Sunday, May 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልበዓለም ሙዚቃ ቀን መነሻ

በዓለም ሙዚቃ ቀን መነሻ

ቀን:

‹‹ፈልቀሽ የተገኘሽ ከሹበርት ራስ

ከቤቶቨን ናላ ከሞዛርት መንፈስ

ከሾፐን ትካዜ ከያሬድ ልቡና

- Advertisement -

መዓዛ የሞላብሽ የብስጭት ቃና

ረቂቋ ድምፅ ሆይ ውቢቷ ሙዚቃ

ውብ እንደ ፀሐይ ንፅህት እንደ ጨረቃ…››

ይህ ታዋቂው ገጣሚና ጸሐፌ ተውኔት ከበደ ሚካኤል የቅኔ አዝመራ በተሰኘው መድበላቸው ስለ ሙዚቃ ከገጠሙት የተወሰደ አንድ አንጓ ነው፡፡

ሙዚቃን የገለጹበት መንገዳቸውን ያስታወሰን ባለፈው ሳምንት የተከበረው የዓለም የሙዚቃ ቀን መምጣቱ ነው፡፡

በጎርጎሮሳዊው የዘመን ቀመር ጁን 21 ቀን በኛ ሰኔ 14 ቀን ላይ የታሰበው የዓለም ሙዚቃ ቀን የመከበሩ ዓላማ፣ ሙዚቀኞችን ከማበረታታት ባለፈ አማተሮችም ሆነ ፕሮፌሽናሎች ተሰጥዖቸውን የሚያሳዩበት መድረክም እንዲሆን ነው፡፡ ለድምፃውያንና ሙዚቀኞች ክብር ለመስጠትም አልሟል፡፡

ብዙዎች ዓለምን ያለሙዚቃ አያስቧትም፡፡ ያለሙዚቃ ትርጉም አይኖራትም ይላሉ፡፡ የዓለም ሙዚቃ ቀን የመከበሩ ፋይዳም ከዚሁ ይመነጫል፡፡ የጥበብን ኃያልነቷን ለማሳየት፡፡

ከ120 በላይ አገሮች የዓለም ሙዘቃ ቀንን የሚያከብሩት ኮንሰርቶችን በፓርኮች፣ በስታዲየሞችና በአደባባዮችና በነፃ ለሙዚቃ ወዳጆች በማቅረብ ነው፡፡

ጠበብቱ ሙዚቃ በሰው ልጅ የመንፈስና የአካል ገጽታ ላይ ጠቀሜታ አላት ይላሉ፡፡ ከበደ ሚካኤልም ሆኑ ተመስገን ገብሬ (በሰንደቅ ዓላማ ጋዜጣ) ሙዚቃን ‹‹የነፍስ እህል ውኃ›› እንዳሏት፡፡

በሌላ በኩል አሜሪካዊው ሙዚቀኛ ጆኤል ኮኸን እ.ኤ.አ. በ1976 የሰመር ሶሊስቲስ (ረዥሙ የፀሓይ ቀን) መባቻ ምክንያት በማድረግ በጁን 21 ሌሊቱን ሙሉ የሙዚቃ ድግስ ጁን 21 እንዲኖር ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ነው ዕለቱ (ሰኔ 14) ለዓለም ሙዚቃ ቀንነት የተመረጠው፡፡  የዓለም ሙዚቃ ቀን መከበርም የተጀመረውም እ.ኤ.አ. በ1982 በፈረንሣይ ነው፡፡

የባህል ሚኒስቴራቸው የሙዚቃን ልዕልናና አስደናቂነት ለማሳየት ቀኑ በየዓመቱ እንዲታሰብና የቀጥታ ሙዚቃ ድግስን ሁሉም ሰው ከክፍያ ነፃ ሆኖ እንዲታደም አድርጓል፡፡

የዓለም ሙዚቃ ቀን በአዲስ አበባ

የዓለም ሙዚቃ ቀንን ቀደም ባሉት ዓመታት አልባብ የቴአትር የሙዚቃ ፕሮሞሽን በተለያዩ ከተሞች በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ያከብር እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በተከታታይ ዓመታት በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በአዲስ አበባ፣ በመቐለና በባህር ዳር ከተማዎች ማክበሩ በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

የሙዚቃ እንዲሁም የኪነ ጥበባት ዝግጅቶችን በማክበርና በማዘጋጀት የሚታወቀው አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ ዘንድሮም በተለያዩ ቀናት ካዘጋጃቸው የሙዚቃ መሰናዶች ባሻገር የዘንድሮውን የዓለም ሙዚቃ ቀን በቅጥር ግቢው ውስጥ ሰኔ 14 ቀን 2014 ዓ.ም. አክብሯል፡፡

ታዳሚዎች ሥነ ሥርዓቱን የተከታተሉት እንደ ሁሌው በነፃ ነው፡፡ ሥራዎቻቸውን ካቀረቡት መካከል ታዋቂው የክላርኔት ተጫዋቹ ዳዊት ፍሬው ኃይሉ ይገኝበታል፡፡ ሌሎቹ ድምፃውያንና ሙዚቀኞች ባርኮት ታደሰ፣ ቤተኢየሱስ ያሬድ፣ መርያም መኰንን፣ ዶን እዝራና ኩኪ፣ ቃል ኪዳን ወርቁ፣ ዲጄ ባብኪም፣ ትሁት ሚዩዚክና ጥለት ኳርተርስም ተገኝተውበታል፡፡

አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ ከዚህም ሌላ በዓለም ሙዚቃ ቀን ዋዜማ ታዋቂው ድምፃዊ ግርማ በየነ ከአካለ ውቤ ጋር በመሆን በሀገር ፍቅር ቴአትር ባዘጋጀው ኮንሰርት በርካቶች ታድመው ነበር፡፡ የሙዚቃ ትርዒትን፣ ዓውደ ርዕዮችን፣ ፊልሞችን፣ የቴአትርና ሌሎች የባህል ዝግጅቶችን በማስተናገድ ላይ የሚገኘው አሊያንስ ኢትዮ ፍራንሴዝ የአገር ውስጥ የጥበብ ዘርፍን ለማዳበር የሚረዱ ፕሮግራሞችን ለመደገፍና ለማደራጀት ወደ ኋላ እንደማይልም ዘወትር የሚያስተጋባው ነው፡፡በኮንሰርቶች ወይም በፌስቲቫሎች በመገኘት የዓለም ሙዚቃ ቀንን ለማክበር ያላጋጠማቸው ሙዚቃ ወዳዶች በዕለቱ በተለይ ቀደምት ሙዚቃዊ ሥራዎችን በተለያዩ መንገዶች መከታተላቸው አልቀረም፡፡በኢትዮጵያ በተለይ በሙዚቃው ቀን አጋጣሚ ታዋቂው ድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የለቀቀው ‹‹ናዕት›› የተሰኘው ሥራው በተለያዩ መንገዶች በአገር ውስጥና በውጭ ከኅብረተሰቡ ዘንድ የደረሰና ይበልታን ያገኘ መሆኑ ታውቋል፡፡ በሁለት ቀን ውስጥ ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ዘፈኑን በዩቲዩብ ማዳመጣቸው፣ ይህም ከፍተኛው ቁጭር መሆኑ ተገልጿል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...