Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የአስታራቂ ያለህ!

ሰላም! ሰላም! እንዲያው ለአፍ ልማድ ሰላም እንባባለው እንጂ፣ የዘንድሮ ነገራችንስ እንጃለት ነው ስል የሰነበትኩት። ‘ምን ገጥሞህ ይህንን ታስባለህ?’ የሚል ካለ መቼም እዚህ አገር እየኖረ የደነቆረ፣ ካልሆነም የራሱን ግዛት ገንብቶ በቅንጦት አበሳውን እያየ የሚኖር ፉግሪ መሆን አለበት። እውነት ነዋ። አንዱ በአንድ ወቅት ሁሉም ነገር ሞልቶለት ሲበላ፣ ሲቅም፣ ሲጠጣ፣ ሲያጨስና ሲያጫጭስ የአገሩ ሰው ሁሉ እንደ እሱ ጥጋብ ላይ ያለ መስሎት፣ ‹‹ኢትዮጵያ በልማት ተመንድጋ የሁሉም ሰው ገቢ በየቀኑ ስለጨመረ እኮ ነው ሥጋ ቤቱ፣ ውስኪ ቤቱ፣ ጭፈራ ቤቱ የደራው…›› እያለ ሲመፃደቅ አንዱ በትዝብት እየሰማው ዝም ይለዋል፡፡ አጅሬው እንደ ነፋስ እጁ ድንገት የገባው ገንዘብ ቁጥሩ አሽቆልቁሎ ሽሮና ጂን ተራ ሲከተው፣ ‹‹ሰው እንዴት ብሎ ነው እዚህ አገር በሞተ ኢኮኖሚ እየኖረ ያለው…›› እያለ ሲያላዝን ያ ሰው ሰምቶት፣ ‹‹አንተ ምን ዓይነቱ ወሽካታ ነህ? የአገራችን ኢኮኖሚ የሚለካው አንተ ኪስ ውስጥ ባለ ገንዘብ ነው ወይ…›› ብሎ ቆሌውን እንደ ገፈፈው የነገረኝ የእኔ ቢጤ ደላላ ነበር፡፡ ዛሬም ከገባበት አዚም ውስጥ እስኪወጣ ድረስ ሞታችንና መፈናቀላችን የማይገደው ስንት አለ መሰላችሁ፡፡ ተከድኖ ይብሰል እንጂ!

ተውኝማ እናንተ! ጉድ በዛ እያላችሁ ወጥ አታስረግጡኝ እስኪ። ግን እንዲያው በእምዬ ይሁንባችሁ ወጥ እየረገጠ ያስቸገራችሁ ሰው የለም? የእኔ ነገር የሚላስ ጠፍቶ ስለሚረገጥ ወጥ ታወራለህ የሚለኝ እንደማይጠፋ እያወቅኩ ምን እንደሚያስለፈልፈኝ አይገባኝም። ምናልባት የክንብንብ ኑሯችን እያደር ሲንር ግልጽነት ከተጠያቂነት ያድናል የሚሏት ቋንቋ ብቻዋን ግልጽ ሆና ሠርታልኝ ይሆናል። ተሠርተን ሳንጨርስ የሚሠራልን ተፈጥሮ ብዛቱ አለመቆጠሩ። አንዱ በቀደም እየሮጠ ድድ ማስጫችን ድረስ መጥቶ፣ ‹‹እናንተ ይህንን ጉድ ሰምታችኋል እንዴ…›› እያለ ሲያለከልክ የሰሞኑን የወለጋ ዕልቂት መስሎን ተጨማሪ ወሬ እንዳለው ስንጠብቀው፣ ‹‹እኔ እኮ የገረመኝ መንግሥት ባለበት አገር ውስጥ ይህ ፌር ነው…›› ብሎ አፍጥጦ አየን፡፡ አንደኛው ደላላ ወዳጃችን፣ ‹‹ምኑ ነው ፌር ያልሆነው…›› ብሎ ጥያቄ ያቀርብለታል፡፡ አጅሬው እንደተናደደ በሚያስታውቅ ገጽታ፣ ‹‹እኛ እዚህ ምሳ በልተን እራት ያርብናል እነሱ የ30 ሚሊዮን ብር መኪና ይነዳሉ…›› ብሎ የበረዶ ዶፍ ለቀቀብን፡፡ አንዳንዱ እኮ ሌላ ዓለም ላይ ነው ያለው፡፡ እንዲያው እኮ!

እስቲ ወደ ሌላ ወግ ልውሰዳችሁ፡፡ በዚህ ዘመን መከዳዳት የተለመደ ነው ብል ማጋነን አይሆንብኝም፡፡ መንግሥት ሕዝብን ይክዳል፣ ሕዝብም መንግሥትን መካዱ አይቀርም፡፡ አንዱ የሌላውን ገንዘብ በልቶ አልመልስም ሲል፣ ሌላው ደግሞ ተራውን ጠብቆ ሲጨረግደው ሽማግሌም ሆነ ሕግ ሥፍራ ያጣሉ። አገርም እንዲህ እየሆነች ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ ይኼን ጉዳይ ለአዛውንቱ ባሻዬ ባነሳላቸው፣ ‹‹ሰው እህል እንጂ ገንዘብ ይበላል እንዴ?›› ብለው ለአገሩ እንግዳ ሆኑብኝ። ይኼኔ ምሁሩ ልጃቸው ደለብ ያለ መጽሐፍ እያነበበ ፈንጠር ብሎ ተቀምጦ ነበር። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹በእህሉ ፈንታ ገንዘቡ ያለ ዋጋ በየቦታው ተዝረክርኮ ሲገኝ ታዲያ ሰው ምን ይብላ? ገንዘቡ አልበቃ ያላቸው ደም ይበሉ አይደል እንዴ…›› አይል መሰላችሁ? ይህንን ምሬት ሰምቼ ወደ ሥራ ልጣደፍ ጉዞ ስጀምር፣ ድንገት ሳላስበው ማኪያቶ 50 ብር መሸጥ የጀመረ አዲስ ካፌ ያለበት ሕንፃ ሥር ቆሜያለሁ ለካ። እንጃ ለምን እንደቆምኩ። ምናልባት በደመነፍስ ከአዲሱ በረከት ያጋባብኝ ይሆናል ብዬ ይሆናል። የሚሉንን ቀርቶ የምንለውን አጥርተን ማወቅ ያቃተን ጊዜ ላይ መሆናችንን ረሳችሁት? መቼ ይሆን ግን እየጎመጀን መኖር የሚበቃን? መቼ ይሆን ግን ሰላም አግኝተን ዕፎይ የምንለው? እንጃ!

በነገራችን ላይ እርስ በርስ መነጋገር ትተን በኢንተርኔት አማካይነት ስንነጋገር ነው መሰል አጉል መደፋፈራችን የበዛው? እውነቴን እኮ ነው። የመደፋፈራችን ዕድገቱ በስንት ፐርሰንት መሆኑን ግን አላወቅኩትም። ጥያቄዬ እኮ አስተያየት ነው። ታዲያ ወጋችንን የታዳጊ አገሮች የኢኮኖሚስቶች ማኅበር ባናስመስለው ደስ ይለኛል። ደግሞ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ያለ አቅሙ መዳፈር አበዛ በሉ አሉዋችሁ። ዳሩ መቼ ቀረልኝ። ስልኬ የአንበርብር ያለህ እያለ አስነጠሰችላችሁ። አውጥቼ ሳይ “አፋልጉኝ” ይላል። ‘ማን ምን ጠፍቶት ይሆን?’ አላልኩም። እንዴት እላለሁ? ወገኔ በየአቅጣጫው የጫረው የትስስርና የፍቅር እሳት ጠፍቶበት፣ ዓይኑ በቁጭት ጭስ እያደር እያነሰ እያየሁ እንዴት ብዬ። ከቤኒሻንጉል እስከ ኦሮሚያ፣ ከጋምቤላ እስከ ሁመራ ወገኑ በጥይት እየተቆላ የአፋላጊ ያለህ ቢባል ምን ይደንቃል? አሁንማ ጠፍቶ ከሚፈለገው ሰው ቀጥሎ አገር ጠፍታብን “የአገር ያለህ” የምንልበት የምፅዓት ቀን እየቀረበ ይመስለኛል፡፡ ጉድ እኮ ነው!

ወዲያው ወረድ ብዬ ሳነብ፣ ‹‹አገራችን ኢትዮጵያ የዛሬ 31 ዓመት ከቤቷ እንደወጣች አልተመለሰችም። ያለችበትን ያየ ወይም የሰማ ቢጠቁመን ወሮታውን እንከፍላለን…›› ይላል። እውነቴን ነው የምላችሁ ካርቱን አለመሆኔ ጠቀመኝ እንጂ፣ ዓይኔ ለተወሰነ ሰከንድ ከቦታው ተነቅሎ ወጥቶ የምሆነውን ሳጣ ወዳጅና ጠላት ቶምና ጄሪን በገሃድ አገኘሁ ብሎ የቱሪስት መስህብ ሆኜላችሁ እናንተም ዜናውን ትሰሙ ነበር። ለነገሩ መርጠው እየዘገቡ ሀቅ ሀቁን መስማት አልቻልንም እየተባለ ነው። እንግዲህ ማን ቶም ማን ጄሪ ነው የሚለውን የሒሳብ ጨዋታ ትቼላችኋለሁ። መቼም የሹም ሽር፣ የባንክ አካውንት ከማስላት የሰንጠረዥ ጨዋታ ይኼ ይሻላል… አንዳችን የአንዳችን ግብር ከፋይ ብንሆን ኖሮ ባለቀ ሰዓት ጦር የሚያስንቅ የሠልፍ ትዕይንት በማድረግ ዓለምን ጉድ ይለን ነበር፡፡ እንዲያው ለጨዋታ ነው እንዳልል ነገራችን ያስፈራል፡፡ በጣም ያስፈራል!

የሚገርመኝ ነገር ታዲያ እንዲህ በነበር ብዙ ነገር ጥለን የማለፋችንን ያህል፣ የዕድሜ ጣሪያችን በአርባ ዙሪያ መሽከርከር አልነበረበትም። አዛውንቱ ባሻዬ አዘውትረው፣ ‹‹ሙሴ በአርባ ዓመቱ ለአገልግሎት ሲሰማራ፣ የሠለጠነው ዓለም ከአርባ ዓመቱ በኋላ የቤተሰቡንና የአገሩን አደራ በዕውቀትና በሙላት ተሸክሞ መሮጥ ይጀምራል፣ እኛ እናሸልባለን…›› ይሉኛል። ‹‹ምን ያደርጉታል ብለው ነው የአርባ ቀን ዕድላችን ነዋ…›› እያልኩ እኔ ደግሞ ዘመንን በቀን አጣፋላቸዋለሁ። እንዲያው ሌላ ሌላው ቢቀር የማጣፋት ዕውቀት ቸግሮን አያውቅማ። ልብ አድርጉልኝ ታዲያ። ያቺን ‘አፋልጉኝ’ አረሳኋትም። እንዲህ ያለው የአፋልጉኝ ስላቅ ደግሞ አይመቸኝም፣ በቃ አይመቸኝም። ስለዚህ ለምን የባሰ አላጣፋቸውም ብዬ፣ ‹‹ያለችበትን አውቃለሁ…›› ብዬ ጻፍኩ። አዳሜ በድብርቱ መጠን በሳቅ እስክተረትረው እየጠበቀ ነው። እንዲያው ለመሆኑ የአገርም ጉዳይ የቀልድ ግብዓት መሆኑ ግርም አይላችሁም? እኔማ ንድድ ያደርገኛል!

‹‹አገራችን የት አለች?›› የሚል ጥያቄ ከየአቅጣጫው ተንጋጋ። እኔም ኮስተር ብዬ፣ ‹‹ያለችበትን ስጠቁምና ስታገኙዋት ይህችን ትመስላለች። የኮንዶሚኒየም ቤት ተመዝግቦ የሚጠብቀው ወገን ብዛት በሚሊዮን ይቆጠራል፡፡ በቀን ሦስቴ መብላት የሚሉት ነገር ከቅዠት ይቆጠራል፡፡ ዘይት ከወርቅ ጋር እኩል መደብ እየሆነ ነው፡፡ ደሃ በሚቆጥበው ገንዘብ ሀብታም እየበለፀገበት ነው፡፡ ወጣቱም ሆነ አዛውንቱ ለቀልድ እንጂ ለቁምነገር ከጠፋ ሰነባበተ፣ ወዘተ፣ ወዘተ…›› እያልኩ ሳልጨርስ የፍረጃና የስድብ ውርጅብኝ አስተናገድኩ። ቆይ ግን እኔ ምለው የአገራችን ካድሬ ከሚናገረው በተቃራኒ መናገር ያስጠቁራል እንዴ? የምሬን እኮ ነው። ይኼ ማኅበራዊ ሚዲያ እያሉ የሚጠሩት የወሬኞች መናኸሪያ በቃ በተቀባባ ማንነት እያደራጀ አገልግሎቱ ሥራ ለማስፈታት ሆኗል ማለት ነው? አልገባህም ብሎኛል!

እናላችሁ ሥራዬን ትቼ በዚያው ‘ላይክና ኮሜንት’ ሳደርግ ሰዓታት ነጎዱ። ድንገት አንድ ሰው የሌለው ዳያስፖራ፣ ‹‹እባካችሁ ከሰላሳ እስከ አርባ ሺሕ ብር የሚከራይ መኖሪያ ቤት ካወቃችሁ አሳውቁኝ…›› ብሎ ስልኩን ቁልጭ አርጎ ጽፎ ለጠፈ። የዛሬ ጊዜ እንጀራ ከቀኝ ይጀምር ከግራ በየት በየት አድርጎ ዞሮ እንደሚቀባ አታውቁትም። ‹‹ያልተቀባ ሲጀምር ምኑን ያውቀዋል?›› የሚሉኝ ባሻዬ ትዝ አሉኝ። ባሻዬ ደግሞ ሰሞኑን መለኮታዊ ዕሳቤዎቻቸው ጨምረዋል። ለነገሩ ወደው አይመስለኝም። እንደ እሳቸው ትረካ ከቅዱሱ መጸሐፍ ሌላ የማይዋሽ የማይዘላብድ አዋጅና ራዕይ አጣሁ ስለሚሉ ነው። የእምነት ነፃነትና እኩልነት በተከበረባት አገር ይኼን በተመለከተ ምንም ወግ መቀመር የሚቻል አይመስለኝም። ብቻ ምሁሩ ልጃቸው ይኼን አባባላቸውን ሲሰማ፣ “ለማወቅ አለማወቅን ማመንና መቀበል እንጂ መቀባትን ምን አመጣው?” እያለ ይሟገታቸዋል። አባትና ልጅን እዚህ ተወት እናደርጋቸዋለን። ምን ይደረግ!

በበኩሌ ግን አላውቅምን ካለማወቃችን የተነሳ ፖስታ ቤት ሲጠይቁን ፖሊስ ጣቢያ እየጠቆምን፣ ስንቱን ‘ነገር ባይኖርህ ምን አቅለብልቦ አመጣህ’ እያስባልን አስላጭተነው ይሆን እያልኩ አስባለሁ። ይኼን እያሰብኩ ወዲያው ወደ ዳያስፖራው የፌስቡክ ደንበኛዬ ደወልኩ። እጄ ላይ ሁለት ቤቶች ነበሩ። አንዱ ካፌ ተቀጣጥረን ካገኘሁት በኋላ ቤቱን አሳይቼው ከባለቤቱ ጋር ለኪራይ ተስማማ። ‹‹ቤቱን ግን በደንብ አይተኸዋል?›› አልኩት በችኮላ የወሰነ ስለመሰለኝ ደግሞ ነገ ዞሮ በፌስቡክ ስሜን እንዳያጠፋው ሰግቼ። ‹‹ምን ምርጫ አለኝ? ነገ ትመጣለች፣ ጊዜ የለኝም እባክህ…›› አለኝ። ‹‹ማን ናት?›› እንደ ዘበት የወረወርኩት ጥያቄ። ‹‹ሚስቴ ናታ፣ በስንት ጭንቅ ስንት ወጪ አውጥተን የሰው ማህፀን ተከራይተን ልጅ ስናገኝ ሆቴል ላሳርፋት ደግሞ?›› አይለኝም? ደግ የለ ክፉ የለ ዲዳ ሆኜ ዋልኩ። ‘ኖ ኮሜንት!’ ብዬ ፖስት ሳደርግ ላይክ አድርጉልኝ እሺ!

በሉ እንሰነባበት። እንዲያው ነገሩ እንደ ገረመኝ እንዳፈዘዘኝ ሰነበተ። ማንጠግቦሽ በወጣሁ በገባሁ ቁጥር፣ ‹‹ምን ሆነሃል አንተ ሰውዬ?›› እያለች ታደርቀኛለች። ‹‹ሰው ሆኖ ምንም አለመሆን አለ እንዴ?›› ትላለች መልሳ ደግሞ። ትክት እያለኝ ቴሌቪዥን እየቀያየርኩ አንድ ፕሮግራም በቅጡ ሳላይ፣ ዜናም ሆነ ዘጋቢ ፊልም እንዳጎረሱኝ እየዋጥኩ ውዬ ከማደሬ፣ የአገራችን በቅጡ የማይናገሩትን የውጭዎቹ ሚዲያዎች የሰሞኑን ጉዳችንን በምሥል እያስደገፉ ሲያቀርቡ ነቃ አልኩ። እንደ ምንም ብዬ በተከታተፈ ትርጉም ከቀውስ ውስጥ መውጣት እንዳቃተን ሲናገሩ ልቤን አመመኝ። ጆሮዬ ቆመ። ወደ ምሁሩ ባሻዬ ልጅ ደውዬ በፈጠረህ የውጮቹ ምን እያሉ እንደሆነ ሰምተህ ንገረኝ አልኩት። እሱ ቀድሞ ሰምቶ ኖሮ፣ ‹‹አንበርብር አላስተረፉንም እባክህ፡፡ እንደ ዘገባዎቻቸው ድምዳሜ ከሆነ ቅኝ ገዥ ሳያስፈልገን አይቀርም፡፡ እኛ ለብዙ ሺሕ ዓመታት በነፃነት መኖራችንን ብንናገርም እነሱ ግን “ብሩታል፣ ባርቤሪክ…” እያሉ የሚያስገቡዋቸው ቃላት አጥንት ይሰብራሉ…›› ሲለኝ ደነዘዝኩ። መደንዘዝም ያንሳል!

ጠቅለል ሳደርገው ታዲያ ስንቱ የሚላስ የሚቀመስ አጥቶና ጎጆው ላዩ ላይ ፈርሶ ተበትኖ፣ በየቦታው ድርቅና ረሃብ መፈጠሩን እያስጠላው እንደሆነ እያየን እየሰማን፣ ይህ ሁሉ መከራ አልበቃ ብሎ ጭፍጨፋ ሲታከልበት እንዴት ተባብረን ማስቆም ያቅተናል? የሚለው ሞጋች ርዕስ እኔንና ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ብዙ አስወራን። አስቆዝሞኝ ስያሜ ያጣሁለትን የማህፀን ኪራይ ጉዳይ ሳነሳለት ደግሞ፣ “ይኼ ምን ይገርማል አንበርብር? ሰውን ከእነ ሙሉ አካሉ፣ እምነቱ፣ ስሜቱና ነፍሱ ያለ ዋጋ እየተሸጠ፣ በዚያ ላይ ይህም ኑሮ ሆኖ በገዛ ወገኑ እንደ አውሬ እየተገደለ ስለአንድ የአካል ክፍል ኪራይ ታወራለህ?” ብሎ በነገር ኩርኩም ኮረኮመኝ። ሰው መሆን እንደ ዘንድሮ ግራ ገብቶኝ አያውቅም ጎበዝ። አንዱ ሰላሙን አጥቶ አኅጉርን በባዶ ሆዱ ያቋርጣል። ሌላው ደሴት ላይ እኮ ቤት የለኝም እያለ ይጨነቃል። እዚያ ከጥይት ተርፎ በውኃ ጥም ሲያልቅ፣ እዚህ በመሬት ወረራ በተገኘ ገንዘብ ውስኪ ሲራጭ፣ በግማሽ ሌሊት ዕድሜ ኩላሊትና ጉበት የአጋዥ ያለህ እያሉ ከጥቅም ውጪ ይሆናሉ። የቱ ተነስቶ የቱ ይተዋል እናንተ? በበኩሌ ላይታረቁ በተቃረኑ ተቃርኖዎች ተዝለፍልፌያለሁ። መልካም ሰንበት!         

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት