Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሚያዳምጥ ጠፋ!

ጉዞ ከሜክሲኮ ወደ ቦሌ። ሕይወት ዛሬም እንደ ትናንቱ ጉዞዋን ቀጥላለች። የሞላው ላይ ስንጨምር እየፈሰሰ፣ የጎደለውን ለመሙላት እየታገልን ምኞታችን ሳይገደብ መንገድ በሚባል ‹‹ቅኔ›› ለመኖር እንታገላለን፡፡ የነገን አናውቅም፣ የትናንትን ረስተናል። ዛሬ ላይ ቆመን ከመሀልም ቢሆንም አነሳሳችንን ለማሳመር ስንታገል፣ ጎዳናው ትዝብት በሚባል አንድምታው እርስ በርሳችንን አሳልፎ ያሰጣጠናል። አግኝቶ በማጣት፣ አጥቶ በማግኘት፣ ስቆ በመከፋት፣ ባዝኖ በማረፍ በዚህች ሕይወት በምትባል ቴአትር ሚናችንን ጠብቀን እንተውናለን። ይህ እውነታ ያልገባው ምንም እንኳ ቴአትሩን ያበላሸ ቢመስልም፣ ሌላ ትዕይንት ፈጥሮ ይታያል። እንዲህ እንዲህ እያለ መኖር፣ ማኗኗር፣ ወይም የኑሮ አሯሯጭነት አብሮን ይዘልቃል። በዚህ መሀል ታዲያ ለአፍታ ዕፎይታ የሚጠይቀውን ጊዜ አልጠብቅም ብሎት ይነጉዳል። ይህም ሌላ ትግል ያስከትላል። ሁሉም ነገር በእያንዳንዳችን የሕይወት ጎዳና ላይ ሲከወን በቅርበት ሆነን እንታዘባዋለን፡፡ ከመንገዱ አስቸጋሪነት አንፃር የሕይወት ትርፍ ግን ምን ይሆን? አይታወቅም!

  ዶፉ እያስፈራራን ተሠልፈን ቆይተን ታክሲው ላይ ከተሳፈርን በኋላ ወያላው ገብቶ በሩን ዘጋ። ሾፌሩ ልብ የሚነካ የእንጉርጉሮ ዓይነት ፉጨት እያፏጨ ገብቶ ሞተሩን ማስነሳት ጀመረ። ነገር ግን ታክሲዋን በጤናዋ አላገኛትም። አሁንም ሞከረ። ትንሽ ተንፈቅፍቃ ዝም። ‹‹ደግሞ ምን ሆንኩ ነው?›› አለ ሾፌሩ ወደ ወያላው ዞሮ። ወያላው ከሚቆምበት ከእግሩ ሥር የሆነ ክዳን ነገር አንስቶ ባትሪውን አገኘና መነካካት ሲጀምር ተረክ ብላ ተነሳች። ‹‹ባለ መድኃኒቷን እስክታገኝ ነው…›› አለው ወያላው በገዛ ፈቃዱ የሐኪምነት ማዕረግ ለራሱ ሊቸር ፈልጎ። ‹‹በቃ የእኛ ሰው ትንሽ ሠርቶ አመስግኑኝ፣ ስንዝር ተራምዶ አክብሩኝ ማለት ሆነ አይደለም ሥራው?›› አለች አንዲት ቀላ ያለች ወጣት ተሳፋሪ። አጠገብዋ የተቀመጠ ተሳፋሪ ደግሞ፣ ‹‹ምን ታደርጊዋለሽ? እንዲህ ለመበላሸታችን ምክንያቱ እኮ ተቀባዩ ነው። ምን ሠራህ? ከየት እስከ የት ተራመድክ? ብሎ የሚጠይቅ አንድ የለም…›› ይላታል። በዚህ ጉዞ ለየት ያለብን የወንዶችና የሴቶች ተሳፋሪዎች ቁጥር እኩል መሆኑ ነው። ይህን የታዘበ አጠገቤ የተቀመጠ ተሳፋሪ፣ ‹‹አስተውለሃል? በዴሞክራሲያዊ መንገድ ያለ ትንቅንቅ መሳፈር ስንጀምር ሴቶቻችንም እኩል ሆነ ቁጥራቸው። እኩልነት ሊረጋገጥ የሚችለው ፍፁም በሆነ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ መሆኑን ዛሬ ገና ተረዳሁ…›› ሲለኝ አንገቴን በአዎንታ ነቀነቅኩ። ‹‹ፍቅርን በውለታ መውደድን በገንዘብ፣ ልግዛሽ ትለኝና እንዳንተዛዘብ?›› የሚለው ዘፈን ትዝ አለኝ። ‹‹አቋራጭ ያስተዛዝበናልና ረጅሙን ጉዞ በትዕግሥት እንያያዘው›› የሚል ጥቅስ ማየት አማረኝ!

ወያላው፣ ‹‹ዝርዝር ብር ያላችሁ ተባበሩኝ?›› እያለ ዝርዝር እንደሌለው ነገረን። ‹‹ከሌለንስ?›› ብሎ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ ግትር ጥያቄ አቀረበለት። ‹‹ግትር አቋምና ግትር አመለካከት ከበበን እኮ?›› ይለኛል አጠገቤ የተቀመጠው ተሳፋሪ። ‹‹እህ!›› እለዋለሁ። ወያላው ግን፣ ‹‹ካለህ ተባበረኝ ነው እንጂ ያልኩህ ከሌለህማ የለህም…›› ብሎት ወደ ተለመደው ተግባሩ ተሰማራ። በሰላም መነጋገርን የመሰለ መልካም ነገር እያለ ለምን እንነጃጀሳለን?›› ሲል ከሾፌሩ ኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ አባባሉ አንገታችንን አስነቀነቀን። ‹‹እውነቴን እኮ ነው፣ በረባና ባረባው ለጠብና ለዱላ ከመገባበዝ ይልቅ በሰላም እየተወያየን ዕውቀት ብንገበያይ ተመራጭ ነበር…›› ሲል ሁላችንም በውስጣችን ያመሰገነው መሰለኝ፡፡ በዚህ ዓይነቱ ጉዞ ላይ ወዝ ያለው ጨዋታ እያነሱ የማያስደምሙንን ያህል የጭቃ ጅራፋቸውን ይዘው የሚመጡ ደግሞ አሉላችሁ፡፡ በትንሽ በትልቁ መደንፋት የሚወዱ፡፡ ‹‹ድንፋታ ሲበዛ የደም ግፊት ይጨምራል…›› ያለው ማን ይሆን?

ወያላው እጅ ላይ የተቆለለውን ገንዘብ ያየ አንድ ተሳፋሪ፣ ‹‹ገንዘብ የተሠራው ለሰው ልጅ መገልገያ ነው። እርግጥ ብዙ የለፋ ብዙ ይሰበስባል። ያልሆነለትና የሰነፈ ደግሞ ያጣል። ነገር ግን ገንዘብ የበላይነት መገለጫ ሊሆን አይችልም…›› አለ፡፡ ‹‹ወንድሜ ሰው ያለ ገንዘብ ምንም ማለት ነው። ገንዘብ ያለ ሰው ግን የተባረከ ነው…›› አለው አንዱ እየተበሳጨ አጠገቡ ለተቀመጠ ጎልማሳ። የቁጣው ምንጩ ባይገባንም ያለውን ሰማን። ‹‹ምን ያበሳጨዋል? ይኼም ንግግር መሆኑ ነው?›› ስትል ከኋላችን ያለች ተሳፋሪ፣ ‹‹ጥቃቅንና አነስተኛ ባህሪዎቻችን እኮ በዙ…›› ብላ ጓደኛዋ ትመልስላታለች። ውይይቱን ያነሳው ተሳፋሪ ግን፣ ‹‹ዛሬ በገንዘብ ከመገልገል አልፈው ማንነትን ለመግዛት የሚያስቡትንና ከእነሱ በገንዘብ ዝቅ ያለውን ሰው አሳንሰው ለመመልከት የሚጥሩትን ሳይ ብስጭቴ ይቀሰቀሳል። ስንትና ስንት ፋብሪካ አቋቁመው ትልቅ የኢኮኖሚ ማገር ሊሆኑ ሲችሉ፣ ጫማችንን ላሱ እያሉ በየሥፍራው ሰውን አላስቀምጥ ያሉትን አለማንሳት ነው…›› ብሎ ዝም አለ። ገንዘብን ሰውን ከሚያህል ታላቅ ፍጡር በማስበለጥ፣ እነሱም በእሱ ተመክተው በልጠው ለመታየት የሚጥሩ ዘመን አፈራሽ ሞልቃቆች ወገናቸውን የሚያሸማቅቁት እዚህ የትዝብት ጎዳና ላይ ነው። ወይ ይኼ ጎዳና፣ የሰውን ልጅ ባህሪ ከሚፈታተኑ አደገኛ ነገሮች መካከል አንዱ ገንዘብ መሆኑን ለተረዳ ሰው ያሳቅቃል፡፡ ማንነትን የሚፈታተን፣ ከሞት የማያስጥል፣ ዕድሜ የማይቀጥል፣ ምን አለፋችሁ ይጫወትብናል!

‹‹ሀብት በጥቂቶች ጓሮ ሲከማች ጠያቂ እንዳይኖር አንዳንዱ ሥርዓት ዘብ ሲቆም ይገርመኛል…›› ሲል አንድ ወጣት፣ ‹‹ሥርዓትስ እሺ ሕግ፣ ደንብና መመርያ ስላለው ነው። ኧረ ህሊና? ምናለበት ሰው ህሊናው ቢያዘው? ዓለማችን እኮ ካላት ሀብት አንፃር ፈጽሞ ድህነት የሚባል ሊኖር አይገባም ነበር…›› ሲል ሌላ እሱን መሰል ወጣት አከለበት። ‹‹ብለነው ብለነው የተውነውን ነገር፣ ቧሏ ዛሬ ሰምቶ ታንቆ ሊሞት ነበር ሲባል ያልሰማ ትውልድ…›› አሉ አንድ አዛውንት ሰው። ‹‹እንዴት?›› አለቻቸው አጠገባቸው የተቀመጠች ተሳፋሪ። ‹‹የገንዘቡን ነገር ትታችሁ ጭካኔያችሁን ብትገሩት ኖሮ እኮ ኢትዮጵያ ሲኦል አትሆንም ነበር። ከገንዘብ በፊት ፍቅር፣ ሰላም፣ ፍትሕና መተሳሰብ ቢቀድም ኖሮ እኮ ጨፍጫፊ ትውልድ አይፈጠርም ነበር…›› አሏት። ‹‹አይ አንቱ! የዛሬ ሰው ከፈጣሪ ትዕዛዝ አፈንግጦ ከአውሬ የባሰው እኮ ለሥልጣንና ለገንዘብ መሆኑን አላውቅ ብለው ነው? በተለይ ከሞት በኋላ ከቤታቸው ጓሮ ገነትን የሚገነቡ ይመስል አምላክን መፍራት የረሱ መብዛታቸው እኮ ያስፈራል…›› ስትላቸው፣ ‹‹ትክክል…›› አሉ። ‹‹ሕግ ተንቆ፣ አምላክ ተረስቶ፣ ህሊና ተዘንግቶና የሰው ልጅ ተጠልቶ ብቻ ይሁን…›› ሲል ከፊታችን ያለ ጎልማሳ፣ ‹‹እሱን ፍራ…›› ይለዋል አጠገቡ የተቀመጠ ወጣት። ድንገት የፍርኃት አየር ነገሠ!

ታክሲያችን ስታዲየም አካባቢ ስትደርስ ‹‹ጉድ! ጉድ! ጉድ!›› አለ አንዱ ተሳፋሪ። ሁላችንም ደንግጠን ‹‹ምነው? ምነው?›› እያልን በጥያቄ እናዋክበው ጀመር። መደናገጣችንን ሲያይ መለስ ብሎ፣ ‹‹ኧረ እኔስ ምንም አልጠፋብኝ። እንዲያው መልካም ጊዜና መንግሥት መጣ ብለን አጨብጭበን ሳንጨርስ አንገት እንድፋ?›› ሲል አንዱ ደንገጥ ብሎ ‹‹ምነው?›› ሲለው፣ ‹‹ወንድሜ እንዴት ተብሎ ነው እዚህች አገር ውስጥ በሰላም የሚኖረው? ወገኖቻችን መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ እንደ እንስሳ ሲታረዱ እንዴት አለን ይባላል…›› ብሎት ፊቱን ወደ ጎዳናው አዞረ። ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ወንድሜ ለውድቀታችንም ሆነ ለሽንፈታችን ምክንያት መደርደር ማቆም አለብን…›› ካለ በኋላ፣ ‹‹እርስ በርስ የመከባበርና የመተሳሰብ ኢትዮጵያዊ ዘመን ተሻጋሪ እሴቶቻችን በማንም ጥራዝ ነጠቅ ፖለቲከኛ ተንቀውና ተዋርደው ሜዳ ላይ ሲጣሉ እኛ የማንን ጎፈሬ እናበጥር ነበር…›› አለና ‘ወራጅ’ ብሎ ወረደ። ‘ያለውን የወረወረ ንፉግ አይባልም’ እንዲሉ ለሐሳቡ መዋጮ አመስግነን ሸኘነው። መቼ ይሆን የሐሳብ ቴሌቶን ሲዘጋጅ የምናየው?

ታክሲያችን መነሻዋ ላይ ብቻ እንዳስቸገረች ያለ ምንም መደናቀፍ እየከነፈች በቦሌ መንገድ በመንጎድ ላይ ነች። ‹‹እኔ የማይገባኝ ማንም ጥጋበኛ እየተነሳ ጥቃትን የትግል መሣሪያ ሲያደርግ እጃችንን አጣጥፈን ማየታችን ነው፡፡ አይደል እንዴ?›› ብሎ አንዱ በንዴት ተናገረ። ሾፌሩ ደግሞ፣ ‹‹እኔ ደግሞ የምለው መንግሥት ውስጡ ካልተበረዘ በስተቀር፣ ሃምሳ ዓመት ሙሉ አንድ መንደር ይዞ የማያውቅ ሽፍታ አገር ላይ እንዲህ አይፈነጭም ነበር…›› አለ። ‹‹ለምሳ ያሰቡንን ለቁርስ አደረስናቸው ያለው መንጌ ነበር በዚህ ጊዜ የሚያስፈልገው። ለሕግና ለሥርዓት ዋጋ የማይሰጥበት አገር፣ ኤድያ አሁንስ በዛ…›› ይላል ሌላው ከመሀል። ሁሉም ሐሳቡን እያንሸራሸረ የሚሠራውን ይቃኛል። ‹‹ግን ለምንድን ነው እዚህ አገር ሥልጣን ላይ የወጡ ሰዎች ሕዝቡን የሚረሱት? እነሱ ዳቢትና ክትፎ ሲያማርጡ የሕዝቡ ሰቆቃ አይታያቸውም እኮ…›› ሲል አንድ ወጣት ተሳፋሪ፣ ‹‹አንተ እነሱን ብቻ ትላለህ? እኛስ ብንሆን በአስመሳይነትና በአድርባይነት ሥራቸው እንርመጠመጥ የለ…›› ብሎ ጓደኛው ይመልስለታል። ችግሩ እየተነሳ መፍትሔው ቢጠፋም፣ አቅም ያጣ ሁሉ እርስ በእርሱ በውይይት ነገሮችን ለማብላላት እየተጣጣረ ጉዞው ተጠናቆ ቦሌ ደረስን። የሚያዳምጥ የለም እንጂ ብዙ ተብሎ ነበር! መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት