Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ይድረስ ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር

ቀን:

በአሰፋ አደፍርስ

ሰላም ለእርስዎና ለሚወዱት ሁሉ ይሁን፡፡ ለኢትዮጵያም ሰላምና ብልፅግናን ያድልልኝ፡፡ ቀደም ሲል በጽሕፈት ቤትዎ በኩል ይህችን ማስታወሻ ልኬ ነበር፡፡ ያልደረሶት ስለመሰለኝ በመልካሟ ሪፖርተር ጋዜጣ አማካይነት ቢደርሶት ብዬ ነው፣ እንደሚደርሶትም አምናለሁ። ይህችን ማስታወሻ ስጽፍሎት፣ ለበላይ አስተያየት መስጠት ተደብቆ ከማማት የተሻለ ነው ብዬ ስለማምን የተቻለኝን ምክረ ሐሳብ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡

እኔ ባለሁበት አገር (አሜሪካ) የወገን አስተያየት የተከበረና የተመሠገነ ነው፡፡ በአገራችን የተለመደ ወይስ አዲስ ነገር ነው ስል ራሴን በመጠየቅ፣ ለመልካም አስተያየት ችግር አይኖርም ስል ራሴን አበረታታሁና እንደሚከተለው ምክሬን ለመለገስ ተነሳሳሁ፡፡ ይህችንም አስተያየት ለመጻፍ የተነሳሳሁበት ዋናው ምክንያት ለውድ አገሬ ያለኝን ፍቅርና ግዴታዬን ለመወጣት እንጂ፣ ሌላ ምንም የምሻው ነገር እንደሌለኝ ላረጋግጥ እወዳለሁ፡፡

- Advertisement -

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በሚያደርጉትና በሚሞክሩት የአገር ማሻሻል ዕርምጃዎ እጅግ ደስ ይለኛል፣ እደግፎታለሁም፡፡ አገራችን መከራና ችግር ተደራርቦ በገጠማት በአሁኑ ዘመን የሁላችን ትብብር እንደሚያስፈልጎት ሁላችንም እንገነዘባለን፡፡ እኔ ደግሞ በመገንዘብ ብቻ ሳይሆን የድርሻዬን ለመወጣት የተቻለኝን እያደረግሁ ነው፡፡ የበለጠ ለማድረግም ዝግጁ ነኝ፡፡ ይሁን እንጂ ስህተት መስሎ ለሚታየኝ አስተያየት ከመስጠት አልቆጠብም፡፡ በምንሰጦት አስተያየት ይህንን አታሳጣኝ ይበሉ እንጂ ቅር እንዳይሰኙ አደራ ለማለት እሻለሁ፡፡ ከምዕራባዊያን ያጋጠሞትን ማናለብኝነት ያለበት ጫና ገትረው በመቋቋሞ ዓለም ለእርሶ አድናቆት አሳይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያውያንም ዳር እስከ ዳር በአገር  ቤትም ሆነ በውጭም ከጎኖ እንደተሠለፉ በፅናት አሳይተዎታል፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ በረዶ፣ ውርጭና ቆፈን ሳይበግራቸው ብዙ ማይሎችን በእግር ተጉዘው ያሳዩትን ቆራጥነትና ያመጡትንም ውጤት እንደሚገነዘቡ አምናለሁ፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅና በአፍሪካም የየአገሩን ግልምጫ፣ ቁጣና ሃሩሩን አየር ተቋቁመው ያሳለፉትን መገንዘብና ለምን ይህ ሁሉ ሆነ ብለው የማስተዋሉን ጉዳይ ለክቡርነቶ መንገር ለአንበሳ መምተር እንዳይሆንብኝ ስል ሐሳቤን እዚህ ላይ እገታለሁ፡፡

ዛሬ የምንመለከተው የፖለቲካ ሩጫ አገርን የሚጠቅም ሳይሆን፣ አገርን የሚያጠፋ ነውና ጥንቃቄ ይደረግበት፡፡ ኢትዮጵያ በ1923 ዓ.ም. ንጉሡ የቀደምቱን የአፄ ምኒልክን ፋና ተከትለው ያደረጉት የልማት ዕርምጃ እንዴት ነበር? ስንት ትምህርት ቤቶች ነበሩ? ስንት ሆስፒታሎች ነበሩ? ሁለት ትምህርት ቤቶች የምኒልክና የተፈሪ መኮንን ብቻ አልነበሩምን? ታዲያ ንጉሡ ከእነዚህ ተነስተው የአንደኛ ደረጃዎችን፣ የሁለተኛ ደረጃዎችንና ኮሌጆችን ሠርተው ዛሬ ለእዚህ ውጥንቅጥ አገሪቱን የዳረገውን ትውልድ አላስተማሩም? በተማርነው መሠረት አገራችንን ከመርዳትና ከማልማት ይልቅ፣ የግል ጥቅማችንን በመሻት ሊያጠፉን አኮብኩበው ለሚጠብቁን ዋና መሣሪያ በመሆን እነሆ ለእዚህ የእርስ በርስ መጠፋፋት ደረስን፡፡

ወደ 1960ዎቹ የሥልጣኔ ጉዟችን ከደረስን በኋላ በዚሁ ሳቢያ የመጣው ለውጥ አሻሽሎን ሄደ ወይስ አጥፍቶን? ባለፉት 40 ዓመታት ውስጥ የታየው ለውጥ በ40 ዓመታት ውስጥ የተቋቋሙትን ልማቶች ተካ ወይስ አጥፍቶ ጠፋ? ብሎ ማመሳከሩና ነባሩን ከማጥፋት አሻሽሎ መሄድን ያሳየን ይሆናልና ይህንን ማመዛዘኑ መልካም ስለሚሆን ያስቡበት፡፡ እርሶ ካለፉት ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያምና ከመለስ ዜናዊ በተሻለ ሲራመዱ በመታየትዎ ደስ ብሎኛል፡፡ ነገር ግን የበሰሉና ልምድን ያካበቱ አማካሪዎች ቢኖሩት ጥሩ ነው፡፡ ዛሬ በሃያዎቹ አጋማሽና በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ዕድሜ ውስጥ ሆነው ተምረው የዶክትሬት ዲግሪ የያዙ፣ ገና ሮጠው ያልጠገቡ፣ የኑሮን ጣዕም በሚገባ ያልቀመሱ፣ በትምህርታቸው ተገቢውን ዕውቀት ቀስመው ገና ልምድን የሚሹትን ሁሉ የቁንጅና ውድድር ይመስል ወደ ከፍተኛ ሥልጣን ማሠለፉ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንዳይብስ ይጠንቀቁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ በእርግጥ በአሜሪካ አገር በሥራ ላይ ልምድ (On the Job Training) በሚሉት በሥራ ልምድ አካብተው ለትልቅ ደረጃ የሚደርሱ አሉ፡፡ ታዲያ ልምድን ሲያካብቱ በሚኒስትርነትና በሚኒስትር ደኤታነት ተደርጎም አይታወቅም፡፡

በእርግጥ በቅኝ ግዛት ሲሰቃዩ የነበሩት የአፍሪካ አገሮች ዕድሜ ለኢትዮጵያ በነበራት ችግርና ድህነት ራሴን ብቻ ልቻል ብላ አፍሪካን ከመርዳት ወደኋላ ሳትል፣ ያስተማረቻቸውና ያሠለጠነቻቸው ያለ ምንም ልምድ በየአገራቸው ሄደው ወደ ከፍተኛ ሹመት መሰየማቸውን እናስታውሳለን፡፡ ለምሳሌ ዳኔል ሲዳ የተባለ ኬንያዊ፣ እንዲያውም ከዓለማያ የእርሻ ኮሌጅ ትምህርቱን እንደ ጨረሰ ዲግሪውን ሳይቀበል በአስቸኳይ ተጠርቶ ኬንያ ሄዶ የቡና ሚኒስትር ተብሎ መሾሙን አስታውሳለሁ፡፡ ይህም የነፃነት ጥም ስለነበራቸው በሥራ ላይ ይማር እንጂ በጠላት አንመራም ከሚል ዕሳቤ መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ እኛ የዚያ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞን ወይስ በዘመኑ ልክፍት ተለክፈን ይሆን? ይህ በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባ ጉዳይ ነውና በእርጋታ ቢታይ መልካም ይመስለኛል፡፡

