Sunday, May 19, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ኢትዮጵያን ተባብሮ መታደግ ላይ ይተኮር!

ማንም አገሩን የሚወድ ዜጋ የወቅቱን አስጨናቂ ጉዳዮች በሚገባ መገንዘብ ይጠበቅበታል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና የሚፈታተኑ ድርጊቶች ገጽታቸውንና አቅጣጫቸውን እየቀያየሩ መሆናቸውን ብቻ ሳይሆን፣ ከድርጊቶቹ በስተጀርባ ያሉትን የሩቅና የቅርብ ኃይሎች ፍላጎትም መረዳት ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ የተሟላ ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ የሚቻለው፣ ኢትዮጵያ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ ከተለያዩ ፍላጎቶች አኳያ በመረዳት የበኩልን ለመወጣት ጥረት ሲደረግ ነው፡፡ በመንግሥትና በሕዝብ፣ እንዲሁም በተለያዩ የፖለቲካ ተዋንያን መካከል ሊኖር የሚገባው ጤነኛ ግንኙነት መታሰብ ይኖርበታል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ደኅንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን እንዴት መወጣት እንዳለበት፣ ሕዝብም ይህ እንዲሳካ ምን ዓይነት ድጋፍ ማድረግ እንደሚኖርበት፣ ተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅቶች ከመንግሥት ጋር ሊኖራቸው የሚገባው በመርህ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት፣ ያኮረፉ የፖለቲካ ኃይሎች ጭምር በሰላማዊ መንገድ የፖለቲካ ምኅዳሩ ተሳታፊ የሚሆኑበት ማዕቀፍ፣ በአጠቃላይ ለሰላማዊና ለሥልጡን መንግሥታዊ አስተዳደር መፈጠር አስተዋጽኦ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ በሴራና በክፋት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት አገርን ቀውስ ውስጥ እንደሚከት ለማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ከስህተት ጎዳና ለመውጣት የሚያግዙ ምክሮች ቢሰጡም፣ ሰሚ ባለመኖሩ ምክንያት ሕዝብም አገርም ተጎድተዋል፡፡  

‹‹የማይሳሳት የሞተ ብቻ ነው›› የሚል ዕድሜ ጠገብ አባባል አለ፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ አገርን እስከሚመሩ ሰዎች ድረስ ሲሠሩ ይሳሳታሉ፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን ስህተትን አለመደጋገም ነው፡፡ በአሁኗ ኢትዮጵያ በየቀኑ የሚከናወኑ ድርጊቶች ከመብዛታቸው የተነሳ፣ ለስህተት የሚዳርጉ በርካታ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ስህተትን እያነፈነፉ በተለያዩ ገጽታዎች ለአደባባይ የሚያበቁም እየበዙ ነው፡፡ መንግሥት በበርካታ ችግሮች የተከበበች አገርን ሲመራ በየቀኑ ከበርካታ ስህተቶች ጋር ይገናኛል፡፡ ገና ለገና ለትችት እዳረጋለሁ በማለት፣ ከስህተት ለመሸሽ ሲል ሥራ መፍታት ግን አይቻለውም፡፡ የሆኖ ሆኖ በጥናት ላይ የተመሠረተ ሥራ ሲያከናውን መሳሳት ቢኖርም፣ ስህተቱ ከፍተኛ ጉዳት ስለማያደርስ ያን ያህል የሚያስቸግር አጣብቂኝ ውስጥ አይገባም፡፡ ጥናት የጎደላቸውና የባለሙያ ዕገዛ የሌላቸው ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› ዓይነት ሥራዎች ግን፣ ከወቀሳ ባለፈ ውግዘት ያስከትላሉ፡፡ ስህተት ተፈርቶ ሥራ መቆም የለበትም ሲባል፣ የሚከናወነው ሥራ በሚገባ የታቀደና ውጤታማነቱ አስተማማኝ ሊሆን ይገባዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት አንዳንድ ጉዳዮችን ማንሳት ተገቢ ነው፡፡

በፖለቲካው መስክ በኢትዮጵያ ከተወሰዱ ዕርምጃዎች መካከል አንዱና ዋነኛው፣ በተለያዩ ምክንያቶች በሥርዓቱ በመገፋታቸው ከአገር ውጪ ሆነው ትጥቅ ያነሱና በስደት የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ወደ አገር ቤት መመለሳቸው ነው፡፡ ይህ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለመክፈት የሚረዳ በጎ ዕርምጃ በሥርዓት ሊከናወን ባለመቻሉ ግን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ደም አፋሳሽ ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካቶች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ሚሊዮኖች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ መጠኑ የማይታወቅ ሀብት ወድሟል፡፡ የአገሪቱ አንፃራዊ ሰላም ደፍርሶ የዜጎች በነፃነት የመዘዋወር፣ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብት ከመገደቡም በላይ ከፍተኛ ሥጋት ደቅኗል፡፡ ትጥቅ አልፈታም ያለ ኃይል ጥቃትን የፖለቲካ ትግል መሣሪያ በማድረግ በተደጋጋሚ ንፁኃንን ጨፍጭፏል፡፡ ምንም እንኳ በለውጥ ውስጥ በምትገኝ አገር የሚጠበቁ ችግሮች ቢኖሩም፣ እንዲህ ዓይነቱን ዓይን ያወጣ ሥርዓተ አልበኝነት አደብ የማስገዛት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን መንግሥት በሕግ በተሰጠው ኃላፊነት የዜጎችን ሕይወት መታደግ አለበት፡፡

አሮጌው የበጀት ዓመት ተጠናቆ አዲሱ ሊጀመር አንድ ሳምንት ቀርቶታል፡፡ በአሮጌው በጀት ዓመት ከታቀደው ምን ያህሉ ተሳካ? ምን ያህሉስ ሳይሳካ ቀረ? ታቅዶ ከእነ ጭራሹ ያልተከናወነውስ ምን ያህል ነው? ለመጪው በጀት ዓመት የሚተላለፈውና አዲሱ ዕቅድስ? ማለት ተገቢ ነው፡፡ ከግለሰብ ጀምሮ እስከ አገር ድረስ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ስንክሳሮች ሲመዘዙ፣ በየቦታው ከሚያጋጥሙ ሰቆቃዎችና ከኑሮ ውድነቱ ጋር የሚያያዙ በርካታ ውጣ ውረዶች ታልፈዋል፡፡ ወደፊትም ሊቀጥሉ የሚችሉ ስለመኖራቸው ጥርጥር አይኖርም፡፡ ከወዲሁ ግን መንግሥት የሚዘጋጅባቸው በርካታ ዕቅዶች ሲኖሩ፣ አፈጻጸማቸውና ውጤታቸው ካለፈው የማይሻል ከሆነ ግን ስህተትን መደጋገም ነው የሚሆነው፡፡ በዜጎች ደረጃም ከግላዊ ሕይወታቸው እስከ አገራቸው ድረስ በሚኖራቸው የሥራ ድርሻ፣ ስህተትን ላለመደጋገም ጥረት ካልተደረገ ውጤት ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ነው የሚሆነው፡፡ መንግሥት የአገርንና የሕዝብን ደኅንነት የሚከላከልበት አሠራር ብቁና ቀልጣፋ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ የዋጋ ግሽበትን የሚከላከልበት፣ አቅርቦትና ፍላጎትን የሚያጣጥምበትና ኢኮኖሚውን ከማነከስ ወደ ማንሰራራት የሚቀይርበት በተግባር የተፈተነ ብልኃት ሊኖረው ይገባል፡፡ በሰንካላ ምክንያቶች ስህተት ውስጥ መዘፈቅ ተገቢ አይደለም፡፡

በኢኮኖሚው መስክ የተወሳሰቡ ችግሮች ይታያሉ፡፡ ጠንክሮ መሥራት ከተቻለ ግን የሚያቅት አንዳችም ነገር የለም፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲውንና ስትራቴጂዎችን ከአንድ ወንዝ በመቅዳት ሳይሆን፣ አዋጭና ጠቃሚ የሆኑ ልምዶችንና ተሞክሮዎችን ከአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ አቀናብሮ ሥራ ላይ ማዋል የግድ ይሆናል፡፡ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ፣ የእስያና የተሳካላቸው የአፍሪካ አገሮችን ልምድ መቅሰም ተገቢ ነው፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የውኃ ሀብት፣ በርካታ የቱሪስት መስህቦች፣ ብዛት ያላቸው ማዕድናትና የመሳሰሉት ፀጋዎች ያሏትና በወጣት በተሞላች አገር የውጭ ምንዛሪ እጥረት፣ የብድር ጫና፣ የሥራ ፈጠራ ችግር፣ ረሃብ፣ ጠኔ፣ አስቸኳይ ዕርዳታ፣ ወዘተ እያሉ ምክንያት መደርደር የስህተቶች ሁሉ ስህተት ነው፡፡ ሀብት ላይ ተቀምጦ ሳይሠሩ መራብ ነውር ነው፡፡ በኢኮኖሚው መስክ ከፍተኛ ባለሙያዎችና ብቃት ያላቸው ስትራቴጂስቶች አሉ በሚባልባት አገር ውስጥ ስንዴ፣ ዘይትና የመሳሰሉትን ከውጭ መለመንም ሆነ መሸመት አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያን የልማትና የዕድገት አውራ ማድረግ እየተቻለ፣ በየዓመቱ የልመና ከረጢት ይዞ መዞር ትልቅ ውርደት ነው፡፡ ይህንን የመሳሰሉ ስህተቶች ማስወገድ ይገባል፡፡ የድህነት አረንቋ ውስጥ ሆኖ መዘባነን ያስገምታል፡፡

ችግሮችን ማወቅ ለመፍትሔ ቅርብ እንደሚያደርግ ሁሉ፣ ያሉ የሌሉ ችግሮችን  እየነቀሱና ስህተቶች ብቻ እያነፈነፉ ጥላሸት መቀባት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ በተለይ በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አገሪቱ ያበቃላት ይመስል ነጋ ጠባ ማላዘን የተለመደ ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያ የታቀፈቻቸው ችግሮች ትናንት የተፈጠሩ ብቻ ሳይሆኑ ዘመናትን የተሻገሩም አሉ፡፡ የተለያዩ ፍላጎቶች ባሏቸው ኃይሎች የተደራጁ ወገኖች፣ ሕዝብ በአገሩ ላይ ያለው እምነት እንዲሸረሸርና መንግሥት ደግሞ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲሽመደመድ ብርቱ ትግል ያደርጋሉ፡፡ በዚህ ላይ ሐሰተኛ ወሬዎች በስፋት እየተሠራጩ በማኅበረሰቦች መካከል ግጭት እንዲቀሰቀስ ያደርጋሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችና ግድያዎች እየበዙ ነው፡፡ ዜጎችን በማንነታቸው ምክንያት በጭካኔ በመጨፍጨፍ የአገሪቱ ሰላም ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ እየገባ እንደሆነ ለማሳየት ጥረቱ ቀጥሏል፡፡ በዚህ መሀል ክቡር የሆነው የሰው ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል፡፡ የአገር ህልውና ፈተና ውስጥ ይወድቃል፡፡ ይህንን የአገር ደዌ በጊዜ ፈውሶ ኢትዮጵያን መስመር ማስያዝ ይገባል፡፡ ዘወትር ከስህተት ጋር ተቃቅፎ መኖር አይቻልም፡፡ የስህተት መንገድ መድረሻው ውድቀት ስለሆነ፣ ኢትዮጵያን ተባብሮ መታደግ ላይ ይተኮር!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...

በስድስተኛው ዙር ጠቅላላና ድጋሚ ምርጫ የሚሳተፉ ፓርቲዎች በገዥው ፓርቲ ላይ ተቃውሞ እያቀረቡ ነው

በ2013 ዓ.ም. ስድስተኛው ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች በጠቅላላና በድጋሚ ምርጫ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...

አገርን ከቀውስ ውስጥ ማውጣት ብሔራዊ አጀንዳ ይሁን!

የአገራቸው መፃኢ ዕድል የሚያሳስባቸው በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ወገኖች፣ በየቀኑ የሚሰሟቸው ማቆሚያ ያጡ ልብ ሰባሪ የግጭትና የጦርነት ዜናዎች እንቅልፍ ይነሷቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ማንኛውም...