Friday, May 24, 2024

በመገናኛ ብዙኃንና ሲቪክ ማኅበራት መካከል ያለው መተማመን ዝቅተኛ ነው ተባለ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሲቪክ ማኅበራትና በመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች መካከል ያለው መተማመን፣ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አንድ ጥናት አመለከተ፡፡

የሲቪል ማኅበረሰብ ድጋፍ ፕሮግራም የተባለ ድርጅት ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር በመተባባር ባለፉት ስድስት ወራት በመገናኛ ብዙኃንና ሲቪክ ማኅበራት መካከል ስላለው ቅንጅታዊ አሠራርና ተግባቦት በተመለከተ ያካሄደውን ጥናት፣ ማክሰኞ ሰኔ 21 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው በሲቪክ ማኅበራትና በመገናኛ ብዙኃን መካከል ያለው መስተጋብር በጥርጣሬ የተሞላ፣ እንዲሁም በመካከለኛ ደረጃ የሚገለጽ አብሮ ለመሥራት የሚታይ ፍላጎት ስለመኖሩ ተገልጿል፡፡

ጥናቱ በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማትን ቁመና በተመለከተ ዳሰሳ ያደረገ ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በሚዲያ ተቋማት የሚገኙ ጋዜጠኞችና ሠራተኞች ብዛት፣ የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ አዘጋገብ፣ እንዲሁም ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ የመሥራትና ያላቸው መስተጋብር ምን ይመስላል የሚሉ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የግልና የንግድ ሚዲያ ተቋማት መካከል፣ ሪፖርተር ጋዜጣና ኢቢኤስ ቴሌቪዥን ከፍተኛ የሠራተኛ ቁጥር ያላቸው የሚዲያ ተቋማት መሆናቸው ተገልጿል፡፡

የጥናቱን ውጤት ያቀረቡት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መምህርና የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ተመራማሪው አቶ ፍሬዘር እጅጉ፣ በመገናኛ ብዙኃንና የሲቪክ ማኅበራት መካከል በጋራ ለመሥራት ያላቸው ፍላጎት በመካከለኛ ደረጃ የሚገለጽ ቢሆንም፣ ሁለቱ አካላት በመተማመን ላይ ተመሥርቶ በመሥራት ፋንታ ጥርጣሬ ላይ ያጋደለ ግንኙነት አላቸው ብለዋል፡፡

ሲቪክ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኃን በኢትዮጵያ የመንግሥትና የተለያዩ ተቋማት የሚያካሂዱትን ተግባርና ኃላፊነት የመከታተልና የመቆጣጠር ሚና፣ እንዲሁም የመንግሥት ሥርዓትን የመለወጥ አቅም ቢኖራቸውም፣ አሁን ባሉበት ቁመናቸው ያንን ማድረግ በማይችሉበት ደረጃ ላይ እንዳሉ አቶ ፍሬዘር አስረድተዋል፡፡

ከ170 በላይ የሚሆኑ የሲቪክ ማኅበራትንና 60 ጋዜጠኞችን በማሳተፍ እንደተከናወነ የተጠቆመው የዳሰሳ ጥናት፣ በአገሪቱ ካሉ አሥር ጋዜጠኞች ውስጥ ዘጠኙ በመንግሥት የሚዲያ ተቋማት የሚሠሩ መሆናቸውን፣ በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ካሉት ጋዜጠኞች አንፃር ሲታይ በግል ሚዲያ ላይ የሚሠሩት ዘጠኝ በመቶ የሚሆኑት ናቸው ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በሲቪክ ማኅበራትና በጋዜጠኞች መካከል ያለው ግንኙነት ‹‹በአድርግልኝ ላድርግልህ›› ዓይነት ዕሳቤ የተመሠረተና ጥቅም ላይ ያማከለ በመሆኑ፣ በዚህ መሀል የአንዱ ጥቅም በሚነካበት ወቅት ግንኙነቱ እንደሚበላሽና በተቃራኒው ደግሞ ጥቅሙ ሲሲተካከል የተሻለ የሚባል ግንኙነት እንደሚኖር አቶ ፍሬዘር ተናግረዋል፡፡

ጥናት አቅራቢው እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት የሚታየው የሁለቱን ግንኙነት ሊያስተካክልና ወደ ተሻል ደረጃ ሊያሳድግ የሚችል ሥራ ካልተሠራ በስተቀር፣ አሁን ካለበት የግንኙነት ሁኔታ የባሰ ሊያሽቆለቁል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው ተብለው የሚጠሩት ሁለቱ ተቋማት አብረው ካልሠሩ፣ በመረጃ ላይ የተመረኮዘ ውሳኔ ሰጪነት እንደማይኖር፣ ዘመናዊና ሁሉን አቀፍ ሥርዓት ለመፍጠር ውስንነት አንደሚፈጥር፣ በመረጃ ላይ ተመርኩዞ ውሳኔ የሚሰጥ ሕዝብ ለመፍጠር የሚደረጉ የፖለቲካና ማኅበራዊ መስተጋብሮች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው አክለው አብራርተዋል፡፡

በተጨማሪም የተሻለ ውይይትና የተረጋጋ ሥርዓት ለመፍጠር የሚኖራቸው ሚና ተፅዕኖ ውስጥ እንደሚወድቅም አቶ ፍሬዘር ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -