክሌር ስምምነት ወደ ቀደመ ሥፍራው መመለስ ነው፡፡

በመሆኑም ይህንን ውዝግብ ይፈታል የተባለ ውይይት በተዘዋዋሪ በኢራንና አሜሪካ መካከል ኳታር ውስጥ ትላንት ተደርጓል፡፡

አልጀዚራ እንደሚለውም፣ በኢራንና አሜሪካ መካከል የተደረገው ውይይት አዎንታዊ ውጤት የሚያመጣ ከሆነ፣ የኢራን ነዳጅ ዘይት ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ ዳግም ይቀላቀላል፡፡

በአውሮፓ ኅብረት አሸማጋይነት የተደረገው ውይይት ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለማምጣት ተስፋ የተጣለበት ነውም ብሏል፡፡

ኢራንና አሜሪካ በተዘዋዋሪ ማለትም ተወካዮቻቸው በተለያየ ክፍል ሆነው በአሸማጋይ በኩል መልዕክት በመለዋወጥ በሚያደርጉት ውይይት ለመሳተፍ ወደ ዶሃ ያቀኑት የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ሮበርት ማሊ እንዲሁም የኢራን ምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዓሊ ባግሃሪ ካን ናቸው፡፡

ኢራን እ.ኤ.አ. በ2015 በተደረሰው ስምምነት መሠረት ቀድሞ የነበረው የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቷ እንዲመለስላት ትፈልጋለች፡፡ አሜሪካ በበኩሏ የስምምነቱን ዳግም ወደ ተግባር መግባት የምትፈልገው የኢራንን የኑኩሌር ፕሮግራም ለመቀልበስ ነው፡፡

እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2021 በኢራን፣ በቻይና፣ በሩሲያ፣ በፈረንሣይ፣ ጀርመንና በብሪታኒያ እንዲሁም አሜሪካ በተዘዋዋሪ የ2015ቱን ስምምነት ዳግም ተግባራዊ ለማድረግ ተወያይተው የነበረ ሲሆን፣ በዚህም በብዙ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ተደርሷል፡፡ ሆኖም የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የሽብር ድርጅት ከሚለው መዝገብ መሰረዝ አለበት ስትል ጠይቃለች፡፡

ትላንት በዝግ በተደረገው ውይይት ይህ ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ የሚያገኝ ከሆነ በኢራንና በስድስቱ አገሮች መካከል በ2015 የተደረሰው ስምምነት ዳግም በቅርቡ ተግባራዊ እንዲሆን ዕድል የሚከፍት ይሆናል፡፡

ሆኖም ኢራን የትላንቱን ውይይት ከማድረጓ በፊት የዓለም አቶሚክ ኤጀንሲ በኢራን ኑክሌር ማብላያ ጣቢያ የተከላቸውን 27 የቁጥጥር ካሜራዎች በማንሳት በምትኩ የተሻሻሉ የኑክሌር ማብላያዎች መትከሏ ሌላ ሥጋት አጭሯል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