አሜሪካ ዛሬ ታላቅ ተብላና ሁሉን ያሰባሰበች በመሆን ለግል ጥቅሟ ሌላውን የምታፋጅ ናት፡፡ የሰውን አገር ቀምታና ሁሉን አሰባስባ ግን ልማት እንጂ ወሰን፣ ቀዬና ቀበሌ ሳትል 360 ሚሊዮን ሕዝብ ከዓለም በሙሉ የመጣውን ስታስተናግድና ሁሉም ዜጋዋ ነን ለማለት የሚኩራራበትን ሁኔታ ስንመለከት፣ እኛ ምን እየሆንን ነው የሚያሰኝ ጥያቄ ያጭርብኛል፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ወዘተ ሆኗል ዘፈኑ፡፡  ጉራጌው፣ ሐዲያው፣ ወላይታው፣ ሲዳማው፣ ካፋው፣ ኩሎው፣ ኮንታው፣ ናኦው፣ ቤኔሾው፣ ትሸናው፣ አርጎባው… እረ ስንቱ? ታዲያ ይህ ሁሉ በወሰንና በቀዬ ከተከፋፈለ ማነው ባላገሩ? መፍትሔውስ ምን ሊሆን ነው? እባክዎን ይታሰብበት፡፡

ይህንን ለአገር የማይበጅ አዲስ አስተሳሰብ በመተው ሁሉም በኢትዮጵያዊነት አብሮና ተባብሮ ለልማት እንዲነሳሳ ለማድረግ፣ ወገንተኛ ባልሆኑ ምሁራን በተረጋጋ ሁኔታ ጥናት ተደርጎ የረጋችና ታሪኳን የጠበቀች አገር ማቆየት ይገባል፡፡ ክብሩንና መብቱን የሚያውቅ ትውልድ መስመር ይዞ የራሱንና የወገኑን ክብር እንዲያስጠብቅ የወሰደውን ያህል ጊዜ ወስዶ መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ለአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ለመላው ኅብረተሰቡ ጠንካራ አቅም ገንብቶ የዕድገት መንገድ ለመቀየስ ዕድሎን ለታሪክ ጥለው ቢያልፉ፣ እንደ እነ አፄ ቴዎድሮስ (ምናልባት አፄ ምኒልክን ይውደዱ አይውደዱ አላውቅም፣ ግን ታሪክ የማይረሳቸው ንጉሠ ነገሥት ስለነበሩ ወይም ከእነ ናፖሊዮን ብሎት ይሻል ይሆን) ብቻ ታላቅ ሥራ ትተው ለማለፍ ይሞክሩ ለማለት ነው፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር፣ በአገራችን እንደ ዛሬ ስብጥርጥሩ ሳይበዛና ሳንራኮት በአንድ ቋንቋ ሁሉም ሕዝብ ተግባብቶ ይኖር ነበር፡፡ ክቡር አቶ ይልማ ዴሬሳ ለንጉሠ ነገሥቱ እንዲህ ሲሉ ሐሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ‹‹አማርኛ ሲባል የአንድ ጎሳና ሁሉንም አንድ የማያደርግ ስለሚመስል፣ አማርኛ ከማለት ኢትዮጵኛ ብንል ሁሉን ያካትታል፤›› ብለው ሐሳብ አቅርበው፣ ሐሳቡንም ንጉሡ ተቀብለው ሥራ ላይ የሚውልበትን መንገድ እንዲያጠኑ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወትን፣ ከንቲባ ሐረጎት ዓባይን፣ ራሳቸው አቶ ይልማን በሊቀመንበርነት፣ ጄኔራል አበበ ገመዳን በአባልነት፣ ጄኔራል ከበደ ገብሬን በአባልነት፣ ጄኔራል ይልማ ሺበሺን በአባልነት፣ ሌሎቹም ነበሩ ይህ ሥራ ላይ ሊውል ሲታሰብ ደርግ የተባለ ተውሳክ ደርሶ ሁሉን አፈረሰው፡፡

አፍሪካውያን የገዛ ቋንቋቸው ጠፍቶባቸው መልሰው ለመማር ጊዜ ወስዶ ከሥልጣኔ ወደኋላ እንዳያስቀራቸው፣ በያዙት የቅኝ ገዥዎች ቋንቋ ቀጥለው እነሆ በዚያው ረግተው አገራቸውን ይመራሉ፡፡ ቋንቋ መገናኛ እንጂ የማንም አይደለምና፡፡                                                                                                  በእኛ አገር የተረሳው ነገር የቤተ ክህነት ትምህርት ባይኖር ኖሮ፣ ነፍጠኛው ጠላትን ተከላክሎና ወሰንን አስከብሮ ነፃነትን ባያስረክበን ኖሮ ዛሬ የምንፈናከትበት መለያየት ይኖር ነበር? ወይስ የፈረንጅ ባሪያ ሆነን እንቀር ነበር? ብለን በማሰብ ሕዝባችን ወደ ልቦናው ተመልሶ ስለአገሩ መልካምነት እንዲያስብና ለልማት እንዲሽቀዳደም እንደሚለፉ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ይበርቱ፡፡ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳዎት፡፡

በመልካም አንደበቶና በማራኪ አቀራረቦ ወቃሽዎችዎንም ደጋፊዎችዎን በማግባባት አስደስተው ይሸኛሉ፡፡ ይህ ደግሞ ዘላቂ ውጤታማ ለመሆን ሳይሆን፣ ጊዜያዊ ማቀዝቀዣ ነው የሚሆነው፣ ከልብዎ አዋቂዎችን አማክረው ተገቢውን ቢሠሩ መልካም ይሆናል፡፡ እዚህ ላይ ገማል አብዱልናስር ትዝ አሉኝ፡፡ የግብፅን ሕዝብ ጉም ሲያስጨብጡ ቆዩና በስድስቱ ቀናት ጦርነት ሲሸነፉ ሥልጣኔን እለቃለሁ አሉ፡፡ ሕዝቡም በዚህ በቀውጢ ጊዜ እንዴት ትለቃለህ አብረንህ እንሞታለን አለ፡፡ ለማንኛውም ገማል አብዱልናስር ተሸነፉ፣ የግብፅ ሕዝብም እስከ ዛሬ እንደ ተሸነፈ ነው፡፡

የእርስዎ ኃላፊነት ለመላው ኢትዮጵያዊያን መሆኑን ሁሌም ስለሚገልጹት፣ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ የለኝም፡፡ ግን አንዳንዴ በጭላንጭል የሚታዩ መንገድ የለቀቁ ሁኔታዎች አሉ፡፡ ምን ይሆኑ ብለው ቢጠይቁኝ በአገር ደረጃ ተነግሮ የሰው አስተያየት ታክሎበት፣ ሁኔታው ምን ያስከትል ይሆን ተብሎ ተጠንቶ አዎንታም አግኝቶ የሚመለከታቸው ተሰባስበው መወሰንና የሁሉንም ተቀባይነት ማግኘት ሲገባዎት፣ ሁሉንም በግሎ የሚወስኑ ይመስላሉ፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሶ መጨረሻው የማያምር ስለሚሆን ቢያስቡበት የተሻለ ይሆናል፡፡ ተመራጭ መሪ ለተወሰነ ጊዜ በሥልጣን ላይ ስለሚቆይ በራሱ ፍላጎት የአገርን ዓርማ አይለውጥም፡፡ እነ መለስ የተጠሉበት ዋናው ምክንያት እንደፈለጋቸው ስለፈነጩ ነው፡፡ ቢሆንም ሰንደቅ ዓላማችንን ከመልኳ በተጨማሪ ኮከብ ሊበርዟት በእጅ አዙር ሲያስነግሩና ሲያስፈራሩ ቆይተው ነው የተለወጡት፡፡ እርሶ ግን ፒ፟ኮክን በዋናው አደባባይ ላይ ዓርማ አድርገው ሲያስቀምጡ ዱብ ዕዳ ነበር፡፡ ይህ ለምን ሆነ ብሎ ለመጠየቅ ሕዝቡ የሚጠይቅበት አደባባይ የለም፡፡ አደባባዩ ክቡርነትዎ ብቻ መሆኖ ነው፡፡

እንዲህ ዓይነት አነስተኛ ስህተቶች መታረም የሚገባቸው ናቸውና ለምን ከሚወድዎት ሕዝብ ሆድ ይባባሳሉ? ገና ብዙ ዘመን ያልዎት ወጣት የኢትዮጵያ ተስፋ የሚሆኑ ሰው ባልታሰበና ባልተጠበቀ ሰዓታት ውስጥ አንዳንድ ያልታሰቡና ያልተጠበቁ ነገሮችን በድንገት ጣል እያደረጉ ደጋፊዎችዎን ያስደነግጣሉ፡፡ በዚህም ጉዳይ በጣም ያስቡበት፡፡ መሪ በመሪነቱ የሚመሠገንም ሆነ የሚጠላው ውሎ አድሮም ከሕዝቡ የሚራራቀው ባልተጠበቀና ባልታሰበ ሁኔታ ስለሆነ ያስቡበት፡፡ እርስዎ ዛሬ በሠለጠነው ዘመን ከአፍ ገና ሲወጣ ወደ ሕዝብ ጆሮ የተነፈሱት ሁሉ በሚደርስበት ዘመን ዕድሉን አግኝተዋል፡፡ የፈለጉትን የሚያዙበትና የሚያገኙበት ዘመንም ነው፡፡ ባሎት መልካም አንደበትና አቀራረብ ጊዜዎን ይጠቀሙበት፣ የሕዝብን ፍቅር ይሸምቱ፡፡

በአፄ ምኒልክ ዘመን መገናኛውም ወሬውም የተፋጠነና የረቀቀ አልነበረም፡፡ ታዲያ አፄ ምኒልክ ከዘመናቸው የቀደሙና የሠለጠኑ ታላቅ መሪ ስለነበሩ አንድን ሰው ከመሾማቸው በፊት ሕዝብ ምን ይል ይሆን? ብለው ያስቡና ሰላዮቻቸውን በየመንደሩ ልከው አቶ እገሌ ሊሾም ነው አሰኝተው ወሬው ይናፈስና የሕዝቡ አስተያየት ከደረሳቸውና የሕዝቡን ሁኔታ ከተረዱ በኋላ እንደ አስተያየቱ ሹመቱ ይፀድቃል ወይም ይቀራል፡፡ እርሶ ግን የሰዎችን አስተያየትም ሆነ ቅቡልነቱን ሳያረጋግጡ እንደ ፈለጎት ወጣቱን ያስደሰቱ እየመሰሎት ትናንትን ያላዩ፣ ለነገም ለማሰብ ተሞክሮ የሌላቸውን ሰብስበው ታላላቅ የኃላፊነት ቦታ በመስጠት የወጣቱን ድጋፍ የሚያገኙ ይመስላሉ፡፡ ከአንድ ታላቅ አገር አስተዳዳሪ የማይጠበቅ የችኩል ሥራ የሚሠሩ ስለሚመስል፣ ይህ ቢጤንና መሠረት ቢይዝ መልካም ይሆናል ብዬ እገምታለሁ፡፡

የተማሩ ወጣቶች በትምህርታቸው ደረጃ መሠረት አይመደቡ ማለቴ አይደለም፡፡ ዛሬ እንደሚያውቁት ከየለብ ለብ ዩኒቨርሲቲዎች በገንዘብና በወዳጅነት የዶክትሬት ዲግሪ እንደሚገዛ ይስቱታል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ ግን እንዲህ ዓይነቱ ለትልቅ ኃላፊነት ለመመደብ ያበቃቸዋል ወይ ነው ጥያቄው? በአሜሪካ የመጀመሪያው ወጣት መሪ የ43 ዓመቱ ጎልማሳ ጆን ኤፍ ኬኔዲ ነበሩ፡፡ ነገር ግን አማካሪዎቻቸው በዕሜያቸው የበሰሉ፣ በሥራቸው ተከብረውና አገርን በማገልገል የተመሰከረላቸው ነበሩ፡፡ እነሱም በኩራዝ ተፈልገው ነበር ለአማካሪነት የሚቀርቡትና የሚያገለግሉት፡፡ ባለፉት አርባ ዓመታት የተፈጠረው የካድሬ ውዥንብር አሁንም አለቀቀንም፡፡ ይህ በአስቸኳይ በእርሶ አገር ወዳድነት መስመር ይዞ አገራችንም በማያጠራጥር ሁኔታ ወደፊት መገስገስ አለባት፡፡ እስከ ዛሬ ካንቀላፋንበት የቀሰቀሱን ይመስላልና ይበርቱበት፡፡ አገር ወዳድነትዎን ብነግሮት በአጀማመርዎ አሳይተዋል፣ እያሳዩም ነው፣ ይበርቱ፡፡ በዘርና በሃይማኖት መለያየት ለሌሎች ሲሳይ ለመሆን ካልሆነ በስተቀር ለወገን ጠቃሚ አይደለምና አገር በዘርና በሃይማኖት ለመለየት የሚሞክሩትን ዋጋ አይስጧቸው፡፡ አገር በቴክኖሎጂና በኢንዱስትሪ ሲፋፋ እንጂ በዘር ተከፋፍሎ ከለማኝነት ሲወጣ እስከ ዛሬ አልታየም፡፡ እነዚያን ሊለያዩ የሚሹ ተላላኪዎች ይህንን እንዲገነዘቡ ቢደረግ መልካም ይሆናል፡፡

ክቡርነትዎ እርግጠኛ ነኝ በየመንገዱ ሕፃን አዝላ ለልጇ ትምህርቱ ሳይሆን፣ አንድ ቁራሽ ገዝታ የምታበላበትን ስጡኝ ብላ የምትለምነዋን ወጣት እንዳዩ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ለ15 እና ለ20 ዓመታት ለአገሩ ሌት ከቀን ለፍቶ ያገለገለ ከሥራው ወጥቶ የሚበላውን አጥቶ የዕለት ጉርሱን እንደሚለምን አላዩም ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ሁኔታ የክልል ሹማምንት እሽቅድምድምና የቋንቋ ፉክክር ምን የሚሉት አባዜ ነው? ይህንን ተመልክተው ለዚህ መፍቴሔ ለመስጠት የሚችሉ ባለሙያዎችን ቢያሰባስቡ ኢትዮጵያን ይለውጧታል ብዬ ከልቤ አምናለሁ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩም ኢትዮጵያውያን ለዘለዓለም ያኑርልን ይልዎታል፡፡ “If we open a quarrel between the present and the past, we shall be in danger of losing the future” ያሉት ወጣቱ ፕሬዚዳንት ኬኔዲ ነበሩ፡፡ ያለፈውን፣ የዛሬውንና የነገውን ለማስታረቅ የተናገሩት ምሳሌያዊ አነጋገር ነበር፡፡

በመቀጠል ካቶሊክ ስለሆንክ አትመረጥም የሚል አድማ ስለተነሳባቸው የሚከተለውን ተናገሩ፡፡ “I do not speak for my church on public matters, and the church does not speak for me.” በግሌ ሳስብ እርስዎም ለኦሮሞ፣ ለአማራ፣ ለትግሬ፣ ለወላይታ ወይም ለአንድ የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ለይተው የቆሙ አይመስለኝም፡፡ “ታላቅ እንሆናለን” ብለው በሕልም ሩጫ እንደተቀጠፉት አዶልፍ ሂትለርና ዱቼ ሞሶሎኒም ለግል ዝና የሚከንፉ አይመስለኝም፡፡ እምነትዎና አካሄድዎ ለኢትዮጵያ አንድነት ይመስለኛል፡፡ ይህ ከሆነ ጆሮዎን ጣልና ዓይንዎን ከፈት አድርገው በቀና ከተንቀሳቀሱ የዋሁ፣ ደጉና እምብዛም ለክፋት ሰፊ ልብ የሌለው የአገሮ ሕዝብ ከጎኖ ይቆማልና ይበርቱ፡፡

    ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው ግለ ሕይወታቸውንና የጉዞ ታሪካቸውን የከተቡበት ‹‹ከባቹማ እስከ ቨርጂኒያ›› በሚል ርዕስ ለአንባቢያን ያቀረቡት መጽሐፍ ደራሲ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው assefadefris@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡                      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...