Monday, May 20, 2024

ምርጫ ቦርድ ለአካባቢ ምርጫ የጠየቀው 6.9 ቢሊዮን ብር ዝግጅቱን ሲያጠናቅቅ እንደሚለቀቅለት ተነገረ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በቀጣዩ ዓመት ሊያካሂደው ላሰበው የአካባቢ ምርጫ የጠየቀውን 6.9 ቢሊዮን ብር፣ የምርጫ ቀኑንና መርሐ ግብሩን ሲያሳውቅ እንደሚለቀቅለት የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ቦርዱ ግንቦት 17 ቀን 2014 ዓ.ም. የቀጣይ ዓመት በጀቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሲያቀርብ ለምርጫው ማስፈጸሚያ 6.94 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልገው ያቀረበ ቢሆንም፣ መንግሥት የተቋማትን የቀጣይ ዓመት በጀት ድልድል ረቂቅ ይፋ ሲያደርግ ለቦርዱ የተመደበለት 212 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ለ2015 ዓ.ም. የቀረበውን 786 ቢሊዮን ብር የበጀት ድልድል አስመልክቶ፣ ከተለያዩ ባለበጀት ተቋማት ጋር ሰኞ ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ውይይት አድርጓል፡፡

በውይይቱ ወቅት ቦርዱ ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን በጀት ዘርዝሮ ቢያቀርብም የተጠየቀው ገንዘብ ለምን እንዳልተመደበለት፣ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ሜላት ወርቅ ኃይሉ ጠይቀዋል፡፡

የአካባቢ ምርጫው ሰፊ ሥራ የሚከናወንበት መሆኑን የገለጹት ኃላፊዋ፣ ምርጫው በ75 ዞኖች፣ በ1,019 ወረዳዎች፣ በ56,375 ምርጫ ጣቢያዎች የሚካሄድ መሆኑን፣ እንዲሁም 281,895 ምርጫ አስፈጻሚዎችና 520 ሺሕ ዕጩዎችን በማሳተፍ፣  44 ሚሊዮን መራጮች ድምፅ ይሰጡበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አክለው አስረድተዋል፡፡

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የአካባቢ ምርጫ ከተካሄደ ከአሥር ዓመታት በላይ እንደሆነ በማስታወስ፣ በቀጣይ ቦርዱ አካሂደዋለሁ ብሎ በጀት የጠየቀበት የአካባቢ ምርጫ መቼ እንደሚካሄድ፣ ይህን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ሁኔታዎች አሉ ወይ? የሚለውን ዝርዝር ሲያቀርብ፣ በጀቱ እንደሚለቀቅ የተናገሩት በገንዘብ ሚኒስቴር የበጀት ጉዳዮች አማካሪ አቶ ተፈሪ ደመቀ ናቸው፡፡

ሰኔ 2013 ዓ.ም. 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ከ547 የምርጫ ክልሎች ውስጥ በ436 የምርጫ ክልሎች ምርጫ የተካሄደ ሲሆን፣ በአጠቃላይ ወደ ስድስት ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል፡፡ በመጪው ዓመት ሊካሄድ ለታሰበው የአካባቢ ምርጫ ከሚያስፈልገው ወጪ የመንግሥትና የልማት አጋሮች ድርሻ ምን ያህል እንደሆነ ተለይቶ፣ እንዲሁም አሁን ያለው አገራዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ ገብቶ በዝርዝር እንዲቀርብ አቶ  ተፈሪ አሳስበዋል፡፡

መንግሥት ከቦርዱ ጋር በመነጋገር በእርግጠኝነት የምርጫ ቀኑ ሲታወቅ፣ ለ2015 ዓ.ም. ከተያዘው 24 ቢሊዮን ብር መጠባበቂያ ገንዘብ እንደሚለቀቅለት አማካሪው አብራርተዋል፡፡

ቦርዱ ከምርጫው ዝግጅት በፊት ለሚያካሂዳቸው ቅደመ ዝግጅቶች ከጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 212 ሚሊዮን ብር እንደተፈቀደለት አክለው ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊ የሆነውን ዝግጅት አድርጎ እንዴትና መቼ የሚለውን ጉዳይ በዝርዝር ሲያቀርብ የሚያስፈልገውን ሀብት መንግሥት ለማቅረብ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ፣ ምርጫ ቦርድ ያስፈልገኛል ያለው የምርጫ ማካሄጃ ገንዘብ አሳማኝ ቢሆንም፣ ቦርዱ የምርጫ ቀኑን ቆርጦ ሲያሳውቅ እንዲሰጠው መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -